>
2:06 pm - Thursday December 8, 2022

አዴፓ (ብአዴን)  በመላው የአማራ ክልል ከተሞች የተጠራውን ሰልፍ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ!!! 

አዴፓ (ብአዴን)  በመላው የአማራ ክልል ከተሞች የተጠራውን ሰልፍ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ!!! 
አ.መ.ብ
 
ከአድማ፤ ሠላማዊ ሰልፍና ግርግር ወጥተን ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በማጎልበት የህዝባችንን ተጨባጭ ችግሮች ወደ መፍታት እንሸጋገር!!
 
በምንመራው የለውጥ መድረክ በህዝባችን ግፊት እና በድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፖ) አመራር ሰጭነት የጋራ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎችን ለይተን ለተፈፃሚነታቸው ርብርብ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡
 
በለውጡ ውስጥ የተመዘገቡ ውጤቶች እንዳሉ ሆኖ ቀሪ በርካታ አጀንዳዎችን ከህዝባችን ጋር ሆነን እልባት ለመስጠት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ሆኖም ከፈታናቸው የህዝብ ጥያቄዎች ይልቅ ያልተመለሱ አጀንዳዎች ይበዛሉ፡፡ የአማራ ህዝብን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አጀንዳዎች በቀጣይነት እየፈቱ ለመሄድ ድርጅታችንና መንግስት ህብረተሰቡን በስፋት እያሳተፈ እና ተጠቃሚ እያደረገ ውጤታማ የለውጥ ሃይል ሆኖ መዝለቅ ይጠበቅበታል፡፡
 
የአማራ ህዝብ በአጠቃላይ እና የክልላችን ህዝቦች ይህ የለውጥ መድረክ እውን እንዲሆን በከፈሉት መስዋዕትነት እና አኩሪ ተጋድሎ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ቢሆኑም አሁንም ከፈተናዎች ጋር በመታገል ላይ ናቸው፡፡
 
በተለይም የዜጎች ሞት እና መፈናቀል እንዲሁም ጥቃቶችን ዛሬም ማስቆም ባለመቻሉ ህዝባችን ከስጋት አልተላቀቀም፡፡ ሆኖም ይህን አይነቱን መሰል ችግር ከምንጩ ለማድረቅ ከለውጡ በተቃራኒ ቆመው በተከታታይነት ጥፋት እንዲፈፀም የሚያደርጉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ኃይሎችን በአግባቡ ለይቶ ቀጣይነት ያለው ትግል ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ከፖለቲካዊ ሁኔታዎች አንፃርም የፖለቲካ ፅንፈኝነት እና አክራሪ ብሄርተኝነት እየተመጋገቡ የህዝባችን ስቃይ በማብዛት እና የድርጅትና የመንግስት መዋቅር በህዝብ ዘንድ ዕምነት እንዲያጣ ብቻ ሳይሆን እንዲፈራርስ ጭምር ያለ ዕረፍት የሚሰሩ ግለሰቦች እና አካላት መኖራቸውም ገሃድ ነው፡፡
 
አማራ እየመሰሉ የአማራን ህዝብ አጀንዳዎች የመንጠቅ እና የማስጣል ድራማዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በመሆኑም በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ እና አድማ እንዲካሄድ፤ መንግስትና ድርጅት ተዳክሞ ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን የሚሰሩ ሃይሎችን በጋራ እና በተባበረ ክንድ በመታገል፤ ውስጣዊ ጥንካሬያችን አጎልብተን የህዝብ ተጨባጭ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ ማድርግ ይኖርብናል፡፡
 
ከባህር ዳር ከተማ አንፃርም 8ኛውን የጣና ፎረም ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለማስተናገድ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ባለበት እና እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ይህን ታላቅ ጉባኤ ለማደብዘዝ እና ገፅታን ለማበላሸት መሞከር ፈፅሞ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ይሆናል፡፡
 
በአጠቃላይ በዚህ ወቅት በሰላማዊ ሰልፍ፤ አድማ እና ግርግር ክልሉን ለማዳከም እና ብሎም ለማፍረስ የሚካሄድ ድብቅ ዓላማን ለማስፈፀም በሚሸረብ ተግባር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለያየ ተሳትፎ ከማድረግ ተቆጥበን ሞትና መፈናቀልን ማስቆም ጨምሮ በግልፅ የሚታወቁ የአማራ ህዝብ አጀንዳዎችን በጋራ ክንድ እና ውስጣዊ ጥንካሬያችንን አጎልበተን መፍታት እንድንችል ለመላው ህዝባችንና የለውጥ ሃይሎች ከመንግስትና ከድርጅታችን ጎን ተሰልፋችሁ ያልተገቡ ድርጊቶችን በማውገዝ የትግላችን አጋርነታችሁን በድጋሜ እንድታረጋግጡ የአክብሮት ጥሪ እናቀርባለን፡፡
 
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
ሚያዚያ 23 ቀን 2011 ዓ.ም
ባህር ዳር
Filed in: Amharic