>
10:09 am - Wednesday December 7, 2022

ኦነግ ሽብር እያካሄደ ያለው ለዐቢይ አሕመድ በገበሩ ክልሎች ውስጥ መሆኑ ምን ያሳየናል? (አቻምየለህ ታምሩ)

ኦነግ ሽብር እያካሄደ ያለው ለዐቢይ አሕመድ በገበሩ ክልሎች ውስጥ መሆኑ ምን ያሳየናል?
አቻምየለህ ታምሩ
ኦነግ ኦሮምያ ሲል የፈጠረው አገር ወያኔ ከፈጠራቸው ክልሎች ጋር ሁሉ ይዋሰናል። ኦነግ ኦሮምያ ሲል የፈጠረው አገር ጎረቤት ከሆኑ ክልሎች መካከል ወረራ ያላካሄደውና ሰራዊቱ በርካታ ንሑጸንን ያልፈጀበት ክልል ቢኖር ትግራይ ክልል ብቻ ነው። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ጋምቤላ ክልል፣ ሶማሌ፣ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ሐረርጌ ክልል፣ አማራ ክልል ወዘተ የሚባሉ ክልሎች ሁሉ ኦሮምያ ከሚባለው የኦነግ አገር ጋር የሚዋሰኑና ኦነግ ጭፍጨፋና ሽብር ያካሄደባቸው አካባቢዎች ናቸው።
ለዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎች ገብረዋል። ኦነግ ደግሞ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ለዐቢይ አሕመድ አገዛዝ የገበሩ ክልሎች ውስጥ በዐቢይ አሕመድ የሚታዘዘው መከላከያ ሰራዊት የታጠቀውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስካፍንጫው ታጥቆ ጭፍጨፋና ሽብር ፈጽሟል። እዚህ ላይ መጠየቅ ያለበት አንድ ጥያቄ ያለ ይመስለኛል። ኦነግ በፈጠረው አገር ውስጥ የትግራይም ጎረቤት ሆኖ ሳለ በሌሎች ለዐቢይ አሕመድ አገዛዝ በበገሩ ክልሎች ውስጥ እየፈጸመው ያለውን ጭፍጨፋ ለምድን ነው ትግራይ ውስጥ ያላካሄደው የሚል ጥያቄ ማንሳትና ሊሆን የሚችል መለስ መስጠቱ ተገቢ ይመስለኛል።
ከወራት በፊት ዐቢይ አሕመድ በአንድ መድረክ በኦሮምኛ ባደረገው ንግግር የሚመራውን አገዛዝ የኦሮሞ መንግሥት አድርጎ በመቁጠር ቤንሻንጉል ጉሙዝ በሚባለው ክልል አዋሳኝ አካባቢ ኦነግ እያኬሄደው ለነበረው ሽብር እርምጃ የማይወስደው ካሁን በኋላ ኦሮሞ ኦሮሞን መግደል የለበትም የሚል አቋም በመያዙ መሆኑን አመላክቷል።
ዐቢይ አሕመድ በኦነግ ላይ ጦር እንደማያዘምት “ኦሮሞ ኦሮሞን አይደድልም” ሲል የተናገረው በድብቅም ቢሆንም በሚስጥር ስላልሆነ ብዙ ሰው የሰማው ይመስለኛል። ሆኖም ግን ለንግግሩ ብዙ ሰው ትኩረት የሰጠው አይምስለኝም።
እኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ስንለው ራሱ የኦሮሞ መንግሥት አድርጎ የሾመው የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ኦነግ ለሚፈጽመው ሽብርና ጭፍጨፋ በሚያዝዘው መከላከያ በኩል እርምጃ ላለመውሰድ ኦነግ ኦሮሞ በመሆኑና ኦሮሞ ኦሮሞን መግደል የለበትም ብሎ ስለሚያምን እርምጃ እንደማይወስድ የሰማ ሁሉ ዛሬ ላይ ኦነግ ከሚፈጽመው ሽብር የዐቢይ አሕመድን አገዛዝ ጥበቃ ሲጠይቅ ስመለከት ይገርመኛል።
የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ባለፈው አንድ ዓመት ኦነግ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ሶማሌ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ሐረርጌ ክልል፣ ወዘተ በሚባሉት አካባቢዎች ውስጥ ሽብር ሲፈጥር ሲከርም ኦሮሞ ኦሮሞን መግደል የለበትም ብሎ ስለሚያምን ሊደርስ እንዳልቻለ ብዙ ሰው ዘንግቶታል።
የሆነው ሆኖ የኦነግ ሽብር ያልደረሰበት ክልል ቢኖር ትግራይ ክልል ብቻ ነው። በእኔ እምነት ይህ ሊሆን የቻለው በሁለት ምክንያት ይመስለኛል። አንደኛው የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ትግራይ እየገዛ ስላልሆነና ትግራ ለዐቢይ አሕመድ ስላልገበረ በዐቢይ አሕመድ ማደፋፈሪያ ስብርና ጭፍጨፋ እያካሄደ የሚገኘው ኦነግ ለዐቢይ አሕመድ ባልገበረ ክልል ውስጥ እንደልቡ ሽብር ማድረግ ስለማይችል የዐቢይ አሕመድን ማደፋፈሪያ በማያገኝበት ክልል ውስጥ ገብቶ ሽብርና ወረራ በማድረግ በ1984 ዓ.ም. በሴት የሕወሓት ወታደሮች ተማርኮ ወደ ማይታወቅ ማጎሪያ የተወሰደበትን ታሪክ መድገም አይፈልግም።
በሌላ አነጋገር ኦነግ ለዐቢይ አሕመድ በገበሩ ክልሎች ውስጥ ሽብርና ጭፍጨፋ እያካሄደ ያለው የዐቢይ አሕመድን ስልጣን ተመክቶና በተሰጠው ማደፋፈሪያ እየታገዘ ነው። በትግራይ ውስጥ የዐቢይ ስልጣን ስለሌለ ኦነግ በትግራይ ውስጥ ወረራ ጭፍጨፍና ሽብር ለመፈጸም የዐቢይ አሕመድ ከለላ፣ ጥበቃና ማደፋፈሪያ አይኖረውም። ዐቢይ ትግራይን ስለማይገዛ ኦሮሞን አይገድለውም የሚለውን የዐቢይ መሀላና ማደፋፈሪያ እየተጠቀመ ወረራ እየፈጸመ ያለው ኦነግ ትግራይ ውስጥ ከዐቢይ የሚገኝ ልዩ እንክብካቤ ስለሌለ ትግራይ ወርሮ ታሪኩን መድገም አይፈግልም።
ከዚህ በተጨማሪ ሕወሓት ዐቢይ አሕመድ የሚያዝዘው መከላከያ ሠራዊት የታጠቀውን ጦር መሣሪያ የታጠቀ ኃይል ስላላት በዐቢይ አሕመድ የሚታጠቀው ኦነግ ትግራይን ቢወር በጦር መሣሪያ ረገድ የኃይል ሚዛን የሚያስጠብቅ ሰራዊት ስለሚጋፈጠው እንደሌሎቹ ያልታጠቁ ክልሎች በትግራይ ውስጥ ንጹሐንን እያረደ ሊፈነጭ አይችልም።
ባጭሩ ኦነግ ሽብር እየፈጸመ ያለው የዐቢይ አሕመድን ከለላ በሚገኝባቸው ክልሎች ውስጥ ብቻ ነው። ኦሮምያ ሲል የፈጠራትን አገር ከሚያዋስኑ ክልሎች ውስጥ ትግራይን ብቻ ያልወረረውና ሽብር ያላካሄደውም ትግራይ ለዐቢይ አሕመድ ስላልገበረች ትግራይን ቢወር የዐቢይ አሕመድ ጥበቃ ስለማይኖርና ሕወሓት ዐቢይ አሕመድ የሚያዝዘው መከላከያ የታጠቀውን ትጥቅ የታጠቀ ኃይል ሥላላት በዐቢይ አሕመድ እየታጠቀ ሽብር የሚፈጽመው ኦነግ ትግራይን ቢወር ሕወሓትም ዐቢይ ቤት ያለው መሣሪያ ስላላት ተመጣጣኝ ምላሽ ስለሚገጥመው ደፍሮ ትግራይን ሊወር አይችልም!
Filed in: Amharic