>

"መሀል አትስፈር...!!!" ብሎ ነገር  (ኤፍሬም እንዳለ)   

“መሀል አትስፈር…!!!” ብሎ ነገር

ኤፍሬም እንዳለ 

ወይ ‘ባርክ፣’ ወይ ‘ኮንን’…‘ሚድል ግራውንድ’ ብሎ እንደ ኳስ ዳኛ መሀል ላይ ቆሞ ፊሽካ መንፋት የለም!!!
 
         “–ስሙኝማ… እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ልንጠቀምባቸው ከምንችለው በላይ ሀኪሞች፣ ኢንጂነሮች፣ የአይ.ቲ. ባለሙያዎች ምናምን ቢኖሩን…አለ አይደል…እጆቻቸውን ስመው የሚቀበሏቸው ሀገራት ይኖራሉ፡፡ ግንማ…ልንጠቀምባቸው ከምንችለው በላይ ፖለቲከኞች ሲኖሩንስ? በአክቲቪስቶቻችንም አካባቢ ተረፈ ምርት ነገር ሲኖርስ?! አሀ…ችግራችንን እኛው እናውቃለና!–”
—‘
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ስማ፣ ምን ይመስልሀል?”
“ምኑ?”
“የሀገራችን ሁኔታ ምን ይመስልሀል?”
“እ…ምን መሰለህ፣ ቁርጥ ያለ መልስ ለመስጠት ትንሽ ግራ ያጋቡኝ ነገሮች አሉ…”
“ምኑ ነው ግራ የሚያጋባህ?”
እንዲሁ… “ምኑ ነው ግራ የሚያጋባህ!” ብሎ ነው የሚጀምርላችሁ፡፡ ጥያቄ እንኳን አይደለም:: እንደውም ወደ ክስነቱ ነው የሚያደላው፡፡ “አንተ ማነህና ነው!” አይነት ነገር ነው፡፡ ወላ ‘ግራ መጋባት’፣ ‘ቀኝ መጋባት’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር የለም፡፡ አሀ…የሆነ አቋም መያዝ አለባችኋ! አቋም መያዝ ‘የምርጫ’ ጉዳይ ሳይሆን ‘የግዴታ’ ጉዳይ የሆነበት ዘመን ላይ ነና! ወይ ‘ባርክ፣’ ወይ ‘ኮንን’…‘ሚድል ግራውንድ’ ብሎ እንደ ኳስ ዳኛ መሀል ላይ ቆሞ ፊሽካ መንፋት የለም፣ አይነት ነገር ነው፡፡ አለ አይደል…ወይ ማን ሲቲ፣ ወይ ሊቨርፑል… አራት ነጥብ፡፡ “አጉዌሮም ጥሩ ድሪብል ያደርጋል፣ መሀመድ ሳላም ፍጥነት አለው” ምናምን ብሎ ነገር አይሠራም፡፡
እናላችሁ… አለ አይደል… ነገሮችን ጠለቅ ብሎ ማሰብ ካልተፈቀደላችሁ እንድታስቡ አልተፈቀደላችሁም ማለት ነው፡፡ አእምሯችሁን እንድታሠሩ አይፈቀድላችሁም፣ በሁለት እግሮቻችሁ እንድትቆሙ አይፈቀድላችሁም ማለት ነው፡፡ ወይ “በዚህማ አልደራደርም፣” ማለት ወይም “ሁሉም ነገር ፈርሶ እንደገና መሠራት አለበት” ማለት አለባችሁ፡፡ “እስቲ ከመወሰኔ በፊት መጀመሪያ እውቀቱ ይኑረኝ” ብሎ ነገር የለም፡፡ “እስቲ ከሆታው ባለፈ የተሟላ መረጃ ይኑረኝ” ማለት ተቀባይነት የለውም፡፡
ልክ እንዳለፈው ዘመን ፖለቲካ… “ለመሀል ሰፋሪዎች ቦታ የለንም…” አይነት ነገር ነው:: ‘መሀል ሰፋሪ’ ማለት ደግሞ ‘ቡድን’ የሌለው ነው፡፡ እኔ የምለው… መአት ቀሽም የፖለቲካም ሆነ የምንም ቡድን በበዘባት ‘ሚናህን ለይ’ ብሎ ነገር አለ እንዴ?!
“እዛ ማዶ የቆመችውን አየሀት አይደል፣ ምን ይመስልሀል?”
“ምኑ ነው ምን የሚመስለኝ?”
“አቦ አትፈላሰፍብኝ፣ ቆንጆ ነች ወይስ ቆንጆ አይደለችም?”
እንዲህ ብሎ ነው የሚጀመረው፡፡ ወይ “ቆንጆ ነች፣” ወይ “ቆንጆ አይደለችም” ብሎ ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት ነው እንጂ “መጀመሪያ በሚገባ መቼ አየኋትና!” ብሎ ነገር የለም፡፡ ወይም “መጀመሪያ ቁንጅና በሚለው መስፈርት ላይ እኔና አንተ መቼ ተስማማንና…”  ብሎ ጨዋታ የለም፡፡ ወይ ‘ጥቁር’ ነው፣ ወይ ‘ነጭ’ ነው፡፡
በዛኛው ዘመን አንዲት ዘፈን ቢጤ ነበረች…
ተው ተጠንቀቅ ዋ፣ ዋ ተው ስማ
መሀል ሜዳ ላይ ቆመህ ተው አታቅማማ
ተው አትወላውል ይቅር ተመከር
ከዚህም ከዚያም እያምታታህ መሀል አትስፈር፣

የምትል የ‘አብዮት’ ዘፈን፡፡

 ወይ አብዮተኛ ነህ፣ ወይ ጸረ-አብዮተኛ ነህ፡፡ እናላችሁ…አሁን ዳር፣ ዳር እያለች ያለች ነገር አለች፡፡ አለ አይደል… ወይ ‘ለውጥ ደጋፊ’ ነህ፣ አለበለዛ ‘ለውጥ አደናቃፊ’ ነህ:: ነገሮች እንዲህ እንደ ጥቁርና ነጭ ግልጽ መስመር ኖሮ፣ በቀላሉ የሚለይ ቢሆን እንዴት መልካም በሆነ ነበር:: እናላችሁ… ለሁለቱ ወገኖች “በምክንያቶቹ ላይ የእናንተ ሀሳብ ጥሩ ነው፣ በመፍትሄ በኩል ደግሞ የእነሱ አማራጭ ይሻላል” አይነት ነገር ማለት… “ሚዛኑን የጠበቀ አስተያየት ሰጥተሀል” የሚያስብል ሳይሆን “ከዚህም ከዚያም እያምታታህ መሀል አትስፈር” የሚያሰኝ ነው፡፡ አሀ… በዘንድሮ ሁኔታችን ‘ሚዛን መጠበቅ” ምናምን ብሎ ነገር ለይቅርታ ቦርድ እንኳን የማያበቃ ሀጢአት ይሆናላ!
“ጠይም ነች፣ ጠይም አሳ መሳይ…” ምናምን ለሚላችሁ ሰው “እኔ ጠይም ሴት አልወድም…” ብትሉት መልሱ ምን መሰላችሁ…“ጠይም ሴት አልወድም የምትለው…ፈረንጅ መሆንህ ነው!” ይሆናል፡፡ መከራ ነው እኮ! በቃ… “አልወድም” ማለት “አልወድም” ማለት ነው፡፡ የምን ‘የሀገር ክህደት’ ምናምን ማስመሰል ነው፡፡
ለምሳሌ ጥንዶቹ ይጋጫሉ፡፡ እሱዬውም ባለቤቱን ‘ለአመል ያህል’ ነካ ያደርጋታል፡፡ በአጉሊ መነጽር ካልሆነ የማትታይ ጭረት ቢጤ ጉንጯ አካባቢ ትታያለች፡፡ እናላችሁ…እውቀት ነካ ያደረገው አስተያየት  ከሆነ…አለ አይደል… “የፈለገ አለመግባባት ይሁን ጫፏን ልትነካት መብት የለህም…” ምናምን ብሎ የግሳጼ አይነት ነገር ተናግሮ ነገሮችን ለማርገብ ይሞክራል፡፡
ደግሞላችሁ… ከእውቀት ነጻ ሆነ አስተያየት ከሆነ ምን ይባላል መሰላችሁ… “አንቺ ምን አስተርፎሻል…ዓይንሽን ሊያጠፋው እግዜሐር አይደል እንዴ ያተረፈሽ! ለምን እድሜ ልክ አይቀፈደዳትም፣ ይሄንማ ዝም ብለሽ ማየት የለብሽም!” አይነት የዘንድሮ ‘አክቲቪስትነት’ የሚመስል የ“በለው በለውና አሳጣው መድረሻ…” ነገር ይላል፡፡ “አሁን አንቺን የመሰልሽ ልጅ እንዲህ አይነት ሰው ላይ ይጣልሽ!” የሚል አይነት ‘ሲ ምናምን’ የነገር ፈንጂ ይወረውራል…ልክ ከተጋቡ ገና ሦስተኛ ወራቸው ይመስል:: ኮሚክ እኮ ነው… የዛሬ አራት ዓመት እኮ የጋብቻቸውን የብር ኢዮቤልዩ ድግስ ግጥም አድርጎ ጠስቋል! እናላችሁ…አለ አይደል… አሳዛኙ ነገር እዚህኛው ሰፈር ያለነው ሰዎች በርከት ማለታችን ነው፡፡
“በልብህ ምን እንደምታስብ የማናውቅ መሰለህ!” አይነት ነገር አለላችሁ፡፡ ይሄ “ወይ ከእኛ ጋር ነህ፣ አለበለዚያ ከእነሱ ጋር ነህ” አይነት ፖለቲካ እኮ መከራ ነው፡፡ በግልጽ የምትናገሩትን በሚገባ መረዳት ሳይችል በውስጣችሁ “ተቀብሯል” የሚለውን ነገር ሊነግራችሁ ይሞክራል፡፡ ለነገሩማ…በአንድ በኩል እሰየው ነው፡፡ ከፍተኛ የልብ ሀኪሞች እጥረት ባለባት ሀገር፣ በሌላው ሰው ልብ ውስጥ የተደበቀውን የምናውቅ መኖራችን እሰየው ነው፡፡
ስሙኝማ… እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ልንጠቀምባቸው ከምንችለው በላይ ሀኪሞች፣ ኢንጂነሮች፣ የአይ.ቲ. ባለሙያዎች ምናምን ቢኖሩን…አለ አይደል…እጆቻቸውን ስመው የሚቀበሏቸው ሀገራት ይኖራሉ፡፡ ግንማ…ልንጠቀምባቸው ከምንችለው በላይ ፖለቲከኞች ሲኖሩንስ? በአክቲቪስቶቻችንም አካባቢ ተረፈ ምርት ነገር ሲኖርስ! አሀ…ችግራችንን እኛው እናውቃለና!
እኔ የምለው…አንዳንዴ እኮ ግራ ግብት ይላል:: እውቀት ይሄን ያህል ሞልቶ ፈሶብናል እንዴ! አገሩ ሁሉ እኮ አዋቂ በአዋቂ ሆነሳ! ሚዲያው እኮ የእውቀት ብዛት እንደ ሱናሚ በሚያንገላታቸው   እንግዶች ተጨናነቀ እኮ! አሀ…እኛና ጠቅላላ ዓለም በ‘ፌክ ኒውስ’ አበሳውን እያየ፣ እኛ በተጨማሪ በ‘ፌክ አዋቂዎች’ አበሳችንን እያየን ነው እኮ! ልክ ነዋ… በተለይ በፖለቲካው የምንሰማቸው ‘ትንተናዎች’ አይደለም ማሳቅ ‘ጨጓራም የሚልጡ’ ናቸው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ነገር በተተነፈሰ ቁጥር “ኒኦ ሊበራል፣” “ኋላቀር” ምናምን እየተባለ ዝም ጭጭ ለማሰኘት መሞከር ቀሺም ነበር፡፡ አሁንም በእንደዛ አይነት አስተሳሰብ መሄድ መሞከሩ መልካም አይሆንም፡፡ አዝማሚያው አልፎ፣ አልፎ ከአዝማሚያነትም እያለፈ ስለመሰለን ነው፡፡ እንዲሁም በቋፍ ላይ ነን፣ እንደገና ሀሳብ ለመስጠት በተሞከረ ቁጥር ማሳቀቂያ ቅጽል መደርደር ከቀጠልን መልካም አይሆነም፡፡ በገመዱ ጫፍ የተንጠለጠልንባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ሰው ሲለፋ ወጥቶ ወርዶ
ከደስታ ነፍሱን ጋርዶ
ጥሮ ግሮ ሲበረታ
ያለብሱታል የሀሜት ኩታ!!!

የምትል የቀደመች የዘፈን ስንኝ ነበረች፡፡
እና በፖለቲካውም ‘የሀሜት ኩታ’ ማልበስ እስከ ዛሬ የትም አላደረሰንም፣ ወደፊትም የትም አያደርሰንም::
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Filed in: Amharic