>

ክቡር ጠ/ሚኒስትር እኛ ከትንሳኤ ይልቅ መቃብር የሚስበን ጨለምተኞች አይደለንም!!! (መስከረም አበራ)

ክቡር ጠ/ሚኒስትር እኛ ከትንሳኤ ይልቅ መቃብር የሚስበን ጨለምተኞች አይደለንም!!!
መስከረም አበራ
ጠ/ሚ አብይ ለትንሳኤ በዓል ያስተላለፉት መልዕክት ከስነ-ፅሁፋዊ ውበቱ በመለስ ለፖለቲካችን ህማም አንዳች የድህነት ተስፋ የሚያቀብል ሆኖ አልታየኝም፨ በጠንካራ መሪ ክንዶች በታች የመተዳደር መተማመንን በኔ ቢጤው ተመሪ ልቦና የሚያሳድር ሆኖ አላገኘሁትም።
ጠ/ሚ አብይ በመግለጫቸው የሃገራችንን ግራ አጋቢ የፖለቲካ ሁኔታ ከክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ መለኮታዊ ተዓምራት ጋር እያናፀሩ በመንፈሳዊው አለም እንደሆነው እንድናደርግ የሚፈልጉ ይመስላሉ። ነገሩ አይከፋም ነበር ግን ትልቁ ችግር የፖለቲካው አለም ከመንፈሳዊው አለም በእጅጉ የሚለይ መሆኑ ነው፨
 እርሳቸው ከሚመሩት ህዝብ ውስጥ ስንት ስንተኛው እሳቸው ያናፀሩበትን መንፈሳዊ መርህ ያምናል? ከሁሉ በላይ ፖለቲካ እንደ መንፈሳዊ አለም እምነት ሁሉ ተጥሎ  የሚረጋጉበት አለም አይደለም። በመንፈሳዊ አለም ሰው ሃሳቡን የሚጥለው በሁሉን ቻይ ታማኝ ፈጣሪ ላይ ነው ፤በፖለቲካው አለም ደግሞ እንደ እርሳቸው ባለ ሰው ላይ ነው።ሰው ደግሞ እንደመለኮት  ቃል ከተግባር ላይገጥምለት ይችላል። ፈጣሪ በሰው አድሮ ፖለቲካውን ያበጃል ብለን እርሳቸው እንደፈለጉት እንደ ዮሃንስ ፀንተን እንዳንጠብቅ ሰው ያውም ፖለቲከኛ ለፈጣሪ ፈቃድ ማህደርነት መብቃት አለመብቃቱን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።የእርሳቸው ፓርቲ  ተለዋዋጭ ባህሪ ለዚህ አንድ ምስክር ይሆናል። “መቃብር ጠባቂ” ያደረገንም ይሄው የማይጨበጠው የፓርቲያቸው አመል እንጅ እኛ ከትንሳኤ መቃብር የሚስበን ጨለምተኞች ስለሆንን አይደለም።
 ነገሩን ከእኛም አንፃር ማየት አለባቸው። በየቀኑ ሞት፣ስደት ፣መፈናቀል እየሰማን፤ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ እየሆነብን ፣በዘረኛ የህግ አካላት ተከበን በምን ተስፋ እናድርግ? እርሳቸው ይህን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ምን እንደሆነ ማወቅ ሳንችል በምን ላይ ቆመን ተስፋ እናድርግ? ዮሃንስ ኮ በትንሳኤው ተስፋ የፀናው የተሰቀለው የእግዚአብሄር ልጅ መሆኑን ያውቅ ስለነበር ነው።እኛ የምናውቀው ሃቅ የእርሳቸው መንግስት በዘር ሃረግ ቆጠራ የቆመ መሆኑን ነው ፣ባልተዘራንበት መሬት ያለን እኛ ታዲያ በምን ተስፋ እናድርግ? ለእኛ ተስፋችን ህግ ሲያድን ስናይ ነበር። በተጨባጭ ግን ዘር ብቻ ያድናል።እንዲህ ዘር ባንዘረዘረው ምድር ተስፋ እና እምነት ከወዴት ይበቅላል?
 በአብይ መግለጫ ውስጥ የእርሳቸውን መቸገርም አስተውያለሁ። ይህ የሚጠበቅ ነው። ወደ ስልጣን ሲጣደፉ ያኔ ጀምሮ ስልጣኑ የደስታ የፍሰሃ እንደማይሆንላቸው ጠርጥሬ ነበር። መለስ ዜናዊ የተቀመጠበት መንበር እንዴት ሊደላ?! መለስ ወንበሩ ለእርሱ ብቻ እንዲመች አድርጎ ያበጃጀው ሰው ነው- ወንበሩ  እሱ ሲነሳበት የሚበቅል እሾክ አሜኬላ ሰግስጎ የሄደ ፨
 ይህን እሾክ ለመንቀል ከእሾክ ተካዩ  መለስ ዜናዊ መንፈስ መላቀቅ ያስፈልጋል። አብይ ከዚህ መንፈስ ነፃ ናቸው?ከሆኑስ እምነታቸው የሚፈልገውን መስዕዋትነት ከፍለው በድል ለመቆም ምን ያህል ፅኑ እና ዝግጁ ናቸው? ባገኛቸው የምጠይቃቸው ዋናው ጥያቄ ይህ ነው!
Filed in: Amharic