>

የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች በኃይል ማዳፈን አይቻልም!

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ህወሓት/ኢህአዲግ ቆምኩለት የሚለውን ህገ-መንግስት እና የቡድን መብት መሰረት በማድረግ የእምነት ነፃነት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች በተደጋጋሚ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ሰማያዊ ፓርቲ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ሁሉን በመንግስታዊ ሽብርና በሀይል የሚያስተናግደው ገዢው ፓርቲ ህወሓት/ኢ
ህአዲግ አሁንም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ያነሱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ በከፋ ሁኔታ የሀይል እርምጃ መውሰዱን አማራጭ አድርጎ ቀጥሎበታል፡፡

አርብ ሐምሌ 11 2006 ዓ.ም በተካሄደው የህዝበ ሙስሊሙ የጁምዓ ሰላት ስነ-ስርዓት ላይ በሰለማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ሲያሰሙ የነበሩ የእምነቱ ተከታዮችና በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በፌደራል ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በትራፊክ ፖሊስና ሲቪል በለበሱ የደህንነት አካላት አማካኝነት ከፍተኛ ድብደባ፣ እንግልትና እስር ተፈፅሞባቸዋል፡፡ መረጃዎቻችን እንደሚያስረዱት ወደ 30 የሚደርሱ ዜጎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በየሆስፒታሉ ይገኛሉ፤ በርካቶችም ጭካኔ በተሞላበት ድብደባ ተጎድተዋል፡፡ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎችም በየእስር ቤቱ ታፍነው ይገኛሉ፡፡

በእለቱ የፓርቲያችን ብሔራዊ ም/ቤት እና የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወ/ት ወይንሸት ሞላ በአካባቢው ተይዛ ደህንነት ነን በሚሉ አካላት ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባታል፡፡ ወይንሸት በወቅቱ በአንድ ህንፃ ውስጥ ከጋዜጠኞችና ከራሱ ከመንግስት አካላት ጋር ጉዳዩን ትከታተል በነበረበት ወቅት በደህንነት አካላት ተለይታ ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስዳለች፡፡ ቅዳሜ ጠዋት ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኝ ፍርድ ቤት ጭንቅላቷ ታሽጎ፣ እጇ ተሰብሮና ክፉኛ ተጎድታ ታይታለች፡፡ ህወሓት/ኢህአዲግ የፓርቲያችንን አባል በህገ-ወጥ እስር ማፈኑ ሳያንስ ያደረሰባት አካለዊ ጉዳትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ ሲበዛ አሳፋሪ እና አሳዛኝ ነው፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ታፍና ሰብዓዊ መብቷ ተጥሶ ባለችበት ወቅት ምንም አይነት ህክምና እና እንዲሁም ማንም ሰው እንዳይጠይቃትና የህግ አማካሪና ከለላ እንዳታገኝ መደረጉ ህወሓት/ኢህአዲግ የማይወጣበት የግፍ ማጥ ውስጥ እንደገባና መንግስታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ያቃተው ቡድን እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ህወሓት/ኢህአዲግ ጥያቄ በሚያነሱ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየወሰደ ያለው የሀይል እርምጃ እጅግ ያሳስበዋል፡፡ በተከታታይ ጊዜያት በተለያዩ አካላት በሰላማዊ መንገድ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የሽብርና የሀይል መንገድን መምረጡም የመንግስትነት ኃላፊነቱን ጨርሶውኑ መሸከም ወደማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ፓርቲያችን ያምናል፡፡ አልፎ ተርፎም በህገ-መንግስት የተደነገጉ መብቶችን፡-
አንቀፅ 27- የሀይማኖት፣ እምነትና የአመለካከት መብት
አንቀፅ 30- የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት
አንቀፅ 29- የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት
አንቀፅ 18- ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ
አንቀፅ 19- የተያዙ ሰዎች መብት
አንቀፅ 28- በስብእና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና – ሌሎች መሰል ድንጋጌዎችን በግልፅ በአደባባይ በመጣስ ለህግ የመገዛት ቁመናና ባህርይ እንደሌለው በድጋሚ አረጋግጧል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በሚያካሂደው ሰላማዊ ትግል የህዝበ ሙስሊሙን ፍፁም ሰላማዊ የእምነት ነፃነት ጥያቄ በቅርብ ይከታተለዋል፡፡ ፓርቲያችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የህወሓት/ኢህአዲግ የእብሪት መንገድ፣ ህገ-ወጥ የሰብዓዊ መብት አያያዝና በሃይል ጥያቄዎችን የመፍታት ብሂል ያወግዛል፤ ይህን አምባገነናዊ አካሄድና ስርዓትም እስከመጨረሻው በፅናት ይታገለዋል፡፡ ገዢው ፓርቲም ህገ-መንግስቱን ከሚጥስ አድራጎቱ ተቆጥቦ ነገሮችን ወደ አላስፈላጊ ሁናቴ ከመግፋት ይልቅ ልብ ገዝቶና ወደ አቅሉ ተመልሶ ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች አፋጣኝ፣ ተገቢና ህገ-መንግስታዊ ምላሽ እንዲሰጥ በድጋሚ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ በተጨማሪም ጥያቄ በማንሳታቸው ታፍነው የታሰሩ ሙስሊም ምእመኖች፣ በህገወጥ ሁኔታ ታስረው የሚገኙ ዜጎች እና የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ወ/ት ወይንሸት ሞላ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲፈቱ በአፅንዖት ያሳስባል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሰማያዊ ፓርቲ
ሐምሌ 13 ቀን 2006 ዓ.ም

Filed in: Amharic