>
5:14 pm - Friday April 20, 8779

የሀማሴኑ ጀግና ዘርዓይ ድረስን ስናስበው !!! (እየሩሳሌም ተስፋው)

የሀማሴኑ ጀግና ዘርዓይ ድረስን ስናስበው !!!
እየሩሳሌም ተስፋው
የተወለደው በኤርትራ ክፍለ ሐገር ሀዝጋ በተባለች መንደር  በ1908 ዓ.ም ነው፣  ኢትዮጵያን በቀኝ ግዛት ለመያዝ በተሞከረበት ጊዜ  እ.ኤ.አ በግንቦት 1937 ዓም ገደማ የጣሊያን ዋና ከተማ በነበረችው  በሮማ በአስተርጓሚነት ሊሰራ ሄደ ።  ዘርዓይ ድረስ ወደ ጣሊያን ለመሄድ ሰበብ የሆነው ጣሊያንኛ ቋንቋ የማይችሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን በዚያ በእስረኘነት ይኖሩ ስለነበረ እነሱን በማስተርጎም ለመርዳት ሲባል ነው ።
ዘርዓይ ድረስ ትግርኛ ፣አማርኛ እና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አጣርቶ ይናገር ነበር ።  ሰኔ 7 1938 በሮም ፒያሳ ዲ ፒያሜንት በዶጋሊ ጦርነት ያለቁ 500 ጣሊያኖችን ለማሰብ ህዝቡ ተጠርቶ ይሰበሰባል ፣ ዘረዓይም በአደባባዩ እንዲገኝ ተጠርቶ ነበር ።
ወጣቱ ዘርዓይም  ወደ አድባባዩ የራስ አሉላ አባ ነጋን ፣ በ1871ዓ.ም በዶጋሊ ጦርነት ጀብዱ የፈፀሙበትን ጎራዴ ይዞ ሲጓዝ ጣሊያኖች ከለገሃር ነቅለው በወስዱት “የይሁዳ አንበሳ” በተባለው ሃዉልት (ዛሬ ተመልሶ ለገሃር ነው የሚገኘው) ዙርያ ተሰብስበው ሲሳለቁበት፣ የኢትዮጵያን ባንዲራም  አንጥፈው ሲረማመዱበት ይደርሳል ። በዚህ ጊዜ ዘረዓይ ንዴት ይገባዉና ሐውልቱን ከበው የቆሙትን ሰዎች በያዘው ጎራዴ ያስፈራራል ፣ ጉዳትም ያደርሳል ፣ ከዚያም በሃዉልቱ ላይ ቆሞ “እናንት ጣሊያኖች ነፃነታችሁን ካገኛቹ ገና ጥቂት ጊዜ በመሆኑና ሰለ ነፃነት የምታውቁት ነገር አንድም ሰለሌለ ነዉራችሁን እዚህ በምታደርጉት ተገልፆዋል” እያለ በቁጣ ንግግር አያደርገ እንዳለ አንድ በርቀት የቆመ የጣሊያን ወታደር ተኩሶ ከእግሩ ላይ ከመታው በኋላ ይይዘዋል እናም ለፍርድ ያቀርቡታል ። ከዚያም  “እብድ ነው” ብለው የአእምሮ ህመምተኞች ከሚታከሙበት ሆስፒታል ያስገቡታል።
ከነፃነት መመለስ በኋላ  ዘርዓይ ድረስ ወደ አገሩ ኢትዮጵያ አንዲመለስ ተወስኖ ለመምጣት በዝግጅት ላይ እንዳለ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ።
የዘርዓይ ድረስን ድንገተኛ አሟሟት  እና መጨርሻ በተመለከተ  ጥላሁን ብርሀነ ስላሴ የተባሉ ፀሃፊ “የ 20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” ባሉት መፅሃፋቸው እንዲህ ይላሉ፤
“ዘርዓይ ድረስ የፈጠረው ሁኔታ ጣሊያኖችን ስላስቆጣቸው፣ በንዴት ጣሊያን ሀገር ከነበሩት እስረኞች 147 ያህሉን ወደ አዚናራ የእስር ደሴት ሲወስዱ፣ ሌሎችን ደግሞ ሰብስበው ወደ ሞቃዲሾ አመጧቸው፡፡ ከነፃነት በኋላ ዘርዓይ ድረስ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተወስኖ ሊመጣ ሲል ክትባት ነው ብለው በመርፌ በሰጡት መርዝ አድርገው ገደሉት”
በኋላም ለስሙ ማስታወሻ የመጀመርያዋ  የኢትዮጵያ የጦር መርከብ  ዘርዓይ ድረስ ተብላ ተሰይማለች።  ዘርዓይ ድረስ ከሞቱ ከብዙ ዓመታት በኋላ ይልማ ሙናዬ የተባሉ ደራሲ ” ዘርዓይ ድረስ” የሚል ታሪካዊ ተውኔት በመፃፍ ለመድረክ እና ለንባብ በማቅረባቸው በወጣቱ ትወልድ ዘንድ የዘርዓይ ድረስ ታሪክ እንዲታወቅ አድርገዋል ።
Filed in: Amharic