>
5:14 pm - Thursday April 20, 4451

ኢትዮጵያ ሁለት ግንቦቶች ነው ያሏት! (ታማኝ በየነ)


ኢትዮጵያ
 ሁለት ግንቦቶች ነው ያሏት! 
ግንቦት ከ1981 በፊት እና ግንቦት ከ1981 በኃላ….!!!!
ታማኝ በየነ
ከ1981 ጀምሮ ያለው ግንቦት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይረሱ በክፉም በደጉም የአገራችንን ዕድሎች የወሰኑ ትልልቅ ክስተቶች የተፈፀመበት ወር ሆኖ ይታሰባል::
በእኔ እይታ የመጀመርያው እና ኢትዮጵያውያን በቁጭት የሚያስታውሱት የግንቦት 8: 1981 የኢትዮጵያ ሰራዊት ታዋቂ ጀኔራሎች የከሸፈባቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እና ያስከተለው መዘዝ ነው:: ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በአንድ በኩል ሥልጣናቸውን በሌላ በኩል ደግሞ ጠላቶቻቸውን ለመዋጋት ሶስትዮሽ (triangle) በሚባል የዕዝ እና የስለላ መዋቅር የተተበተበውን የኢትዮጵያ ሠራዊት አደረጃጀት አልፈው መፈንቅለ መንግሥት የሞከሩት ጀነራሎች ውጥናቸው ተሳክቶ ቢሆን ኢትዮጵያ ወዴት ትሄድ እንደነበር ከተስፋ በላይ መተንበይ ቢከብድም ባለመሳካቱ ግን ኢትዮጵያ ምን እንዳጣች ምስክሮች ሆነናል::
ኢትዮጵያ በዘመኗ ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች ጋር ባደረገቻቸው ግጭቶች 6 ጄኔራሎችን መስዋዕት አድርጋለች:: በመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ ዙሪያ በነበሩ ሶስት ቀናት ኢትዮጵያ 27 ጄነራሎችን አጥታለች:: ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ በ1981 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው የደርግ መንግስት ከመውደቁ ወራት በፊት ህይወታቸውን ያጡት የ12ቱ ጀነራሎች ህይወት ነው:: ሁሉንም ባስብኳቸው ቁጥር አዝናለሁ:: የኢትዮጵያ ሰራዊት ሶማሊያን ወያኔን እና ሻዕቢያን ብቻ ሳይሆን የስልጣን ጥመኞችን በትከሻው ተሸክሞ ለ17 አመት ያደረገውን ተጋድሎ ሳሰላስለው ለሰራዊቱ ያለኝ ክብር ይጨምራል::
የግንቦት 8 : 1981 መፈንቅለ መንግስት መክሸፍ ሰራዊቱ በየደረጃው ያሉትን ባለብዙ ልምድ አመራሮቹን እንዲያጣ ሆነ:: ቀደም ሲልም በተለያዩ አወደ ውጊያዎች ጉልበቱ እየላላ የነበረው ጦር በአጭር ግዜ ውስጥ ተገፍትሮ ወያኔ አዲስ አበባን ሻዕብያ ደግሞ አስመራን ተቆጣጠሩ:: ይህም የኢትዮጵያን ቀጣይ ዘመናት ዕጣ ፈንታን ያተመ ክስተት የግንቦት 1983 ውጤት ነው!
የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 27 የመከራ ዘመናት ወደብ በሌለው የድንጋይ እና አፈር ድንበር የታጠረውም በግንቦት 1983 ነው:: መለስ ዜናዊ ጮሌነትን እንደእውቀት የያዘ በዘረኝነት በሽታ የታመሙ ኢትዮጵያ ጠል ካድሬዎች ሰብስቦ አገሪቷን በግድያ እስር ስደት ረሃብ ሙስና መፈናቀል ሌብነትን ሙያ አድርጎ እንደ ቆላ ተምች ያስወረራት ከወርሃ ግንቦት 83 ጀምሮ ነበር::
መለስ ዜናዊ የገዛ የውሸት ዲስኩሩን ተማምኖ በውጭ አገራትም ግፊት ያለአቅሙ በኢትዮጵያ ምድር የተሻለ እና ተዓማኒ ምርጫ አድርጌ ከ83 ጀምሮ ተቀባይነት ሳይኖረኝ የገዛሁብትን ዘመን በእውነተኛ ምርጫ አርጋግጣለሁ ብሎም የሞከረው በግንቦት 1997 ነበር:: ምርጫ 1997! ብዙዎች ምርጫ 97 ወያኔ ብቻ የተሸነፈበት ክስትት ይመስላቸዋል:: ምርጫ 97 የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን ብቻ ሳይሆን “ከቅንጅት” ፓርቲዎች ውጪ የቀረበለትን በ”አንድነት” ውስጥ የተሰባሰቡትን የብሄር እና የአይዲዮሎጂ ፓርቲዎችንም ጭምር ነበር የማሸነፍ ድምፅ የነፈገው:: ምርጫ 97 በኢትዮጵያ ምድር ገዥዎች ለዴሞክራሲ እንዳልደረሱ ተገዥዎች ግን ሁልግዜም ተዘጋጅተው እንደኖሩ ለአለም የተገለፀበት ውቅት ነበር::
ሲሸነፍ ኳሷን ይዞ ወደቤቱ እንደሚሄድ ህጻን መለስ ዜናዊም በምርጫ 97 አልተሸነፍኩም ብሎ እገሩን በደም እና እንባ አጠበው:: ኢትዮጵያ ልትሻገረው የሞከረችውን የሙከራ ድልድይ አፈረሰው:: ህይወቱ እስከምታልፍ በቁሙ ከራሱም በኃላ በካድሬዎቹ እና ተባባሪ ስብስቦች የኢትዮጵያን ህዝብ ድምፅ በግፍ አፍነው መውጫ ሊያሳጣን ለ14 አመት አገሪቷን አገታት! ርግጫቸው በበዛ ቁጥር ግን የኢትዮጵያውያንን የፍትህ እና ርዕትህ ፍላጎትን ሊገታው ስላልቻለ መፍረሱ የማይቀረውን የስርዓቱንም ሲቃ እየታዘብን ነው::
ያለፈውንም አንድ አመት በስጋት እና በተስፋ ባላ ተሰቅለን ትግላችን ኢትዮጵያ የሚገባት ዳርቻ እስከምትደርስ መቀጠል ነው:: በኢትዮጵያ ህዝብ በእጅጉ መተማመን ያለኝ ሰው ነኝ:: ለእኔ ድምፁን ከፍ አድርጎ ከሚናገረው ዝም ያለው የወገኔ ድምፅ ይሰማኛል:: የአሁኑ አውቅልሃለሁ ሰክኖ ሁሉም ምርጫ በገብታ ሲቀርብለት የኢትዮጵያ ህዝብ በእውነተኛ ምርጫ ብዙውን ነገር እንደሚያስተነፍሰው እምነቴ ነው!
አንድ ህዝብ አንድ ኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic