>
10:24 am - Tuesday July 5, 2022

የአዴፓ መግለጫ ተገቢም ትክክልም አይደለም! (ውብሸት ሙላት)


የአዴፓ መግለጫ ተገቢም ትክክልም አይደለም!
ውብሸት ሙላት
ስለ ታቀደዉ ሰልፍ እስካሁን ድረስ ምንም አስተያየት አልሰጠሁም ነበር፡፡ ሰልፉንበመቃወም ግን አይደለም፡፡ በፍጹም ሊሆንም ስለማይችል፡፡ አሁን አስተያየት እንድሰጥ ያደረገኝ አዴፓ ከመሸ በኋላ የሰጠዉ ነዉ፡፡
በዛሬዉ ዕለት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች የተጠራዉን ሰላማዊ ሰልፍ በሚመለከት አዴፓ ያወጣዉን መግለጫ አየሁት፡፡ ይህ መግለጫ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡
አንዱ መግለጫዉ የወጣበት ጊዜን የሚመለከት ነዉ፡፡  ሀሙስ የሚካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ የተጠራዉ ዛሬ አይደለም፡፡ ቀናት አልፈዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት ዉስጥ በአዎንታም በአሉታም መግለጫ አላወጣም፡፡ ሰልፍ ለመዉጣት የሚያስፈልጉ ጥሪዎች ከተደረጉ፣ የተለያዩ መግለጫዎች ከወጡ፣ በሰልፉ መያዝ ያለባቸዉ መልእክቶች ከተዘጋጁ በኋላ በሞተ ሰዓት ሰልፍ መደረግ የለበትም ብሎ መግለጫ ማዉጣት የሰልፉን ሁኔታ የሚያበላሽ፣ እየሞተ እየተበደለ ያለን ሕዝብን እልክ የሚያስገባ መግለጫ ነዉ፡፡ ሰልፉንም ወደ ግጭት ሊቀይር የሚችል መግለጫ ነዉ፡፡ ባለቀ ሰዓት ሰልፍን መኮነን፣ ሰልፉ እንኳን ቢደረግ የሚያቀርቡትን መልእክት መስማት አለመፈለግን ያሳያል፡፡ ይህ መግለጫ መዉጣት ከነበረበት በሞተ ሰዓት ሊሆን በጭራሽ አይገባዉም ነበር፡፡ በጭራሽ….. በጭራሽ!!!!!
ሁለተኛዉ መግለጫዉ ቅድሚያ የሰጠዉ ጉዳይን የሚመለከት እና የተገለጸበት ድምጸት ጋር የተገናኘ ነዉ፡፡ መግለጫዉ አርብ በባህርዳር ስለሚከናወነዉ የጣናፎረም ቅድሚያ ሰጥቷል፡፡ አዎ ልክ ነዉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉባኤዎች ለመልካም ገጽታም፣ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም የሚኖራቸዉን ፋይዳ ማንም ሰዉ አይስተዉም፡፡ ደግሞም፣ የአማራ ሕዝብ እየተጎዳም እየሞተም እንዲህ ዓይነት ጉባኤዎች እንዲከናወኑ ሁልጊዜም ሲሰራ ኑሯል፡፡ አሁንም ይሰራል፡፡ ወደፊትም ይሰራል፡፡
 ሕይወቱንም ሁሉ እየገበረ የሰሜን ተራራን ቃጠሎ ለማዳን ሲዋደቁ ከርመዋል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ እንኳን አማራ ላይ ደረሰዉን በደልና ጥቃት አዴፓም ያዉቀዋል፡፡ ሕዝብም ያዉቀዋል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡ አማራ እየሞተ ነዉ፡፡ በጫካዉና በየጥሻዉ በአሰቃቂ ሁኔታ በቀስት እየሞተ አዴፓ ቅድሚያ ለገጽታ ግንባታ መጨነቁ ኢሰብአዊ  ያደርገዋል፡፡ መግለጫዉ ከህልዉና ይልቅ ስምን ማስቀደሙ ጨካኝ አድርጎታል፡፡ ጨካኝ መግለጫ ነዉ፡፡ ቢያንስ በሌላ መልኩ መግለጽ እየተቻለ ስለ ገጽታ ግንባታ መጨነቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
 በዚያ ላይ፣ በዚህ መንገድ የማይወዳደሩ ጉዳዮችን አወዳድሮ ለመልካም ስም ቅድሚያ መስጠት ሕዝብን የሚያበሳጭና እልክ ዉስጥ ሊያስገባ ስለሚችል እንደዉም ሰላማዊ የመሆኑን እድል የማወክ ሚና አለዉ፡፡ ከዚህ ይልቅ፣ ባህርዳርን በሚመለከት አጠር ባለሰዓት እንዲጠናቀቅ፣ ሕዝቡም ባህርዳርን ከአዴፓ በላይ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚጠብቃት የሚሳሳለት ስለሆነች ሰልፉ የባህርዳር ሕዝብን የጨዋነት ልክ የሚያሳይ እንዲሆን ማገዝ ተመራጭ ነዉ፡፡ ባለቀ ሰዓት የባህርዳርን ሕዝብ ማስከፋት ተገቢ አይደለም፡፡
ሦስተኛዉ የመግለጫዉ ስህተት የይዘት ነዉ፡፡  በዉስጡ የያዛቸዉ እዉነታዎች አሉ፡፡ ይህ ግልጽ ነዉ፡፡ የይዘት ስህተቱ ብዙ ነዉ፡፡ በዚያ ላይ ሕዝብን የመከፋፈል ዓላማ ያደረገ መግለጫ ነዉ፡፡ የይዘት ችግሮቹን መግለጽ አንድምታዉ ለአዴፓም ጥሩ ስላልሆነ ልተወዉ፡፡
በአጭሩ ግን፡- በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ብቻ የአማራ ሕዝብ ላይ ከደረሰዉ በደል አንጻር፣ (የጎንደሩን ትቼ) አዴፓ ሥልጣኑን ለሕዝብ ማስረከብ ነበረበት፡፡ እንደዚያም ሆኖ ሕዝብ አዴፓን እያገዘ ነዉ፡፡ ሕዝብ እያገዘዉ ሳለ፣አዴፓ ግን እንደ መታገዙ እየሠራ አይደለም፡፡ እየሠራም ባይሆንም እንኳን አሁንም ሕዝቡ እያገዛችሁ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግሥት ከሥራዉ በበለጠ የ Communication Crisis ላይ ወድቋል፡፡ አንዳንድ የአዴፓ አመራሮች ከሥራችሁ ይልቅ ንግግራችሁ ሕዝብን እያስቆጣ ነዉ፡፡ ይህንን የተግባቦት ቀዉስ በፍጥነት አስተካክሉ፡፡ በቀዉስ ወቅት ላይ አነጋገራችሁ ከተቃወሰ ተጨማሪ ቀውስ እየጨመራችሁ ነዉ፡፡ የአሁኑ መግለጫም ቢሆን ከዚሁ አልተላቀቀም፡፡
የሆነዉ ሆኖ፣ የነገዉ ሰልፍ አዴፓን ሥልጣን ለማስለቀቅ አይደለም፤አይሆንምም፡፡ በግሌም እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሲፈጸም ብመለከት የመጀመሪያዉ ተቃዋሚ ነዉ የምሆነዉ፡፡ ስለሆነም፣እየሞተ ያለን፣ እየሞተም የሚደግፋችሁን ሕዝብ አታስቀይሙት!!!! የነገዉ ሰልፍ የአማራ ሞት እና በደል ይቆም ዘንድ ምናልባትም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያደርገዉ ሰልፍ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ አዴፓዎችም መግለጫችሁን ተዉት! አይጠቅማችሁም፡፡ ጎጂ ነዉ፡፡ መግለጫዉ የበረከት ስምኦን ነዉ የሚመስለዉ! እጠፉት ዉሳኔያችሁን!
የሰልፉ አዘጋጅ ባልሆንም የዐማራ ሞትና ሥቃይ እንቅልፍ ያሳጣኝ፣ አሁን ደግሞ ምን ሆኖ ይሆን እያልኩ ሌሊቱን አላምነዉ ብዬ ቁጭ ብዬ የማድር፣ የማንም ፓርቲ አባል ያልሆንኩ አማራ ነኝ!!!!
Filed in: Amharic