>
5:13 pm - Sunday April 20, 5834

የዶ/ር አብይ አቧራና አሻራ!!! (ታሪኩ ቢረዳ )

የዶ/ር አብይ አቧራና አሻራ!!!

ታሪኩ ቢረዳ 

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሸገር ገበታ ንግግር አንብቤ ጽሁፌን በራሴው ጥቅስ እንዲህ እጀምራለሁ፣ “ቢቻላችሁስ በአቧራና በአሻራ መካከል ሁኑ!” መልእክቱ ከጫፍ ላለኸው እና አቧራው ለጋረደህ ወንድሜ ነው።ይህ ጽሁፍ አቧራው የጋረዳቸውን እንጂ አቧራውን የሚያስነሱትን አይመለከትም።

እኔ ጸሃፊው በአቧራና በአሻራ መካከል ነኝ።እንዳልኩት የመካከለኛው ሃሳቤ መነሻ የባለአሻራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ነው።ባለመዳፍ በጠፋበት የአቧራ ውስጥ ዘመን ስለአሻራ መነጋገሩ በቀላሉ ለመግባባት አዳጋች እንደሚሆን አውቀዋለሁ።ያም ሆኖ ከአቧራው ግዝፈት በላይ ስለሚታይ አሻራ መነጋገር ግድ ነው።እናም በአቧራና በአሻራ መካከል ቆሜ ከአቧራው መካከል ውጣ እያልኩ እጠራሃለሁ።እኔና አንተ የተፈጠርነው በአቧራ ዘመን ነውና ስለታሪካችን፣ ስለትላንትና፣ ስለዛሬና ስለነገ ስናወራ የሁለት አስርት አመታት ወቅታዊ አቧራ ያፍነናል።በታሪካችን መንገድ ላይ ሁሉ እንዳንግባባ አቧራ መጋረጃ እንዲሆን ታስቦ ተቀስቅሷል።በዚህም በድላችን ይሁን በሽንፈታችን፣ በከፍታችን ይሁን በውድቀታችን በጋራ ታሪኮቻችን ላይ ስምምነት የለንም።በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ያለው ቅርስ ለደቡቡ፣ የምስራቁ ለምእራቡ እንዳይሆን የአቧራ መጋረጃ ሲሰሩ የኖሩ ብዙ ናቸው።የኔ ትውልድ ፈተና ብሄራዊ ጀግናው ላይ እንኳን የማይግባባ፣ አሻራ ያለው ብሄራዊ ጀግንነት ከመፈጸም ይልቅ፣ ብሄራዊ ፈተና ሰርቆ አቧራ ማስነሳት የሚሻ ነው።

ወደ ኋላም ዞረህ እንዳታይ ወደ ፊትም እንዳትራመድ የሚያፍንህ አቧራ አለ።ለዚህ ደግሞ አንተም ምቹ ሆነሃል።ታሪክህን ከአባትህና ከአያትህ ይልቅ ከአክቲቪስት ትፈልጋለህ፣ የማንነትህን እውነት ካደግህበት ከቤተሰብ ከቀየህ ይልቅ፣ ከሊቀመንበሩ፣ ከካድሬው፣ ከሹመኛው ትሻለህ፣ እውነትህን ከመጽሃፍ፣ ከድርሳናት ይልቅ፣ ከፌስቡክ እና ከዩቲዩብ ትጋታለህ፣ ታዲያ አንተ አቧራ እንጅ ምን አሻራ አለህ? አቧራው በሁሉም ቦታ አለ።አሻራው ግን እሩቅ ነው፣ እውነት፣ ትጋትና መዳፍ ይፈልጋል።አቧራው በስሜት ሁካታ ይነሳል፤ አሻራው ግን በጠንካራ ሃሳብ እና በብርቱ ክንድ ካልሆነ አይሳካም።ጠቅላዬ እንዳሉት አቧራው ለአፍታ ነው፣ አሻራው ግን ለትውልድ የሚተላለፍ።አቧራው ላፍታ ተነስቶ ብን ብሎ ይጠፋል፣ አሻራው ግን ሲጻፍ ያደክማል፤ ግን ዘላለም ይኖራል።እኔና አንተ የአቧራ ትውልድ ሆነን ብዙው ነገር ያፍነናል። ስምህን ስትናገር ያፍንሃል፣ ሰፈርህን ስትናገር ያፍንሃል፣ ቀየህን መንደርህን ሃገርህን ስትናገር ያፍንሃል፣ ቋንቋህን ማንነትህን ያልህ እንደሆንማ አቧራው በአፍንጫህ እየመጣ ያፍንሃል።አትችልም።ምክንያቱም አንተ እና እኔ የአቧራ ዘመን ሰዎች ነንና፣ በአቧራ ተከበን አሻራ የሌለን ሁነናልና የነገር ውሽንፍራችን ብዙ ነው።የጥላቻ ድንግዝግዙ ያደናቅፋል፣ በእውር ድንብር ጉዟችን ይወለካከፋ።ለዚህም ነው የኔና ያንተ ትውልድ አሻራ ሊተው አይደለም መዳፍ አልባ ያህል ነው የምልህ።ለተሰራ እውቅና አይሰጥም የተሰራ ያፈርሳል እንጂ፡፡

በዚህ መካከል አቧራው ሳያግደን አሻራ እናኖራለን የሚሉ ሰዎችን ማግኘት በራሱ እድል ነው።ዶክተር አብይ ያሉት ይህንን ነው።አቧራው ሳያግደኝ አሻራ አኖራለሁ።ይህ ሃሳብ የአባት ነው

።የኋላውን አይቶ ወደ ፊት የሚሻገር።ዛሬን ሆኖ ነገን መፍጠር የሚያስችል ሃሳብ ነው።እንዲህ ያለው የሃሳብና የተግባር ብርታት ትልቅ ጥረት፣ ወፍራም እውነት ይፈልጋል።በዚህ መሃል የእኔና ያንተ ትውልድ የቆመበትን ስፍራ ማስተዋል አለበት ብዬ አምናለሁ፣ ለአሻራ ስራ የቀረበ ድፍረት ብናጣ እንኳን ከአቧራ የመውጣት ጥረት ያስፈልገናል።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ እንዳሉት “ወደ ፊት መውደቅም መንገድ ማሳጠር ነው” አሻራ መተው ባትችል በመካከሉ ላይ ተገኝ።እኔ እንዲያ ነኝ።ከአቧራው ወጥቼ በአሻራውና በአቧራው መካከል ላይ ቆሜአለሁ።

ሰውየው በዚያኛው ጫፍ ላይ ነው።በአቧራው ውስጥ አሻራ ማተሜን ማንም አያቆመኝም እያለህ ነው።ይህንን ለማየት አይንህን መግለጥ ብቻ አይበቃህም ወንድሜ፣ ምክንያቱም ያለኽው አቧራው ውስጥ ስለሆነ ብትገልጥም ላፍታ የምታስተውልበት ብርሃን የሚሰጥህ ፋታ የለም።ስለዚህ ከሚለው በላይ የሚያደርገው እንዲታይህ አይንህን ጨፍነህም ቢሆን ከአቧራ ወደ አሻራ ለመውጣት መሞከር አለብህ።ወደ መካከል ስትመጣ አቧራውንም አሻራውንም ለማየት እድል ታገኛለህ፡፡

ለዚህ ነው በሁሉም አቅጣጫ በውስጡ በማይኖሩ አቧራ አስነሽዎች መካከል ሳትሆን ከአቧራቸው ርቀህ በተቻለህ ሁሉ የሰላም ቀጣና ፈልግ የምልህ።አቧራው ባስነሱትና እፍ በሚሉት ሰዎች መንገድ ቀንህ እንዲነጉድ አትፍቀድ።በተበጀልህ ተረክ እየተላጋህ በትንሽነትና በትልቅነት፣ በአጥቂና ተጠቂ፣ በበዳይና ተበዳይ፣ በአሸናፊና ተሸናፊ በበላይና በበታችነት የስሜት ማእበል አትላጋ።አንዳንዱ ተረክ አንሰህ የሽንፈት ትቢያ፣ አሊያም የእብሪት ኩይሳ እንዲፈጥር ያደርጋል።

ሁለቱም ግን አቧራ ነው። ጊዜን አይሻገርም።ኩይሳ ሃውልት መሆን እንደማይቻለው እፍ ሲሉት እንደሚጠፋ ጊዜያዊ ነው።

እሳቸው በንግግራቸው ያሉትን ልድገምልህ ወዳጄ በዚህ ዘመን አቧራ አስነስተው ስም ለማስጠራት፣ ታሪክ ለመስራት የሚደክሙ ሰዎች አሉ።ለጊዜው ያደናግራል።አቧራ ማስነሳት የጉብዝና ምልክት ይመስላል።ለስሟ ማስጠሪያ ቁና ሰፋች እንደሚባለው” ለጊዜው ስምን ያስጠራ ይመስላል።የአቧራና የአቧራ አስነሽዎች ታሪክና ስራ ግን እንኳን ዘመን ወቅትን አይሻገርም።የሃገራችን ታሪክም ይህንን ይነግረናል።መከራና ችግርን ተቋቁመው እዚህ የደረሱልን የሃገራችን ቅርሶች አሻራዎች እንጅ አቧራዎች አይደሉም።በየዘመኑ የተነሱት አቧራዎች ለጊዜው ታይተው፣ አስደንቀው፣ አደባልቀው፣ አናውጠው ሄደዋል፤ አልፈዋል” ይልሃል፡፡

ለዚህም ነው ወዳጄ እውነት ካለህ አሻራ ሁን የምልህ።ዛሬ ላይ አሻራውን የሚያኖር ትውልድ የመዳፉን ጥንካሬ ከግንባሩ ማየት የሚቻል ይመስለኛል።እውነቱ ልክ እንደ ገበሬ ውሎ በፊቱ ላይ ይገለጣል።የገበሬ ሳቅ የእውነት ነው ወዳጄ።የውሸት አይስቅም።የውሸት አይከፋም። ዝምታውም ራሱ ቋንቋ ነው።ወደ ማሳው ሲሄድ ፣ በሬውን ሲጠምድም ፣ ማረስ ሲጀምር ዝናብ አሻግሮ የሚያይ፣ በትልሙ ውስጥ ፍሬ የሚያስተውል፣ መዳፉ በጨበጠው እርፍና ጅራፍ የፍሬ አሻራ የሚያነብ አስተዋይ ነው-ጌታዬ።ገበሬ አፈር እንጅ አቧራ አያስጨንቀውም።ሰማዩ ዳመና ሲያይ ከልቡ ፈገግ የሚል ሲዘንብ ጥርሶቹን የምታየው እሸቱን እንደ ህጻን እራስ የሚዳስስ ከልቡ ፈገግ የሚል ነው ዘመንኛው።እያንዳንዷን ፍሬ ባቅማዳህ ልክ የሚቆጥርልህ ሲሞላ የሚስቅ ነው ገበሬው።በሚኒሊክ አዳራሽ በገበታ ለሸገር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአቧራው በላይ አሻራችን ሊያስጨንቀን ይገባል የሚል መልእክት ያለው ንግግራቸው ሲያደርጉ ብርታትና እምነት ከውስጣቸው እንዳለ ግልጽ ነው።

በዚህ እርግጠኝነቴ ውስጥ ሆኜ ነው።ትላንት አሻራ ያኖሩ ሰዎችን ማየት የተሳነው የአቧራ ትውልድ ስለጠንካራ መዳፍ፣ ስለጠንካራ ነገ፣ ማሰቡን የማወድሰው።ባንተ ቋንቋ ልንገርህ “ጠ/ሚኒስትሩ አሻራውን እያኖረ ያሁነያ” እልሃለሁ።ይህንን ንግግር ብዙዎች ላይረዱኝ ይችላሉ።ከአቧራው ብዙ ሳይርቅ በአሻራና በአቧራ መካከል ላለሁት ለእኔና ላንተ ግን ግልጽ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻራውን እያኖረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው! ይህንን ከአቧራ ሁካታ ካልወጡ ማስተዋል አይቻልም።ልባም ሰው እምነቱም መዳፉም ጠንካራ ነው።ህልሙን በእውን፣ ተስፋውን በጥረት፣ ቃሉን ተግባር እንዲሆን ያደርጋል፡፡

ከአለት የተጠረቡት ቅርሶች ከአለት በላይ የጠነከሩ እምነትና ጥረቶች ውጤት ናቸው።እልፍ ዘመን የተሻገሩ ስርዓቶች ከዘመን በላይ የገዘፉ የሺህ አመታት ልምምዶች ናቸው።አሻራ የሆኑት በትጋት ነው።ትጋት ባይኖር እምነትና ተከታይ ባይኖር፣ አቧራ እንጂ አሻራ አይሆኑም ነበር።እናም እኒህ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ሃሳብና ተግባራት በቅዠታችን መካከል የመጡት ትጋቶች፣ በዛሬያችን ውስጥ የሆኑት ትላንትና ነገዎች፣ በውሸታችን ውስጥ የመጡት እውነቶች፣ በጥላቻችን መካከል ፍቅራችን…….ወዘተረፈ… ሲደመር….ሲቀጥል አቧራው ሲያልፍ አሻራው እውን ሆኖ የሚታይ ነው።ለዚህ ነው ወደ መካከል ና የምልህ!!! መግቢያው በመካከል ነው፣ ከጫፍ ያለው መግቢያ አያስገባህም፤ ቢያስገባህም እያጋጨ ነው።ዞሮ ዘሮ ስትገባ ሃገሩ መሃል ነው፡፡

Filed in: Amharic