>

ያ'ባራሪው ያለህ.... (መስከረም አበራ)

ያ’ባራሪው ያለህ….
መስከረም አበራ
አንዳንዴ ከእውነቱ ይልቅ ህልማችን ሃቅ ቢሆን የሚያሰኙኝ አጋጣሚዎች አሉ። ሰዎችን በሩቁ አይተን፣ አንደበታቸውን ተንተርሰን፣ “ነኝ!” የሚሉትን አምነን በትልቁ እንሾማቸዋለን። ይህን ያወቁ እነሱ እምነታችን የማይሰበር፣ያልሆኑትን አድርጎ የሾማቸው ቅን ልቦናችን የማያገናዝብ የዘላለም ተጎታቻቸው ይመስላቸዋል። ይሄኔ እውነተኛ ማንነታቸውን ለመግለፅ በሞኝነታችን ላይ እርግጠኛ ይሆናሉና ማስመሰል ተሽቀንጥሮ መሆን ይመጣል ።የሆኑት ሲገለፅ ሳይሆኑ ያደረግናቸው ይናፍቀናል! “ህልም እና እውን በተቀያየሩ” የምለው እንዲህ ያለው ሲገጥመኝ ነው-ያመንኩትን እንዳመንኩ፣ያከበርኩትን እንዳከበርኩ ለመኖር!ያመንነው በእምነታችን ላይ ባይሳለቅ አምባገነኖች ምን ይውጣቸው ነበር?
የሃገራችንን ፖለቲካ በእጅጉ የጎዳው የፖለቲከኞቻችን ባለ ሁለት ነፍስ ማንነት ነው – አንዱ ብዙ ጊዜ ስናየው የኖርነው ህዝባዊ ወገንተኝነት ሌላው ድንገት የሚገለጠው ከሃዲነት። ድንገት የሚመጣው ከሃዲነታቸው የሃገራችንን ፖለቲካ ከዲሞክራሲ በተቃራኒ አቅጣጫ የኋሊት አስሩጦ መቀመቅ የሚከተው ነው። ከዲሞክራሲ ያጣላን፣ ከድህነት ያጋባን የክፉ ገዥዎቻችን ክፋት ብቻ አይደለም -በብላሽ የሚሸጡን የኔ ያልናቸው መቅጠፍጠፍ ጭምር እንጅ!
ኢሳትን የሚያምሰው ይሄው የእምነት ክህደት ስንክሳር ነው! ያልደላው ሃገርቤት ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚሊኒየም አዳራሽ ለኢሳት ያዋጣውን ገንዘብ ግዝፈት ብቻ የሰማ ኢሳት በገንዘብ እጥረት ሰራተኛ ቀነሰ ቢሉት እንዴት በገረመው?ይህን ምክንያት ብለው የሚነግሩን እነሱን ያመነው ተላላው ልባችን ምንም ብንለው ይቀበላል በሚል ነው። ሆኖም ሰው መሆናችን መረሳት የለበትም፤ ቅን ነን አማኝ ነን ማለት ሞኝ ነን ማለት አይደለም! ቅንነትን ሞኝነት ብሎ ሚያስብ ብቻ ነው ሞኝ! ሞኝ የምንሆነው ከእንግዲህ እነሱን በቀድሞ ቅንነታችን ካመንን ነው!
የኢሳት ስልጣናት እና አለቆች እንዳሰቡት እነሱ ያሉንን ሁሉ የምንቀበል ሞኝ ሆነን ኢሳት ሰራተኛ የሚያስቀንስ የገንዘብ እጥረት ገጠመው እንበል። ይህ የገንዘብ እጥረት እራሱ ከየት መጣ ብንል ብንጠይቅ የእነሱው የንጉስ ባለሟልነት የወለደው አፈና በኢሳት ላይ በማንዣበቡ፣ ቃና ሁኔታው ኢቲቪን ልምሰል በማለቱ የቀድሞ እምነታችን መትነን ጀምሮ ነው። እንጅ እኛ አንደ እነሱ ትግል ተገባደደ ደህና ቀን መጣ ብለን የኢሳት አስፈላጊነት አልታይ ብሎን ገንዘባችን ቤት ይደር ተብሎ አይደለም። ስናምን ዝም አልን ማለት ገልቱ ነን ማለት አይደለም!ከዚህ ወዲያ የሚኖረው ኢሳት ወደ ምንናፍቀው የዲሞክራሲ ጉዞ የሚወስደን የአብሮነታችን ማህተም ሳይሆን የመካካዳችን ምልክት መሆኑን ለአባራሪ ተባራሪው ለእኛም ለታዛቢዎች ግልፅ ነው።
የኢሳት ሰራተኞችን የማባረሩ ነገር ሰው ማባረር ብቻ ሆኖ አይታየኝም- የሃሳብ ብዝሃነትን ማሳደድ፣ መተማመንን አርቆ መቅበር፣ፖለቲካችንን እንደ አደረ ገንፎ መስህብ አልቦ ማድረግ ነው።ይህ ከነቀፍናቸው አምባገነኖች የምንወርሰው፣በአፈናቸው ካንቋሸሽናቸው የትናንት ረጋጮች የምንጋራው ግን ደግም ግብዝነታችን ለጊዜው የሚደብቀው እውነተኛው ማንነታችን ነው-ዲሞክራሲን ማባረር! አብዮታችን ትግላችን አባራሪን እና ተባራሪን ያቀያይራል እንጅ ማባረር መባረሩን አላስቀረው።
#ያባራሪው_ያለህ_የት_ታደርሰናለህ!
Filed in: Amharic