>

እነ ራስ በዛብህ... (አቻምየለህ ታምሩ)


እነ ራስ በዛብህ…
አቻምየለህ ታምሩ
«የሶማሌ ክልል» የሚባለው የአገራችን ክፍል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ኡመር ባለፈው ሰሞን በጅግጅጋ አንድ ትምህርት ቤት ተገኝቶ ስለነ ራስ በዛብህ ውስጠ ወይራ ግጥም በጥቁር ሰሌዳ ላይ በመጻፍ የቅኔ ብቃቱን አስመስክሮ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ሙስጠፋ ስለተቀኛላቸው ስለነራስ በዛብህ የተገጠመውን ግጥም የጀርባ ታሪክ፣ ራስ በዛብህ ማን እንደሆኑና «እነራስ በዛብህ» ተብሎ በግጥሙ በድርብ ቁጥር የተካተቱት ራሶች እነ ማን እንደሆኑ ስናነብ ያገኘነውን እናካፍላለልን።
ራስ በዛዝብ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘጎጃም ወከፋ የበኩር ልጅ ናቸው። አባታቸው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በዳሞት አውራጃ ራስ አሰኝተው ሾመዋቸው ነበር። በ1883 ዓ.ም. ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ወደ ከፋ ዘምተው ሳለ በብርቱ ታመው ነበርና የተከተሏቸው ካህናት ጸሎት እየጸለዩ ሲጠምቋቸው ከሰነበቱ በኋላ በንጉሡ ላይ ሰፈረ የተባለው ጋኔን ሲመረመር «አባ ገብረ ኪሮስ ያቆራኘኝ ጋኔን ነኝ» ብሎ ተናገረ አሉ። ይህ እኔ የማምንበት ሳይሆን በበሽተኛው ንጉሥ አድሮ ተናገረ ተብሎ የተመዘገበው ቃል ነው። የሆነው ሆኖ አባ ገብረ ኪሮስም ከነጉሡ ጋር አብረው ዘምተው ነበርና ተይዘው ሲመረመሩ ሰፈረባቸው የተባለው ጋኔን ለፈለፈ የተባለውን ቃል «አዎን ራስ በዛብህ አድርግልኝ ብሎኝ ያደረግሁት ነው» ብለው ስለአመኑ ራስ በዛብህ ባባታቸው ላይ ስዒረ መንግሥት በማድረግ ተከሰው ጅበላ ታሰሩ።
ከአስር ዓመታት እስር በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በኮሶ መድኃኒት ምክንያት በድንገት ታመው አንድ ወር ያህል ቆይተው ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም. ዐርፈው በደብረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ። ራስ በዛብህም በታሰሩበት ስፍራ በጅበላ አምባ ሳሉ የአባታቸውን የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ሞት ተረድተው ሲያለቅሱ እንዲህ የሚል የግጥም ቃል ተናገሩ፤
ንጉሥ ትናንት ሞተው ጎጃም ተሸበረ፣
እግሬ ባይታሰር ልቅሶዬ ነበር፤
ይህን ማለታቸው አዲስ አበባ ተሰምቶ በዳግማዊ ምኒልክ ትዕዛዝ ከእስር እንዲፈቱ ተደረገና በአባታቸው ሐዘን ላይ ተቀመጡ። የልቅሶውም ወራት ከተፈጸመ በኋላ የንጉሡ ልጆችና መኳንንቱ የወግ ዕቃ ይዘው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ እቃውን ለዳግማዊ ምኒልክ አስረከቡ። ዳግማዊ ምኒልክም ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ግዛት ዳሞትና አገው ምድርን ለራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ሰጥተው ሾሙና በተቀረው የጎጃም ክፍል ደግሞ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ታናሽ ልጅ ራስ ኃይሉን ሾሙበት።
ራስ ኃይሉ ምስራቁን የጎጃም ክፍል አንድ ዓመት ከገዙ በኋላ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከምን ገድለው ጎጃምን በሙሉ ጠቅልለው ለመግዛት አሲረዋል፤ በራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ላይ የተንኮል ቃል አሳትመው በዳሞትና አገው ምድር አሰራጭተዋል ተብለው በዐፄ ምኒልክ ፊት ክስ ስለቀረበባቸው፤ ከተከራከሩ በኋላ በማስረጃና በምስክር ስለተረቱ፣ እርሳቸውም ማድረጋቸውን ስላመኑ ሚያዚያ 30 ቀን 1894 ዓ.ም. ተፈርዶባቸው በአፍቀራ ኮረብታ ታሰሩ።
ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ምኒልክ ራስ በዛብህን በወንድማቸው በራስ ኃይሉ ግዛት ሾመው ሰደዷቸው። በዓመቱም የልጅ ልጃቸውን ወይዘሮ ዘነበ ወርቅ ሚካኤልን ሚያዚያ 19 ቀን 1895 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ዳሩላቸው። ወይዘሮ ዘነበ ወርቅ ከዳግማዊ ምኒልክ ልጅ ከወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክና ከራስ ሚካኤል የተወለዱ ሲሆን የልጅ እያሱ እኅት ናቸው። ለባለቤታቸው በጎጃም አንድ ዓመት ያህል ከቆየች በኋላ በ1896 ዓ.ም. ባልታወቀ ምክንያት ሞተው በደብረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል።
ራስ በዛብህም ምስራቁን የጎጃም ክፍል ሶስት ዓመት ያህል እንደገዙ እንደ ወንድማቸው እንደራስ ኃይሉ የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ግዛት የሆኑትን ዳሞትና አገው ምድርን ደርበው ለመያዝ ስለፈለጉ ራስ ቢትወደድ መንገሻን ለመውጋት ምክር ያዙ። ከምክሩ አንዱ ደጃዝማች ወዳጄ የተባሉ ባለሟላቸውንም ከዳሞትና የአገው ምድር ተዋጊ እንዲመለምሉ ደብዳቤ ጽፈው፣ ማኅተም አትመው የላኩት ሚስጥር ነው። በዚህ መካከል ደጃዝማች ወዳጄ አምባጓሮ ተፈጥሮ ሰው ስለገደሉ በ1897 ዓ.ም. ሸፈቱ። እጃቸውን የሚይዝ ወታደር ቢላክ አልያዝም ብለው አስቸገሩ። የማች ዘመዶች ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለዐፄ ምኒልክ አቤት ስላሉ ዐፄ ምኒልክም «በግዛትህ የሸፈተውን ነፍሰ ገዳይ ወዳዝማች ወዳጄን ይዘህ በቶሎ ስደደው፤ አለበዚያ አንተ ታልፍበታለህ» የሚል የንጉሠ ነገሥቱ ጥብቅ ትዕዛዝ ወደ ራስ በዛብህ ላኩ።
ራስ በዛብህም ይህ ጥብቅ ትዕዛዝ ከደረሳቸው በኋላ ወደ ደጃዝማች ወዳጆ «አስታርቅሀለሁና አይዞህ ግባ» ብለው ላኩባቸው። ነገር ግን በእምቢታቸው ስለጸኑ በጦር ኃይል አስከብበው አስይዘው ወደ አዲስ አበባ ሰደዷቸው። ደጃዝማች ወዳጆም አዲስ አበባ በደረሱ ጊዜ ይዘው የሰጧቸውን ራስ በዛብህን ለመበቀል ራብ ቢትወደድ መንገሻ አቲከምን ለመግደል መነሳታቸውንና ለዚህም ከዳሞትና የአገው ምድር ተዋጊ እንዲመለምሉ ደብዳቤ ጽፈው፣ ማኅተም አትመው የላኩባቸው መሆኑን ሚስጥር አወጡ። ለማስረጃም ራስ በዛብህ የላኩላቸውን ደብዳቤ ከነማኅተሙ ለዐፄ ምኒልክ አቅርበው አሳዩ።
ዳግማዊ ምኒልክም ማኅተሙን ከተመለከቱ በኋላ ራስ በዛብህን ከጎጃም ጠርተው «ይህ ማኅተምህ አይደለም ወይ?» ብለው ቢጠይቋቸው «ደጃዝማች ወዳጄ ደመኛዬ ነበርና ምናልባት ማኅተሜን ከአሽከሮቼ ዘንድ አግኝቶ አትሞት ይሆናል፤ በዚህ ማኅተም ሊፈረድብኝ አይገባም» ብለው ተከራከሩ። ደጃዝማች ወዳጄም «ማኅመቱ ቢቀር በምስክር እረታለሁ» አሉና ሚስጢሩን የሚያውቁ ሦስት የጎጃም መኳንንትን ምስክር ጠርተው አስመሰከሩ። በዚህ ጊዜ ራስ በዛብህ «አዎ ጥፋቴ ነው» ብለው ስላመኑ ግንቦት 16 ቀን 1897 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ችሎት ላይ ቅጣት ተፈረደባቸው። ከዚያም ወደ አፍቀራ ኮረብታ ተወስደው ከወንድማቸው ከራስ ኃይሉ ጋር ታሰሩ።
ራስ በዛብህ በአፍቀራ ሶስት ወር ያህል ከወንድማቸው ጋር እንደታሰሩ በድንገት ታመሙማ ነሐሴ 12 ቀን 1897 ዓ.ም. በ45 ዓመታቸው ሞተው አፍቀራ አምባ ተቀበሩ። ከወንድማቸው ጋር አንድ ቦታ ታስረው ሳለ መሞታቸውን የሰማችዋ አዝማሪም፤
ሞጣ ቀራንዮ ሞልቶ ካህናቱ፣
እነራስ በዛብህ ሳይፈቱ ሞቱ፤
ብላ ገጠመች። ገጣሚዋ እነ ራስ በዛብህ ያለችው ራስ በዛብህንና አብረዋቸው ታስረው የነበሩትን ወንድማቸውን ራስ ኃይሉን ነበር። የግጥሙ ወርቅ ከወንድማቸው ጋር የታሰሩት ራስ በዛብህ ከወህኒ ቤት ሳይወጡና ከግዞት ሳይለቀቁ እንደ ታሰሩ ሞቱ ወይንም ዐረፉ ማለት ሲሆን ሰሙ ደግሞ የቁም ፍትሐት ሳይደርስላቸው ምሕላ ሳይደረግላቸው ሞቱ ማለት ነው።
ራስ በዛብህ የጸረ ፋሽስቱ አርበኛ የጀግናው ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ አባት ናቸው። ቢትወደድ ነጋሽ ፋሽስት ጥሊያንን አቧራ ባስገሱበት የአምስቱ ዓመት የተጋድሎ ዘመን እንዲህ ተብሎ የተገጠመላቸው ጀግና ነበሩ፤
የታጠቀ ጎበዝ ይዞት ጎጃምን፣
ተጨንቆ ሊሞት ነው ሰላቶ ጥሊያን፣
ሲያየው ይጨነቃል ደምስ ነጋሽን፤ 
የጥሊያን ፋሽስቶች ከሮማ ተነስተው መጡ ገሰገሱ፣
ኢትዮጵያን ሊይዙ ሃይማኖት ሊያፈርሱ፣
የነጋሽ መሪያችን ደምስ ፈረሱ፣
መልሰው ተዋጋው አንተነህ ንጉሡ፤
 
ደምስ የቢትወደድ ነጋሽ የፈረስ ስም ነው። አሳዛኙ ነገር የቢትወደድ ነጋሽ በዛብህን  ሕይዎትም የአባታቸው እጣ  ፈንታ ማጋጠሙ ነው። በ1943 ዓ.ም. ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪና መቶ አለቃ በቀለ አናሲሞስ ጋር በመሆ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ገድለው መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሲያሴሩ በመገኘታቸውና የተፈራረሙበት ወረቀት ወረቀትም በመያዙ፤ እነሱም ዙፋን ችሎት ቀርበው ስዒረ መንግሥት ለማድረግ የተፈራረሙበት ወረቀት የነሱ መሆኑን በማረጋገጣቸው የበሞት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው።
ሆኖም ግን ንጉሡ ምህረት አድርገውላቸው የሞት ቅጣቱ ወደ እስር ተለመጠላቸው። ጅማ ወደ ሀያ ዓመታት የሚጠጋ ታስረው ተቀመጡ። በእስር ላይ እንዳሉ ስለታመሙ እንዲፈቱ ተደርጎ አዲስ አበባ ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው ነሐሴ 2 ቀን 1964 ዓ.ም. ከዚህ ዓመት በሞት ተለዩ። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ነሐሴ 4 ቀን 1964 ዓ.ም. የተፈጸመ ሲሆን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ልጃቸው አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፉ ተደርጓል።
Filed in: Amharic