>

ኢትዮጵያዊነታችን ለፖለቲካ ቡድኖች በምንሰጠው አስተያየት አይለካም!  (አበበ ቶላ)

ኢትዮጵያዊነታችን ለፖለቲካ ቡድኖች በምንሰጠው አስተያየት አይለካም! 
አበበ ቶላ
ይህ የአቋም መግለጫ … 
እኔ የምነግርህ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በጠላትነት የምፈርጀው የፖለቲካ ድርጅት የለም። ለምሳሌ ህውሃትን ጥቀስ ህውሃት ብዙ ጠንካራ ጎኖች አሉት በርካታ ድክመቶችም አሉት። ጥሩውን ህውሃት ስለሆነ ብዬ አላጣጥልም በይፋ ሳደንቅ ልታየኝ ትችላለህ አትደንግጥ ወዳጄ! መጥፎውንም ተው ከማለት ወደኋላ እንደማልል ራስህ ምስክር ነህ፤ እሺ ሌላ ላምጣልህ፤ አብን እንደ ፖለቲካ ንቅናቄ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ለተነሳለት አላማ ብዙ የተዋጣለት እንቅስቃሴ ያደርጋል። የተዋጣለት እንቅስቃሴውን አድንቃለሁ አንዳንዴ ቆሜ የማጨበጭብላቸው ግዜያቶች አሉ። በዛው ልክ ደግሞ ከአብን ብዙ የምቃወማቸው ነገሮች አሉኝ። እነርሱንም በአደባባይ እቃወማለሁ። ኦነግንም ብትል ብዙ የማደንቅለት ነገር አለኝ። ከኢ… ብዬ እንዲተው የምመክረው እና አጥብቄ የምቃወመውም ነገር አለኝ። ኢ-ዜማ ጋ ስትደርስ አዲስ መስመር ያስፈልገዋል።
ልክ በአሁኑ ሰዓት የግድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አለብህ የሚል አስገዳጅ አዋጅ ቢመጣ ያለ ምንም ማወላወል አባል የምሆነው የኢ-ዜማ ፓርቲ አባል እንደሆነ ልነግርህ እወዳለሁ። ባለፈው ግዜ ሰምተከኝ ከሆነ እንጃ እንጂ፤ ኢህአዴግ መዋሃድ ደረጃ ከደረሰ ከፋይ አባል እንደምሆን ነግሬህ ነበር። ከዚህ በፊት ያልነገርኩህ የአንድነት ፓርቲ አባል ልሆን ለትንሽ ነው የተረፍኩት። የሆነ ወቅትም ከምኖርበት እንግሊዝ ተነስቼ ግንቦት ሰባትን ተከትዬ ኤርትራ ጫካ ልገባ ስል ለጥቂት ነው ሃሳቤን የሰረዝኩት (እየቀለድኩ አይምሰልህ የምሬን ነው) ይሄ የሚነግርህ ምንድነው መሰለህ ከብሄር ፓርቲዎች ይልቅ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ይበልጥ ቀልቤን እንደሚስቡት ነው።
ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ቀልቤን ይስበዋል ማለት ሁሉም ሰው እንደኔ ማሰብ አለበት እንደኔ ያላሰበ ሁሉ ከኢትዮጵያዊነት የጎደለ ነው የሚል እምነት አያሳድርብኝም። ኢትዮጵያዊነታችን አባል በምንሆንበት ወይም በምንደግፈው እና ፓርቲ ፈጽሞ መወሰን የለበትም።
ስለኔ የምነግርህ፤ ራሳቸውን በብሄረሰባቸው ያደራጁ ቡድኖች ውስጥ አባል ሆኜ መቼም አታየኝም። ነገር ግን ደግሞ  ዘረኞች ናቸው ብዬ በደፈናው ሳጣጥላቸውም አትሰማኝም። ከላይ እንዳልኩህ አንዳንድ ግዜም እደግፋቸዋለሁ እንደ ኦዲፒ እና አዴፓ ያሉት በዚህ ወቅት ለዘብተኛ ብሄርተኛ ይመስሉኛል እና ብዙ ሃሳቦቻቸውን እደግፋለሁ (እነርሱም ጋር ቢሆን አባል ወይም የተመዘገበ ደጋፊ ለመሆን ፍላጎትም ሃሳብም የለኝም) በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የተደራጁ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ቀልቤን ይስቡታል ስልህም ምንም ቢያጠፉ ባላየ አልፋቸዋለሁ ማለት አይደለም።
ለኔ አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት አንድ አይደለም። ብዙ ነው። በውስጡ ብዙ መልካም ህሳቦች እንዲሁም ብዙ ጥፋት ሃሳቦች አሉት። ጥፋት ጥፋቱን እየነቀስኩ እቃወመዋለሁ። መልካም መልካሙን ሃሳብ ደግሞ በርታ እሰይ እለዋለሁ። በርካታ ወዳጆቼ ይሄ ድርጊቴ ግራ ያጋባቸዋል። አስመሳይ፣ ዥዋዥዌ፣ አቋመ ቢስ፣ ወላዋይ… የሚሉ ስሞችን በተደጋጋሚ ተሸልሜያለሁ።
ይሄውልህ ወዳጄ፤ ለአንተም ቢሆን ከዚህ በፊት በፌስ ቡኬ ላይ ያልኳትን ድጋሚ ላምጣልህ፤
እንካ ምክር፤ ጉዳዩን ጠበቅ ባለጉዳዩን ለቀቅ አድርገው!
በሰው ላይ ወይም በድርጅት ላይ አንድ አቋም አትያዝ። ለምን በለኝማ… አንድ ሰው አንድ አይደለም። አንድ ድርጅትም አንድ ባህርይ ብቻ የለውም። በአንድ ጉዳይ ላይ ጠምደህ የያዝከው ሰው በሌላ ጉዳይ ላይ ምርጥ ከምትላቸው መካከል ይሆንና ቀድመህ አቋም ከያዝክበት ‘’እሰይ የኔ አንበሳ’’ ማለቱ አበሳ ይሆንብሃል። ድርጅትም እንደዛው ነው፤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ‘’ሰይጣን’’ ብለህ ደምድመከው፤ አቋም የያዝክበት ድርጅት የሆነ ቀን ከመከራ የሚያወጣህ ይሆንና ‘ሰይጣንዬ ምስጋና ይግባህ’ አትለው ነገር ይጨንቅሃል።
እውነቴን ነው የምልህ፤ አቋም መያዝ ካለብህ ጉዳዩ ላይ አቋም ያዝ። ስትጠላም ሆነ ስትወድ ጉዳዩን እንጂ ባለ ገዳዩን እርሳው፤ ‘’የምንፈራው ግፍን እንጂ ግፈኛን አይደለም’’ እንዳለው እስክንድር ነጋ ግፍ እና ግፈኛን ለይ። ትክክል ያልሆነን ጉዳይ ማንም ያራምደው ማ በቃ አትስማማ! የምትወደው ድርጅት ወይም የምትወደው ሰውዬ ትክክል ያልሆነ ጉዳይ ሲያነሳ ተው ለማለት አትፍራ። ትክክለኛ ጉዳይን ደግሞ ማንም ያንሳው ማ ለመደገፍ አትሽኮርመም።
በአንድ ግዜ በሆነ ጉዳይ ላይ የወቀስከውን ሰው በሌላ ግዜ ጥሩ ነገር ሲያደርግ ስታገኘው ለማመስገን አትስነፍ። ምናልባት ሰዎች ወላዋይ፤ ወይም ደግሞ አቋም የለሽ ሊሉህ ይችላሉ። ይበሉህ ስላልገባቸው ነው። እኔ በጉዳይ ላይ እንጂ በባለ ጉዳይ ላይ አቋም አልይዝም በላቸው!
Filed in: Amharic