>

" ለምለም እንጀራዋ ቅድስት ኢትዮጵያና"  የበላተኛ ጠላቶቿ ፍጻሜ (ዘመድኩን በቀለ)

” ለምለም እንጀራዋ ቅድስት ኢትዮጵያና”  የበላተኛ ጠላቶቿ ፍጻሜ።  ክፍል አንድ 
 ዘመድኩን በቀለ
~ ሶማሊያ ~ ሱዳን~ ሊቢያ~ ሶሪያ~ ኢጣሊያ። 
 
” ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።” መዝ 68፣ 31። ” በፊቱም ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።” መዝ 72፣ 9።
•••
እርግጥ ነው ኢትዮጵያዬ ችግር ላይ ናት። ችግሩ ግን አብሯት የኖረ ነው። ከአፈጣጠሯ ጋር የተያያዘም ነው። ሃብቷና ውበቷ ጠላት ያፈራባት፤ ችግርም ፀጋዋ የሆነላት ሀገር ናት ኢትዮጵያዬ። ወደቀች ብለው የገፏትን ሁሉ በአፍጢማቸው የምትደፋ፣ ሊከፋፍሏት ያሴሩትን ሁሉ ፈንጅ ላይ እንደቆመ መኪና ብትንትናቸውን የምታወጣ፣ በዝምታ የምትገድል፣ የምታወድም። አመንምና፣ እንደጨው የምታሟማ፣ ክብራቸውን፣ ገናናነታቸውን ከላያቸው ገፍፎ አምላኳ ጠላቶቿን ጊዜ ጠብቆ የሚቀጣላትም ሀገር ናት ኢትዮጵያዬ። [ ህውሓት ትመስክር ]
•••
ኢትዮጵያ ሃገረ እግዚአብሔር ናት። በመለኮታዊ ኃይል የምትጠበቅ መንፈሳዊት ሃገርም ናት። ኢትዮጵያ የአማኞች ሀገር ናት። የብሉይ ኪዳኑ ታቦት፣ የሃዲስ ኪዳኑ መስቀለ ክርስቶስ መገኛ፣ ማረፊያ መቀመጫ ዙፋንም ናት። በብዙ ዐውሎና ወጀብ ውስጥ ሌላውን ዓለም በሚያስደምም የፈጣሪ ጥበቃ የምትኖር ተአምረኛ ሀገርም ናት ሀገሬ።
•••
በዮዲት ጉዲት የጀመረው ኢትዮጵያን የማውደም ዘመቻ በግራኝ አህመድም ቀጥሎ አልተሳካም። ዮዲት ጉዲትም፣ ግራኝ አህመድም ሁለቱም ትቢያ ሆነው ጠፍተዋል። ኢትዮጵያ ግን እስከዛሬ ይኸው እንዳለች አለች። የጣሊያን ወረራ፣ የአቶማን ቱርኮች ሴራ፣ የግብጾች ትንኮሳ፣ የእንግሊዞችን ተንኮልና ሴራም ተቋቁማና አክሽፋ ኢትዮጵያዬ ከዛሬ ደርሳለች። ዛሬንም በድል ተሻግራ የነገውን የአሸናፊነት ካባ ትጎናጸፋለች። ዛሬ የምናየው ችግር የሚመስል ችግር ራሱ እንደ ደመና ያለ ነው። ቆይቶ ይጠራል።
•••
ኢትዮጵያን በማፍረስ ሴራ የተሳተፉ ሰዎችም ሆኑ ሀገራት እንደ አሞሌ ጨው በቁማቸው ሟምተው ነው የቀሩት። መለስ ዜናዊ፣ ሙአመር ጋዳፊ፣ ሆስኒ ሙባረክ፣ ወዘተን መጥቀስ ይቻላል። ሞሶሎኒ እንኳ አልቀረም ተዋርዶ ሲሞት። የኢትዮጵያ ተዋጊዋ ፈጣሪዋ ነው። አምላኳ ነው። ኢትዮጵያን የተተናኮሉ ሁሉ ምን እንደገጠማቸው ከብዙ በጥቂቱ ቆንጠር፣ ቆንጠር አድርገን እስቲ ተራ በተራ ለማየት እንሞክር።
• ፩ኛ፦ #ሶማልያ
•••
ቀድሞ የኢትዮጵያ ግዛት የኢትዮጵያ አካልም የነበረች ናት። ልክ እንደ ትግራይ፣ እንደ ኤርትራ፣ እንደ ጅቡቲ፣ እንደ ቤተ ዐማራ፣ እንደ ኦሮሚያ የኢትዮጵያ አካል የነበረች ሀገር ነበረች። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በእንግሊዞች ሴራ የተገነጠለች፣ ኋላም ራሷን የቻለች ሀገር ለመባል የበቃችም ሀገር ናት ሶማሊያ። ኋላ ላይ ግን ጠገበች። ጥጋብ አናቷ ላይ ወጣ፣ ያደርግ ይሠራትንም አሳጣት። ወላጅ እናቷን ኢትዮጵያዬን በእግሯ ገብታ ወገቧን ቆርጣ ለመጣል በብዙ ደከመች። ኢትዮጵያን የወረረች ሃገርም ለመባል እጅጉን ጣረች። እስከ ናዝሬት ድረስ የእኔ ግዛት ነው ብላም ጦር አደራጅታ እስከማዝመት ደረሰች። ድሬደዋ ለመግባትም ከጫፍ የደረሰች፣ ጅጅጋን አልፋ ሐረር ለመግባትም መከራዋን የበላች ደፋር ሃገርም ለመባል በቃች። ለእነ መለስ ዜናዊ ፓስፖርት አሠርታ የሻአቢያንና የወያኔን የመገንጠል ትግል የደገፈች ደፋርም ነበረች። ይሄን ድፍረቷን ያየው የኢትዮጵያ አምላክም ሶማሊያን ተቆጣት። ቀኙንም አከበደባት። ሦስት ቦታም ጎማመዳት፣ ስፍር ቁጥር በሌላቸው የጎሳ መሪዎች እጅም ጣላት። ሶማሊያ እንደ ሃገር ለመቀጠል እንኳ ከተሳናት እነሆ ይኸው 40 ዓመታት አለፏት። በቁሟ ፈረሰች። ኢትዮጵያ ግን ከነቁስሏ፣ ከነህመሟም ቢሆን እንዳለች አለች።
፪ኛ፦ #ሱዳን ፦
•••
በአፄ ዮሐንስ ለእንግሊዝ ተደርቦ የነፃነት ተዋጊዎቿ ላይ ትንኮሳ የመፈጸም ጥፋት የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ ካቄመች ቆየች። በዚሁ ንዴት የንጉሡን የአፄ ዮሐንስን አንገት ቆርጣ መውሰዷም አላረካትም። ልክ እንደ አፄ ዮሐንስ አንገት ሁሉ የኢትዮጵያንም አንገቷን መቁረጥ አሰኛት። አማራትም።  እናም ለሻአቢያና ለህወሓት ከመዋጊያ ነጻ መሬት እስከ ወታደራዊ ድጋፍ የደረሰ ልግስና በመስጠት ኢትዮጵያዬን ምድራዊ ሲዖል አደረገቻት። በመጨረሻም ህልሟ ተሰካቶላት ሻአቢያን አስመራ ልካ በኢሳይያስና በአቶ መለስ አራጅነት የኢትዮጵያን አንገት ኤርትራን አስቆረጠች። ቀድሞ የአጼ ዮሐንስን አንገት የቆረጠችው ሱዳን ኋላም የንጉሡን ሀገር የኢትዮጵያን አንገት አስቆረጠች።
•••
የኢትዮጵያም አምላክ ከላይ ከዙፋኑ ሆኖ ይህንንም የሱዳንን ሴራ ዓየ፣ ተመለከተም። እናም ፈረደ። ሱዳንን ዓይኗ እያየ፣ ጆሮዋም እየሰማ፣ ያለማደንዘዣ ወገብ ዛላዋን ብሎ ለሁለት ጎምዶ ጣላት። ሰሜን ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ብሎም ሀራምባና ቆቦ አድርጎ ከፋፍሎና አራቁቶ ሁለት ሀገር አድርጎ አስቀራት። ሁለት ባንዲራም ተውለበለበባት። ሴረኛዋ ሰሜን ሱዳን የነዳጅ ሃብቷን ሳይቀር ደቡብ ሱዳን በቁሟ ወረሰቻት። የሱዳን መከራዋ በዚህ ብቻ አያበቃም። ገና በዳርፉርና በምሥራቅ ሱዳንም እንደ ዳቦ የመቆራረስ ዕጣ ይጠብቃታል። በኢትዮጵያ እንደሳቀች፣ እንደተሳለቀችም በተራዋ ገና ይሳቅባታል፣ ጀምሯታል፣ ዳቦ አምስት ሳንቲም ጨመረ ተብሎ እሳት ለቆባታል። ገና ደም ታለቅሳለች። [ ከዚህ ጦማሬ በኋላ የህወሓት ቀኝ እጅ፣ መመኪያ ፈጣሪያቸው የነበረው የሱዳኑ አልበሽር አፈር ከደቼ በልቷል]
•፫ኛ፦ #ሊቢያ
•••
የሙሀመድ ጋዳፊዋ ሊቢያ ትዕቢት ደግሞ ገራሚ ነበር። የኢትዮጵያ ስም በተነሳ ቁጥር ዛር እንዳለበት ሰው ያስጓራት ያንቀጠቅጣትም ነበር። የኢትዮጵያን ስም ስትሰማ መስቀል እንዳየ፣ ጠበልም እንዳረፈበት አጋንንት ያቅበጠብጣት ያስጮሃትም ነበር። የጋዳፊዋ ሊቢያ ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በደርግም ዘመን የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይላት እስኪነስራቸው ድረስ ስትረዳ፣ እስከ አፍንጫቸውም ታስታጥቅ የነበረች ሀገር ነበረች። የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽህፈት ቤቱ እንኳ ከአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ያልፈነቀለችው ድንጋይም አልነበረም። ስለት የተሳለች ይመስል ኢትዮጵያ ፍርስርሷ ወጥቶ እንድትታይም በብዙ ጣረች። ደከመችም። ነገር ግን የተገላቢጦሽ ሆነ። ሊቢያ በቁሟ እንደ ሳር ቤት ነደደች። ወደ ትቢያነትም ተቀየረች። የሆነው ይኸው ነው።
•፬ኛ፦ #ሶርያ
•••
ምን እንዳደረግናት ፈጣሪ ይወቅ። ሻአቢያንና ጀብሃን ኋላም ወያኔን እንደ ስለት ልጅ እየተንከባከበች አሳደገች። በደማስቆ የቆመን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን ሳይቀር ለማጋየት ሞከረች። ብቻ የኢትዮጵያን መፍረስ አጥብቃ ፈለገች። የነዳጅ ብሯን ቦንብና ክላሽ እየገዛች ለሻብያ እስከ አፍንጫው አስታጠቀች። ኢትዮጵያን ባለ በሌለ ኃይሏ አሰወጋች፣ አደማች። ተሳክቶላትም  የኢትዮጵያንም አንገት ባሳደገቻቸው ቡችሎቿ አማካኝነት አስቆረጠች።
•••
ይኼንንም የኢትዮጵያ አምላኳና ጠባቂ መከታዋ ልዑል እግዚአብሔር ከላይ ከዙፋኑ ሆኖ ዓየው። ተመለከተውም። እነ ሊቢያ ላይ ያነሳውን ጅራፉንም ሶሪያ ላይ አነሳ። ቀኙም በሶሪያ ላይ ከበደች። ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ሶሪያ ዓይኗ እያየ፣ ጆሮዋም እየሰማ ፍርስርሷ ወጣ። ጥንታውያን የሶሪያ ከተሞችም ወደ ትቢያነት ተቀየሩ። ሶሪያውያን በዓለም ላይ ተሰደዱ። የስደት እግራቸውም በአባቶቻቸው ሴራ እንድትፈራርስ በብዙ የደከሙባት ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ አደረሳቸው። ዛሬ እነዚያ በሃብት መጠናቸው ከአውሮጳውያን ይተካከሉና ያስንቁ የነበሩ ሶሪያውያን በመርካቶና በቦሌ ጎዳናዎች እየተንከራተቱ ይለምናሉ። ኢትዮጵያ ባለመፍረሷ የስደተኞቹን ነፍስ ማቆያ ሀገር ሆነች። እምጷ ኢትዮጵያዬ።
ጣልያን፦ 
•••
ሁለት ጊዜ አወደመችን። በ3 ቀን ብቻ ከ30 ሺ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አርዳ ጭካኔዋን አሳየችን። ከሞት የተረፉትን አዲስ አበቤዎች ግማሹን አስመራ፣ ገሚሱን መቋዲሾ ወስዳ በግዞት መልክ በወዘችን። በዓለም ላይ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ ተጠቅማም ያለ ርህራሄ ፈጀችን። ጳጳሷ ታንክ ባርከው ኢትዮጵያውያንን እንዲጨፈጭፉ ወታደሮቿን መስቀል አሳልመው ጠበል ረጭተው ላኩብን። መጀመሪያ ዓድዋ ላይ ሞከረችን ሞተን መለስናት። 40 ዓመት ቆይታና አድብታ በብዙም ስትዘጋጅ ቆይታና ቂም ይዛ ተመልሳ መጣች። 5 ዓመት አንገብግበን አሳሯን አብልተን ወደመጣችበት መለስናት። ኢትዮጵያን መርዝ ተክላባት ሄደች። ለኤርትራ አዲስ ስም አውጥታ፤ ሀገርነሽ ብላም ሰብካ፣ አድቅቃን፣ ዘርፋን፣ ገድላን፣ አሁን ህወሓት ከፋፍላ እኛን የሚታባላበትን የዘር ፖለቲካ ካርታ ሠርታልን ወደ አውሮጳ ወደ አህጉሯ በሽንፈት አንገት ደፍታ ተመለሰች።
•••
የኢትዮጵያ አምላክ ይሄንንም የኢጣልያን ክፋት ዐየ፣  ተመለከተም። እነሆ ክርስቲያን ነኝ ባይዋ ኢጣሊያ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከደፈረችበት ጊዜ አንስቶ ጣልያንን ፈጣሪ ረገማት። ቀኙንም አከበደባት። በአውሮጳ እየኖረች እንደ አፍሪካ ድኻ የድኻ ድኻም አደረጋት። ክብሯን፣ ገናንነቷንም ገፈፈው። ቀልበቢስ የዓለም ስደተኞችም መናሃሪያ አድረጋት። ስሟ ከኳስ በዘለለ የማይነሳባት፣ ስደተኞች እንኳ ቢሆኑ እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ እንጂ በእርሷ ዘንድ ለመቆየት የሚጠየፏት በአውሮጳ የምትኖር ድኻ ሃገር አደረጋት።
ይቀጥላል… ዋና ዋናዎቹን ከነሴራቸው ገና አልነካኋቸውም። የሌሎችም እንዲሁ ይቀጥላል ! 
ሻሎም !  ሰላም !
 ነኝ።
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic