>
10:45 am - Friday May 20, 2022

በአገራችን የችግሮች ሁሉ ምንጭ ሕገ-መንግስቱ ስለሆነ አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ አለበት!!! (ኤፍሬም ለገሰ)

በአገራችን የችግሮች ሁሉ ምንጭ ሕገ-መንግስቱ ስለሆነ አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ አለበት!!!
ኤፍሬም ለገሰ
ስለ ኢህአዴግ የአቅጣጫ መግለጫ ከሳምንት በኋላ፥ ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በብሄር ፖለቲካ ተተብትቦ በመሰሪው የህወሃት-ኢህአዴግ ሕገ-መንግስት የብሄር ክልሎችን መብት ከመጠን በላይ ለጥጦ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር የራሳቸውን ሰራዊትና የራስን እድል በራስ መወሰን በመደንገግ ከፌዴራል መንግስት የበለጠ መብት በመስጠቱ ስለ ተጀመረው ለውጥ አቅጣጫ ለመስጠት ውሉና አቅጣጫው የጠፋበት ይመስላል።
በአሁኑ ወቅት የሚታዩት ግጭቶችም ሆኑ መፈናቀሎች የፅንፈኛ ቡድኖች መኖር ብቻ ሳይሆን በአመራር ላይ ያለው አካል ከመጀመሪያው አንስቶ   በፅንፈኞቹ ቡድኖችና በተለይ በአመራሮቻቸው ላይ ቆራጥ የሆነ እርምጃና አቋም መውሰድ አለመቻሉ ጉዳዩ እንዲዛዛና ወደ አስከፊነት እንዲለወጥ አድርጎታል። የሚገርመው ነገር ይህ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ ሌሎች ፅንፈኛ የብሄር ድርጅቶች ሕገ መንግሥቱና የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር የሚነካው በኛ እሬሳ ላይ ነው የሚሉ መፈልፈላቸው ነው።
ይህ የቀጥታ አቅጣጫ መግለጫ ግልጽነት እና ትኩረት የጎደለው ጊዜ ለማሸነፍ የተድበሰበሰ ወይም የተሸፋፈነ ፍራቻም የተሞላበት ነው።
የአገራችን ዋናው ችግር የሚጀምረው ከህወሃት-ኢህአዴግ ሕገ-መንግስት ስለሆነ ዋናው አቅጣጫና አቋም እንዲሁም አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ ያለበት በዚሁ ላይ ነው።
የናሺናሊም ፖለቲካ በኛ አገር የብሄርተኝነት ፖለቲካ የሚባለው ሲሆን ይህንን መርዘኛ ፖለቲካ በአገራችን ያስፋፉት ብሄርተኞች የማርክስንና የሌኒንን የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ለራሳቸው እንደ ሚመቻቸው አጣሞ በመተርጎም ነው። የብሄርተኝነት   ፖለቲካ አቀንቃኞች የሕዝብን ብሶትና በደል  ብሄርተኝነትን ለግብር ሰብሳቢነትና የግል ኪሳቸውን ለማደለብ እንጅ የሕዝብ ጉዳይ ወይም ችግር  እንደማያሳስባቸውና በነሱ ላይም ክትትልና ጥንቃቄ እንደ ሚያስፈልግ ማርክስ ይጠቅሳል። ይህ የማርክስ አስተያየት በአገራችን ከ1983 ዓም ጀምሮ በሰፊውና በግልፅ የታየና እየታየ ያለ ነው። ለዚህም እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉት የፅንፈኞቹ የሕወሃትና የኦነግ አቀንቃኞችና ቁንጮ አመራሮች በደሃው ሕዝብ ስም ሃብት እንዳጋበሱና እንደዘረፉ የሚታወቅ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ስለዚህ መፍትሄው አገራችንና ባህላችንን እንዲሁም ዛሬ አሉን የምንላቸው “ብሄረሰቦች ብሄሮችና ሕዝቦች” ከነ ባህል ቋንቋቸውና እሴቶቻቸው  የቆዩልንና ዛሬ በኬኛና የኛ ነው የምጣላውባቸው ጉዳዮች ሁሉ በጥንት እናት አባቶቻችን በሀይማኖት በጎሳ ሳይለያዩ  በፍቅርና በአንድነት ያቆዩልን በኢትዮጵያ ጥላ ስር በመሰባሰብ ነው። በትንንሽ መንደሮች ከመከፋፈል በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም እንደ ትላንቱ እንሰባሰብ።
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ተጀምሮ ለነበረው ለውጥ  ስር ነቀል አቋም አስፈላጊ ነው።
በአገራችን ፖለቲካ ሌሎች ግራ የተጋቡና አቅጣጫ የጠፋባቸው ወይም ኢህአዴግን መስለው የሚኖሩት ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በተለያዩ የአገራችን ቦታዋችና ጊዜዓት ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ቁጥራቸው ከሀሳባቸው በብዙ እጥፍ የሚበዛ ድርጅቶች የቀረው ቀርቶ ምንም አይነት ተቃውሞ ወይም አስተያየት ወይም ድምፃቸውን  አለማሰማታቸው ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና የብሄር ፖለቲካ ማጥ ውስጥ ገብቶ ለዉጡ ቆሞ ፅንፈኞችና እብሪተኞች ደግሞ ውስጥ ውስጡን ሴራቸውን እየሸረቡ ይገኛሉ ስለዚህ ለውጡ  አቅጣጫ እንዲይዝና ከግቡ እንዲደርስ ሁሉንም ተቋማትና የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ከሕዝብ የተውጣጡ የባህላዊና ሃይማኖታዊ ተወካዮችን በማካተት የሽግግር መንግስት ቢቋቋም አስታራቂ ይመስለኛል።
ሕዝብ አምኖበት ያፀደቀው ህገ_ኢትዮጵያ እስከሚወጣ ድረስ በአሁኑ ሰዓት ያለው ሕገ_መንግስት ከአገልግሎት መውጣት ወይም መሻር ይኖርበታል።
በተረፈ የብሄር የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ የብሄር ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴቶችና በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ ቢሰማሩና የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ አገር አቀፋዊ  በሆነ መልኩ ቢደራጁ ጥሩ የሰላም፣ የአብሮነትና የዴሞክራሲ እንዲሁም የምንመኘው ልማትም ሊመጣ ይችላል።
በተረፈ ፈጣሪ ሰላሙን ያብዛልን።
Filed in: Amharic