>

ሕዝባዊ ከያኒው!!! (እንዳለጌታ ከበደ)

ሕዝባዊ ከያኒው!!!
እንዳለጌታ ከበደ
 ሕዝባዊ ገጣምያን፣ እነዚያ ሬዲዮ ጣቢያ የሌላቸው፣ ግጥም ማንበብያ መድረክ ያልተዘረጋላቸው፣ ግጥሞቻቸው  የሚያሳትሙበት ጋዜጣም ሆነ ሌላ ሚዲያ ያልተመቻቸላቸው እነዚያ አዝማሪያንና አልቃሾች ነገሥታቱን ብቻ ሳይሆን፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ልሂቅና ጉልህ የተባለውን ሁሉ ይተቻሉ፡፡ ቃሉን ያጠፈውን፣ በሕዝብ ላይ የቀለደውን ይገስፃሉ፡፡
ንጉሥ ሣህለሥላሴ  ንጉሥ ፣ ብርቄ የተባለ ታማኝ አሽከር ነበራቸው ይላሉ ዶክተር ሥርግው፡፡ ‹… እርሱ የሚያማክረው ሁሉ ትክክል ስለነበረ ንጉሡ እጅግ ይወደው ነበር፡፡ ሣህለሥላሴ በሚመገብበት ሰዓት ያስጠራውና በአፍ ባፉ ያጎርሰዋል፡፡ ብርቄም የሣህለሥላሴን ሞት አታሳየኝ፣ እኔን አስቀድመኝ፡፡ምናልባት እርሳቸው ቢቀድሙኝ አንኮበርን ለቅቄ፣ ቤቴን ንብረቴን ትቼ፣ ደብረ ሊባኖስ እገባለሁ እያለ፣ ሁልጊዜ ስለሚናገር ይህን አባባሉን ሰው ሁሉ ያውቅ ነበረ፡፡ ብርቄ ግን የትም ንቅንቅ አላለም፤ እዚያው አንኮበር ነበር፡፡ ብዙ ንብረት ነበረውና አሳስቶት ሳይመንን ቆየ፡፡ በዚህን ጊዜ አንድ ሰው ሞተና በሸዋ እንደተለመደው ወንዶች በአንድ ተርታ፣ ሴቶች በሌላ ተርታ ቆመው በሚያረግዱበት ጊዜ፣ ብርቄም ከእነዚያ መካከል ነበር፡፡ አንድ ድንክ የሙሾ ግጥም ለመንገር ፈለገና አጭር በመሆኑ አልተሳካለትም፡፡ አንዱን ረዥም ሰውዬ፣ ‹እባክህ እንኮኮ በለኝ!› ቢለው፣ ‹ወግድ ወዲያ፣ ድንክ የምሸከመው ምን በወጣኝ ነው› ብሎ አሻፈረኝ አለው፡፡ የዚህን ጊዜ ልመደው ጨው አውጥቶ እንካ ይህን ጨው እሰጥሃለሁና ተሸከመኝ አለው፡፡ ሰውዬውም ‹ልመደው ከሰጠኸኝማ ምን ቆርጦኝ ና!› ብሎ ተሸከመው፡፡ ከአርጋጆቹ ተቀላቀሉና ድንኩ እንዲህ ሲል ለአልቃሹ ግጥም ሰጠ፡፡
      ትናንትና ማታ- ዛሬ ጠዋት በ‹ልሜ፣ 
       ንጉሥ አገኙኝ፣
            ‹ልጆች በረቱ ወይ- አገር ተስማማ ወይ፣
             ደሀ ተፅናና ወይ- ብርቄ መነነ ወይ፣›
      ብለው ጠየቁኝ፤
                   እኔም በበኩሌ፣ 
                       ‹ልጆች በርትተዋል፣
                       አገርም ተስማምቷል፣
                       ደሀው አልተፅናናም፤
                      ብርቄም አልመነነም
        ብዬ ብነግራቸው፣
      እየፈተፈቱ፣ ያጎረሱበቱ- እርግፍ ጣታቸው፡፡
ብርቄ ይህን ከሰማ በኋላ ብዙ አልዋለም፤ አላደረም፤ ትችቱ፣ ነቀፌታው ነፍሱ ድረስ ዘለቀ፡፡ ጨርቁን ጠቅልሎ  ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም መንኖ ገባ፡፡
ያ ድንክ ከያኒ ስሙ አልተገለፀም፡፡ የተናገረው ግጥም ግን ለውጥ አምጥቷል፡፡ ሀቅ ነበረው፡፡ ተራ ዘለፋ፣ ተራ የስድብ ውርጅብኝ አልነበረም፡፡ ማስተባበያ ለመስጠት የሚያስችል አልነበረም፡፡ ይህ ገጣሚ፣ ቁመቱ በማጠሩ የአልቃሾቹን ጆሮ መስረቅ እንደማይችል ታውቆታል፡፡ አልቃሾቹ፣ ስለሟቹ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በዙሪያቸው የተፈፀመ በደል እና ገድል ማነሳሳት ይጠበቅባቸዋልና፣ የዚህን ድንክ ግጥም አልቀበልም አላሉም፡፡ ግጥሙ ስም የማጥፋት ዘመቻ መስሎ የታየው ሌላ ሰው ካለ በግጥም የፊተኛውን ሃሳብ እንደሚያጣጥልበት ያውቃሉ፡፡ብርቄን ለመተቸት ሕዝባዊው ገጣሚ፣‹ምን አገባኝ› አላለም፤ ‹ምኔ ተነካና› አላለም፤ ‹ከዚህ ሁሉ ሕዝብ እኔ በልጬ ነው ወይ፤ ማን ወከለኝ› አላለም፤ ‹ቁመቴ አጥሯል፤  ድምጼም አይሰማም› ብሎ የልቡን ፈቃድ ከመከተል አልቦዘነም፡፡
ያቺ ግጥም የምትነገርበት ትክክለኛ ጊዜ እና ቦታ፣ እዚያው ስፍራ መሆኑ ታውቆታል፡፡ሕዝቡ አለ – ታዛቢ፤ታዳሚ፤ ገምጋሚ፡፡ የሆነውን እና የተባለውን ጠንቅቆ የሚያውቅ፡፡ተተቺው ብርቄም አለ፡፡ ተገኝቷል ለቀብር፡፡ ስለሆነም፣ ያ ድንክ ሰው፣  ዋጋ ከፍሎ፣ በረዥም ሰው ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ፣ እውነቱን ማውጣት ነበረበት፡፡ አወጣው፡፡ ለውጥም አመጣ፡፡
ሕዝባዊ ገጣሚ ሃሳቡን ከሚያስተላልፍባቸው ቦታዎች መካከል፣ ሠርግ ላይ፣ ቀብር ላይና ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለይ ቀብር ላይ፣ በአልቃሾች አማካይነት የሙዋቹ ማንነት በተመጠኑ ቃላት ይገለጻሉ፤ የሙዋቹ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ስለሚያስከትለው መዘዝና ስለሚያመጣው ጉድለት ይተነትናል፡፡
 (ያልተቀበልናቸው ከሚለው መጽሐፌ የተቀነጨበ)
Filed in: Amharic