>
1:19 pm - Thursday December 8, 2022

ክልልነት ምን ማለት ነው? የመጨረሻ ግቡስ ምንድነው? ለምንስ ያሰጋሃል? (ዳንኤል ገዛህኝ)

ክልልነት ምን ማለት ነው? የመጨረሻ ግቡስ ምንድነው? ለምንስ ያሰጋሃል?
ዳንኤል ገዛህኝ
ውዝፍ እና አዳዲስ የክልልነት ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ አደባባይ እየወጡ ነው፡፡ ይህ የሚያስደነግጠውና የሚያስቆጣው ወገንም አለ፣ የፌደራል ሥርዓትን የሚደግፈው ጎራም ቢሆን፡፡
ግን ክልልነት የመጨረሻ ግቡ ምንድነው?
– የፌደራል ሥርዓቱ «በመርህ ደረጃ» እስከ ዞን እና ወረዳ ድረስ እራስን የማስተዳደር ዓላማ አለው፤
– ክልል መሆን ግን የሚለየው በቀጥታ ከፌደሬሽን አባላቱ አንዱን መሆን ማለት መሆኑ ነው (በዋነኛነት)፤
– ይህ ደግሞ የራስን መተዳደሪያ በጀት በቀጥታ ከፌደራል መንግሥቱ ተቀብሎ ጥቅም ላይ ማዋል ማለት ነው፤
– በጀት ደግሞ ቀመሩ (ወይም የክፍፍል ምጣኔው) ሕዝብ ቁጥርን መሠረት ያደረገ ሲሆን ልዩ ድጋፍ ወይም እገዛ የሚሻ ክልል መሆንም ሌላው የድጎማ መስፈርት ነው፤
– የፌዴራል ሕገመንግሥቱን ካየነው ፌደሬሽኑን የመሠረቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ናቸው ይላል፤ ይህም ማንኛውም ብሔር ወይም እንደ አዲስ አበባ ነዋሪ ዓይነት ሕዝብ ክልል ልሁን ቢል የማያስገርም ብቻ ሳይሆን ሕገመንግሥታዊም መብት ነው፤
– ይሁንና ክልል መሆን በዓመት ከአንድ መለስተኛ ትምህርት ቤት መገንቢያ በጀት በላይ ለማያስገኝለት ብሔር ከስም ያለፈ አዋጭነት አይኖረውም፤ ማለትም ዞን ሆኖ የተቀናጀ አሰራርና የተማረ የሰው ኃይል ይዞ በሚዛናዊነት በሚያስተዳድር ክልል ስር መተዳደር የተሻለ አዋጭነት ሊኖረው ይችላል፤
– በሌላ በኩል ደግሞ አምራች፣ እንዲሁም ለአጠቃላይ ሀገሪቱ ደህና ገቢ የሚያቀርብ ብሔር፣ ምናልባትም በጀቱን በራሱ ፖሊሲና ራዕይ ቢያፈስ ተጠቃሚ የሚሆን ሕዝብ ክልልነት ሊያዋጣው ይችላል፤
– ስለዚህም በደቡብ ክልል የሚገኙ 50+ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሁሉም ክልል የመሆን መብት ቢኖራቸውም፣ ለሁሉም አዋጭ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
ስጋቶችን ስለመጋራት . . .
– ክልል መሆን ቅጥ-ያጣ ባለቤትነት ነው ከሚልና ሌላውን ነዋሪ እንደሌላ ዜጋ ቆጥሮ የማባረር እቅድ ላይ የተመረኮዘ ከሆነ ነውር ነው፤
– ነውር ብቻ ሳይሆን ዋናውን የሕጎች ሁሉ የበላይ፣ የፌደራል ሕገመንግሥት መጣስ ነው፤
– ይህ በርግጥ አዲስ ከሚወለዱት በላይ አሁን የሚገኙት አብዛኛዎቹ ክልሎች የተገበሩት ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ነው፤
– አሁን ያሉት ክልሎች በሕገመንግሥቶቻቸው ያሰፈርዋቸው የአንድ ወይም የተወሰኑ ብሔሮች የበላይነትና የክልሉን ባለቤትነት የሚያንፀባርቁ አንቀጾች ከዋናውና ከፌደሬሽኑ መሥራች ሕገመንግሥት ጋር የሚቃረኑ ናቸው፤
– የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የመስራት፣ ንብረት የማፍራት፣ የመምረጥ እና የመመረጥ የፌደሬሽኑ ዜጎች መብቶች በብዙ የክልል ሕገመንግሥቶች ተጥሰዋል፤ እነዚህ የክልል ሕገመንግስቶች ወይም የተወሰኑ አንቀጾቻቸው ኢ-ሕገመንግሥታዊ (Unconstitutional) ተብለው ሊወገዱ ይገባል፤ አዲስ ክልሎች ተወልደው ተመሳሳይ ሕግ አውጥተው ተመሳሳይ በደል ከመፈፀማቸው በፊት፤
– የፌደራሉ ሕገመንግሥት አንድ የምርጫ ክልል ለማይሞሉና የፌደራል የፖለቲካ ውክልና በመደበኛ ምርጫ ማግኘት ለማይችሉ «አናሳ» ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስከ 20 የሚደርስ የፓርላማ መቀመጫ «ሪዘርቨ» አድርግዋል፤ በቂ ይሁንም አይሁንም ወይም እስከዛሬ ቢተገበርም ባይተገበርም ይህን እድል ግን በፌደራል ደረጃ አቅርቦ እናየዋለን፤
– አብዛኞቹ የክልል ሕገመንግሥቶች ግን በክልሉ ለሚኖሩ አናሳ ብሔሮች፣ እንዲሁም በቁጥር አናሳ ባይሆኑም ክልሉ በእነሱ ላልተሰየመ የክልሉ ነዋሪ ሌላ ብሔሮች ተመሳሳይ የፖለቲካ ውክልና ሲያበረክቱ አላየንም፤ እንዲያውም የማግለልና የመጨቆን ባህሪይ አላቸው፤
– ስለዚህም እነዚ የሕግ ጥሰቶችና የአስተዳደር ወሰን የግንዛቤም ሆነ የቅንነት እጥረት በሰፈነበት ሁናቴ አዲስ ክልል መወለድ ከስጋት ላይ ቢጥል አይገርምም፡፡
Filed in: Amharic