>
5:13 pm - Thursday April 20, 8395

ማንም ከኢትዮጵያዊነት ማማ"ሊያወርደኝ አይችልም"! (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)


ማንም ከኢትዮጵያዊነት ማማ”ሊያወርደኝ አይችልም”!

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
ለእኔ ቋንቋዬ የሀሳብ መግለጫ፣ ባህሌ የአኗኗሬ መንገድ ብቻ ነው፡፡
እናቴ ጉራጌ ናት – ክስታኔ፡፡ አባቴና አባቱ ክስታንኛ አቀላጥፈው የሚናገሩትን ያህል ኦሮምኛም ይናገራሉ፡፡ በድሉ – ዋቅጅራ – ደበላ – ወልደጊዮርጊስ – ካሳ እያለ የሚዘልቀው የአባቴ ወገን መጠሪያ ሌሎችን የሚያስጨንቃቸውን፣ ግራ የሚያጋባቸውን ያህል እኔን አስጨንቆኝ አያውቅም፤ ግራም አያጋባኝም፡፡ የማያስጨንቀኝ እነሱን ስለምጠየፍ አይደለም፡፡ የማያስጨንቀኝ በማኛቸውም ማንነት ማንነቴን መበየን፣ ስለማልፈልግ ነው፡፡
እናቴ ኬርአለም ክስታኔ ናት፤ አባቴና አያቴ የኦሮሞና የጉራጌ ድብልቅ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወልደጊዮርጊስና ካሳ ትግሬ ወይም አማራ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ እኔ ውስጥ ያለው ግን ከነዚህ ሰዎች ጎሳ በላይ ነው፡፡ እኔ ውስጥ በደም ከዝርያዎቼ ከተቀበልኩት ይልቅ፣ ካደግኩበት የኦሮሞ ማህበረሰብ ከልጅነት እስከ ጉርምስና የቀሰምኩት ይበልጣል፡፡
በወጣትነቴ ባሌ ለሶስት አመታት፣ ጎንደርና ጎጃም ለአስር አመታት ስኖር ማንነታቸውን አትመውብኛል፡፡ ባህር ተሻግሬም አውሮፓ ላይ ያን ያህል ኖሬያለሁ፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የእኔን ማንነት በእናትና አባቴ ጎሳ (ምንም ይሁን ምን) የሚገለጸው? አዎ የክስታኝና ቋንቋን አፌን ፈትቼበታለሁ፤ እርግጥ ነው በጉራጌና በኦሮሞ ባህል ከልደት እስከ ጉርምስና ጥሪት ቋጥሬበታለሁ፤ አንድም ቀን ግን እራሴን ጉራጌ ወይም ኦሮሞ ብዬው አላውቅም፡፡ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ማንነትን በጎሳ የመበየን ፖለቲካ ተንሰራፍቶ እንኳን ጎሳዬን የማንነቴ መበየኛ አድርጌው፣ ወይን ሆኖ ተሰምቶኝ አላውቅም፡፡
ለዚህ ነው ጉራጌ ወይም ኦሮሞ መሆን አለመሆኔ የማያስጨንቀኝ፡፡ እኔ ከዚያ የበለጠ ሳልሸራረፍ የሚገልጠኝ ማንነት አለኝ – ኢትዮጵያዊነት፡፡
Filed in: Amharic