>
5:13 pm - Saturday April 19, 0425

የመንጋ ክፋቱ እረኛ ማጣቱ!!! (በድሉ ዋቅጅራ)

የመንጋ ክፋቱ እረኛ ማጣቱ!!!
በድሉ ዋቅጅራ
.
.
 . . . መንጋ መሆን ችግር አይደለም፤ ችግሩ ጥሩ እረኛ አለማግኘት ነው፡፡ ጥሩ እረኛ ያለው መንጋ ውሎ ይገባል፡፡ ጥሩ እረኛ መንጋው አይራብም – ግጦሽ የለመለመበትን ያውቃል፤ ጥሩ እረኛ መንጋው አይጠማም –  ምንጩ የሚንፎለፎልበትን፣ ዥረቱ የሚገማሸርበትን ያውቃል፡፡ ባለ ጥሩ እረኛ መንጋ እግር በጣለው አይሄድም – መንገዱ በእረኛው ይመረጣል፡፡ ባለ ጥሩ እረኛ መንጋ የአውሬ እራት አይሆንም –  በእረኛው ይጠበቃል፡፡ የመንጋ ችግሩ ጥሩ እረኛ ማጣት ነው፡፡
.
 . . . ህዝብ መንጋ ነው፡፡ ጥሩ እረኞች አስካሉት ድረስ ህዝብ ጥሩ መንጋ ነው፡፡ ጥሩ እረኞች ከሌሉት ህዝብ መጥፎ መንጋ ይሆናል፡፡ የህዝብ እረኞች የሀሳብ ልእልና ያላቸው መሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የመብት ተሟጋቿች፣ . . . ወዘተ. ናቸው፡፡
.
 . . . .እረኛው እሾህና ጋሬጣው እየዘነጠለው፣ ዝናብና ጸሀይ እየተፈራረቀበት ለመንጋው ግጦሽና ምንጭ እንደሚያመቻች፣ ከአውሬ እንደሚጠብቅ፣ መሪዎች የህዝባቸውን ብልጽግናና ሰላም ለመጠበቅ መከራን ወደው ይቀበላሉ፤ መከራን ሸሽተው ወይም ድሎትን ፈልገው መንጋ ህዝባቸውን ለአፍታ ቸል አይሉም፡፡
.
 . . . አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ዝምድናው ምክንያትን መሰረት ካደረገ ሀሳብ ልእልና ይልቅ ጎሳዊነት የወለደው ስሜት ነው፡፡ ይህ የመጣው ደግሞ የሀሳብ ልእልናን የጨበጠ፣  እውነትን በድርጎ ያልለወጠ እረኛ መሪ በመጥፋቱ ነው፡፡ የፖለቲካ ኢሊቶች፣ የመብት ተሟጋቿች (አክቲቪስቶች)፣ የሀይማኖት አባቶች፣ . . . ወዘተ. አንድም የሀሳብ ልእልና የላቸውም፣ አንድም በእለት ድርጎ ለውጠውታል፡፡
.
. . . .መንጋ መሪ ሲያጣ ወይም የሀሳብ ልእልና የሌለው ‹‹መሪ›› ሲያጋጥመው፣ እራሱን በራሱ ይመራል፡፡ እንደህ ሲሆን ነው – በመንጋ መደገፍ፣ በመንጋ መቃወም፣ በመንጋ ማፍቀር፣ በመንጋ መጥላት፣ የመንጋ ፍትህ . . . ወዘተ. የሚጀመረው፡፡ እንዲህ ሲሆን መንጋው በሀሳብ ልእልና መመራቱ ይቀርና፣ በደመነፍስ ይመራል፡፡
Filed in: Amharic