>

የሸገር ነገር... (አቻምየለህ ታምሩ)

የሸገር ነገር…
አቻምየለህ ታምሩ
አዲስ አበባ ፊንፊኔ እንዳልሆነ፤ ፊንፊኔም እንደ አዲስ አበባ ሁሉ  የአማርኛ ቃል እንጂ ኦሮምኛ እንዳልሆነ የተረዳው ብልጡ ዐቢይ አሕመድ የኦሮምኛ ቃል መስሎት የዋና ከተማችንን ስም  ሸገር በሚል ቀይሮ  የአዲስ አበባን ስም የሚያስረሳ ሰም  ከፍ አድርጎ እያስተዋወቀው ይገኛል። ሸገርን በማስዋብ ስም የአዲስ አበባ ቀደምት ኗሪዎች አፈናቅሎ  የከተማዋን ዲሞግራፊ ለመቀየር  የሚያስችለውን ገንዘብ ለማሰባሰብም አምስት ሚሊዮን የሚከፈሉበት  ግብር ሊያበላ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።
ዐቢይ ለስሙ በርዕሰ መንግሥትነት የተሰየመው በሕገ መንግሥት ተብዮው ቃለ መሐላ ፈጽሞ ነው። በሕገ መንግሥት ተብዮው ቃለ መሐላ የፈፀመ ደግሞ ንግግሩም ሆነ ሥራው በሕጉ መሰረት መሆን ነበረበት።  ሕገ መንግሥት ተብዮውን አክብሩ የሚለን ብልጡ  ዐቢይ ግን  ዐቢይ  ቃለ መሐላ የፈፀመበት ሕገ መንገሥት አዲስ አበባ እንጂ ሸገር የሚባል ዋና ከተማ  የሚያውቅ ይመስል  ሕገ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደረጃ  በሚያወጣቸው ሰነዶች ሳይቀር «ሸገርን እናስውብ» እያለ ሰነዶችን ያሰራጫል። ዐቢይ «ሸገርን እናስውብ» ሲል በውስጡ ያለችው «ኦሮምያ»  የሚባለው ክልል ዋና ከተማ እንጂ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ አይደለችም።
ሕገ መንግሥት ተብዮው የሚያውቃትን አዲስ አበባን  ሕገ መንግሥት ተብዮው በማያውቃት ሸገር የቀየረው  ዐቢይ አሕመድ የአጭር ጊዜ አላማው  አዲስ አበባ የሚለውን ስም ለማደብዘዝና አዲስ አበባን እያስረሳ  በሸገር ለመተካት  ሲሆን የረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ  ከተወነሱ አመታት በኋላ የሚመጡ ልጆች የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ሳይሆን ሸገር ነው ብለው የሚከራከሩበት ሰነድ ትቶ ማለፍ ነው። ይህ ያልገባቸው ሰልፍ አሳማሪዎች ሸገር፣ ሸገር እያሉ አዲስ አበባን ሲያደበዝዙ ይውላሉ። እነዚህ ሰልፍ አሳማሪዎች የኢትዮጵያን ስም ወደ ኩሽ ለመቀየር ጅግጅጋ ላይ በነ  ዐቢይ  የተጠራውን ስብሰባም ታድመው ነበር።
ዐቢይ ሸገርም ልክ እንደ ፊንፊኔ ሁሉ አማርኛ እንጂ ኦሮምኛ እንዳልሆነ ቢይውቅ ኖሮ   የዴሞግራፊ ለውጥ ሊያደርግ እየሰራባት ላለችው አዲስ አበባን በሌላ ስም ይዞ ይመጣ ነው።
የሆነው ሆኖ ሸገር  የአዲስ አበባ አንድ  መንደር  መጠሪያ እንጂ የአዲስ አበባ የቀድሞ መጠሪያም ከአዲስ አበባም ጋር አንድ  አይደለም። ሸገር የሚባለው አዲስ አበባ ሰፈር አሁንም ደረስ  በቦታው ይገኛል። ሸገር የሚባለው የአዲስ አበባ ሰፈር  ሸገር መናፈሻን ይዞ ያለው የጉለሌ አካባቢ ነው።  ሌላኛው የአዲስ አበባ ሰፈር  ፊንፊኔ  ሲሆን የሚገኘው ደግሞ የፍል ውሀ አካባቢ ነው። ዛሬ ኦሮምያ የሚባለው ክልል ውስጥ የሚገኘው ገፈርሳም የአዲስ አበባ መንደር ነበር።
አሳዛኙ ነገር የኢትዮጵያን ስም ወደ ኩሽ፤ የአዲስ አበባን ስም ደግሞ ወደ ሸገር ለመቀየር የዐቢይ አገዛዝ  ሌት ተቀን  እየሰራ ያለውን ሴራ ላለማየት ብዙ ሰው ሰልፍ አሳማሪ ሆኖ  ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ቀብሯል።
Filed in: Amharic