>
9:03 am - Wednesday December 7, 2022

ባብሩ መስመሩን የሳተው  መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ነው!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ባብሩ መስመሩን የሳተው  መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ነው!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ከሰሞኑ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም. ስለተካሄደው መፈንቅለ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ብዙ እየተወራ ይገኛል። ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በግፍ የረሸናቸው መኮንኖች ስም እየተጠራ መፈንቅለ መንግሥቱ ቢሳካ ኖሮ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የተሻለ ይሆን እንደነበር ትንተና እየሰተሰጠው ነው። እኔ ግን መፈንቅለ መንግሥቱ ቢሳካ ኖሮ ኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ላይ ልትደርስ ትችል ነበር ከሚሉት ሳያዩ ከሚያምኑ ወገን አይደለሁም።
በኔ እምነት ባቡሩ መስመሩን የሳተው ኢትዮጵያን የሚያውቋት እነ ይልማ ደሬሳና ሐዲስ አለማየሁ ያዘጋጁት ፍኖተ መርህ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. በወታደሮች ተቀዶ ተጥሎ የሳንድረስትና የሳንሲዬር ምሩቃን በነበሩባት አገር ምንም የማያውቁና ኢትዮጵያን የማያውቋት ደመወዝ ለማስጨመር የተሰባሰቡና በጥላቻ የናወዙ ሻለቆችና ሌጣ የበታች መኮንኖች በመንግሥትነት ተሰይመው የኢትዮያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል የሆኑት የነመኢሶን፣ ኢሕአፖ፣ ኦነግና መሰል የግራ ድርጅቶች ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሲሆኑ ነው።
ያ ትውልድ የተጠማ ትውልድ ነው። ከፋሽስት ጥሊያን ባልተናነሰ በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ደም እንደ ያ ትውልድ የተጨማለቀ የኢትዮጵያ ጠላት የለም። እነ መንግሥቱና አጥናፉ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ያስጠሉ መስሏቸው ደጃዝማች በላይ ዘለቀንና አፈ ንጉሥ ታከለ ወልደ ወልደ ሐዋርያትን ከፍ ከፍ ሲያደርጓቸው ነበር። እነዚህ ሁለት አርበኞች ግን የ1953ቱን የመንግሥቱ ንዋይ ጭፍጨፋ ቢያልፉ የኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግድያ አያልፉም ነበር።
ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የደርግ ሊቀመንበር ለመሆን የበቃው ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም. የደርግ ሊቀመንበርና ርዕሰ ብሔር የነበረውን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን አርዶ ነው። በዚህ ቀን ሻምበል አለማየሁ ኃይሌን ጨምሮ ሌሎች አምስት የደርግ አባላት ተረሽነዋል። ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እነ ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከገደለ በኋላ «መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርጉ የተነሱትን አድመኞች ምሳ ሲያስቡ ቁርስ አደርግናቸው» ፤ «አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል» አለን።
ይታያችሁ! መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርጉብኝ ተነስተው ቁርስ አደርግኋቸው የሚለንኮ ሊቀመንበሩንና ርዕሰ ብሔሩን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ነው! ለወትሮው መፈንቅለ መንግሥት የሚደረገው ከታች ወደ ላይ ነበር። መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግን ካላይ ያሉት የደንጉን ሊቀመንበርና የአገሪቱን ርዕሰ ብሔር ጀኔራል ተፈሪ በንቲ ከታች ወዳለሁ ወደሱ መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርግ ስል ሲል ቁርስ አደረግሁት አለን! በዚህም መንግሥቱን በአለም ታሪክ መፈንቅለ መንግሥት ከላይ ወደታች የተደረገበት ብቸኛው ሰው ያደርገዋል።
ወደ ጀኔራል ተፈሪ ስንመለስ ደግሞ ጀኔራሉ የደርግ ሊቀመንበር ለመሆን የበቃው የንጉሠ ነገሥቱ የእልፍኝ አስከልካይ የነበሩትን ጀኔራል አሰፋ ደምሴን እንዲረሸኑ አድርጎ ነው። ለዚህ ማስረጃ የሚሻ ቢኖር የጀኔራል ተፈሪ በንቲ ረዳት የነበሩት ጀኔራል ኃይሉ በረቅዋ የጻፉትን የሕይዎት ዘመን ማስታወሻ ያንብብ።
የ1981ዱ መፈንቅለ መንግሥት ከከሸፈባቸው ምክንያቶች ዋነኛው የጀኔራል መርዕድ ንጉሴና የጀኔራል ፋንታ በላይ የስልጣን ሽኩቻ ነበር። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁለቱ ጀኔራሎች እንደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ተፈሪ በንቲ መኋኋናቸው አይቀሬ ነበር። ሁለቱም ጀኔራሎች በፍቅረ ንዋይና በፍቅረ ሥልጣን ያበደው ትውልድ አባላት ነበሩ። ሁለቱም በወንበር ጠብ ውስጥ የገቡት ገና መፈንቅለ መንግሥቱ ይሳካ አይሳካ ሳይታወቅ ነበር።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ የመጣው የፋሽስት ወያኔና የናዚ ኦነግ የግፍ አገዛዝ ነው። የዚህ የግፍ አገዛዝ ክፋት የምንኖርበት ስለሆን ስለዚህ ዘመን ጭካኔ ነጋሪ አያሻም።
ባጠቃላይ ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. በኋላ የመጣንበት መንገድ የቁልቁለቱ፣ የጭካና የድንቁርና መንገድ ነው። በ1969 ዓ.ም. እና የ1981 ዓ.ም. የተከሰቱት የስዒረ መንግሥት ሙከራዎች ሁሉ የመቀዳደም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁለቱም ደም በተጠሙ ያ ትውልዶች የተካሄዱ ንቅናቄዎች የተካሄዱ ናቸው። በመሆኑም ብዙ ሰው ከሰሞኑ እያወራው እንዳለው የ1981ዱ ስዒረ መንግሥትም ቢሳካ ኖሮ ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣ ነበር ብዬ አላስብም።
ኢትዮጵያን የሚነካ መንገድ ያመለጠን ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን የሚያውቋት አንጋፋ ምሁራን አዕምሯቸውን ጨምቀው ያዘጋጁትን ፍኖተ ካርታ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጥለው ከውጭ ሳይመረምሩ የገለበጡት ቅራቅንቦ ጭነውብን ፍዳችንን እያሳዩ እስከዚህ የመጠንበትን ቁልቁለት መንገድ ስንከተል ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሔ ሊመነጭ የሚችለው ፈረንጆች እንደሚሉት ወደ drawing boardዱ ተመልሰን ባለፉት አርባ አራት ዓመታት የመከራ አመታት ውስጥ ኢትዮጵያን የማያውቋትና ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁት ዋለልኞችና መንግሥቱዎች ኢትዮጵያን ይዘው የወረዱበትን ቁልቁለት በእውቀት መመርመር ከጀመርን ብቻ ነው።
«ብሔር፣ ብሔረሰቦች» የሚባሉት ሁሉ ኢትዮጵያ በምትባል ዛፍ ስር የበቀሉ ሳሮች መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው። ተወደደም ተጠላም ሁላችንም ዛፍ ስር የበቀልን ዛፍ ነን። ዛፉ ሲወድቅ የምንጠፋው ሁላችንም አብረን ነው። የተቆረጠ ካርታ አንጠልጥሎ ሲዞር የሚውለው ሁሉ ግን ይህን ማሰብ አይፈልግም።
ዛሬ ባገራችን እየሆነ ያለው ሁሉ ባቡሩ መስመሩን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ከሳተ በኋላ እጣፈንታው አንድ በሆነ ሕዝብ መካከል የተዘራው አቤልና ቃኤልን የሚያስንቅ የጥላቻ ፖለቲካ ነው። በኔ እምነት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. የተሰበረውን የሰላምና የእድገት ምሰሶ መልሶ ለማቆም ብቸኛው መፍትሔ ያለፉት 44 ዓመታት የተፈጠሩትን ችግሮችና ምንጮቻቸውን ከጥግ እስከ ጥግ መመርመርና በጥሞና መፈተሽ ከቻልን ብቻ ነው። በደርግ ዘመን የተሞከሩ ሲዒረ መንግሥቶችና በወያኔ-ኦነግ የአገዛዝ ዓመታት ምርጫ 97ን ጨምሮ ያሳለፍቸው አጣሚዎች ተደርገው የሚቆጠሩት ሁነቶች ሁሉ አንዳቸውም ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ የሚያስችሉ እድሎች አልነበሩም።
ኢትዮጵያን የእጃቸው መዳፍ ያህል የሚያውቋት ትላልቆቹ እነ ይልማ ደሬሳና ሐዲ አለማየሁ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ፍኖተ መርህ አፈር ድሜ በልቶ ኢትዮጵያን የማያውቋትና ተሰርተው ያላለቁቱ ትናንሾቹ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና መለስ ዜናዊ በደረቱት ዝባዝንኬ እየተጓዝን የተለየ ውጤት መጠበቅ ትርፉ መድረሻችን አሁን ያጋመስነው እንደ አገር የመኖር እጣችን ለጊዜውም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት አሊያም የሚያቆምበት ደረጃ መድረስ ብቻ ነው። ይህንን የሚጠራጠር ካለ እስካዚያው ብርታቱን ይስጠው እንጅ ወደሜዳው እየዘለቅን ስለሆነ ስንደርስበት ያየዋል።
ከቻች የታተመው ተንቀሳቃሽ ምስል ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርም እነ ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከገደለ በኋላ ያስነገረው ዜና ነው። ሳይቀድሙት የመቅደም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ያ ትውልድ ሁሉ ሲያደርግ የኖረው ወይንም ቢያደርግ የሚሻው ይህን መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሲያደርግ የኖረውን አብዮታዊ እርምጃ ነበር።
Filed in: Amharic