>

ጠ/ሚንስትር አቢይ አህመድ በገበታ ለሸገር ግብዣ ላይ ያደረጉት ንግግር!!!

ጠ/ሚንስትር አቢይ አህመድ በገበታ ለሸገር ግብዣ ላይ ያደረጉት ንግግር!!!

ክቡራትና ክቡራን
እንደምን አመሻችሁ !
አሰላም አለይኩም 
Good Evening
ኒ ሐው
ናማስቲ
ቦና ሴራ   
‹በሰላምታህ አስቀድመህ ልቤን ረታህው› “You had me at ‘Hello’” ይላሉ እንግሊዛውያን፡፡ አገላለጹን ጠለቅ ብለን ከመረመርነው በውስጡ ታላቅ ፍሬ ነገር እንዳዘለ መገንዘብ አንቸገርም፡፡ በመጀመሪያው የግንኙነት ወቅት ለእንግዳችን የምናቀርበው ሰላምታ ከድምፀቱ እስከምንደረድራቸው ቃላትና እስከምናሳካው ሐረግ ለቀጣይ ግንኙነታችን መንገድ ጠራጊ ነው፡፡
 ሁሌም ግርምት የሚያጭርብኝ ጉዳይ በእንግዳ ተቀባይነታችንና በትኅትናችን የምንታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ከአብዛኞቹ ሀገራት በተለየ የግንኙነት ሰላምታ አሰጣጣችን በቀጥታ መልካም ከመመኘት ይልቅ የውሎና አዳር ደኅንነታችንን የሚጠይቅ ለምን ሆነ? የሚለው ነው፡፡
እንደምን አደርክ? እንደምን ዋልክ? እንደምን አመሸህ?
ከንጋት እስከ ምሽት ያለው የሰላምታ መግለጫ ሐረጎቻችን በልባችን ውስጥ ያለንን ጥልቅ ሐሳብና ፍቅር አያመለክቱም፡፡ ለምሳሌ ያህል በእንግሊዘኛ ቋንቋ ጠዋት ስንገናኝ Good Morning – መልካም ጠዋት እንላለን፡፡ በዐረብኛ ቋንቋም ‹አሰላም አለይኩም› (ሰላም በአንተ ላይ ይሁን፣ ሰላም ካንተ ጋር ይሁን) የሚል የሰላምታ ልውውጥ አለ፡፡ በጣልያንኛም ቢሆን  “Buon giorno” or “Buona sera”  ‹መልካም ጠዋት፣መልካም ምሽት› የሚል የሰላምታ ሐረግ ይገኛል፡፡ በሕንድ እጅን አጣምሮ የሚሰጠው ሰላምታ ከዚያም በላይ ርቆ በመጓዝ bhaarat mein namaskaar ‹በአንተ ውስጥ ላለው አምላክ ሰላምታ እሰጣለሁ› እስከ ማለት ይጓዛል፡፡
ታላቅ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕልና ዕምቅ የቋንቋ ክምችት ያለን ኢትዮጵያውያን የሰላምታ ቋንቋችንን መልሰን ማየት ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ ከሥጋትና ከጭንቀት በመውጣት የተስፋ ብርሃንን በልባችን ማሳደር ያሻናል፡፡ አዎን ከፊታችን አዲስ ቀንና አዲስ ተስፋ በመኖሩ እንደ ከተማችንና እንደ ሀገራችን ሁሉ ሰላምታችንም በሰላምና በአዲስ ተስፋ መታጀብ ይኖርበታል፡፡ የመኖር ደኅንነት ሰላምታችን ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡
በዚህ ታሪካዊ ቦታ ታሪክ ለመሥራት የተሰበሰባችሁ፣ ክቡራትና ክቡራን ዛሬ ለእናንተ የማነሣው አንድ ጉዳይ አለኝ፡፡
ስለ አቧራና አሻራ ጉዳይ፡፡
በትውልድ ጉዞ ውስጥ አቧራ ያስነሡም፣ አሻራ ያተሙም ሰዎች ነበሩ፤አሉ፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ አቧራ ማስነሣት ቀላል ነው፡፡ አካባቢን ማናወጥ ይበቃዋል፡፡ መርገጥ መረጋገጥ ከበቂ በላይ አቧራ ያስነሣል፡፡ አቧራው በቀላሉ ይታያል፡፡ ወደ ላይ በቀላሉ ይንሳፈፋል፡፡ በቶሎም በአካባቢው ሁሉ ይዳረሳል፡፡ በሀገራችንም ‹አቧራ ሲነሣ፣ ጉፋያ ሲያገሣ በቀላሉ ይታወቃል› ይባላል፡፡ ጉፋያ የተባለው ያረጀ የጃጀ አንበሳ ነው፡፡ አንድ ቦታ ሆኖ፣ ያለ የሌለ ዐቅሙን ሰብስቦ ሲጮኽ ሁሉም ስለሚሰማው ነው፡፡
አቧራ ችግሩ ዓይንን ጋርዶ ከእይታ፣ ጉሮሮን አፍኖ ከመናገር፣ ጆሮን ደፍኖ ከመስማት – ከማዳመጥ ይከለክላል፡፡ አካባቢውንም የሕይወት ሳይሆን የሞት ቀጣና ያስመስለዋል፡፡ ምንም እንኳን ላስነሣው ሰውዬ ‹ጨሰ አቧራው ጨሰ› ተብሎ ቢዘፈንለትም፤ አቧራው እየባሰ ሲሄድ ግን ዘፋኞቹ ወደ አልቃሽነት መቀየራቸው አይቀሬ ነው፡፡
አሻራ የአቧራ ያህል ቶሎ አይታይም፤ ቶሎም ወደ ላይ አይነሣም፤ በቶሎም ስም አያስጠራም፡፡ በቀላሉም አሻራ ጥሎ መሄድ አይቻልም፡፡ ብዙም ድምፅ የለውም፣ ብዙም ታይታ አይገኝበትም፡፡ አድካሚ ነው፣ አሰልቺም ነው፡፡ ሐሜትና ትችት፣ ነቀፋና ውረፋ ያስከትላል፡፡ ያልተረዱ እስኪረዱ፣ የተረዱ እስኪሠሩ፣ የሚሠሩ እስኪፈጽሙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ትዕግሥትን ይፈታተናል፡፡ በዓለም ላይ የትውልድ አሻራን ያኖሩ ሁሉ ይህ ገጥሟቸዋል፡፡
በዛሬዋ ምሽት በፊታችን የተዘረጋው ጥያቄ ይሄው ነው፡፡ አሻራ ወይስ አቧራ? የሚል፡፡ የአክሱም ሐውልቶች የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል ቤተ መንግሥት፣ የጀጎል ግንብ፣ የጂማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት አሻራ እንጂ አቧራ አይደሉም፡፡ የዐድዋና የካራማራ ድሎች አሻራ እንጂ አቧራ አይደሉም፡፡ የነ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ የነ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የነ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ የነ ጥላሁን ገሠሠ፣ የነ ዓሊ ቢራ፣ የነ አበበ ቢቂላ፣ የነ ምሩጽ ይፍጠር፣ የነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ የነ ደራርቱ ቱሉ ሥራዎችና ድሎች ሁሉ አሻራ እንጂ አቧራ አልነበሩም፤አይደሉምም፡፡ ሁሉም አሻራቸውን ያስቀመጡት በየመስካቸው ነው፡፡ ብንጠይቃቸው ግን አንድ ተመሳሳይ ነገር ይነግሩናል፡፡ አሻራን ማስቀመጥ ሲጀመር ፈታኝ – ሲፈጸም  አስመስጋኝ የመሆኑን ዘላለማዊ እውነት፡፡
በዚህ ዘመንም አቧራ አስነሥተው ስም ለማስጠራት፣ ታሪክ ለመሥራት የሚደክሙ ሰዎች አሉ፡፡ ለጊዜው ያደናግራል፡፡ አቧራ ማስነሣት የጉብዝና ምልክትም ይመስላል፡፡ ‹ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች› እንደተባለውም ለጊዜው ስምን ያስጠራ ይመስላል፡፡ የአቧራና የአቧራ አስነሽዎች ታሪክና ሥራ ግን እንኳን ዘመን ወቅትን አይሻገርም፡፡ ‹ያማ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ› እንደሚባለው ፋሽን ሆኖ መጥቶ እንደ ፋሽን ያልፋል፡፡ የሀገራችን ታሪክም ይሄን ይነግረናል፡፡ መከራና ችግርን ተቋቁመው እዚህ የደረሱልን የሀገራችን መኩሪያ ቅርሶች አሻራዎች እንጂ አቧራዎች አይደሉም፡፡ በየዘመኑ የተነሡት አቧራዎች ለጊዜው ታይተው፣ አስደንቀው፣ አደባልቀው፣ አነዋውጠው ሄደዋል፤ አልፈዋል፡፡
መልካም ሥራን የመከወኛ ጥሩው ጊዜ መቼ ነው? ተብለው ይጠየቃሉ – ጠቢቡ ሰው….፤ አላመነቱም ሲመልሱ፡፡ በልበ ሙሉነት ‹መልካም ሥራ የመከወኛ ጊዜዋ ትናንት ነው ሲሉ መለሱ፡፡ ዛሬማ ይዘገያል፡፡ ነገ – ይብሱኑ ይረፍድብናል፡፡ ጊዜ የለንም ብለን በቁጭት ጥድፊያ ውስጥ መግባት የሚኖርብን በዚህ የተነሣ ነው፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ የተከማቸ ታላቅ ሀብት ምሥጢሩ ታላቅ ሐሳብ እንጂ ተፈጥሯዊ ችሮታ አይደለም፡፡ ታላቅ ሐሳብ የደማቅ አሻራ መነሻ መሠረት ነው፡፡ ደማቅ አሻራ አብዝቶ በመስጠት እንጂ በመቀበል የሚገኝ ፍሬ አይደለም፡፡ የጋራ ቤትን ተባብሮ ለመሥራት  በቆረጥን ጊዜ ሁሉ፣ በአብሮነትም በጋራ ለመቆም በተነሣን ጊዜ ድል ከፊታችን ትቀርባለች፡፡ እናሸንፋለን እንጂ ሽንፈት አጠገባችን አይቀርብም፡፡ በጎ ተግባርና ምግባር በመስጠታችን ልክ፣ ለማጣት በተዘጋጀን መጠን ዋጋው ከፍ ይላል፡፡ በትልቁ ማትረፍንና አሻራውን ማኖር የሚሻ ቢኖር አሁንም ዛሬም ሆነ ነገ ከመስጠት ጋር በጽናት ይቁም፡፡
መሰናከልን አይፍራ፡፡ ፈተናንም አይሽሻት፤ በአሻራው ዘለዓለማዊነት ይካሳልና፡፡ ያለመሞት ምሥጢር – እንደ ዋዛ ተረስቶ ያለመቅረት የሐውልትነት ትንግርት – ዛሬን ከወደፊት የማሰናኘት እውነት የሚገኘው ከመስጠት እንጂ ከመቀበል አይደለም፡፡
አሻራ የሚተው ሰዎች የዚያን ዘመን ባለ ሥልጣናት፣ የዚያን ዘመን ፖለቲካ፣ የዚያን ዘመን ድጋፍና ተቃውሞ ከቁብ አይቆጥሩትም፡፡ አሻራ የሚተው ሰው አሻራውን የሚያስቀምጠው ለመንግሥት ሲል አይደለም፤ ለባለ ሥልጣናት ሲልም አይደለም፤ ለፓርቲዎች ሲልም አይደለም፤ ለድርጅቶችም ሲባል አይደለም፤ ለሀገሩ ሲል ብቻ ነው፡፡ አሻራ የሚቀመጠው ለሀገር ነው፡፡
‹ሀገራችን ቆላ እርሻው በደጃችን፤
ያ ቢሾም ያ ቢሻር እኛ ምን ተዳችን›
እንዳለው ገበሬ አሻራ ከሚሾሙና ከሚሻሩ ባለ ሥልጣናት ጋር አይገናኝም፡፡ ከማትሾምና ከማትሻር የጋራ ቤታችን ከሆነች፣ ሁላችንንም እንደ አመላችን ከምታቅፈን ውድ ሀገራችን ጋር እንጂ፡፡ ያ ሲሾም ያ ሲሻር የሚጨንቀው አቧራ የሚያስነሣ ሰው ነው፤ እኛ ከእነርሱ ወገን አይደለንም፡፡
በዛሬው ምሽት የተገናኘንበትን መስጠት የላቀ መስጠት የሚያደርገው የዓላማው ቅድስና ነው፡፡ በተቀደሰ ተግባርና በተቀደሰ ዓላማ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆን ሁሉ ነገ አንገቱን ያቀናል እንጂ አይሰብርም፡፡ በተከለው አንድ ፍሬ ምትክ ሺሕ ፍሬዎችን ለመልቀም የሚታደል ቅን ገበሬ መደሰት ያንሰው እንደሁ እንጂ አይበዛበትም፡፡ እናንተ የመስጠት ገበሬዎች ናችሁ፡፡ ሁሌም ስጡ፡፡ የምትሰጡት ከኪስና ከእጃችሁ እንዳይጠፋ ሰግታቸሁ ካልሆነ በቀር መስጠትን አትሽሹት፡፡
ቀደምት ወላጆቻችን ከመስጠት ጋር ተያይዞ አንዲት ሸጋ ምርቃት አላቸው፡፡ ‹የሰጠም አብዝቶ ይስጠው፣ ያልሰጠም እንዲሰጥ ይስጠው› ይላሉ፡፡ መልካም ብለዋል፡፡ የምንሰጠው ብቻም ሳንሆን የምንቀበለውም ጭምር መዳረሻ ግባችን መስጠት፣ ደግሞ ደጋግሞ መስጠት እና አሻራ ማኖር ነው፡፡ ለሰጣችሁ አብዝቶ ይስጣችሁ – ላልሰጠንም እንሰጥ ዘንድ አብዝቶ ይስጠን፡፡
ዛሬ እዚህ ቦታ የተሰበሰብነው ራት ለመብላት አይደለም፡፡ አሻራ ለማኖር ነው፡፡ የከፈላችሁት ገንዘብ ለእራት የሚከፈል አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ዕድገትና ሥልጣኔ ላይ አሻራችሁን ለማኖር ነው፡፡ አስቡት ከዛሬ ሠላሳና ዐርባ ዓመት በኋላ፤ ሁላችንም አርጅተን በዚህ የአዲስ አበባ ተፋሰስ ግራና ቀኝ፣ ከዘራችንን ይዘን ወዲያና ወዲህ ስንል የሚሰማንን ስሜት፤ የዛሬውን ቀን ስታስቡት የሚሰማችሁን ደስታ – አስቡት እስኪ፡፡ እውነት ለመናገር ያ ደስታ በ5 ሚሊዮን ብር የሚገኝ እንዳልሆነ ለእናንተ ማስረዳት – ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ልጆቻችን በዚህ የትውልድ ፕሮጀክት ላይ ስማችንን ሲያዩት፣ የዛሬው ፎቶ ግራፋችንን ሲመለከቱት፣ የዚያ ዘመን ትውልድ በወንዞቹ ዳርቻ እየተዝናና፣ በዛፎቹ ሥር እያወጋ፣ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ እያነበበ፣ ይህንን አሻራ የተዉለትን አባቶቹንና እናቶቹን ሲያመሰግን ምን ሊሰማን እንደሚችል እስቲ ለአፍታ አስቡት፡፡
ዛሬ እዚህ የተገናኘነው ለአባቶቻችን ክብር እና ለልጆቻችን ፍቅር ስንል ሁላችንም ለምንወዳት ቤታችን፤ የኢትዮጵያውያን የወል ካስማ – የታላቂቱ አፍሪካ ዋና ከተማ እና የብዙ ታሪካችን ማማ ለሆነችው ለአዲስ አበባ አደይ አበባዋን እንመልስላት ዘንድ ነው፡፡ ከተማችን ከመስከረም ወፍ እና ከቢራቢሮዎች ውብ ትእይንት ከተፋታች ቆይታለች፡፡ ከተማችን ከተክሎች የተፈጥሮ መዓዛ – በስሱ ከሚነፍስ ቀዝቃዛ ንፋስ እና ዝቅ ብለው ከሚበሩ መንፈስ ጠጋኝ ድንቅ ወፎች ከተኳረፈች ከራርማለች፡፡ ይሄንን ማጣታችን እኛንም ሆነ ልጆቻችንን ያሳጣን ብዙ ነገር አለ፡፡
የደጋጎቹ አባቶቻችን ለልጆቻችን ጨካኝ እንሆን ዘንድ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን – እምነታችን – ባሕላችን እና የትናንት ታሪካችን አይፈቅድልንም፤ በፍጹም፡፡ እናም እኛ የእኛን አደይ አይተናል- የእኛን የመስከረም ወፍ ቆጥረናል፣ አባቶቻችን ቆሻሻ ያላሸነፈው ቀበና፣ ውኃ ያልነጠፈው ግንፍሌ፣ መኖሩ ያላሠጋው ጎርደሜ፣ የፋብሪካ ፍሳሽ ያልገደለው አቃቂን አስረክበውናል፤ እኛስ ለልጆቻችን ምን እንስጣቸው!? ዛሬ እዚህ ያገናኘን ይህ ጥያቄ ነው፡፡
የዛሬ ድካማችን፣ ትችቱና ነቀፌታው፣ የልክ አይደለም ማስረገጫ እልፍ ሰበቡ፣ የአይሆንም – ይሆናል ውዝግቡ…ሁሉ ያኔ ይረሳል፡፡ ግራ ቀኝ ሆነው የሚሟገቱት ሁሉ ያኔ አይኖሩም፤ እንዳይሠራ ዕንቅፋት፣ እንዳይሳካ የጎን ውጋት የሆኑት ሁሉ በሂደት ያልፋሉ፡፡ የሚያስታውሳቸውም አይኖርም፡፡ ሥራ ግን አሻራ ነው፡፡ አሻራ ደግሞ ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡ የዛሬዋን ቀን ማሰብ ያለብን ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ሆነን ነው፡፡ ዛሬን ለነገ እየተከልን ነው፡፡
አባቶቻችን ልበ ሩኅሩኅ ደጎች – ወኔ ሙሉ ጀግኖች – ሆደ ሰፊ ቅኖች ስለነበሩ ዛሬ እኛ የምንመካባትን – ግን የመመካታችንን እና የነጻነታችን ቀንዲል እያልን የማዜማችንን ያህል ያልተንከባከብናትን ውብ ሀገር አወረሱን፡፡ ደጋግሜ እንደምለውም ይህች ሀገር ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትሆን ከልጆቻችንም የተዋስናት ናትና እኛስ ላዋሱን ልጆቻችን ይህችን ሀገር ስናስረክብ እጃችን ከምን? ከልጆቻችን የሚጠብቀን – ኅሊናችንም የሚጠይቀን ጥለነው ስለምናልፈው ታሪክም ስናስብ የሚያስጨንቀን እና የሚያሳቅቀን ቁልፍ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ በመዋስ እና በመውረስ መካከል ያለው ክፍተት የሚሞላው እና የትውልድ ሠንሰለት ጤናማ ሆኖ የሚቀጥለው በመስጠት ነው፤ በመስጠትም ብቻ ሳይሆን በመሰጠት – በተራዛሚውም አሻራ ለማኖር በመጀገን ጭምር ነው፡፡
በራሱ ላብ ራሱን ሊከፍል የሚተጋ ሕዝብ ቢዘገይም እንኳ ከራሱ አልፎ ለሌሎች መትረፉ አይቀሬ ነው፡፡ ከመቀበል ይልቅ መስጠትን መርጠን እንድንቆም የሚያስወድደን የመደመር ዕሴት መነሻ አንዱ መሠረትም ይኸው ሐቅ ነው፡፡  በጋራ፣ በመተባበርና በአብሮነትም እንጂ በነጠላ የግል ጉዞ አካባቢን መጠበቅ አይቻልም፡፡ በመጥፋት ላይ ያለውን የአካባቢ ሕይወትና ውበት፣ ውድመት እና ጥፋት ከመደመር ፍልስፍናና እሳቤ ውጭ መልሶ እንዲያገመግም ማስቻል አይቻልም፤ እናለዝበው ብንል እንኳን እጅጉን ከባድ ነው፡፡  በተፈጥሮ ሚዛን ጥበቃ ውስጥ እኔ እንድኖር ሌሎችም መኖር ይኖርባቸዋል ብሎ መነሣት ቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡ መጨፈን ምንአልባት ሥራና ወጪን እንጂ ጥፋትን አያስቀርም፡፡ በሸገር ፕሮጀክት ከተማችንን እንደስሟ የማስዋብ፣ የማሣመርና ከፍ የማድረግ እርምጃ መነሻ የመደመር ታላቅ ሐሳብና የአርቆ አስተዋይነት ውጤት ነው፡፡
ልጆቻችን ገሚሶቹ በአካል ሌሎቹም በሥነ ልቦናና በምናብ ስደተኛ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያዊውን ቀለም፣ ማንነትና ሰብእና እየተዉ፤ የቆጡን ለማውረድ የብብታቸውን እየጣሉ ያሉ ልጆቻችንን ወደሚወዷት ቤታቸው የመመለስና የሚወዷትን ከተማ የመገንባት ኃላፊነት የእኛ የሁላችንም ነው፡፡ እኛ ዛሬ ልጆቻችን የዚህች ሀገር ትምህርት ባይጥማቸው አሜሪካና አወሮፓ – ዕረፍት ቢያምራቸው ዱባይና ጣልያን – ሕክምና ቢያስፈልጋቸው ባንኮክና ጀርመን ልከን ያሻንን እናደርግ ይሆናል፡፡ ስለ ሁለት ነገር ቆም ብለን እንድናስብ እፈልጋለሁ፤ አንድም ይህንን ማድረግ ስለማይችሉ – ግን ይህችን ሀገር በሥጋቸው ብቻ ሳይሆን በነፍሳቸውም ጭምር ስላዘሉ ብዙ ወገኖቻችን፤ ሁለትም ይህች ሀገር እየፈለገቻቸው – እየፈለጓት የታሪካቸው ብዙ ገጽ በባዕዳን ቀለም በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በሩቅ ምሥራቅ እየተጻፈባቸው ስላሉ ልጆቻችን፡፡
ኒውዮርክ የዓለማችን መዲና ከተማ ብቻ ሳትሆን የማታንቀላፋዋ ከተማ በመባልም ትታወቃለች፡፡ አዲስ አበባም የአፍሪካ መዲና ብቻ ከመባል አልፋ የአፍሪካ ውብና ጽዱዋ ከተማ የምትባልበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አልማለሁም፡፡ እነሆ ከባዱን የመጀመሪያ ርምጃ አንድ ብለን ጀምረናል፡፡ በንጽሕና ባሕሉ እና በተግባራዊ መልኩ እንጂ ከተማ በስሙ አይወደድም፡፡ በግብሩ እንጂ በባዶ ቃሉ አይመሰገንም፡፡
ሀገራት ሀገራትን በተምሳሌነት እንደሚያዩ ሁሉ ከተማዎችም በተምሳሌነት ከተማን እንደሚያዩ እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ በሀገራችን ላሉ ሁሉም ከተማዎች በአረንጓዴ አጸድና በንጹሕ ምንጭ መፍለቂያነቷ ለአፍሪካ ከተማዎች ሁሉ ተምሳሌት እንደምትሆን አሁንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በጽዳት ባሕሏም ላይ ከተማችን ሥር ነቀል ለውጥ ለማስመዝገብ በነዋሪዎቿ ፊት ቃል ኪዷኗን ታሥራለች፡፡ መጭው ትውልድ፣ የመስቀል አዕዋፍ ውርውር ሲሉ፣ የአደይ አበቦችም ሲፈኩ ያያል፡፡ ልጆቻችን፣ በኅብረ ቀለማት ሸማ ያጌጡ ቢራቢሮዎችን በየበራቸው ማየት ብርቃቸው አይሆንም፡፡ በአጸዶችና በጫካዎቻችን ውስጥ አጋምና ቀጋ፣ ኮሽም እና ዶቃ ያብባሉ፡፡ በኩሬና በምንጮቻችን ውስጥ የውኃ እናት ከዓሣ ዘር ጋር በነጻነት እንደሚዋኙ ተስፋ አደርጋለሁ፣ አምናለሁም፡፡
ለዚህች ታላቅ ሀገር ለዚህችም ታላቅ ከተማ፣ ለዚህም ታላቅ ሕዝብ ገጽታውን፣ ታሪኩንና ደረጃውን የሚለውጥ አሻራ ለማኖር እንኳን በዚህ ታሪካዊ ሥፍራ ተገናኘን፡፡ አቧራው ይጭስ ተዉት፤ ስለ እርሱ ብዙ አታስቡ፡፡ እኛ አሻራችንን በክብር እናኖራለን፡፡ በክብርም በዚህች ሀገር ታሪክ እንታወሳለን፡፡
ሁላችሁንም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፡፡ የቀኝ እጃችሁን አውራ ጣት አውጥታችሁ፣ ጠረጴዛው ላይ አብራችሁኝ አሻራችሁን እንድታሳርፉ – የምለውንም አብራችሁኝ እንድትሉ፡፡ በአክብሮት ጠይቃለሁ!
አቧራውን አልፈዋለሁ፤
አሻራዬን አኖራለሁ
ታሪኬንም እሠራለሁ፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
Filed in: Amharic