>

"የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ በተለይ የጌድዮ ተፈናቃዮችን በሐይል ወደ ቀያቸው እየመለሰ ነው!!!" (የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ መግለጫ) 

“የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ በተለይ የጌድዮ ተፈናቃዮችን በሐይል ወደ ቀያቸው እየመለሰ ነው!!!”
የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ መግለጫ
ባለፈው ዓመት በጎሳዎች መሐል በተነሳ ግጭት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ተሰደዱ። Refugees International (RI) የኢትዮጵያ መንግስት ያለ በቂ ጥናት በሐይል አስገድዶ ወደ ነበሩበት ቀዬ ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት በፅኑ ይኮንናል።
የRI አንጋፋው የመብት ተሟጋች የሆነው ማርክ ያርኔል ወደ ቦታው የተጓዘው በመስከረም 2018 እኤአ ነው።
«እዚያ ስደርስ በጣም የሚዘገንን ክስተት ሸሽተው የመጡ የተጎሳቆሉ ተፈናቃዮች ገጠሙኝ። ሙሉ መንደራቸው በእሳት የጋየባቸው አሉ። የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ተፈናቃዮች ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅት ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት በጣም አሳሳቢና የተፈናቃዮቹን ሁኔታ ምንም ያላገናዘበ ነው…» ይላል።
የRI እርዳያ ሰጪ ሰራተኞች በመስከረም ወር ቦታው ሲደርሱ የታዘቡት ነገር የመንግስት አካላት ተፈናቃዮቹን እርዳታ እንዳያገኙ በመከልከል «እርዳታ የምንሰጣችሁ ቀያችሁ ከተመለሳችሁ ብቻ ነው!» በማለት በግዴታ ተፈናቃዮቹን ለመመለስ እየሞከሩ እንደሆነ ነበረ። በወቅቱ በዚህ ግዴታ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች ከወደመው መኖርያቸው አቅራቢያ እንዲሰፍሩ ከመደረጉ ውጭ ቃል የተገባላቸውን መቋቋምያ እርዳታ ሊያገኙ አልቻሉም። አብዛኞቹ ደግሞ በወርኃ ታህሳስ ላይ ባገረሸው ሁለተኛ ዙር ግጭት ምክንያት ተመልሰው ተፈናቅለዋል።
•°•
ባለፈው ወር (ሚያዝያ) የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከባለፈው ስህተታችን ተምረናል በማለት አዲስ የሐገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለስ ፕሮግራም ይፋ አደረጉ። ፕሮግራሙ ተፈናቃዮቹ የሚመለሱት «ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ፣ በራሳቸው ሙሉ በጎ ፈቃድ ብቻ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩና ሲመለሱ ተመሳሳይ መፈናቀል እንዳይደርስባቸው ባረጋገጠ መልኩ…» እንደሚሆን ይገልፃል። ሆኖም በቅርቡ እየታየ ያለው መንግስት ባወጣው ፕሮግራም ላይ ያስቀመጠውን ቃሉን በማጠፍ ተፈናቃዮችን ከማስገደድ ጀምሮ የሰፈሩበትን ቦታ ሆን ብሎ በማፈራረስ አማራጭ በማሳጣትም ጭምር ወደ ተፈናቀሉበት ቦታ እየመለሷቸው ይገኛል።
•°•
ማርክ ያርንሌ አስተያየቱን ሲቋጭ «እጅግ በጣም አሳፋሪ የሚያደርገው ኢትዮጵያ የራሷን ተፈናቃዮች በዚህ መልኩ እያጉላላችና እያሰቃየች የሌላ ሐገር ስደተኞችን የሚያርሱበት መሬት እና የስራ ፈቃድ እሰጣለሁ ብላ ከተለያዩ ሐገራትና ዓለማቀፍ ተቋማት እየጎረፈላት ያለው ከንቱ ውዳሴ ነው!» ይላል።
ዮናስ ሀጎስ
Filed in: Amharic