>
10:52 pm - Sunday May 22, 2022

"ለኦህዴድ ልጓም ከየት ይምጣለት!!!" (መስከረም አበራ)

“ለኦህዴድ ልጓም ከየት ይምጣለት!!!”
መስከረም አበራ

በሃገራችን ፖለቲካ ልማድ ስልጣን የያዘ አካል ያሻውን ለማድረግ የሚያግደው ነገር የለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ስልጣንን ሊገሩ የሚችሉ የዲሞክራሲ ተቋማት አቅም አለመዳበር ነው:: ደርግ ያሻውን ሲገድል የኖረው፣ ህወሃት እጁ የቻለውን ሁሉ ሲዘርፍ የከረመው፣ አሁን ደግሞ ባለተራው ኦህዴድ ለዚሁ ልማድ እየተንደረደረ ያለው ስልጣን እንዳያባልግ ልጓም ማስገባት ስላልተቻለ ነው፡፡ ስልጣንን ያለ ገደብ የልብን ለመስራት የመጠቀሙ ፖለቲካዊ ልምድ እንዲቀር ካልተደረገ፣ አምባገነን እየቀያየርን በመኖሩ እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምንፈልገው ነገር ስላልሆነ እንዲቀር መስራት አለብን፡፡

የስልጣን ገደብ አልቦ አድራጊ ፈጣሪነት እንዲቀር ለመስራት፣ በመጀመሪያ በስልጣን አለመገራት የሚያመጣውን ችግር ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ስልጣን ባለመገራቱ ሃገራችን ቀይ ሽብርን የመሰለ ዘግናኝ ሁነት አሳልፋለች፣ ህወሃት/ኢህአዴግ  በእስር ቤቶች ያደረገውን  ክፉ ጭካኔ፣ ጆሮ የሚያስይዝ ዘረፋ፣ ሃገር እስከ ማፍረስ የደረሰ ዘረኝነት ወለድ ብልሹ ፖለቲካ አስተናግዳለች፡፡ ህወሃትን ተክቶ ስልጣን ላይ የተሰየመው ኦህዴድም በዚሁ አቅጣጫ  ለመጓዝ መንገድ ጀምሯል፡፡

ይህ ዝንባሌው በብዙ መንገድ ይገለፃል- ስልጣን ጠቅልሎ ለጎሳው ሰዎች በመስጠት፣ የጎሳውን የፖለቲካ ጥቅም ለማስከበር ሃገሪቱን እንደ ሃገር መቆም ጭምር የሚጎዱ መግለጫዎች በማውጣት፣ ስለተናገረውና ስላደረገው ድርጊት መጠየቅን በመሸሽ፣ አንዳንዴም ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ፣ የጎጡ ታጣቂዎች/ጎረምሶች/አክቲቪስቶች/ፖለቲከኞች ለሚያጠፉት ጥፋት ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጥፋቱን ማለባበስ፣ በተቃራኒው ከጎጡ ውጭ ያሉ ሰዎች ህግን ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ችኩልና አፋኝ እርምጃዎች መውሰድ ኦህዴድ ወደ ልጓም አልቦ ስልጣን እያዘገመ እንደሆነ ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ነገሩን አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ኦህዴድ እንዲህ ወደ ልጓም አልቦ ስልጣን እተየጓዘ ባለበት ወቅት ሰፊውን ህዝብ ጨምሮ  በሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድ የኦህዴድ አካሄድ ወዴት እንደሆነ ለመረዳት አለመቻሉ ነው:: ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ኦህዴድ በሚያሳየው እጅግ ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው፡፡ ፓርቲው ወደ ስልጣን ሲመጣ የጎሳ ፓርቲ መሆኑን እስኪረሳ ድረስ ሊብራል የሚያስመስለውን ዲሞክራሲያዊነትና እኩልነት እየደጋገመ ሲሰብክ ሰነበተ፡፡ ይህን የሚያመሳክሩ ጥሩ የሚባሉ እርምጃዎችንም ወሰደ፤ ለምሳሌ የሚዲያዎች መከፈትና የእስረኞች መፈታት፡፡

ይህ በመጠነኛ ተግባራዊ እርምጃ የታጀበው ብዙ ስብከቱ፤ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ የሚፈልገው ሰፊውን ኢትዮጵያዊ፣ ሃሳቡን ጥሎ ኦህዴድ/ኦዴፓን ተስፋ እንዲያደርግ አስገደደው፡፡ ሃገሩ ወደ ተሻለ የፖለቲካ ልማድ እልፍ እንድትል የሚፈልገው ይህ ተስፈኛ ቡድን፤ ኦህዴድ በአደባባይ ሌላ፣ በጓዳ ሌላ (በአማርኛ ሌላ በኦሮምኛ ሌላ) እያወራ የሚያደርገውን እጅግ አደገኛ አካሄድ ለመረዳትና አንድ አቋም ለመያዝ ተቸግሯል፡፡ በበኩሌ ይህ የሚያስቸግር ነገር መሆኑ ማብቃት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በኋላ ኦህዴድ መመዘን ያለበት በሚፈጽመው  ድርጊት መሆን አለበት፡፡ የሚያወራው ነገርም ቢሆን ወጥነቱ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ የንግግር ወጥ አለመሆን አፍና ልብ ልዩነት እንዳላቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ኦህዴድ ሰላምና ፍቅርን በሰበከበት አፉ ድብልቅልቅ ያለ ጦርነት ሊያነሳ የሚችል ኮማንዶ መሆኑንም የሚናገር፣ የንግግር ወጥነት የሌለው ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ ላይ የማይሰማ መስሎት በር ዘግቶ ያወራውን ወዲህ ወዲያ የማያስብል ሃቅ ሊክድ የሚፋትር፣ ሰሚን ለመናቅም የሚሞክር ፓርቲ ነው፡፡ የተናገረውን ሊል እንዳልተናገረ ሲያስረዳን ለማመን ተዘጋጅቶ መቀመጣችን ሊያበቃ ይገባል፡፡ ይህን ያቆምን ጊዜ ኦህዴድ/ኦዴፓም የስልጣን ፈረሱ ላይ ልጓም እንዳለ ያስብና በጥንቃቄ ይጓዛል፡፡ ይህ ደግሞ ለእርሱም ለእኛም የሚበጅ ነገር ነው፡፡

የዐቢይ/ለማን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ያስመዘገበው ድል ከህግ በላይ ሆኖ በአዲስ አበባ ላይ ባለቤት ለመሆን መንደርደር ብቻ አይደለም:: የሃገሪቱን ዋነኛ ስልጣን በኦሮሞ መኳንንት እጅ ማስገባት፣ የዜግነት ፖለቲከኛውን እግር አስሮ ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች እንደ ልባቸው እንዲሆኑ መፍቀድ (ለምሳሌ መንግስት ለሃሮምሳ ፊንፊኔ እና ለባላደራ ምክር ቤት ያለው የተለያየ እይታ፤ ለኢሳት ዘገባዎች ያለው ቁጠኝነት እና ለOMN  ፕሮግራሞች ያለው ለዘብተኝነት)፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች አፍራሽ ንግግሮችን ለመናገር እንኳን የሚሰማቸው የመዝናናት ስሜትና ሌላው ላይ ሲሆን መንግስት ያለው ተቆጭነት ሁሉ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከእነ ዐቢይ/ለማ ወደ ስልጣን መምጣት ያገኛቸው ትርፎቹ ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ የማባበል ስራ መሰራቱ ሃገሪቱ እንዳትበታተን ለመታደግ ሲባል መደረግ ያለበት ትክክለኛ አካሄድ ነው የሚል በሰፊው የሚነገር ግን ደግሞ ልክ የማይመስለኝ ክርክር አለ፡፡ የዚህ ክርክር ትልቁ ስህተት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞችንም ሆነ ሌላ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችን እያባበሉ መኖር ይቻላል ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ ይህ እሳቤ ልክ ቢሆን ኖሮ ሁለተኛው የአለም ጦርነት አይካሄድም ነበር፡፡ ልክ ስላልሆነ ሂትለር የፈለገውን ሲሰጡ የኖሩት እንግሊዝና ፈረንሳይ የማታ ማታ ወደ ፈሩት ጦርነት መግባታቸው አልቀረም፡፡ የማባበል ፖለቲካቸውም የሂትለርን ጡንቻ ማፈርጠሚያ ጊዜ ሰጥቶ፣ ባላጋራቸውን የማይጋፉት ተራራ አደረገባችው እንጂ የረዳቸው ነገር የለም፡፡

የዘር ፖለቲካ በተፈጥሮው የማይጠረቃ ፍላጎት ያለው እሳቤ ነው፡፡ የዘር ፖለቲከኛ የጠየቀውን እየሰጡ በማባበል ለመኖር መንገዱ ሲጀመር በስተመጨረሻው የራስን ፖለቲካዊ ፍላጎትም አስረክቦ፣ በዘር ፖለቲከኛ ስር ለማደር ለመስማማት መወሰን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል:: መጠየቅ የማይታክተው የዘር ፖለቲከኛ፣ የራሴ የሚለውን ሁሉ ጠይቆ ካበቃ በኋላ የሌላውንም የኔ ነው ማለቱ አይቀርም፡፡ በጀመርነው የኦሮሞ ብሄርተኞችን የማባበል አካሄድ፣ አዲስ አበባ የእኔ ናት ከማለት አልፈው ወደ ወሎም፣ ጎንደርም፣ ራያም እያማተሩ ያሉት ለዚህ ነው:: በማባበል የምንፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ማምጣት አንችልም፡፡
የምንፈልገውን የሰለጠነ፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ፖለቲካ ማምጣት የምንችለው በስልጣን ላይ ያለውን ኦህዴድ/አዴፓን ስልጣን በመግራት ነው፡፡ የኦህዴድን/አዴፓን ስልጣን ለመግራት ስናስብ የሚያስቸግረን፣ ዐቢይ/ለማ  የልዩ ናቸው የሚለው ስህተት የማያጣው ስሜት ነው፡፡ ይህን እሳቤ ለመቋቋም እነዚሀ ሰዎች ልዩ ቢሆኑ እንኳን ሁለት ብቻ መሆናቸውን፣ ለእኛ የሚስማማንን የእኩልነት ፖለቲካ ለማራመድ ሃሳባቸውን የሚጋራ ሌላ  በርከት ያለ አጋር የሌላቸው በመሆኑ ስልጣን ላይ ያለው ኦህዴድ የሚይዘው የአብዛኛውን አባል መልክ  መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ኦህዴድ እኛ የምንፈልገውን መልክ የያዘ ድርጅት አለመሆኑን ደግሞ ማመሳከሪያው ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ የምንፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ለማምጣት ኦህዴድ፣ ከህወሃት ከተማረው የእበልጣለሁ ባይነት መንገድ እንዲመለስ ልጓም ሊገባለት ይገባል፡፡

ኦህዴድ ከተያያዘበት የማያዋጣ አካሄድ እንዲመለስ ልጓም የማስገባቱ ስራ በመጀመሪያ ደረጃ መምጣት ያለበት ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ነው፡፡ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ ስልጣን በመነጠቁ ያኮረፈውና ከሌላው እህት ድርጅት ኦዴፓ ጋር ክፉኛ ባለጋራነት የሚሰማው ህወሃት፣ ለዚህ ስራ የሚሆን ተፈጥሮ ያለው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ኦህዴድን የመግራቱ ሃላፊነት በቀዳሚነት የሚወድቀው ብአዴን/አዴፓ እና ደኢህዴን ላይ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ኦህዴድን አደብ ለማስገዛት የመጀመሪያው እርምጃቸው መሆን ያለበት አጋር ፓርቲዎች ወደ አባልነት እንዲያድጉ መስራት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ፓርቲያቸው፣ ኢህአዴግ አስቸኳይ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ጠርቶ፣ ሃገሪቱ ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ በአራት ፓርቲዎች ብቻ የማይቻል፣ ይልቅስ የአጋር ድርጅቶችንም ተሳትፎ የሚፈልግ ስለሆነ  እነዚህ ፓርቲዎች ከአባል ፓርቲዎች እኩል ድምፅ ኖሯቸው፣ በሃገራቸው ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጡ ማስወሰን አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ የኢህአዴግ ምክር ቤት (ማዕከላዊ ኮሚቴ) ጉባኤ መጠራት ካለበትም ተጠርቶ፣ አጋር ፓርቲዎች፣ በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ የማድረጉ እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት፡፡

የአጋር ፓርቲዎች በሙሉ ድምፅና ውሳኔ ሰጭነት በተገኙበት ሁኔታ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሃገሪቱ ፀጥታና ደህንነት፣ የህግ የበላይነት፣ ታጣቂ ፓርቲዎችን አደብ በማስገዛት ጉዳይ፣ በኦህዴድ በተለይ በአዲስ አበባ ላይ በሚያሳየው የአፈና አካሄድ ዙሪያ በፓርቲው ቁጥጥር ኮሚቴ አማካይነት ሂሳዊ ምክከር መደረግ አለበት፡፡ አሁን ኦህዴድ እያሳየ ያለውን አይነት በገዥነት ላይ የተቀመጠን ፓርቲ ጥፋቶች ለማረም የሚደረግ የውስጠ ፓርቲ እንቅስቃሴ መመራት ያለበት በፓርቲው ቁጥጥር ኮሚቴ እንጂ  በራሱ በታራሚው ባለስልጣን ፓርቲ አይደለም፡፡
እንዲህ ያለውን መደበኛ የፓርቲ ቁጥጥር ከማካሄዱ ባሻገር የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች (አጋር የሚለው መጥፋት አለበት) ኦህዴድ እያሳየ ያለውን ህወሃትን የመተካት አምባገነናዊ አካሄድ ለመቆጣጠር፣ የእርስበርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡ የሃገር አንድነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከተውን የኦህዴድ ኦነጋዊ ዝንባሌ በመድፈቅ ረገድ በጋራም ሆነ በተናጠል ጠንካራ አቋም ሊኖራቸው ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ ኦዴፓ፣ የአዲስ አበባ የእኔ ናት የሚል መግለጫውን ተከትሎ፣ ብአዴን/አዴፓ እና ደኢህዴን ያወጡት ጠንከር ያለ መግለጫ በጥሩ ጅማሬነቱ የሚያዝ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በሃገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ከኦህዴድ ጋር ሆነው የህወሃትን የበላይነት ለማስወገድ የታገሉ እንደመሆናቸው፣ አሁን እያኮበኮበ ያለውን የኦህዴድ የበላይነት ለመዋጋትም ቀዳሚዎቹ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ የሚሆናቸውን ጉልበት ለማግኘት ሁለቱ አባል ፓርቲዎች እርስበርስ ተናበው ከመስራት ባለፈ አጋር ድርጅቶችንም ከጎናቸው አሰልፈው ሃገርን ከአስፈሪ ውድቀት፣ ከእርስበርስ መተላለቅ የማዳን ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚመሩትን ህዝብ አስተባብረው ሰላማዊ ትግሎችን በማካሄድ፣ ተገዳዳሪ ጉልበት እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ፡፡

ኦህዴድ/ኦዴፓ የበላይነቱን ለማስተማመን እየሰራ ያለው፣ የኦሮሞ ብሄርተኞችም የፖለቲካ ጥቅማቸውን እጅግ በተለጠጠ መንገድ ለማስከበር እየተራወጡ ያሉት የሃገሪቱ ብዙ ቁጥር ያለውን የኦሮሞ ህዝብን ወክለናል በማለት ነው፡፡ ይህን የብዙ ነኝ ትምክህትን ለመገዳደርና ሃገርን ከውድቀት ለማዳን ሲነጣጠሉ ንዑስ የሆኑት ሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲ ድርጅቶች በአንድ መቆም አለባቸው፡፡ እነሱ በአንድ ሲቆሙ የኦሮሞ ብሄርተኞች የብዙነት ትምክህት ያበቃል፡፡ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ይህን ማድረግ ተስኗቸው፣ አሁን እያደረጉ እንዳሉት ኦህዴድ የሚሰራውን  ዝም ብለው በማየቱ ከቀጠሉ፣ ሃገራችን ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ ትርምስ መግባቷ አይቀርም፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች የኦህዴድን አካሄድ መግራት ከቻሉና በውይይት ከስህተቱ እንዲታረም ማድረግ ከቻሉ እዳ ቀለለ ማለት ነው:: ነገር ግን ኦህዴድ በተያያዘው የአምባገነንነትና የሃገርን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል ቸልተኝነት የሚቀጥል ከሆነ፣ ሃገሪቱ የሽግግር መንግስት ወደ ማቋቋም እንድትሄድ ፓርቲው ፍላጎት እንዲያሳይ ግፊት የማድረግ ህጋዊ ሰውነትም አላቸው፤ እነዚህ ፓርቲዎች፡፡ እነሱ ተጠናክረው የአንድ ፓርቲውን አምባገነንነት ለመገዳደር ከሞከሩ፣ የሃገሪቱ ህዝብም ከጎናቸው መሰለፉ አይቀርም፡፡

ከኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች በመቀጠል ኦህዴድን የማረቅ ሃላፊነት ያለው ህገ-መንግስትን የመተርጎምን ጨምሮ በርካታ የህግ ማስከበር ስልጣን ያላቸው የፌደራሉ  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት የወ/ሮ መዓዛ መስሪያ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ናቸው፡፡ ኦህዴድ መራሹ መንግስት እንደ ፓርቲ፣ የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የሚያራምደው አቋም  ህገ-መንግስቱን የሚጥስ መሆኑን ጠቅሶ፣ ወደ መስመር እንዲገባ ለማድረግ፣ ከፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ከፌደሬሽን ምክር ቤት የሚቀድም ሃላፊነት ያለው አካል የለም:: እነዚህ አካላት ከመነሻው ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ አዲስ አበባ የንትርክ መነሾ ሆና ቀጥላለች፡፡ ይህ ንትርክ አድጎና ቀጥሎ ለሚያመጣው ጥፋት፣ የወ/ሮ መዓዛ መስሪያ ቤትም ሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

የኦህዴድን ስልጣን በመግራቱ ረገድ ሦስተኛው ባለድርሻ፣ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በመሃል እጁ የያዘው የዲያስፖራው ማህበረሰብ ነው፡፡ ሃገራችን የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ ቢሆንም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቷን ለማሟላት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የምትደገፈው በዲያስፖራው መሆኑ የማያነጋግር ሃቅ ነው፡፡ ዲያስፖራው የውጭ ምንዛሬውን በመከልከልም ሆነ ተከታታይ ሰልፎችን በማድረግ በህወሃት ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ኦህዴድ የማያውቅ ስላልሆነ ዲያስፖራው ኦህዴድ እየሄደበት ያለውን አላስፈላጊ የአምባገነንነት መንገድ እንዲያቆም በተለያዩ መንገዶች መጠየቅ አለበት፡፡ ኦህዴድ ከህወሃት በተሻለ የህዝብ ድምፅ ሰምቶ የመስተካከል ነገር ካለው መልካም፤ ካልሆነ ግን የውጭ ምንዛሬን እስከ ማገድ በደረሰ ጫና ዲያስፖራው ኦህዴድ መራሹን መንግስት ማስገደድ አለበት፡፡

የኦህዴድን አላስፈላጊ አካሄድ በመግራት ረገድ ከሁሉም በላይ ጉልበታም የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ኦህዴድ መራሹ መንግስት የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በአንክሮ ተከታትሎ፣ ከፍላጎቱና ጥቅሙ ውጭ የሆኑ፣ ወደ መተላለቅ ሊመሩ የሚችሉ አካሄዶቹን እንዲያርም በተለያዩ የሰላማዊ ትግል መንገዶች ትግሉን መቀጠል አለበት፡፡
ከህዝቡ ጎን ለጎን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራንና የሲቪክ ማህበራትም እያደገ ያለውን የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ተያያዥ ጥፋቶች ለማስወገድ፣ መንግስትን ታገስ ተመለስ ማለት አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህን ነገር ለመስራት ተቀዳሚዎቹ ባለድርሻዎች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ሃላፊነትም እምነትም የሚጣልበት ፓርቲ ስላልታየኝ፣ ስለ እነሱ ምንም ማለት አልችልም፡፡

Filed in: Amharic