>

ተምሬ ተምሬ...¡ ተምሬ ተምሬ....¡ (ዳንኤል ክብረት)

ተምሬ ተምሬ…¡ ተምሬ ተምሬ….¡
ዳንኤል ክብረት
አብሮ አደግ ጓደኛዬን ባለፈው አሜሪካ አገኘሁት፡፡ ጽኑ ሰው ብርቱ ኃይል፡፡ በትምህርት ድህነት ይፈረከሳል ከተባለ ቁጥር አንድ መዶሻው እርሱ ነው፡፡ የእናት የአባቱ ቤት ከትምህርት ቤታችን ስድስት ሰዓት ይርቃል፡፡ ይህን ሁሉ እየተጓዘ መማር ስለማይችል ከትምህርት ቤቱ የአንድ ሰዓት ርቀት ላይ ቤት ተከራይቶ ነበር የሚማረው፡፡ ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ገጠር ቅዳሜ ጠዋት ይሄድና እሑድ ከሰዓት ስንቁን ቋጥሮ ይመለሳል፡፡ ያችን ስንቅ ቆጥቦ ከሰኞ እስከ ዓርብ ይመገባል፡፡ ነገን ዛሬ ላይ ለመትከል እንደሚቻል አምኖ የሚያገኘውን ዕድል ሁሉ ይጠቀማል፡፡ እርሱን ፈተና አያሸንፈውም፤ እርሱ ራሱ የኑሮ ፈተናዋ ነው፡፡ እርሱ ፈተና የሚገጥመው ወላጅ አምጡ የተባለ ዕለት ነው፡፡ ስድስት ሰዓት ተጉዞ የሚመጣ ወላጅ አያገኝም፡፡ ጉዳዩን ራሱ ለወላጆቹ ማስረዳት ከባድ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የርሱ ወላጆች ይቀያየራሉ፡፡ አንድ ቀን ያንዱን፣ ሌላ ቀን ደግሞ የሌላውን ወላጅ ይወስዳል፡፡
ጽሑፉ እንደ ጤፍ የደቀቀ፣ ነገር ግን እንደ ቆሎ የደመቀ ነው፡፡ ለምንድን ነው? ስንለው ‹ደብተር ቶሎ እንዳያልቅብኝ ነው› ይላል፡፡ የተሰጠውን የቤት ሥራ እዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ በጊዜ ይሠራል፤ የታዘዘውን ያለ ማመንታት ይፈጽማል፤ ክፍል ውስጥ ላለመረበሽ ሁልጊዜ ይጥራል፡፡ ከመምህራኑ ጋር የጌታና ሎሌ ዝምድና አለው፡፡ ይታዘዛቸዋል፤ ያገለግላቸዋል፡፡ ለምንድን ነው? ስንለው ‹ወላጅ አምጣ እንዳይሉኝ ነው› ይላል፡፡ ለእርሱ አንድ ኤክስ ማግኘት ማለት ከሕይወቱ መሥመር አንድ ርምጃ ወደኋላ መመለስ ማለት ነው፡፡
ከሁሉም ነገር የማይረሳኝ ቀልዱ ነው፡፡ ችግሩን ሁሉ የሚረሳው በቀልድ ነው፡፡ አንድም ቀን አመመኝ ብሎ ቀርቶ አያውቅም፡፡ ሲያመር እንጂ ሲያማርር አይቼው አላውቅም፡፡ ሲቆርጥ እንጂ ሲያቋርጥ አላውቀውም፤ ድኻ ካልቀለደ፣ ሀብታም ካልሳቀ እድሜው ያጥራል ይል ነበር፡፡
ዛሬ ያ ሁሉ አልፎ አሜሪካ ገብቶ፤ ሳንፍራንሲስኮ ውስጥ ለአንድ ትልቅ የኮምፒውተር ፕሮግራም ሠሪ ኩባንያ ባለ ሥልጣን ሆኖ ይሠራል፡፡ ስንገናኝ የጥንቱን ብርታቱንና ጽናቱን አንሥቼ አደነቅኩት፡፡ ቀልዱ አሁንም አልተለየውም፡፡
‹መቼም ጀግና ነህ፤ ያንን ሁሉ አልፍህ እዚህ ደረስክ፤ እኔ ለልጆቼ የትጋትና የጽናት ተምሳሌት አድርጌ ሁሌ ስላንተ እነግራቸዋለሁ፡፡ ትምህርት ራስንም ዓለምንም እንደሚቀይር ስነግራቸው አንተን አነሣላቸዋለሁ፡፡ ‹ተማር ልጄ› የሚለው ዘፈን ላንተ የተሠራ ሁሉ ይመስለኛል፡፡› አልኩት፡፡
‹ምን ዋጋ አለው› አለኝ እየቀለደ፡፡
‹እንዴት ነው ዋጋ ሌለው፤ አንተን ከእንትን ገጠር አንሥቶ ሳንፍራንሲስኮ እዚህ ትልቅ ኩባንያ የዶለህ ትምህርት አይደለም እንዴ!› አልኩት፡፡
‹ባክህ የተማርኩበትን አላገኘሁትም› አለኝ፡፡
‹ከዚህ በላይ ምን ለማግኘት ነበር የፈለግከው፤ የሰው ፍላጎትና መቃብር መቼም አይሞላም› አልኩት ተገርሜ፡፡
‹ትዝ ይልሃል? የቡድን ሥራ ተሰጥቶን እነ ሜላት ቤት ስንሄድ› አለኝ፡፡ አስታወስኩ፡፡ ሜላት የሞጃ(የሀብታም) ልጅ ናት፡፡ አባቷ ባለ ሥልጣን ነበሩ፡፡ የቡድን ሥራችንን ሠርተን ልንወጣ ስል እናቷ ሻሽ የመሰለ እንጀራ በአዋዜ ያቀርባሉ፡፡
‹እነ ሜላት ቤት ያንን ሻሽ የመሰለ ነጭ ጤፍ ስንበላ ምን እንደምመኝ ታውቃለህ?›
አንገቴን ዘምበል አድርጌ ‹ምን ነበር?› በሚል ስሜት አየሁት›
‹ተምሬ፣ ሥራ ይዤ፣ ነጭ ጤፍ መብላት› አለና ሳቀ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ነጭ ጤፍን ማን ያገኘዋል፡፡ ለዚያውም ቀበሌ ካመጣው ነው፡፡ መጀመሪያ የኢሠፓ አባላት፣ ከዚያ ተለዋጭ አባላት፣ ቀጥሎ ሌሎች ባለ ሥልጣናት ወስደው በመጨረሻ ሕዝቡ ጋ ሲደርስ ያልቃል፡፡
‹ምን ዋጋ አለው ታድያ፤ እኔ ነጭ ጤፍ እበላለሁ ብዬ ተምሬ ስደርስበት፤ ነጭ ጤፍ መብላት አይጠቅምም፤ ዋናው ጠቃሚው ጥቁር ጤፍ ነው ብለውኝ ዕርፍ፤ ጥቁር ጤፍ ለመብላት ምን ትምህርት ያስፈልገው ነበር፡፡ አባቴኮ ነጩን ጤፍ በውድ ዋጋ ስለሚሸጠው ነው ለቤታችን ጥቁር ጤፍ የሚፈጨው፡፡ ጥቁር ጤፍ ለመብላትማ ያን ሁሉ ለፍቶ መማር አያስፈልገኝም ነበር፡፡› ሳቀ፡፡ ገረመኝ፡፡
‹የአብዮት በዓል ሲከበር ቀበሌ ተጠርተን ለስላሳ ስንጠጣ ታስታውሳለህ› አለኝ፡፡ ትዝታውን ቀሰቀሰብኝ፡፡ የአብዮት በዓል ብቻ ሳይሆን የሕጻናት በዓል ሲከበርም ቀበሌ ተጠርተን ለስላሳና ኩኪስ ተጋብዘን ስለ አብዮቱ ይነገረን ነበር፡፡የአብዮት መዝሙርም እንዘምር ነበር፡፡ ብዙዎቻችን ለስላሳ እንደልብ የምናገኘው ያን ቀን ስለሆነ በዓሉን እንናፍቀዋለን፡፡ ካልታመመክ ለስላሳ ማን ይሰጥሃል?
‹ያኔ ምን እንደምመኝ ታውቃለህ? ተምሬ ሥራ ይዤ ገንዘብ ሲኖረኝ እንደልቤ ኮካ፣ ሚሪንዳ፣ ፔፕሲ፣ ስፕራይት በያይነቱ መጠጣት፡፡ ውኃ ከዚያ በኋላ ንክች የማደርግ አይመስለኝም ነበር፡፡ ውኃማ የሬሳ ማጠቢያ ነው ይሉ ነበር ሐጅ ዓሊ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው› አለና አሁንም ሳቀ፡፡
‹ደግሞ ምን ልትል ነው?› አልኩት
‹ተምሬ፣ ለፍቼ፣ ደክሜ፣ ታግዬ እዚህ ደረስኩና ገንዘቤን ሆጨጭ አድርጌ ያንን የናፈቅኩትን ለስላሳ እጠጣለሁ ስል ምን ቢባል ጥሩ ነው? ለስላሳ መጠጣት ለጤና ጥሩ አይደለም፤ መጠጣት ያለበት ንጹሕ ውኃ ነው ብለው ቁጭ፡፡ እኔ ያንን ሁሉ የለፋሁት የጣናን ውኃ ለመጠጣት ነው እንዴ? እርሱንማ ሳልማር አገኘው ነበርኮ፤ ዋናው የተማርኩት ለስላሳ እንደልቤ ለመጨለጥ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤት ወጥተን ስንሄድ እነ ሳሙኤል ከጮርናቄ ቤት ለስላሳ ገዝተው እየጠጡ እንዴት ነበር የሚያስቀኑን? ‹ኮካውን ጠጥቼ ውኃው ሲቀር እሰጣችኋለሁ› እያለ ያሾፍብን ነበር፡፡ አሁን እዚህ ስደርስ የተማሩና ሀብታሞች ውኃ ይጠጣሉ፤ ያልተማሩና ድኾች ለስላሳ ይጠጣሉ፡፡ ተምሬ ተምሬ ሳልደርስበት ቀረሁ፡፡› አለ ውኃውን እየተጎነጨ፡፡
‹ያቺ የማደርጋትን ቁምጣ ታስታውሳታለህ. አለኝ በእጁ የቁምጣዋን መጠን ጭኑ ላይ እያሳየ፡፡ ትዝ አለኝ፡፡ ከግልገል ሱሪ ትንሽ ከፍ ያለች ቁምጣ ያደርግ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ‹እንደ ስሜነህ ልትሸፍት ነው እንዴ› እያሉ ይቀልዱበት ነበር፡፡
‹ቦላሌ ማጥለቅኮ እንደኔ ላለ ሰው ብርቅ ነበር፡፡ እኛ ሠፈር አንድ የከተማ ሰው ቦላሌ አጥልቆ ሲመጣ ‹እገሌኮ ተምሮ ቦላሌ ሰደደ› ይባልለት ነበር፡፡ እኔም የተማርኩት ቦላሌ ለመስደድ ነበር፡፡ አሁን እዚህ ደርሼ ጎረምሳው ሁሉ በውድ ዋጋ ምን የመሰለ ቁምጣ ሲያደርግ ሳየው ገረመኝ፡፡ እንዲያውም ቁምጣ ለብሶ፣ ባርባሶ የመሰለ ጫማ አድርጎ እንደ ቀትር ጋኔን አሸዋ ላሸዋ የሚንከራተተው ሀብታሙ ነው፡፡ ቦላሌ እኔ ስደርስባት ሸሸች፡፡ ለቁምጣ ለቁምጣማ ምን ምን የመሰሉ ቁምጣዎች ነበሩኝ፡፡ አልተገናኝቶም ወዳጄ፡፡ ድሮ ቀዳዳ ሱሪ ስታደርግ ‹የድኻ ልጅ› ትባል ነበር፡፡ እኔኮ ቦላሊዬ ሲቀደድ የሰው መሳቂያ ላለመሆን ብዬ ነበር ጎምጄ ጎምጄ ቁምጣ የማደርገው፡፡ እኔ ስደርስበት ቀዳዳ ሱሪ ፋሽን ይሁን? ቀዳዳ ሱሪ በገንዘብ ለመግዛትማ አልማርም ነበር!›
‹ኀሙስ ምረቴ ሥጋ ቤትን ታስታውሰዋለህ?›
‹ዛሬ ይሄ ሰው ምን ነክቶታል› አልኩ፡፡ በትዝታ ሊጨርሰኝ ነው እንዴ፡፡ እንዴት እረሳዋለሁ፡፡ ‹ኀሙስ ምረቴ፣ ምሳና እራቴ፣ ብር ባይኖረኝም ጣልልኝ በሞቴ‹ የተባለለት ምርጡን ሥጋ ቤት እንዴት እረሳዋለሁ፡፡
‹እኔ በዚያ በኩል ነበር ትምህርት ቤት የምመላሰው፡፡ ሁልጊዜ ምራቄን እንደዋጥኩ ነው፡፡ የቢላዋው የፍጭት ድምጽ ራሱ አሁን ድረስ ይሰማኛል፡፡በዚያ ባለፍኩ ቁጥር አድጌ፣ ተምሬ፣ ገንዘብ አግኝቼ ሥጋ ለመቁረጥ ለራሴ ቃል እገባለሁ፡፡ ‹ጠጅ ጨለጠ፣ ሥጋ ቆረጠ› የሚለውን አማርኛ ላይ ብቻ ተምሬውማ አልቀርም እል ነበር፡፡ ሄድኩ፣ ደረስኩበት፡፡ ግና ምን ዋጋ አለው›
‹እንዴ አንተ ሰውዬ ሁሉንም ነገር ምን ዋጋ አለው ብለህ ልትጨርሰው ነው እንዴ? ሲያትልኮ ጥሬ ሥጋ ይሸጣል ለምን አትሄድም› አልኩት፡፡
‹ስደርስበት ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ሥጋ ለሰውነት ጥሩ አይደለም፡፡ መበላት ያለበት ቅጠላ ቅጠል ነው ብለውኝ እርፍ፡፡ እኔ የትምህርት መጨረሻው ቅጠል መብላት መሆኑን ባውቅ መች እንዲያ እለፋ ነበር፡፡ ቅጠልማ ዓባይ ዳር ሞልቶ አልነበር አይደል እንዴ፤ ምን ሳንፍራንሲስኮ ድረስ ያለፋኛል፡፡ እዚህ ወዳጄ ሞጃው ሁሉ ‹ኦርጋኒክ› እያለ ቅጠል ሲሰበስብ ይውልልሃል፡፡ ቅጠል ቢሉህ ደግሞ ቅጠል መሰለህ? ሣሩንም አረሙንም፤ ሙጃውንም፣ አረግሬሳውንም፣ ሳማውንም፣ ኮሸሽላውንም ነው ሰላጣ እያሉ የሚበሉት፡፡ እሱንማ እንኳን እኔ ከብቶቻችንም እንደልብ ያገኙት ነበር፡፡›
‹ወይ አንተ ሰው፤ በቃ ቀልደኛነትህ አልለቀቀህም› አልኩት ተገርሜ
‹ልንገርህ ይልቅ፤ አባ አድጎን ታስታውሳቸዋለህ› አለኝ፡፡ እንዴት ይረሳሉ፡፡ የከተማው ዝነኛ ባለ ዳቦ ቤት፤ ዳቦ ሸጠው ሸጠው ሊጨርሱ ሲሉ ቀሪውን ለድኻ የሚያከፋፍሉት አቦይ ሐድጎ እንዴት ይረሱኛል፡፡ ዳቦ ሊገዙ ለተላኩ የድኻ ልጆች ‹ይሄ ላንተ ነው› ብለው ዳቦ የሚሰጡት ደግ ሰው እንዴት ይረሱኛል፡፡
አባ አድጎን በልቼ ሆዴ ከተነፋ
እንደ ጣና ልስፋ እንደ ዓባይ ልጋፋ
የተባለላቸው ሰው እንዴት ይረሱኛል፡፡
‹የርሳቸውን መኪናስ ታስታውሳታለህ› የአባ አድጎ መኪናኮ የከተማው መኪና ናት፡፡ ማን ይረሳታል፡፡ ዳቦ ዳቦ የምትሸት መኪና፡፡
‹እኔ ተምሬ የአባ አድጎን ዓይነት መኪና መንዳት ነበር የምመኘው፡፡ የግራ እጃቸውን ክንድ በመስኮት ወጣ አድርገው በቀኛቸው በኩል ከተቀመጠው ሰው ጋር እያወሩ፤ አላፊ አግዳሚው ክንብንቡን አውርዶ እጅ እየነሣቸው ከተማዋን ያቋርጧታል፡፡ እንደዚያ ሆኜ መንዳት ነበር የሚያምረኝ፡፡ አሁን እዚህ ስደርስ ‹ወክ አርግ› ይሉኛል፡፡ እኔ ለራሴ እድሜ ልኬን ወክ ሳደርግ የኖርኩ ነኝ፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ በዚህ ዞረን፣ በዚያ ወርደን፣ በወዲያ ወጥተን ወክ አደረግን፤ ሮጥን፣ ሸመጠጥን ይላሉ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ መሥሪያ ቤቱ ወክ የሚደረግበት ቀን ያዘጋጃል፡፡ ዓለመኞች ናቸው፡፡ ወክ ለማድረግ ምን ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ እኔ የተማርኩት መኪና ልጋልብ እንጂ ወክ ላደርግ ነው እንዴ? ለወክ ለወክማ ምን ማትሪክ መበጠስ ያስፈልጋል፡፡›
‹ዛሬ ተነሥቶብሃል፤ ና ወክ እያደረግን አውራኝ› እልኩና ከመቀመጫዬ ተነሣሁ፡፡
‹ወክ አላረግም፤ ከፈለግክ ና በመኪና እየሄድን ላውራህ› አለና መኪናውን ከፈተ፡፡
‹በመጨረሻ አንድ ነገር ላውራህ›
‹አሁን ቅቤ ለምኔ ዘይት ቤት ነው የቀረህ› አልኩት፡፡
‹አየህ ካብሮ አደግ ጋር ማውራት የረሱትን ለማስታወስ ይጠቅማል፡፡ ቅቤ ለምኔ የተባለውኮ ቅቤ ውድ ስለሆነ ነው፡፡ የጥባ ኑግ ሽሮ እየበላሁ ያደግኩትን ልጅ ‹ቅቤ ጥሩ አይደለም፤ ኮለስትሮል ያመጣል› ሲሉኝ እናደዳለሁ፡፡ ባዶውን ለመብላትማ የእናቴ ማርሳ ወጥ ምን አለኝና ስድስት ሰዓት በበርባሶ እየተጓዝኩ እማራለሁ?›
‹መኪናውን ሳያስነሳ ተወዉ፡፡
‹እንሂድ እንጂ› አልኩት፡፡ ቀበቶዬን እያሠርኩ፡፡
‹እኔ ቤት ስትመጣ አልጋዬን ታስታውሰዋለህ?›
‹እሱ ደግሞ ምን አረገህ?›
‹በሰባት ብር ከቅዳሜ ገበያ ነበር የገዛሁት፡፡ የአልጋው ቦንዳ እየረገበ ሲያስቸግረኝ ከጣውላ ቤት ለመንኩና ኮምፔልሳቶ አጋደምኩበት፡፡ ደረቅ ነው፡፡ ሬሳ ሳጥን ውስጥ ማደር በለው፡፡ ለነገሩ ስገላበጥ ቋ-ቋ-ቋ ሲል ይቀሰቅሰኝና አጠናለሁ፡፡ አንድ ቀን እነ ሳምሶን ቤት ሄጄ ያየሁት አልጋ፡፡ ሞዝቦልድ ይባላል ነበር ያለኝ፡፡ ፍራሹ፣ አልጋው ሲመች፡፡ እላዩ ላይ ስትወጣ ይዞህ ይሰምጣል፡፡ እዚያ አልጋ ላይ ዕንቅልፍ ሳይሆን የሚወስድህ ራሱ አልጋው ዕንቅልፍ ነው፡፡ እነርሱ ታድያ ዘበናዮች ይዘሉበት ነበር፡፡ ያ አልጋ ዓይኔ ላይ አለ፡፡ ‹ተምሬማ እርሱን አልጋ ካልዘረጋሁት ሞቻለሁ› ነበር የምለው፡፡ እዚህ መጣሁና ሁለት ፍራሽ የተደራረበበት ቤተ መንግሥት የመሰለ አልጋ ገዛሁልህ፡፡ ያንን የኮምፔልሳቶ አልጋ ልበቀል፡፡ በኋላ ወገቤን ሲያመኝ ሐኪም ቤት ሄድኩ፡፡ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ለጤና ጥሩ ደረቅ አልጋ ነው ብሎኝ እርፍ፡፡ ደረቅ አልጋማ ሳልማርም ነበረችኝኮ፡፡ እኔ የተማርኩት ትምቡክ ትምቡክ የሚል ፍራሽ ላይ ለመተኛት እንጂ ለደረቅ አልጋማ ያገሬ መደብስ መች አነሰኝ ብዬው ዞር በል አልኩት፡፡ በየጓደኞቼ ቤት ስሄድ ይሄንን ደረቅ አልጋ ገድግደው ገድግደው እንደ ሞያ ያወሩታል፡፡ አይ መማር ከንቱ እላቸዋለሁ፡፡›
‹የት ነው ግን የምትወስደኝ?› አልኩት መልሶ የመኪናውን ሞተር ሲያስነሣ
‹እዚህ አደባባዩ ጋ ምርጥ ኬክ ቤት አለ፤ ልጋብዝህ› አለኝ፡፡
‹ጣፋጭስ ተዉ አላሉህም›
ሳቀና ‹የተዉኩትን ታስታውሰኛለህ› አለኝ፡፡ ‹እናቴ የምትጋግረውን ሽልጦ ታስታውሰዋለህ? እኔ ጋ ስትመጣ የምትበላው፡፡ ጠቆር ቢልም ምርጥ ሽልጦ ነው፡፡ ኦሜድላ ኬክ ቤትን ታስታውሰዋለህ አይደል? በዚያ ስናልፍ ሽታው ልብን ይሠውራል፡፡ እንዳማረኝ ነው አገሩን የለቀቅኩት፡፡ ሥራ ስይዝ ጠረጲዛዬን ኬክ በኬክ እንደማደርገው ርግጠኛ ነበርኩ፡፡ አሁን ምን ይሉኛል ጣፋጭ ነገር ጥሩ አይደለም ስኳር ያመጣል ምናምን፡፡ ታድያ ምን ልብላ ስላቸው የጥቁር ገብስ ዳቦ፡፡ ቀምጣላ በላቸው፡፡ የገብስ ዳቦማ ከኛ ቤት መች ጠፍቶ ያውቃል፡፡ ያውም ልጥልጥ የመሰለ ጥቁር ገብስ፡፡ ኬክ እበላለሁ ብዬ ተማርኩ እንጂ እዚህ ደርሼ ጥቁር የገብስ ዳቦ እንደምበላ ባውቅ ኖሮ ከገጠር ጎጆዬ መች እወጣ ነበር? እኔኮ አድጌ፣ ተምሬ፣ እነ ገመቹ በኪሳቸው ደብቀው ከቤት የሚያመጡትን ስኳር ለመቃም ነበር ምኞቴ፡፡ አሁን ስኳር በሽታ ነው ባዶውን ጠጡት ይላሉ፡፡ ባዶ ስጠጣ መርሮኝ አይደል እንዴ የተማርኩት?›
‹እና ተምረህ ተምረህ ምንድን ነው እሺ ያገኘኸው?› አልኩት ወደ ኬክ ቤቱ እየገባን፡፡
‹ዓለምን አትደርስባትም፤ስትደርስባት ወይ እንደ ጥላ ትሸሻለች አለበለዚያም እንደ ማያ ትቀየራለች፡፡ በኔ መማር የኔን ፍላጎት ካረካሁት በላይ የወላጆቼንና የዘመዶቼን ፍላጎት ያረካሁት ይበልጣል፡፡ መማርህን የምታውቀውም በዚህ ይመስለኛል፡፡ ካንተ በላይ ሀገርና ወገን የሚጠቀም ከሆነ ተምረሃል፤ ከሀገርና ከወገን በላይ አንተ የምትጠቀም ከሆነ ግን ደንቁረሃል – ይሄን ነው የደረስኩበት እንጂ ነጭ ጤፉን፣ኬኩን፣ መኪናውን፣ አልጋውን፣ ልብሱን፤ ስኳሩን፣ ለስላሳውን አልደረስኩበትም፡፡
Filed in: Amharic