>
3:38 am - Monday July 4, 2022

"ፍላጎቴ ኢህአዴግ እንዲነቀል ሳይሆን በምርጫ እንድናሸንፈው ነበር!!!"  (አቶ አንዱአለም አራጌ )

“ፍላጎቴ ኢህአዴግ እንዲነቀል ሳይሆን በምርጫ እንድናሸንፈው ነበር!!!”

 አቶ አንዱአለም አራጌ 


የኢትዮጵያ ዜጐች ማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ምክትል መሪ

ለሰው ልጅ ሰብአዊ መብት መከበርና ልዕልና በርካት ዋጋ ከፍሏል በምርጫ 97 በነበረው ትግል ከፖለቲከኞች አንዱ ሆኖ ከሲቪክ ማህበራት አመራሮችና ከጋዜጠኞች ጋር ሁለት ዓመታትን በእስር አሳልፏል፡፡

በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፖርቲ / አንድነት/ ውስጥ በነበረው ብርቱ ትግልና ተቃውሞ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት 6 ዓመት ተኩል አካባቢ በእስር ማቅቋል፡፡ በድምሩ 8 ዓመት ተኩል ያህል ወህኒ ተወርውሮ ሁለት አይነት መልክም አውጥቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር የዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞች ሲለቀቁ እሱም አብሮ ወጥቶ ከሚናፍቁት ልጆቹ ተቀላቅሏል፡፡ የዛሬው እንግዳችን የፖለቲካ ሰውና የነፃነት ታጋይ አንዱአለም አራጌ፡፡

አንዱአለም በአንድ ዓመት ውስጥ የታዩትን ለውጦች በመመልከት እኔ የነፃነት ታጋይ ነኝ አገሪቱ ላይ ነፃነት ሰፍኗል ከዚህ በኃላ በፖለቲካው ውስጥ አስፈላጊ አይደለሁም የሚል እምነት የነበረው ሲሆን አሁን ላይ አገሪቱ ላይ ያለው ነፃነት ገና መሬት ያልረገጠ ሆኖ በመገኘቱ እንደ ገና ወደ ፖለቲካው ተመልሶ ባለፈው ሳምንት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዜጐች ማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ምክትል መሪ በመሆን ተመርጧል፡፡ ሸገር ታይምስ ባልደረባ መክሊት ኃብታሙ በአዲሱ ፖርቲና በአመሰራረቱ  እንዲሁም በፖርቲው ራዕይና ግብ ፤ ከመመስረቱ በፊት ስለ ተከናውኑ ተግባራት ፤ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ፤ በ2012 ዓ.ም ይካሄዳል ስለሚባለው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይና በተያያዥ ጉዳዩች ዙሪያ ከአንዱአለም አራጌ ጋር ተከታታዩን ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡

ምንም እንኳን የተመረጥከውና ሀላፊነት የወሰድከው ለሥራ ለትግል ቢሆንም ከዚያ ሁሉ መከራ ወጥተህ ለዚህ ስለበቃህ እንኳን ደስ አለህ፡፡

እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

በአዲሱ ፖርቲያችሁ ዙሪያ ሰሞኑን ብዙ እየተባለ ነው በተለይ የኢትዮጵያ ዜጐች ማህበራዊ ፍትህ  / ኢዜማ/ አመሰራረት ወረዳን ማዕከል ያደረገ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

ወረዳን ማዕከል ያደረገነው ማለት ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ነው ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ስልጣን ከማዕከል እየተነሳ ወደ ሕዝቡ የሚወርዱ የተወሰኑ ታዋቂ ሰዎችና የተወሰኑ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ አመራሮች ከላይ ወደታች እየወረዱ ነበር የሚያደራጁት አሁን ግን ከታች ሕዝቡ የሚፈልጋቸውን እየመረጠ ከወረዳ ነው የሚልከው እንግዲህ ወረዳ ስንል የአስተዳደር ወረዳ ሳይሆን የምርጫ ወረዳን ማለታችን ነው፡፡ ከወረዳው ለጠቅላላ ጉባኤ የሚሆኑ አባላት የሚሆኑትንም ወኪሎች የሚመረጡት በምርጫ ወረዳ ያሉ የፖርቲያችን አባላት ናቸው፡፡ 15 አባላት ያሉትንም የሚመርጠው የወረዳው ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ከታች ወደ ላይ የሚያድግ ከሕዝቡ ፍላጐት የመነጨ አባላትና አመራር የሚመርጥበት ስለሆነ ነው የእኛን ፖርቲ ልዩ የሚያደርገው፡፡

ከተለመደውና ቀድሞ ከሚሰራበት አሰራር የተለየ በመሆኑ የተቀባይነቱ ነገርስ እንዴት ነው?

ሰሞኑን በየሚዲያው እንደሰማችሁት ዙ ተቀባይነትን ያገኘ ይመስለኛል፡፡ ከሕዝብ ፍላጐት ተነስቶ ሊሰራ የተደራጀን ፖርቲ የማይቀበል እንግዲህ በቀደመው አሰራር ተጠቃሚ የሆነና በዚያው እንቀጥላለሁ የሚል ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ያነገባችሁት ርዕዮተ ዓለም የዜጐች እኩል ተሳትፎና ማህበራዊ ፍትህ ነው ይህን ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል በቁርጠኝነት በኩል እንዴት ናችሁ?

የእኛን ድርጅት ለየት የሚያደርገው ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ማህበራዊ ፍትህና ወረዳ አስተዳደር ላይ ተስርቶ መቋቋሙ ነው፡፡ ሌሎቹ ቀደም ብለሽ የምታውቅያቸው ፖርቲዎች የሚያራምዷቸው እምነቶች አሁንም የእኛ እምነቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያም ሕዝብ እምነቶች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አለን፡፡ ለአላማችን ቁርጠኞች ነን፡፡ ሰው ሊደግፈንም ላይደግፈንም ይችላል፡፡ ሰው ደገፈንም አልደገፈንም የምንለውን ነገር መርጠም አልመረጠም ሕዝቡ በመብቱ ላይ የሚወስንበትን መንገድ ማመቻቸትና ሰዎች ልዕልና እንዲኖራቸው እንዲሁም ሰዎች እውነትም ሉአላዊ ፍጡሮች መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትን  አንዱ ከላይ ተጭኖ እንደ እንስሳ የሚነዳቸውና የሚጓዝባቸው ዘመን ማብቃት አለበት የሚል ቁርጠኝነት ነው ያለን ዋናው ትልቁ ነገር ሰውንም ሰው የሚያሰኘው ልዕልናው ነውና፡፡ ከፈጣሪም የተቸረው ነገር የሰብአዊ ልዕልና ባለቤት መሆኑ ነው፡፡ የራሱን ፈቃድ በራስ መፈፀም መቻሉ ነው፡፡ ሲፈጠርም የራሱን ፈቃድ እንጂ የሰዎችን ፈቃድ ለመፈፀም አልተፈጠረም፡፡ እስካሁን የቆየው ግን የራሱን ሳይሆን የሌሎችን ፈቃድ ሲፈፅምና ሲያስፈፅም ነው፡፡ አሁን የእኛ ዋናው አላማና ግባችን ሰዎች ልዕልናቸው ተከብሮ የራሳቸውን ፈቃድ በራሳቸው የሚፈፅሙበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን ነው ለዚህ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ወይ አዎ ያስፈልጋል እኛ ደግሞ ቁርጠኝነቱ አለን፡፡

ፓርቲያችሁ ኢዜማ የተመሰረተው በ6 የቀድሞ ፓርቲዎችና በአንድ ስብስብ / ንቅናቄ/ ጥምረት ነው አደረጃጀቱና የአመራር ምርጫ ከወረዳ ይጀምራል ሲባል ሕዝቡ ሲጠብቅ የነበረው አመራሮች አዳዲሶችና ከዚህ ቀደም እንደ እናንተ በፖለቲካው ጉልህ ሚና ያልነበራቸው ይሆናሉ ብሎ ነበር፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው ይህን እንዴት ታየዋለህ?

እኛ ሚዲያዎች ባሉበት በኃላም ያካሄድነው ምርጫ ቪዲዬ ለሌሎች ሼር ተደርጐ በታየበት ሁኔታ ነው የተመረጥነው ስለዚህ ምርጫው በአባላት ፍፁም ነፃ ፈቃድ ነው የተካሄደው እሱን ለማረጋገጥ የዴሞክራሲውን ናሙና በእኛ ፖርቲ ምስረታና ምርጫ ላይ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ በጣም ግልፅና የአባላት ነፃነት የሰፈነበት ምርጫ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ተሳክቶልናል፡፡ ነገር ግን ሰፊ ክርክር ተደርጐ ብዙ ሂደት ለማለፍ ግዜው አጭር ነበር ሆኖም ከየአካባቢው የተወከሉ አባላት በነፃ ፈቃድ ያደረጉት ምርጫ ነው፡፡

ሌላው መከራከሪያና መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ጉዳይ በፖርቲያችሁ አመራር ምርጫ ላይ ዋና መሪ፣ ምክትል መሪ ይልና የፖርቲው ሊቀንበር ምክትል ሊቀመንበር ከዚያ ዋና ፀሐፊ እያለ የሚሄደው የአመራሮች ምርጫ ነው እስኪ የኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ / ዋና መሪ/ እና የአቶ የሺዋስ አሰፋ / የፖርቲው ሊቀመንበር/ ፣ የአንተ የምክትል መሪውና የጫኔ ከበደ / ምክትል ሊቀመንበር/ ሥራና ሃላፊነት ልዩነት ምን እንደሆነ አስረዳኝ?

በጣም ትክክል ነሽ ይሄ አዲስና ያልተለመደ የሀላፊነት ምርጫ ሰውን ግራ ሲያጋባና ሲያነጋግር ሰንብቷል እዚህ ላይ ማንሳትሽም ወሳኝና ተገቢ ነው፡፡ በእኛ አገር ብዙ ግዜ ሶሻሊስታዊ አመራር እንከተል ስለነበር የተለመደው አደረጃጀቶቻችን ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበርና ዋና ፀሐፊ እያለ የሚሄድ ነበር፡፡ አሁን የመጣው ያልተለመደው ምንድን ነው ካልሽኝ የፖርቲው ዋና ምክትል መሪ በአንድ ወገን የፖርቲው ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ደግሞ በአንድ ወገን ይሆናል ይሰራሉ ይሄ ማለት ድርጅቱ ሁለት ክንፍ አለው ማለት ነው፡፡ አንዱ ክንፍ የፖርቲው ሊቀመንበር ምክትል ሊቀመንበርና ዋና ፀሐፊው የሚመሩት ሲሆን የፖርቲውን መዋቅራዊ ይዘት እስከታች ድረስ የሚደርስ ሆኖ አባላትን ማደራጀት የፋይናንስና በስልጠና ማብቃት እንዲሁም ፖርቲው ለምርጫ ሲወዳደር ሕዝቡ ውስጥ እየገባ እያደራጀ እያነቃና እያስተባበረ የሚሰራ ሰፊ ትከሻ ያለው ፍፁም የፖርቲውን ስራ ብቻ የሚሰራ አካል ነው፡፡ በፖርቲው መሪና ምክትል መሪ የሚመራው የፖለቲካው ክንፍ ዘርፍ ሲሆን የፖርላማ አባላት የሚመለከት፣ የፖለቲካ ጉዳዩችንና ፖሊሲዎችን የሚመለከት ጉዳዩችንና ፖሊሲዎችን የሚመለከተ ጉዳዩችን የሚያደራጅ ፣ ስትራቴጂዎችን የሚነድፍና የሚያደራጅና ፖርቲው ካሸነፈ አገር የሚመራው ክንፍ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ክንፎች በጣም የተለያየ ሥራ ነው የሚሰሩት፡፡ በሊቀመንበሩ በምክትል ሊቀንበሩና በዋና ፀሐፊው የሚመራው ክንፍ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ድጋፍ በመስጠት የፖለቲካው ክንፍ እንዲያሸንፍ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ማለት ነው፡፡ ይሄ በሌላው ዓለም የተለመደ ነው፡፡ እኛ ግን በዚህ አሰራር የመጀመሪያዎቹ ስንሆን አንቀርም፡፡

በአንዳንድ ግለሰቦችና በህዝቡም አካባቢ እንደሰማሁት ፓርቲያችሁ የተከተለው የስልጣን ተዋረድ ከየፓርቲዎቹ የመጡት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት እንዳያኮርፉ ሲባል የፈጠረ ነው ይላሉ አንዷለም ይሄንን እንዴት ታየዋለህ?

እንግዲህ እንዲህ ያሉ ካሉ ቢሉም አልፈረድባቸውም ምክንያቱም እዚህ አገር በስልጣን ምክንያት ብዙ ችግር ተከስቶ አልፏል፡፡ ስለዚህ ኩርፊያ እንዳይመጣ ከመሰላቸው ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ትንሽ ለሚያይ ሰውና ለሚያነብ ሰው እንደዛ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የአሜካ ፖርቲዎችን ማየት ብንችል ዴሞክራቲክ ፖርቲው አደረጃጀቱ እንደዛ ነው፡፡ ለምሣሌ ኘሬዝደንት ኦባማ በሚመረጡበት ግዜ እሳቸው የፖለቲካ ክንፉን ሲመሩ ዶክተር ዲን የሚባሉ ሰው ደግሞ የፖርቲው ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ መቼም ይህንን የእነሱን የስልጣን ጥም ለማርካት ተብሎ የተፈጠረ አወቃቀር ነው ሊሉን አይችሉም፡፡ እኛም ከጅምሩና ከመሰረቱ ጀምሮ ኢህአዴግን ስንወቅስበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ የፓርቲና የመንግስት አሰራር እየተቀላቀለ ፓርቲውን በሕዝብ ንብረት፣ በሕዝብ መኪና፣ በሕዝብ ገንዘብና ግዜ ሲቀልዱ እንደኖሩ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ፓርቲና መንግስት መለየት አለበት እየተባለ ሲጮህ ነው የተኖረው፡፡ አሁን እኛ ከወዲሁ ይህንን ለይተናል ካሸነፍንም አገር የምንመራው ፓርቲና መንግስትን ለይተን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሊቀመንበሩ የሚመራው ክንፋችን የፓርቲውን ስራ ሙሉ ለሙሉ በጥንካሬ በመስራት ፓርቲውን ለመንግስትነት ያበቃል እንጂ ራሱ መንግስት አይሆንም፡፡ በዚህ  ክንፍ ያለው ይህ አመራር የስራ ዘመኑ እስከሚያልቅ የፖርቲውን ሥራ ይሰራል እንዲሁም በምርጫ አይሳተፍም የስራ ዘመኑን ሲጨርስና ለሌላ ሲያስረክቡ ወደ ፖለቲካው ክንፍ ሊመጡ ይችላሉ፡፡

በምን ያህል ወረዳዎች ደረሳችሁ አጠቃላይ እንቅስቃሴያችሁ ምን ይመስል ነበር?

እስካሁን 312 ወረዳዎች ላይ የምርጫ ምክር ቤት አቋቁመናል፡፡ ካሉት 547 ወረዳዎች ከግማሽ በላይ ያህል ላይ ነው የምርጫ ምክር ቤት ያቋቋምነው፡፡ ይሄ ማለት ሌላው አባል በብዛት ተሰብስቦ 15 አባላት ያሉት የምርጫ ምክር ቤት አቋቁመናል ነገር ግን ወደ 400 በሚጠጉ ወረዳዎች አባላት አሉን፡፡ በቀጣይ በቀሪዎቹም ላይ የምርጫ ምክር ቤቶች ማቋቋማችንን እንቀጥላለን፡፡

በመጪው አመት 2012 ዓ.ም አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል ነገር ግን ፓርቲያችሁ በምስረታው ማግስት ምርጫው መራዘም አለበት የሚል አቋም ይዟል በዚህ ላይ አንተ ምን ትላለህ?

በዚህ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሳሉ ምላሾችም ይሰጣሉ፡፡ እውነት ለመናገር እኛ ለማሸነፍ የሚመቸን ምርጫው አሁን ቢካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ከራሳችን በላይ ቀዳሚ ነገሮችን ማየት አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ይህንን አቋማችንን በተሳሳተ መንገድ ያዩታል፡፡ ምርጫ ማሸነፍ እንዳልፈለግን አድርገውም የሚወስዱት አሉ፡፡ ነገር ግን የተረጋጋ አገር ሲኖር ነው ምርጫ የሚኖረው፡፡ ካልተረጋጋና የጐበዝ አለቃ በበዛበት አገር ምርጫ እናካሂድ ሲባል ከዚህ ቀደም መንግስት ነበር ኮረጆ የሚዘርፈው አሁን ደግሞ የጐበዝ አለቆች ይዘርፋሉ አገሪቷን በሙሉ ሰራዊቱና የፀጥታ አካላት በደንብ አልተቆጣጠሩም ለምርጫ መሰረታዊ ምሰሶ የሚባሉት ተቋማት አልቆሙም ምርጫ ቦርድም ገና እየዳኸ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ዘሎ ምርጫ ላይ መግባት የተለመደው አይነት ምርጫ አይደለም የምናካሂደው፡፡ ታሪክ የመቀየር ኃላፊነት አለብን፡፡ እስካሁን ዘመናችንን በሙሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨለማ ውስጥ በጭቆና አገዛዝ ውስጥ ነው የኖረው አሁን ደግሞ ፀሀይ እንዲወጣና ሕዝብ ሉአላዊ ስልጣኑን እንዲወስን በቀንና በብርሃን እንዲመላለስ እንፈልጋለን፡፡ ይሄ ከተሳካልን ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ከየትኛውም ታሪክ ጋር አይወዳደርም እሱን እውን ለማድረግ የአንድ ሰሞን ምርጫ አድርጐ እሱን በሚዲያ ማስነገር ዋጋ የለውም፡፡ ስራዎቻችንን በደንብ መስራት አለብን እንጂ አሁን ኢህአዴግ ወከባ ወስጥ ባለበት ጊዜ እኛ ምርጫ ብናደርግ ምናልባትም የተሻለ ውጤት የምናገኝበት እድል ይኖረን ነበር፡፡

የእናንተ አቋም ይራዘም ነው ግን የመንግስት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላ ል ብለህ ትገምታለህ?

ያራዝሙታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ አሁን ያለንበት ወቅት ለማንም ግልፅ ነው፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታም ይታወቃል እንጂ እኛኮ ከ 300 በላይ ወረዳዎች ላይ የምርጫ ምክር ቤት አቋቁመናል የቀረውን በአጭር ግዜ ውስጥ መሸፈን እንችላለን የምናነሳውም ኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ያለውን ሀሳብ ነው፡፡ ይሄ ብዙ ማስረዳት የሚያስፈልገው አይደለም ስለፍቅር ስለአንድነትና ወንድማማችነት በጋራ ስለተጀመረ ተስፋችን የሚነገር ነገር ብዙ ስብከትን የሚጠይቅ አይደለም፡፡

አንተ የነፃነት ታጋይ ነህ፡፡ ቀደም ብለህ እንዳልከው ተሳክቶ ማየት የምትፈልገው የሰው ልጅ ልዕልና ነው ለዚህም በግልህ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለህ ሁለት መልክ አውጥተሃል ፖለቲካ አልደከመህም በዚህ ፓርቲ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት እመርጣለሁ ብለህስ ገምተህ ነበር?

እኔ እስሩ በጣም አዳክሞኛል፡፡ ድጋሚ የመሳተፍ ብዙም ፍላጐት አልነበረኝም በጣም ደክሞኝ ነው የወጣሁት ሁለተኛ እኔ ራሴን የነፃነት ታጋይ አድርጌ ነው የምቆጥረው እናም አሁን ነፃነት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ነፃነት ከመጣ እኔ ምን አደርጋለሁ፡፡ ነፃነት ከመጣ በኃላ እኔ ስልጣን ነው የምፈልገው ወይም ምን ቀረኝ እያልኩ እራሴ ጋር እሟገት ነበር፡፡ ለምን የምኖርለት አለማዬና ህልሜ ነፃነት ነው ስለዚህ እኔ ጥሪዬን አሳክቻለሁ የሚል ስሜት መጥቶብኝ ነበር፡፡

አሁን ነፃነት ሙሉ ለሙሉ ሰፍኗል ብለህ ነው የምታምነው?

አይደለም! እኛ በፊት ጥያቄ አንስተን ወደ እስር ቤት የምንወረወርባቸውን ጥያቄዎች አሁን ያለው አመራር ለመመለስ በጐ ፈቃድ እያሳየ ነው፡፡ ዋና የምንላቸውን ማለቴ ነው እነዚህ ከተሳኩ እኔ ምን እሰራለሁ እልነበር ነገር ግን ከብዙ ወገኖቼ ጋር ስንነጋገር ገና መሬት የረገጠ ነገር ሰለሌለ ትግሉን መቀጠል አለብን የሚለው ነገር አመዘነ እንጂ እኔ ሀሳቡ አልነበረኝም፡፡ እኔ ከዚህ በኃላ ከልጆቼ ጋር ግዜ ቢኖረኝ የሚል ፍላጐት ነበረኝ ነገር ግን በሕይወቴ የምደሰትበት የፖለቲካ ስራ መስራት ነው፡፡ መታሰር ለእኔ የስቃይ ብቻ ሳይሆን የእርካታም ምንጭ ነበር፡፡ ለአላማዬ ዋጋ ስከፍል ነው የምደሰተው፡፡ ስለዚህ አሁን ደግሞ የሻለ ግዜ መጥቷል፡፡ ብዙ የጠበቅኩት ባይሆንም ሀላፊነት ተቀብያለሁ፡፡

የብሔር ፌደራሊዝም ከፈረሰ አገሪቱ ትፈርሳለች የሚል አቋም ይዘው እየታገሉ ያሉ አካላት አሉ እናንተ የዜግነት ፖለቲካ ብቻ ነው ለዚህች አገር የሚበጀት ብላችሁ ተነስታችኋል ሌሎች ተቃዋሚዎች ደግሞ በአገሪቱ ላይ ጫናና ውጥረት ፈጥረዋል አንተ ተቃዋሚውን እንዴት ነው የምታየው?

እንግዲህ የብሔር ፌደራሊዝም የ27 ዓመት ታሪክ ነው ኢትዮጵያ ደግሞ የሺህ አመታ ታሪክ ያላት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በብሔር ባለመደራጀት የፈረሰች አገር አይደለችም፡፡ በብሔርም ስለተደራጀችም አልፈረሰችም በእርግጥ ብዙ ፈተናና ተግዳሮት ውስጥ ገብተናል ብዙ አይተነው የማናውቀው ነገር ተፈጥሯል እኔ በበኩሌ ወንድሞቼና እህቶቼ የመሰላቸውን ሀሳብ ለማራመድ መብት አላቸው አራምዱ አታራምዱ የሚላቸው እንዳለ ሆኖ  በእኔ እምነት ግን የብሔር ፖለቲካ ባለመኖሩ የፈረሰ አገር አላውቅም፡፡ ከእኛ በላይ በብሔር ብሔረሰቦች የበዙባቸው አገሮች በብሔር ፌደራሊዝም ሳይሆን ሌሎች ጉዳዩችን ግምት ውስጥ በከተተ ፌደራሊዝም እየተዳደሩ በጣም ጠንካራ ሆነው ፈርጣማ ኢኮኖሚ፤ ጠንካራ ሰላም ያላቸው አገሮችን ነው በዓለም ላይ የምናየው፡፡

በአንተ እምነት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ፖርቲዎችን የመሰረተው ኢህአዴግ አለ ብለህ ታምናለህ?  

እኔ አላምንም ነገር ግን ክርክሬ ምን ያህል እንደሚወስደኝ አላውቅም አንዳንዴ ግራ ይገባኛል እንደሚመስለኝ የቀድሞው ኢህአዴግ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግን ኢህአዴግ የሚያሰኘው ገዳይነቱ ፣ አፋኝነነቱናና ጨቋኝነቱ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያነሱትን ብሔራዊ እርቅን የሚዲያን ነፃነት የማይቀበል በአፈና የተለከፈ ነበር፡፡ የኢህአዴግ ዋና ሶፍትዌር ደግሞ አፈሩ ይቅለላቸውና አቶ መለስ ነበሩ፡፡

አጥብቀህ ትቃወማቸውና ትኮንናቸው ነበር አሁን አፈሩ ይቀላላቸው ማለትህ ይገርማል…

እሳቸው አፈሩ ስለከበዳቸው እኛ አንደሰትም በሰው ስቃይ እንኳን አሁን ፈጣሪ ፍርዱን ሰጥቶ ፈጣሪ ፍርድንም ሳይሰጥ በሰው ስቃይ አንደሰትም፡፡ በሰው ስቃይ የእኔ ስቃይ አይታገስም የእኔ ልጆች ማልቀስ ለእነሱ ልጆች ደስታ ሊሆን አይችልም፡፡ በማንም ስቃይ ማንም አይደሰትም ካለማስተዋል የሚመጣ ነገር ነው እና አሁንም አፈሩ ይቀለላቸውና እሳቸው ነበሩ ዋናው አድራጊ ፈጣሪ፡፡ እኔም አቶ መለስ  ላይ መረር ብዬ የምቃወመው ዋናው እሳቸው እንደሆኑ ስለማወቅ ነው አሁን ሶፍትዌሩ ተቀይሯል ኢህአዴግ የሚለው ሀርድዌሩ ግን አለ፡፡ አሁን ዶ/ር አብይ የሚያራምዱት ሶፍትዌር አለ፡፡ ዶ/ር አብይ ደግሞ አቶ መለስ ለመተግበር ቀርቶ ለማስብ የማይደፍሯቸውን ብዙ ነገሮች ደፍረዋል፡፡ ስለፍቅር ስለ ወንድማማችነት ከመግደል ይልቅ ሁሉ ምንም ነገር በፍቅር ለማሸነፍ ፍቅር የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ብሔራዊ እርቅም ብዙ የተከለለበት ነበር፡፡ ምርጫውን ዘርፋችሁታል ግን ምርጫ ቦርድ ይስተካከል በማለታችን እንደታሰርን ታቂያለሽ፡፡ እንዲህ አይነት ጥያቄ ከእኛ ጋር በማንሳቷ ከሁሉት ዓመት በላይ የታሰረችው ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆናለች፡፡ ይህ ቀላል የምንለው ለውጥ አይደለም ፡፡ ተቃዋሚዎች በፊት መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ሲባሉ ነበር፣አሁን መንገዱ ጨርቅ ሆኖላቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

በአቶ መለስ ጊዜ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ሲባሉ ከሀገራችሁ መፈርጠጥ ትችላላችሁ ማለት ነበር፡፡ ስለዚህ በዶ/ር አብይ የተወሰዱት እነዚህ እርምጃዎች በቀድሞው ኢሀአዲግ እውነተኛ ባህሪዎች የሚሞከሩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የኢህአዲግ ሶፍትዌሩ ተቀይሯል፡፡ ሀርድ ዌሩ አለ፡፡ ሶፍትዌሩን በደንብ ማስፋት እና ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ ወደታች ማውረድም ገና በደንብ ይቀረዋል፡፡ ምን ማለት ነው ኢህአዲግ ፀጉሩና ጥፍሩ አካባቢ ገና እየተንፈራገጠ ነው፡፡ በየወረዳው እና በየአካባቢው ገና ተግዳሮቶች አሉ፡፡ የካድሬዎቹ ከጫፍ እስከጫፍ ያለ መዋቅር ገና አሁንም አልሞተም፤አልዳነም ገና እየተንፈራገጠ ነው፡፡  እኔ በበኩሌ የኢህአዲግ ካድሬዎች ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደጠፉ እና እንዲጎዱ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን የህዝብን ፈቃድ ሙሉ ለሙሉ እንዲያከብሩ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ በኃላ የምንታገስበት ነገር የለም፡፡ሁላችንም ከሕግ ስር ሆነን የህዝብን ፈቃድ ማክበር እና ለዛ መገዛት አለብን፡፡

በርካቶች አሁን በየቦታው ያለውን ግጭት፣ግድያ እና መፈናቀል ከለውጡ ድክመት ጋር ያይዙታል፡፡ አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ? ይህ ሁሉ የሚከሰተው ስር ነቀል ለውጥ ባለመምጣቱ ነው ?

ሞት እና መፈናቀሉን ያመጣው ኢህአዴግ ነው ወይ? እኔ እጠራጠራለሁ፡፡አሁን ኢህአዴግ ከስሩ ባለመነቀሉ እንግልቱ መፈናቀሉ እና ግድያው በዶ/ር አብይ መሰሪነት ነው ብሎ የሚያምን ካለ እኔ በበኩሌ አይመስለኝም፡፡ ይሄ ነገር እየተከሰተ ያለው በተለያየ አካባቢ ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ታፍኖ እና ተጨቁኖ ነው የኖረው፡፡ ስለዚህ እንደሚመስለኝ የችግሩ መንስኤ ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ አንቺ አንድ አካባቢ ሄደሽ በቀናት ውስጥ የሆነ ነገር ተናግረሽ 40 እና 50 ሺህ ሰው ማሳለፍ የምትችይበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፣ ነፃነት አለ መሰለፍ ይቻላል መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ያንን ነፃነት ለበጐ ነገር ሰዎች እየተጠቀሙበት አይደለም፡፡ ይሄ ነፃነትን በግባቡ ማስተዳደር አለመቻል ነው፡፡ ኢህአዴግ ከስሩ ቢነቀል ምን ትርፍ እናገኝ ነበር እኔ አላውቅም፡፡ ድሮም ቢሆን እኔ ኢህአዴግ እንዲነቀል ሳይሆን በምርጫ እንድናሸንፈው ነበር ፍላጐቴ ማንኛውም ቡድን በሀሳብ እንዲሸነፍ ነው የምፈለገው፡፡ ይሄ ባህል እንደቀጥል እንጂ የተለየ ሀሳብ ያለው ይነቀል አይደለም፡፡ ስለዚህ ለውጡ ስርነቀል ስላልሆነ ይሄ ሁሉ መፈናቀልና ግጭት ደረሰ ማለት ይከብደል ስርነቀል ለውጥ ብዙ ግጭት ደም መፋሰስና ንብረት መውደም ያመጣል፡፡  ደርግም ተነቅሎ ኢህአዴግ ሲመጣ ወደ ተረጋጋ ነገር አላመጣንም ሥርነቀል ለውጥ በራሺያም በሌላውም አገር እንዳየነው በመፍትሄ የተሞላ ነው ማለት አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ አሁን ላይ ያለው ግጭትና መፈናቀል መንስኤው ነፃነትን በአግባቡ ያለመያዝና ያለመረዳት ችግር ይመስለኛል፡፡

ከለውጡ በኃላ አንዱ የውጥረት መነሻ የአዲስ አበባ ጉደይ ነው ብዙዎች ብዙ ብለዋል አቋማቸውን ገልፀዋል ኢዜማ በአዲስ አባ ጉዳይ ላይ አዲስ እንደመሆኑ አቋሙ ምን ይሆናል?

አሁን እኔና አንቺ ስንነጋገር ከተቋቋምን ገና ሁለተኛ ቀናችን ነው ገና ከድካሙም አልወጣንም፡፡ ስለዚህ ገና በአጀንዳዎች ላይ መወያየት አልጀመርንም ተወያይተን ብንነጋገር ይሻላል፡፡ ዞሮ ዞሮ እኛ እንደምናምነው ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ነች፡፡ አዲስ አበባም የኢትዮጵያ ክፍል ናት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ቦታ መኖር ይችላሉ የኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ቦታ ተከልሎ ለእከሌ ይሁን የሚባል ነገር የለም ለምሳሌ መቀሌም በይው ጐንደር ፣ ሐዋሳም ይሁን አዲስ አበባ የአንድ የተለየ ብሔረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያን ከተሞች ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ከዚህ የተለየ ሀሳብ ካለን ወደ ፊት እናየዋለን፡፡

አሁን ባለው የአገሪቷ ሁኔታ የዜግነት ፖለቲካ ለማራመድና ማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን በምታደርጉት እንቅስቃሴ ምን አይነት ተግዳሮት ይገጥመናል የሚል ስጋት አላችሁ?

አሁን ዝም ብዬ በግምት ይሄ ሊገጥመን ይችላል ይሄ ሊያስጋን ይችላል ልልሽ አልፈልግም፡፡ እስካሁን ስንሰራ የነበረው አንድን ጉዳይ በአንድ ጊዜ ለመስራትና ሌላውን ለማስከተል ነው ቁጭ ብለንም ለመወያየት ጊዜ አልነበረንም ድርጀቱን በደንብ መሰረት አስይዘን ችግሮችን እንዲሸከም አድርጐ ማቆሙ 8 ወራትን ፈጅቶብናል፡፡ አሁን ባነሳሻቸውም ባላነሳሻቸውም ጉዳዩች ላይ መግለጫ ሳንሰጥ ዝም ብለን ስንሰራ ነበር የቆየነው የሰራነውም ትልቅ ሥራ ነው፡፡ 312 ወረዳዎች ላይ ምክር ቤት ማቋቋም 400 ያህል አሰልጣኞችን ከየአካባቢው ማሰባሰብና ማሰልጠን እንደገና አነሱን በየወረዳው አሰማርቶ ስልጠና እንዲሰጡ ማድረግ፣ ከባድ ነው፡፡ ብዙ የሰው ሀይል ብዙ ገንዘብ ነው የወጣው፡፡ ከዛ ደግሞ በርካታ የፖርቲውን ፖሊሲዎች ስንሰራ ነው የቆየው፡፡ ስለዚህ ፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጂዎቻችንን አይተን በዛ ላይ ብዙ ማለት እንችላለን አሁን ግን ምንም ማለት አንችልም ገና ሁለት ቀናችን ነው ከተቋቀዋምን ዋና የቢሯችን ማዕከል የት የሁን የሚለውን እንኳን አልወሰንም፡፡

ጥሩ ወዳንተ ጉዳይ እንመለስ በእስር ላይ እያለህ “ያልተሄደበት መንገድ”፣ “የአገር ፍቅር እዳ” እና “በዘመናት መካከል” የሰኙ ሶስት ድንቅ መፅሀፍትን ለንባብ አብቅተሀል ወደ ፊትስ ምን ያሰብከው አለ የቀረህ ነገር ያለ ስለሚመስለኝ ነው?

እስር ቤት እያለሁ የጻፍኩት የእስር ቤት ማስታሻ መፅሀፍ በቅርቡ ለንባብ ይበቃል ብዬ አስባለሁ የእስር ቤት ግዜዬን ማለትም በቅንጅት ሁለት ዓመት አሁን ደግሞ 6 ዓመት ከ3 ወር ያህል በወህኒ ያሳለፍኩትን በዚያ ያሁትን በአጠቃላይ ባለፋት 12 ዓመታት ውስጥ 8 ዓመት ተኩል ያህሉን በእስር የቆየሁበትን አጠቃላይ ነገር ፅፌ ጨርሼ ነው የወጣሁት፡፡ አሁን እሱ እየተተየበ ነው ቃሊቲ ጨርሼው ስለወጣሁ የምጨምረው ነገር የለም፡፡ በዚህ ክረምት ለማሳተም አቅጄ ነበር ሁኔታዎችን አይቼ በቅርቡ ለህትመት ይበቃል፡፡ ሌላ ሁለት መፅሀፍት አሉኝ፡፡ አንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አድናቆት የተቸረው የማርቲን ሉተርኪንግ I have a dream የተሰኘው መፅሀፍ ሌሎችም ተካትትውበት ተርጉሜዋለሁ ሌሎች እኔ የፃፍኳቸው ሁለት መፅሀፍት አሉ ባጠቃላይ ከዚህ በኃላ ወደ 4 ያህል መፅሀፍት ተሰርቶ ተቀምጧል፡፡ የእስር ቤት ማስታወሻዬ ግን በጣም የሚገርምና ብዙ ሰው ሊያነበው የሚፈልገው ይመስለኛል ብዙ መሳጭ ታሪኮች አሉት እሱን አስቀድሜአለሁ ብያለሁ፡፡

እድሜ ልክ የፈረደበት ሰው እስር ቤት ሆኖ ምን እንደሚያስብ ባውቅ ደስ ይለኛል ሌለው በእስር ቤት ቆይታህ እነ እስክንድርም ተጐሳቁለዋል የአንተ ጉስቁልናና አካላዊ ጉዳት የተለየ ነበር ምግብ አትመገብም ወይስ ምንድነው?

እድሜ ልክ ሲፈረድ የሚሰማው ስሜት እንደያዝሽው አላማ ይለያያል እድሜ ልክ የማይሞት አላማ ከያዝሽ ከመፈረዱም በፊት ታውቂዋለሽ እያወቅነው ይህንን ለመጋፈጥ ነው ቆርጠን የተነሳነው ጠፍቼ በሱዳን ወይ በኬኒያ በኩል ከአገር መውጣት እችል ነበር በመሸሽ ለውጥ እንደማይመጣ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ ትግል ለውጥ እንደሚመጣ አውቅ ነበር ግን ይሄ እምነት ካለሽ ለሕይወትሽ እንኳን መሳሳት የለብሽም አለኝ በምትይው ሁሉ ነገር ላይ ከጨከንሽ ለውጥ ይመጣል እኔ በልጆቼ በባለቤቴ በሕይወትና አለኝ በምለው ነገር ውስጥ ሁሉ ጨከንኩ ሌሎች ጓደኞቼም እንዲህ ጨክነዋል፡፡ እንዲህ ስጨክን አሁን አንቺን ፊት ለፊቴ የማይሽን ያህል ነፃነት እንደሚመጣ እርግጠኛ ነበርኩ ነገር ግን ነፃነቱ እኔ ከምገምተው በላይ አጥሯል፡፡ ማዕከላዊ ሲያሰሩኝ እኔን በግፍ እንደሰራችኝ በክብር እንደምወጣ እርግጠኛ ነኝ ብያቸው ነበር፡፡ እኔ ከሞትም ነፃነት እንደሚመጣ እያወቅኩ ስለምሞት የህሊና እረፍት ነበረኝ፡፡ ስለዚህ እድሜ ልክ ሲፈረደብኝ እኔ እንዲህ ነበር የማስበው ተስፋና እምነት ነበረኝ፡፡

ጉስቁልናዬን በተለየ እኔም አላወቅኩትም ነበር በአብዛኛው ብቻዬን ነበር የምታሰረው ወይ አብሮኝ ያለ ሰው ወዳጅ ዘመድ ይጠይቀዋል እዛ ውሎ ይመጣል እኔ ግን እዛች መዳፍ የምታክል ቆርቆሮ ስር እንደ እርግብ ቁጭ ብዬ ነው የምውለው ቤቱ መስኮት የለውም ደረጃ ስትወጪና ስትወርጂ በግራም በቀኝም ወታደር ነው እኔ ራሴ እንደላብድ እፈራ ነበር፡፡ ቀኑ እና ሰአቱ  ከአመት ሁሉ ይረዝምብኝ ነበር ትወጫለሽ ትገብያለሽ ጠባብ ክፍል ትታጐሪያለሽ፡፡ ያንን ሰዓት በደንብ ካልተጠቀምሽው ለማበድ ቅርብ ትሆኛለሽ፡፡ ያንን ስለማሰብ በደንብ ስፖርት እሰራ ነበር ከሰኞ እስከ አርብ በየቀኑ ሁት ሁለት ሰዓት ነበር የምሰራው ከዚያ ለብ ያለብኝና ውሃ በሌለበት ጊዜ ላቤ ፊቴ ላይ ደርቆ ይውላል፡፡ ያ ከላብ ጋር ያለው ጨው ፊቴን ያበላሸው ይመስለኛል እናም የምሰራው ስፖርትና የምምገበው ምግብም አይመጣጠንም ነበር፡፡

የምግብ እጥረት ነበር እንዴ?  

በፍፁም እኔና እስክንድር ከአስር ብዛት የጐዳነውን ቤተሰብ ላለማስቸገር እያልን ብዙ እንዲመጣልን አንፈልግም ነበር፡፡ እኔ  ምግብ ሲመጣ ከልጆቼ ጉሮሮ ተነጥቆ የሚመጣ ነው የሚመስለኝ እና ብዙ ሲመጣልኝ ደስተኛ አልነበርኩም እኔ እንደአባት ለልጆቼ የማቀርበው ነገር የለም እዛ ታስሬ 6 ዓመት ሙሉ ከነሱ እየነጠቁ መብላት ደስ አይለኝም የጥፋተኝነት ስሜቴን ለማስታገስ ማለቴ ነው፡፡ በብዛት የእስር ቤቱን ደያስ ነበር  የምመገበው እሱ ለሰውነት የሚያስፈልገውን ነገር ይዟል አልያዘም ሌላ ነገር ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ነው ጉስቁልናው የመጣው፡፡

በመጨረሻ ምን ማለት ትፈልጋለህ ?

እንግዲህ የተጀመሩ በጐ ጅምሮች አሉ በጐና ቀና ሀሳቦችን እየሰማን ነው፡፡ በጐ ሀሳብ ያላቸው ሰዎችን እያየንም ነው ይሄ በጐ ሀሳብ ታዲያ በራሱ መሬት ላይ አይወርድም በርትቶ በመስራት መሬት እንዲረግጥና እቅዱ ተግባር ላይ እንዲውል ያስፈለጋል፡፡ በዶ/ር አብይ አህመድ ውስጥ ያለው የለውጥ ሀሳብ በእያንዳንዱ ካድሬ ልብ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ይሄ እስከሌለ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል አሁንም እኛ ይህንን ያህል ፓርቲና ስብስቦች ተዋህደን አንድ ሆነናል ብዙ የለያየ አስተሳሰብና ልዩነት በሌለበት በየቦታው ተበታትኖ ከመስራት አንድ ላይ ሆነው እንዲታገሉና በሰው ሀይልም በእውቀትም እንዲደራጁ ምኞቴ ነው፡፡ ህዝቡም በትዕግስትና በእርጋታ በሰላማዊ መንገድ መታገል አለበት እላለሁ፡፡

Filed in: Amharic