>
3:43 am - Wednesday May 18, 2022

የዶ/ር አቢይ ትዕግስት፡ በተስፋ ከምንጠብቀው ጣፋጭ ፍሬ የበለጠ ዋጋ ያለውን የሰው ህይወት እየበላች ነው (ሳምሶን አስፋው)

የዶ/ር አቢይ ትዕግስት፡ በተስፋ ከምንጠብቀው ጣፋጭ ፍሬ የበለጠ ዋጋ ያለውን የሰው ህይወት እየበላች ነው

ሳምሶን አስፋው ቋጠሮ ገጽ

 

የትዕግስት ፍሬዋ ጣፋጭ ነው ይባላል። እውነት ነው። እውነትነቱ የሚጎላው ደግሞ አፍስሶ እንደ መልቀም ካለ የችኩልነት ጦስ ጋር ሲነጻጸር ብቻ ነው።

ዶ/ር አቢይ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግርም ችኩልነት ከሚያመጣው ጣጣ ለመዳን ትዕግስት በብዛት ሊኖረን ይገባል ብለውናል። ይህን ምክራቸውን እንደ ምክር ለመቀበል የሚቸገር ያለ አይመስለኝም።

ጥያቄው..፡ የትዕግስታችን ድንበር የት ድረስ ነው? የሚል ነው ጥያቄው..፡ስንት ሰው እስኪሞት ነው የምንታገሰው ? የሚል ነው ጥያቄው..፡ ስንት ዜጋ ተፈንናቅሎ በርሃብ እስኪያልቅ እንታገስ ? የሚል ነው።

አዋ! የትዕግስታችንን ድንበር በአሃዝ ብናውቀው ለስሌት ይመቸናል። የቡራዩን ፤ የኬሚሴን፤ የጎንደርን፤ …ሟቾች አስልተን ምን ያህል ሟች እንደሚያስፈልጉን አውቀን እንዘጋጃለን።  የጌዲዮን፤ የሶማሌን፤ የኦሮሚያን፤ የቤንሻጉልን….ተፈናቃዮች ደምረን ምን ያህል መፈናቀል እንደሚቀረን ከወዲሁ እንረዳለን ።አልያማ ድንበር በሌለው ትዕግስት እስከመቼ…?

የጠ/ሚ አቢይ ትዕግስት በበዛ ቁጥር እየተከፈለ ያለውም የሰው ህይወት በዛው መጠን እየበዛ ነው። ከክቡሩ የሰው ህይወት እኩል ዋጋ ያለው ነገር የለምና ድንበር የለሿ ትዕግስት ከዋጋዋ በላይ ዋጋ እያስከፈለች ነው። ትዕግስት፡ ነገ ታበላናልች ብለን በተስፋ ከምንጠብቀው ጣፋጭ ፍሬ የበለጠ ዋጋ ያለውን የንጹሃንን ህይወት እየበላች ነው ። ይህ ደግሞ ከጠ/ሚ አቢይ አባባል ልዋስና “ኪሳራ ነው!” ::  ትዕግስት ለህይወት ስኬት ዛሬ የሚከፈል ዋጋ እንጂ ህይወት ለትዕግስት የሚከፈል ዋጋ አይደለም። መታገስ ነገ በስኬት እንድትኖር የምንደክምላትን ህይወት ካሳጣን ምን ዋጋ አለው ?  ፍቅር እንጂ ትዕግስት እስከ መቃብር አብራን ልትጓዝ አይገባም። ታግሶ ማሳለፍ እንጂ ታግሶ ማለፍ (መሞት) ከፍርሃት እንጂ ከገድል አይጻፍም።

ውድ ጠ/ሚ  “መግደል መሽነፍ ነው!” በሚለው አባባልዎ ብስማማም፤ በትዕግስት መሞትም ጀግንነት አይደለምና ከትዕግስትዎ ቀነስ አድርገው ፤ የንጹሃንን ህይወት ይታደጉ ዘንድ ግድ በሚል የታሪክ ጥግ ላይ ይገኛሉ።

በነቂስ ወጥቶ “አቢዬ ለኔ አቢዬ ለኔ አንተን ባየው አይኔ ሌላው ለምኔ” ሲል ፍቅሩንና ክብሩን በዜማ የገለጸልዎ ህዝብዎ ቅኝቱን  ለውጦ “ወይ ውረድ ወይ ፍረድ” እያለ ነው።

ግልቢያ ላይ እያሉ ፈረስ አይለወጥምና የርስዎ በመሪነት መቀጠል አሁንም አማራጭ ያሌለው ጉዳይ ስለመሆኑ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚስማማ ይመስለኛል። ህዝብ እያለ ያለው ታጋሽ ሟች አያድርጉን ነው። የህዝብ አቤቱታ ታጋሽ ተፈናቃይ ከመሆን ይታደጉን ነው….

ያልተገራ ፈረስ ወደ ገደል እያንደረደረው ያለውን ሰው ቆመው ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች፤ ልጓሙን ጭምድደው፤ ኮርኩረው፤ እንዲህ አድርገው፤ እንዲያ አድርገው በሚል ሲንጫጩበት “አይ መሬት ላይ ያለ ሰው!” እንዳለው የጨነቀው ጋላቢ እርስዎም ሰሞኑን ከግራ ቀኝ በሚሰነዘረው እሮሮና አቤቱታ …. “አይ ጠ/ሚር ያልሆነ ሰው” የሚሉ ይመስለኛል። ልክ ነው! መሪነት ጣጣ ነው። ይሁንና አንዳንዴ በዋልድባም ይዘፈናል ይባላልና እርስዎም አንዳንዴ ለዲሞክራሲያዊ አገር ግምባታ ዲሞክራሲያዊ አርጩሜ ይጠቀሙ…። በኔ ይሁንብዎ! እንደ ኢትዮጵያ ሥርአተ አልበኝነት በነገሰበት ሃገር የሰላምና መረጋጋት ጣፋጭ ፍሬን ለመልቀም የሚያስፈልገው ጠንካራ የመንግስት ክንድ እንጂ ድንበር የሌለው ትዕግስት አይደለም።

Filed in: Amharic