>

“አሁንም የሕወሓት ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አልከሰመም!!!”  (አምባሳደር ካሳ ከበደ)

አሁንም የሕወሓት ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አልከሰመም!!!” 
አምባሳደር ካሳ ከበደ
* “በአጋዚ ንቅናቄ ፕሮጀክት የኤርትራን ደጋማ ክፍል ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ታስቧል”
#Ethiopia : አምባሳደር ዶ/ር ካሳ ከበደ ባለፉት መንግስታት የማህበራዊ ጉዳዮች ሚንስትር  ሆነው ለበርካታ አመታት እገልግለዋል በአምባሳደርነት በኢሰፓ የውጭ ጉዳይና የካድሬዎች ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊነት በመሆን ያገለገሉባቸው መስኮች ጥቂቶቹ ናቸው፡ በመሆኑም በፓለቲካዊ፣ በውጭ ጉዳይና  ዲፕሎማሲያዊ መስኮች የጸጥታና የደንነት ጉዳዮችና ፓሊሲዎች፣ እንዲሁም በማበራዊ ጉዳዮችና ፓሊሲ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው። በሀገር ውስጥ የሚታተመው ግዮን መጽሄት የሀገራችንን ወቅታዊ ፓለቲካ፣ የተጀመረውን ለውጥና ፣ በለውጡ መሪዎች ዙሪያ ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጎዋል። የመጀመሪያው ክፍል እነሆ። 
ግዮን፡- የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ አንድ ዓመት የስልለጣን ዘመን በእርስዎ ዕይታ እንዴት አለፈ?
አምባሳደደር ካሳ፡- የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድን እንድ ዓመት የምመለከተው ከመነሻቸው ጋር አያይዤ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የማስተዳደሩን ስልጣን ከመረከባቸው በፊት የነበረው ሁኔታ ምን ዓይነት ነበረ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል:: ያንን ከረሳነው፣ ይሄንንን አንድ አመት በቅጡ መመዘን የምንችል አይመስለኝም::
ያው ሁላችንም እንደምናስታውሰው፣ ሰሞኑን ደግሞ መባል እንደጀመረው “ኢትዮጵያ አለቀላት፣ ፈረሰች” ምናምን ተብሎ የበርካታ ሕዝብ ስሜት ተሸብሮ የነበረበት ወቅት ነው:: እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የነበሩት ሶስት ዓመታት፤ በየሳምንቱና በየዕለቱ ሊባል በሚችል መልኩ የሐገራችን አጠቃላይ ሁኔታ ቁልቁል እየወረደ የመጣበት ጊዜ እንደነበር ይታወቃል:: ሁላችንም በከፍተኛ ስጋት ተውጠን ነበር ማለት ይቻላል::
እዛ ላይ፤ በእውነት ተአምር ሊባል በሚችል ሁኔታ፣ ፍጹም ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ፤ ኢህአዴግ ውስጡ ባካሄደው የፖለቲካ ትግል፣ የፖለቲካ ድርድርና የፖለቲካ ሂደት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሊመረጡ ችለዋል:: እርሳቸው እንደተመረጡ ኢትዮጵያዊነትን አጉልተው በመናገራቸው፣ “የኢትዮጵያን ገናነት እናድሳለን” የሚል ተስፋ በመፈንጠቃቸው፤ ነገሮች ተዓምራዊ ሊባል በሚችል ሁኔታ
ሊለወጡ መቻላቸውን እናስታውሳለን::
ከዛ በኋላ እንግዲህ በተከታታይ የወሰዷቸው ዕርምጃዎች አሉ:: የፖለቲካ ዕስረኞችን መፍታት በሚመለከት፣ ፕሬሱን በሚመለከት፣ የመፃፍ የመናገር የመሰብሰብና ሌሎች መሰል ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በሚመለከት፤ ብዙ ዝርዝር ሁኔዎችን በስልጣን ጅማሬያቸው ወቅት ወደ ተግባር መለወጣቸውን መጥቀስ ይቻላል::
ግዮን፡- በሽብርተኝነት የተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች፤ እርስዎን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦችም ወደ ሀገር ቤት ለመግባት የቻላችሁት በጠ/ሚኒስትሩ ስልጣን ማግስት ነበር…
አምባሳደር ካሳ፡- ትክክል:: የእኔ ዓይነት የፖለቲካ ሰው ብዙ ሰው፣ ከአመታት በኋላ ለሀገር የበቃበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን በዝርዝር ሁሉም ሰው ስለሚያውቃቸው ብዙም እዛ ውስጥ አልገባም:: ጅምሩ ላይ የነበረውን ሁኔታ እናስታውስ እንደሆነ፤ እንደውም ጠ/ሚኒስትሩ አይደለም “ፋታ፣ ጊዜ ስጡኝ” የሚለው ሕዝቡ ነበር:: ምክንያቱም “ለውጡ ፈጠነ” የሚል ትችት ሁሉ ይሰማ እንደነበረ መዘንጋት የለብንም::
በዛን ወቅት፤ እኔ አንድ ቃለ ምልልስ ከኢሳት ጋር አድርጌ ነበረ:: እዛ ቃለ ምልልስ ላይ “የለውጡን ሂደት በምዕራቦቹ አይን ማየት አለብን:: ሁሉንም ነገር በአንዴ አዲሱ ጠ/ሚ/ ርና ካቢኔያቸው መተግበር አለበት ማለት አንችልም፤ እሱ አያስኬድም:: እርሳቸውም ቢሆኑ የሚያከናውኑትን ነገር በምዕራባውያን ሀገሮች መልኩ ቢያዩ ጥሩ ነው” የሚል ሀሳብ አቅርቤ ነበር::
በተጠቀሰው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሊሰሩ ይችላሉ የተባሉ ነገሮች አብዛኛዎቹ ተሰርተዋል:: ሲተገበሩም አይተናል:: የቀሩት ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው፤ እንግዲህ ሪፎርም ነው የተባለው:: ይሄን ሪፎርም እንግዲህ ሽግግር ለማለት አስቸጋሪ ነው፤ ተሃድሶ ማለት የሚቀል ይመስለኛል:: የእዚህ ተሃድሶ ሂደት በራሱ የለውጥ ሂደት ስላለው፣ በዚህ የተሃድሶ ሂደት ውስጥ የሚደረጉት ለውጦች ደግሞ የራሳቸው የሆነ ባህሪይ አላቸው:: ስለዚህ ነገሮች አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገና በፊት ከጀምሩ ግልፅ ነበር::
ግዮን፡- የለውጡ ሂደት ማለት ነው?
አምባሳደር ካሳ፡- አዎ:: ለውጡ እንግዲህ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተሳትፎበት፣ በሙሉ ህዝብ ይሁንታ የመጣ አስተዳደር አለመሆኑን እናውቃለን:: ጅምሩ ላይ እንግዲህ ለውጡ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ የመጣ ለውጥ ነው ብለናል:: ከዛ በፊት ሁሉን ነገር ተቆጣጥሮ የነበረው ሕወሓት ነው፤ ሕወሓትን ለመተካት በተደረገው ትግል ጎልተው የወጡት የአሁኖቹ ኦዴፓና አዴፓ ናቸው:: እነዚህ ሁለቱ እንዴት እንደተናበቡና ውጤታማ እንደሆኑ፣ ስብስባቸውንም “ቲም ለማ” ብለን እስከማድነቅ ደርሰናል:: የቲም ለማ አባላት በአመራር ደረጃ አራት ግለሰቦች ናቸው:: አቶ ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶ/ር ዐቢይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን እንደሆኑ ስንናገር፣ ስንመሰክር ቆይተናል::
ይሄ ቡድን የሀገሪቱን የአመራር ስልጣን ከተረከበ በኋላ፤ እንዲሁም የቡድኑ መሪ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ከሆኑ በኋላም ቢሆን፤ አሁን ጠ/ሚኒስትሩም ሆኑ አቶ ደመቀ፣ እንዲሁም አቶ ለማና አቶ ገዱ በሚገባ እየተናበቡ እየሰሩ እዚህ መድረሳቸውን እናውቃለን:: እነዚህ ግለሰቦች የሚመሯቸው ድርጅቶች የብሔር ድርጅቶች ናቸው፤ ወይም ብሔር ተኮር ድርጅቶች ናቸው:: የኦሮሞና የአማራ ብሔር ማለታችን ነው:: ኦዴፓና አዴፓ በሁለቱም ብሔሮች ህዝብ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አላቸው ማለት ያስቸግራል:: የኢትዮጵያ አማራ ሙሉ በሙሉ የመረጠው፣ የኢትዮጵያ ኦሮሞ ሙሉ በሙሉ የመረጠው ድርጅት አለ፤ ብለን አይደለም የምንናገረው::
እነዚህን ሁሉቱንም ድርጅቶች ያየናቸው እንደሆነ ሕወሓት የመንግስት ስልጣኑን ለመያዝ በተንደረደረበት ጊዜ የፈጠራቸው ወይም የተጎዳኛቸው ድርጅቶ ናቸው:: በሕወሓት አመራሮች የተፈጠሩና የተቀረፁ ድርጅቶች ናቸው:: በርግጥ ኦዴፓ (ብአዴን) ኢህዴን የሚባል እርሾ ነበረው፤ ኦዴፓ(ኦህዴድ) ደግሞ በአብዛኛው በምርኮኛ ወታደሮች፣ በሕወሓት ተጠፍጥፎ የተሰራ ስለነበረ፤ ታሪካቸው ይለያያል:: ግን ሕወሓት የመንግስታቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ሁለቱንም ድርጅቶች መሳሪያ አድርጎ፤ አንዱን በኦሮምያ ክልል፣ ሌላኛውን በአማራ ክልል ላለው አገዛዝ ሲጠቀምባቸው እንደነበረ እናስታውሳለን:: ከእነዛ ሁለት ድርጅቶች ውስጥ የወጡ ሰዎች ናቸው የኦዴፓና አዴፓ መሪዎች::
ስለሆነም በመጀመሪያ ደረጃ ሕወሓት ይቆጣጠረው የነበረውን መዋቀር ሙሉ ለሙሉ የማጥራት ግዴታም ነበረባቸው:: በዛ ረገድ በከፍተኛው አመራር ደረጃ፣ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴያቸው፣ በማዕከላዊ ኮሚቴያቸው ሁለቱም ድርጅቶች የሕወሓትን ተፅዕኖና መሪነት ለማምከን ተንቀሳቅሰዋል:: እንግዲህ እዚህ ላይ ማየት ያለብን ሁለቱ ድርጅቶች ሕወሓትን ነው የተኩት፤ ሕወሓት ደግሞ እንዲሁ በዝምታና “አሜን” ብሎ አይደለም ስልጣኑን ያስረከበው::
ግዮን፡- ሙሉ በሙሉ ሕወሓት በሽንፈት ነው ስልጣኑን የሰጠው ማለት ይቻላል?
አምባሳደር ካሳ፡- በሽንፈት ነው:: ከሽንፈት ባሻገር ደግሞ ሕወሓት የኢህአዴግ መሪ በነበረበት ጊዜ የተፈፀሙ በደሎች፣ የተከናወኑ ዝርፊያና ሌብነቶችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ነገሮች በአንድ ዓመቱ የጠ/ሚ/ሩ የስልጣን ጅማሬ ላይ ተጋልጠዋል:: ይሄ ደግሞ የአመራር አቋም ብቻ ሳይሆን የህዝብም ጥያቄ ስለነበረ፤ ሕወሓት ወደ መከላከልና ወደ መሸሽ ፣ወደ መመሸግ የሄደበትን ሁኔታ ተመልክተናል::
የሕወሓት መሪዎች መቀሌ ሲመሽጉ፤ ሕወሓት ያደራጃቸው ድርጅቶች ኦዴፓና አዴፓ በአንፃሩ ስልጣኑን ሲይዙ፤ እነዚህን ድርጅታዊ ባህሪያቸውንና በድርጅቱ መዋቅር ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማንነት ጠንቅቆ የሚያውቀው ሕወሓት፤ በዚህ መረጃው ተጠቅሞ እሱን የተኩት የለውጥ ኃይሎች አሰራር እንዳይሳካ፣ ለማደናቀፍ አልሞከረም ለማለት አይቻልም:: በግልፅም እየታየ ነው፤ እየሞከረም ነው::
አኔ አሁን የማየው ችግር፤ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የአዴፓን በቅርበት ተመልክቻለሁ፣ ኦዴፓ ውስጥ የነበረውንም እንዲሁ ከርቀትም ቢሆን ታዝቤያለሁ:: ሁለቱም እነዚህ የሕወሓት መሳሪያ ናቸው የሚሉትን የቀድሞ አመራሮች እያስወገዱ የሄዱበትን መንገድ ተመልክተናል::
ግዮን፡- የሕወሓት መጠቀሚያ ናቸው የሚባሉትን አመራሮች፤ ሁለቱ ድርጅቶች እስከመጨረሻው አስወግደዋል ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር ካሳ፡- በከፍተኛ አመራር ደረጃ ስል እንግዲህ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ከሞላ ጎደል በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ያስወገዱ ይመስለኛል:: በአብዛኛው አስወግደዋል ማለት ይቻላል:: በአዴፓ በኩል የበለጠ በቅርበት ያለውን ስለማውቅ ነው፤ በኦዴፓ በኩልም የእዚሁ ዓይነት ሂደት ነው ያየነው:: ይሄ ብቻ ሳይሆን በዛ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎችን በአዲስ አመራር የመተካቱ ሂደት ቀላል አይደለም:: በዛ ረገድ ከኦዴፓ (ኦህዴድ) ይልቅ አዴፓ (ብአዴን) ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል፤ አንፃራዊ በሆነ መልክ:: ግን በሁለቱም በኩል አይበጁም ያሏቸውን ማስወገዳቸውን አይተናል::
እነዛ የሚወገዱት ሰዎች ስልጣኑን ይልቀቁ እንጂ የሚኖሩት እዛው ቀድመው የሚኖሩበት አካባቢ ነው:: እነሱ እንግዲህ በኩርፊያም ሆነ በሌላ
ስሜት፤ በለውጡ ሂደት ላይ ተግዳሮት አላሰደሩም ማለት አንችልም:: ይሄ አካሄድ ወይም በላይኞቹ አመራሮች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ መቀጠል አለበት:: በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ተደረገ ማለት፣ ወይም ደግሞ ከክልሉ ስራ አስፈፃሚና በክልሉ ስር ባሉ ቢሮዎች ከእነዛ ተነስተን ደግሞ በዞንም፣ በወረዳም እስከ ቀበሌ የእኛ የሚሏቸውንና ከለውጡ ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ካድሬዎችን የመመደቡ ስራ ገና አልተጠናቀቀም:: በጅምር ነው ያለው::
ግዮን፡- ስለዚህ የህዝቡ ማኩረፍ፣ የሀዝቡ ለውጥ መፈለግና መጓጓት በቂ ምላሽ ለማስገኘት ገና ብዙ ስራ ይቀራል ነው የሚሉን?
አምባሳደር ካሳ፡- በአንድ በኩል ይሄ ስራ እየተሰራ ያለና ያልተጠናቀቀ መሆኑን መገንዘብ አለብን:: ይሄ መደረግ አለበት የሚባለውን እኮ አስቀድመንም አስበናል:: እየተደረገ መሆኑንም እያየን ነው ያለነው:: ለምን በዚህ በአንድ ዓመት ውስጥ አልተጠናቀቀም? የሚል አቋም ይዞ መውቀስ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” የሚባለው ዓይነት ሂስ ሊያሰነዝር ይችላል:: ሌላኛው እንግዲህ ምን ዓይነት ህብረተሰብ? ምን ዓይነት ኢኮኖሚ? እንደው በአጠቃላይ ምን ዓይነት የፀጥታና የደህንነት የፖለቲካ ሁኔታዎችን ነው ይሄ የለውጥ ሃይል የተረከበው? የሚለውንም ደግሞ በጥንቃቄ መመልከት ያለብን ይመስለኛል::
በዛ ረገድ መጀመሪያ ለኢኮኖሚው እኔ ቅድሚያ የምሰጠው:: ሀገራችን የወጣቶች ሀገር ነች እንላለን፤ ምክንያቱም ወደ ሰባ በመቶ የሚሆነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድሜው ከሰላሳ ዓመት በታች ነው እያልን ነው:: ኢኮኖሚው በሕወሓት የአመራር ዘመን ያው እንደምናውቀው በኢንቨስትመንት መልክም ሆነ በብድርም ሆነ በእርዳታ፣ ኢትዮየጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ከፍተኛ የውጭ ሀብት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ነበር::
እነ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሌሎች አግባብ ያላቸው አካላት አሁን እንደገለፁት ያን የሚያህል በብዙ ቢልየን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ገንዘብ ወደ አገራችን ቢገባም፣ ለሀገሪቱ ዕድገት የዋለው በጣም መጠነኛ ነው:: ምክንያቱም ብዙው ገንዘብ ተዘርፏልና:: ይሄን በተመለከተ ብዙ ትችት ቀርቧል:: በዚህ ምክንያት በማህበራዊ አገልግሎቶች ረገድ ጤናን በተመለከተ፣ ትምህርትን በተመለከተ ዕድገት የታየ ቢሆንም፤ ይሄ ዕድገት በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ የነበረው ዕድገት ምን ፈየደ? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል:: ምክንያቱም ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መጠን የወጣቶች ስራ አጥነት ጎልቶ መጥቷል::
ወጣቱ ይማራል፤ እንግዲህ ትምህርት ማለት አንፃራዊ ነው:: ግን በየደረጃው ዕድሜው ሲፈቅድለት፣ ከትምህርት ገበታው ትምህርቱን ጨርሶም ሆነ ሳይጨርስ፤ ስራ ፍለጋ የሚሰማራ ወጣት አለ:: ይሄን ወጣት ለሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን:: ቀደም ባለው ጊዜ በየምክንያቱ ትምህርቱን እያቋረጠ፣ ዕድሜው ለስራ ደርሶ ስራ ፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ፤ ወላጆቹ ሰፋ ያለ የመሬት ይዞታ ስለነበራቸው፤ የወላጆቹን መሬት እየተጋራ፣ አብሮ እያረሰ እዛው ወላጆቹ አከባቢ ቤት ሰርቶ ትዳሩን መስርቶ የሚኖርበት ሁኔታ ነበረ::
ያ አርሶ አደር የነበረው አካባቢ ዛሬ ያለው መሬት እየተጣበበ ስለመጣ፣ ወላጆቹ ወትሮ ያደርጉት የነበረ የመሬት ቦታቸውን አካፍለው ወጣቱን እዛው በእርሻ ስራ መሰማራት አልቻለም:: በዚህ ምክንያት ትምህርት ቀመስ የሆነው ወጣት ዕድሜው ለስራ በሚደርስበት ጊዜ በቤተሰቦቹ እየተደጎመም ሆነ በሌላ ዘዴ ኑሮውን ለመግፋት ወደ ከተሞች ነው የጎረፈው:: ከተሞች ስል እነዚህ የንግድ ቦታ የሚባሉት ትንንሽ ከተሞችን ጭምር ማለቴ ነው:: ይሄ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ወጣት ክምችት በኢኮኖሚ ረገድ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ባህሪይውም መታየት ያለበት ይመስለኛል::
ስራ ያጣ ወጣት ማለት ተስፋ እየቆረጠ ያለ ወጣት ማለት ነው:: ተስፋ እየቆረጠ ያለ ወጣት ደግሞ ብስጩ ወጣት ማለት ነው:: ብስጩ ወጣት ደግሞ ከዛ ብስጭት የሚያስለቅቀውን ነገር ይፈልጋል፤ ዕፅ መጠቀምን ይመርጣል:: ያ አምሮቱ ካልተሳካለት አቅሙ በፈቀደ ዜዴ ሁሉ ያንን ነገር ለማግኘት ይመኛል:: ይሄንንን በምልበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን፤ እንደው ወጣቱ ሁሉ፣ ስራ አጥ ወጣቱ ሁሉ በዚህ ከታጎሪ የሚፈረጅ ነው የሚል ግንዛቤ እንዳንወስድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል:: እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ወራት ቆይቼ፣ ብዙ አካባቢዎች ተዘዋውሬ ለማየት ሞክሬያለሁ:: በዚህ የሰራተኛ ጉዳይ ቀዳሚ የስራ ልምድም ነበረኝ፤ በፊት በስራም ተሳትፌ ስለማውቅ፤ ችግሩ ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነና ዛሬ ኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉ “ሶሾ ኢኮኖሚ ችግሮች ሁሉ ትልቁ ችግር የወጣቶቻችን ስራ አጥነት ነው:: ይሄንን ነገር በሆነ መንገድ መፍታትና ከችግሩ መውጣት አለብን የሚል ስሜት አድሮብኝ ነው ወደ አሜሪካ የተመለስኩት::
ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ ላገኘኋቸው አመራር አካላት ሁሉ አስተያየቴን በቃልም በፅኁፍም ስገልፅ ነበር:: ከአንዳንዶቹ ጋራ ስለመፍትሔው ስመካከር ነበር፡ እንግዲህ ይሄን የሥራ አጥነት ችግር እነ ዶ/ር ዐቢይ የፈጠሩት አይደለም:: የወረሱት ነው::በወረሱት ላይ ደግሞ የአንድ አመት ተመራቂዎችም ሆኑ ድሮፕ አውት (የሚያቋርጡ) ወጣቶች ደግሞ ተጨምረውበታል:: በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የተመረቁትንና ያቋረጡትን፣ ስራ አግኝተው ከተሰማሩት ወጣቶች ጋር ብናስተያይ ስራ ያገኙት ወጣቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው::
የእዚህ የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ቀላል አይደለም:: ከዚህ ጋር ተዛምዶ አሁን ሀገር ውስጥ ያለውና ሁሌ የምንነጋገርበት አንዱ “ኢትዮጵያ ፈረሰች”፣ “ኢትዮጵያ ተገነጣጠለች” የሚለው ስሜት ያሳደረው የሰላምና የመረጋጋ ዕጦት ነው:: ሰላምና መረጋጋት በምንልበት ጊዜ ማህበረሰባችንም ስራ አጥቶ፣ ተስፋ ቆርጦ የተበሳጨ ወጣት በብዛት የሚገኝበት መሆኑን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም:: በተጓዳኝ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ::
ግዮን፡- ምን ምን ናቸው እነዛ ስራዎች?
አምባሳደር ካሳ፡- በአንድ በኩል ሰላምና መረጋጋቱን የማስፈን ሂደት ነው:: በሌላ በኩል ኢኮኖሚውን አንቀሳቅሶ ለእነዚህ ወጣቶች ስራ መፍጠር ነው:: ስለዚህ ስራ ፈጣሪ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል:: አሁን ኢንዱስትሪያል ዞን የሚባሉትን አንድ ሁለቱን ተመልክቻለሁ፤ በርግጥ የውጭ ኢንቨስተሮች ኢንዲመጡ የሚጋብዙ ናቸው:: ግን የተከማቸውን የስራ አጥ ወጣት ችግር ይቀንሳሉ ወይ? በእነሱ በኩል የሚፈሰው ሌላው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ፣ ከዚህ ችግር አንፃር እንዴት ይታያል? በምንልበት ጊዜ ማየት ያለብን፤ ያንን ካፒታል ይዘው የሚመጡ ኢንቬስተሮች በእነዚህ ኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ለመስራት የሚፈልጉት ለማትረፍ ነው::
ለማትረፍ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ካፒታል ኢንሴቲቭ ናቸው:: በመሳሪያ (በማሽን) ኃይል የሚሰሩ ናቸው:: በሰው ኃይል የሚሰሩ አይደሉም:: በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ካፒታል ኢንሴንቲቭና ሌቨር ኢንሴንቲቭ የሚባሉ ነገሮች አሉ:: በኢንዱስትሪው ሌቨር ኢንሴንቲቭ የሚባለው የሚቻለውን ያህል፣ ከማሽን (መሳሪያ) ይልቅ በሰው ኃይል ለማምረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው:: ግን ደግሞ የሰው ኃይል በብዛት ማሰማራቱ የራሱ የሆነ የአስተዳደር ችግር አለው፤ ሌላም ተዛማጅ ጉዳይ አለው:: ስለዚህ ትርፍ ላይ ብቻ በሚያተኩሩበት ጊዜ ኢንቨስተሮች በሰው ሀይል ሊሰራ የሚችለውን ነገር ሁሉ በተቻለ መጠን በማሽን ለመስራት ያተኩራሉ:: እሱ ካፒታል ኢንሴንቲቭ ይባላል::
አሁን በኢንዱስትሪ መንደሮች ውስጥ የሚቋቋሙት ካፒታል ኢንቴንሲቭ ናቸው:: ምክንያቱም ከውጭ የሚመጡት ኢንቬስተሮች የሰው ሃይል ክፍያው አናሳ ስለሆነ፤ አንፃራዊ አድቫንቴጅ እናገኛለን ብለው ነው የሚመጡት:: በዛ ምክንያት የሚያስፈልጋቸውን የሰራተኛ ኃይል በተቻለ መጠን ለመቀነስ ይሞክራሉ:: በተቻለ መጠን ለሰራተኛ የሚከፈለውን ደሞዝ ለማሳነስ ይሞክራሉ::እነዚህ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መጠነኛ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ቢችሉም ለዚህ ችግር መቅረፊያ ይሆናሉ ማለት ግን ያስችግራል:: ብዙ የእኛ ዓይነት ፈተና የገጠማቸው ሀገሮች አሉ፤ አሜሪካም ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የነበራቸውን ዘመን ብንመለከት፣ ያንን ችግር የተወጡት የበለጠ ገጠራማው ክፍል ላይ በማተኮር ነው:: ከተሞች ውስጥ ደግሞ የፐብሊክ ወርክ ፕሮጀክቶችን በመቀረፅ ነው ችግሮቻቸውን የፈቱት::
በዛ ረገድ አሁን እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳየሁት ከሌሎቹ ሴክተሮች የበለጠ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጥሯል:: ያ ግን የሚቀጥል አይመስልም:: የግብዓትም፣ የገበያም ሆነ ሌላ ተዛማጅ ነገሮች አሉና:: ተደጋግሞ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሀብት የሰው ኃይሏ ነው፣ መሬቷና ውሃዎቿ ናቸው:: ኢትዮጵያውያን በዚህ በእርሻ የተሻለ ዕድል ሊኖረን ይችላል ብዬ እገምታለሁ:: የገጠሩ ልማት ደግሞ አስፈላጊ ነው፤ መሬቱም ውሃውም አለ:: ለእዛ የሚሆን ካፒታል በማፈላለግ ላይ እንዳሉ አውቃለሁ:: እነርሱ በፍጥነት ስራ ላይ ሊውሉ አልቻምሉ፣ ዝግጅት ይጠይቃልና::
በተለይ እነዚህን የገጠር ፕሮጀክቶች ለመተግበር ካፒታል ያስፈልጋል:: የውጪ ምንዛሬ ኮምፖናንትም አላቸው፤ የዘመነ የእርሻ ስርዓት ማካሄድ ስለሚታሰብ:: ይሄ ሁሉ በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለምን አልተተገበረም? ለማለት ያስቸግራል:: ይሄንን የጠቆምኩት የስራ አጥነቱን ችግር በተመለከተ እርሱ ካለው የሰላምና መረጋጋት ችግር ጋር ዝምድናም እንዳለው ጭምር ለማመልከት ነው:: ብዙ ጊዜ ሰላምና መረጋጋት ስንል በብዛት የምናስተውለው ወጣቶች ላይ ነው::
በሌላ በኩል ከላይ እንደገለፅኩት፤ አሁን የአመራር ስልጣኑን የጨበጡት ኦዴፓና አዴፓ ናቸው በምንልበት ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የመረጠው አመራር እንዳሆልነ ገልፀናል:: ስለዚህ ሁለቱም ድርጅቶች ተቀናቃኞች አሏቸው ማለት ነው:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድን ያየን እንደሆነ ድርጅቶቹን ወደ ጎን ትተን፤ በመስመር ደረጃ ብንመለከት እነሱ ኢትዮጵያዊነት የሚሉት፣ የኢትዮጵያ አንድነት የሚሉት፣ ዴሞክራሲና እኩልነት የሚለውን ህብረ ብሄራዊነት በማለት የሚያቀነቅኑትን፣ የሚነግሩንን ነገር ከልባቸው እንደሚመኙ፤ መተግበርም እንደሚፈልጉ እኔ አምናለሁ፤ አልጠራጠራቸውም:: ግን በርካታ ተግዳሮቶች አሉባቸው::
ግዮን፡- እነዚህን ፈታኝ የሚሏቸውን ተግዳሮቶች በግልፅ ቢያስቀምጧቸው?
አምባሳደር ካሳ፡-የእነሱን ኮንሰስታንሲ ወደድንም ጠላንም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን የኦሮሞ ሕብረተሰብ ክፍል ነው:: ይሄ ኮንሰስታሲያቸውን ፖለቲከኞች እንደመሆናቸው መጠን ህዝብ እንዲከተላቸው ይፈልጋሉ:: ግን እዛ ኮንስታንሲ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ነው ያለው? በምንልበት ጊዜ አሁንም ቢሆን በዚህ በኦሮሞው ህብረተሰብ ክፍል ውስጥ መጠኑ እየቀነሱ ቢሄድም በኦነግ 50 እና 60 ዓመት የተቀነቀነ የመገንጠል አባዜ ከህዝቡ አዕምሮ ውስጥ ሙልጭ ብሎ ወጥቷል ማለት አይቻልም:: ከኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ማለቴ ነው::
ያንን የሚመኙ ኤለመንቶች አሁንም አሉ፤ ይባስ ብለው ደግሞ ከእነዚህ ኤልመንቶች መካከል ትጥቅ ያልፈቱና በትጥቅ ጭምር አመራሩን የሚገዳደሩ ኃይሎች አሉ:: በዚህ በምዕራብ ወለጋ የነበረውን፣ በቦረና የነበረውን ሁኔታ እናውቃለን:: በርግጥ ዕርምጃ ተወስዶ ለማርገብ ተሞክሯል፤ ግን ሙሉ በሙሉ መፍትሄ አግኝቷል ማለት አይደለም:: በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓት ከአገዛዙ ሲወገድ አርፎ አልተቀመጠምና የለውጡ ኃይል አንዳይሳካለት አንዳንድ ችግር እየፈጠረ ነው ብለናል፤ እነዚህ እንገነጠላለን ብለው አመራሩን ለማድከም በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ቡድኖች ሕወሓት ባለው አቅም አይረዳቸውም ማለትም አይቻልም::
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች እንዳሉን መርሳት የለብንም:: እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች ዳግም ውስጣችን ያለውን ሁኔታ እያደመጡ ሊያዳክሙን የሚችሉ ዕርምጃዎችን አይወስዱም ማለት አይቻልም:: አንዱ ተግዳሮት እነዚህ እንገነጠላለን የሚሉትን የኦሮሞ ሃይሎች ለማርገብ እየሞከሩ እንደሆኑ እናያለን::
ሁለተኛው ሕወሓት ከተወገደ፣ የትግሬዎቹ ጠቅላይነት ከተነሳ አሁን ደግሞ ተራው የኦሮሞ ሆኖ “እኛው ጠቅላይ ሆነን መውጣት አለብን” የሚል ኃይል ደግሞ አለ፡፤ ይሄ ሃይል አደገኛ ሃይል ነው:: ይሄንን የሚሉት እነዚህ ልሂቃን የምንላቸውና ፖለቲከኞች ናቸው:: በኦነግ ውስጥ ያሉ::
የእነዚህ ኃይሎች የኦሮሞ ጠቅላይነት እሳቤ ለእዚህ ስራ ላጣው ወጣት ያጓጓዋል ያስጎመጀዋል:: ችግሩን የሚቀርፍለት ይመስለውና በቀላሉ በእዛ ስር ሊሰለፍ ይችላል:: ይህ እንዳይሆን ደግሞ እነ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ይሄንን ወጣት ላለመዘረፍ የሚሄዱበት መንገድም እንዳለም እያየን ነው:: ስለዚህ ከእዚህ ሁለት ተወዳዳሪ ሃይሎች እየታገሉ እያሉ፤ እኛ የምንፈልገውን ብቻ እንዲያደርጉ መመኘት የዋህነት ይመስለኛል:: ስለዚህ መታገስና ጊዜ መስለጠት አለብን:: ደግሞም ይገባል::
ግዮን፡- በቅርቡ የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባ አጋር ድርጅቶችን ባካተተ መልኩ ወደ አንድ ድርጅትነት ይቀየራል ቢባልም ይሄ ሀሳብ በጉባኤው አልተነሳም፤ ጉባኤውም የተከናወነው በዝግ ነበር:: ከስብሰባ አስቀድሞ ሕወሓት ባወጣው መግለጫ የውህደቱን መንገድ እንደማይደግፍና እሱም እንደማይካተት አሳውቋል:: በሌላ መልኩ በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እስከ ዛሬ ባልታየ መልኩ አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል:: እነዚህን ሁኔታዎች እርስዎ እንዴት አገኟቸው?
አምባሳደር ካሳ፡- አሁን ያለው ብሔር ተኮር ፌደራል አደራረጀት መነካት እንደሌለበት፣ ሕገ መንግስቱ መነካት እንደሌለበት፣ ወደ አንድነት የሚያስኬድ ምቹ ሁኔታ እንደሌለ ተገልጧል:: ስለዚህ ኢህአዴግ ወደ አንድ ወጥ ኢትዮጵያዊ ፓርቲነት ይለወጣል የሚለው ሀሳብ ሕወሓትን በአሁኑ ደረጃ ሊጨምር የሚችል አይመስልም:: በሌላ በኩል እነዚህ አጋር ድርጅቶች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ መደረጉ ደግሞ፤ ቀደም ብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገልፆ የነበረውን የመዋሃድ ሂደት እውን ለማድረግ እንደ ጅማሮ ነው ብዬ እገምታለሁ::
ስለዚህ ሕወሓትን ሳይጨምሩ ሶስቱ (ኦዴፓ፣ አዴፓ፣ ደኢህዴን) የኦሮሞ፣ የአማራና የደቡብ ድርጅቶች እነዚህን አጋር ድርጅቶች ይዘው ወጥ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ወይም ውህድ ሆነው ራሳቸውን ለምርጫ ያቀርባሉ የሚለው ነው የሚታየኝ:: በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕወሓትን አቋም ማስለወጥ የሚችሉ አይመስልም:: ሕወሓት ደግሞ እንደምንሰማው በራሱ ለሶስት የተከፈለ ሆኗል:: እነ ደብረፂዮን ሊፈልጉም፣ ሊስማሙም ይችሉ ይሆናል:: ግን ሌሎቹ ኃይሎች አሁንም የመወሰን ስልጣን ስላላቸው ደፍረው ላይሄዱበት ይችላሉ::
ከዚህ በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ የተፈጠረ የሕዝብ መከፋፈል አለ፤ ዛሬ ምስራቅ ትግራይና ምዕራብ ትግራይ እንደ በፊቱ እየተናበቡ ያለ አይመስልም:: ትንሽ የአሻፈረኝ ስሜት በምስራቁ በኩል እየተንፀባረቀ ነው:: ይህ ሁኔታ ደግሞ እያደገ ሊሄድ የሚችል ይመስላል:: ታሪካዊ መሰረትም አለው::
ግዮን፡- ምንድን ነው ታሪካዊ መሰረቱ?
አምባሳደር ካሳ፡- ታሪካዊ መሰረቱ ይሄ ቀዳማይ ወያኔ የምንለው በ1934 እና 1935 ዓ.ም በትግራይ ተከስቶ የነበረውን እንቅስቃሴ ከተመለከትን ያኔ በማዕከላዊ መንግስት ላይ አምጾ የተነሳው ምስራቅ ትግራይ በተለይ እንደርታ ነው:: አሁን መቀሌ የምንለው አካባቢ:: እንግዲህ ልዩነቱን መቀሌና አደዋ ልትለው ትችላለህ:: የምስራቁ ማዕከል መቀሌ ነው፣ የምዕራቡ ማዕከል አድዋ ነው:: ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ገና ልጅ እያሉ ደጃዝማች ተብለው እሳቸውን በመያዝ ያንን አመፅ ያካሄዱት የምስራቅ ትግራይ ተወላጆች ናቸው:: ይሄንን አመፅና መነሳሳት ያከሸፉት ደግሞ ራስ አበበ አረጋይ የበላይ ሆነው ጦሩን ቢያዘምቱም፣ አካባቢውን ለተወሰነ ጊዜ ቢያስተዳድሩም እነ ደጃዝማጅ በላይ ካሳ ናቸው የድሉ ባለቤት::
ደጃዝማች በላይ ካሳ አርበኛ ናቸው፣ የአድዋ ተወላጅ ናቸው:: ያንን አመፅ የደመሰሱት እነዚህ ሰዎች ናቸውና ከዛን ጊዜ ጀምሮ በአድዋና በመቀሌ ተወላጆች መካከል መቀናናትና አለመግባባት አለ:: መፎካከርም አለ:: ሁለተኛውንና 27 ዓመት ስልጣን ላይ የነበረውን ወያኔ ያየን እንደሆነ መሰረቱን አድዋ ላይ አድርጎ ነው የተነሳው:: ከዛ በኋላ አክሱምና ሽሬን ጨምሯል:: አሁን ይሄ ቡድን ለሶስት ተከፍሏል:: የድረብፂዮን ግሩፕ አንዱ ሲሆን፣ አንዱ የጌታቸው አሰፋ ሌላው ደግሞ የስብሃት ነጋ ግሩፕ ልትለው ትችላለህ::
ግዮን፡- ይሄ መከፋፈል በሕወሓት ውስጥ ካለ የጠ/ሚ/ር ዐቢይን ሀሳብ የሚደግፈው ቡድን ሙሉ ለሙሉ ወደ ለውጡ መቀላቀል ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? ዳር ዳር ማለቱስ የት ድረስ ያስኬዳል?
አምባሳደር ካሳ፡- ትልቁ ዳርዳርታ ሕወሓት ቅድም እንዳልነው ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ቢመሰረትም፣ ቢደራጅም ምስራቁን ደግሞ ማቀፍ ስለነበረበት “ወያኔ” የሚለውን ቃል ድርጅቱ ውስጥ የጨመረው ምስራቅ ትግራይን ለማቀፍ ወይም ለማከል እንዲረዳው ነው:: ከዛ በኋላ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ተንቀሳቀስሶ ምስራቅ ውስጥም ድርጅታዊ መዋቅሩን መዘርጋት ችሎ ነበር::፡
ወደ መነሻው ከሄድንና ሂደቱንም እስከ ደርግ ውድቀት ከተከታተልን ኢትዮጵያን የመግዛት፣ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ነገር የተመኘው ኢ.ህ.ዴ.ን ከተቀላቀለውና ወደ አማራው ህዝብ፤ ወደ ወሎና ጎንደር መሻገር ከቻለ በኋላ ነው:: እስከ እዛ ድረስ የታገለው ግን ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ነው:: ስሙም፣ ማኒፌስቶውም በዛው መሰረት የተዘጋጀ ነው::
ከሻዕቢያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ብንመለከት ሕወሓት ከሻዕቢያ ጋር የነበረው ችግር “እገነጠላለሁ፣ አትገነጠልም” የሚል ነው:: ሻዕቢያ “እኛ የቅኝ ተገዢነት ታሪክ ስላለን፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ጥያቄ ይዘን ነው የተነሳነው:: እናንተ የኢትዮጵያ አካል ሆናችሁ የኖራችሁ ናችሁ፣ እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ስልጣን ለመንጠቅ ታገሉ እንጂ መገንጠል አያስፈልጋችሁም” የሚል አቋም ነበረው:: እነሱ ደግሞ “እናንተ የትግል አጋራችን ናችሁ እንጂ ሞግዚታችን አይደላችሁም፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ልትጠቁሙን አይገባም” በሚል በየጊዜው ይናቆሩ ነበር፤ ፅሁፍ ይለዋወጡ ነበር፤ ይነቃቀፉ ነበር::
አሁንም የሕወሓት ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አልከሰመም :: ውህደቱን የማይፈልገው ሃይል ዋነኛው ምክንያቱ ይሄ ነው:: እንደውም ከዚህ ዘለል ብለው በእነሱ ምኞት ከትግራይ በተጨማሪ፤ የትግራይን ክልል የማስፋቱን ሂደት እያየን ነው:: ወደ ወልቃይትና ወደ ጠገዴ ተስፋፍተው መሬት በመያዝ ትግራይን ከሱዳን ጋር ማገናኘትና ትግራይን የጎረቤት ሀገር ድንበር ባለቤት የማድረግ፤ በዛው ደግሞ ወደፊት ለሚያቋቁሙት ትግራይ ግብርና ስራ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ መሬት ማግኘት:: እንደዚሁ በራያ በኩል አካባቢው በጣም ለም ስለሆነ፣ ወደ ፊት ለምትቋቋመው ትግራይ እንዲሁ ለም መሬት ለማግኘት፤ ከዛም ከፍ ካለና ከተሳካላቸው ደግሞ እንደውም ወደ አፋር ተሻግረው የቀይ ባህር ዳርቻ ሀገር የመሆን ህልምም አላቸው::
ይሄ ብቻ አይደለም የአጋዚ ሙቭመንት ብለው የጀመሩት ፕሮጀክት አላቸው፤ አዲስ ፕሮጀክት:: የእዚህ ፕሮጀክት ዓላማ በኤርትራ በኩል ደገኛውን የአካለጉዛይ፣ የሀማሴንን፣ የሰርዓይን ህዝብ አንድ ነን ብለው በመቀስቀስ በኢኮኖሚ ችግሩ በኩል በመግባት ወደ ትግራይ ለመሳብና ከትግራይ ጋር ደጋውን ኤርትራ አዋህዶ “ትግራይ ትግርኝ” በሚለው ኮንሰፕት አዲስ ጠንካራ ሀገር ሆና መውጣት ይቻላል የሚል ህልም ውስጥ ያሉ ተጋሩዎችም አሉ:: እና ይሄ ህልም እያለ ይሄንን ስማቸውን የመለወጡ፣ በተለይ ደግሞ ነፃነታቸውን ሰውተው ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር ተዋህደው፤ ወጥ ፓርቲ ሆነው የመውጣቱ ፈተና የገጠማቸው ነው የሚመስለው:: የሚያደርጉትም አይመስለኝም::
በአቶ ለማ መገርሳና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሹመት፤ በአዲስ አበባና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ በቀጣይ ዕትማችን ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እንገልፃለን:
Filed in: Amharic