>
9:52 pm - Sunday August 7, 2022

ቀይ መስመር!!! በእስክንድር ነጋ ትግል ወደ ስልጣን የመጣው ዶ/ር አብይ የወያኔን ስህተት እየደገመ ነው!! (ስዩም ተሾመ)

ቀይ መስመር!!!
በእስክንድር_ነጋ ትግል ወደ ስልጣን የመጣው ዶ/ር አብይ የወያኔን ስህተት እየደገመ ነው!!
ስዩም ተሾመ
የወያኔ ጭቆና ቀንበር እንዳልነበር ሆኖ ከመውደቁ በፊት፣ ያኔ… በፈረጠመ ጡንቻው አለሁ ባይን ሁሉ በሚደመስስበት፣ የአምባገነኖች እብሪትና ንቀት ጣሪያ በነካበት፣ መለስ ዜናዊ እንደ ጣዖት በሚመለክበት፣ እንደ አምላክ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ላይ የመወሰን ስልጣን በነበረው ግዜ… ከሺህ ጦር ሰራዊት በላይ አንድ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ይፈራ ነበር፡፡
 በወቅቱ ብዙዎች የወያኔን ፍርሃት ጠንቅቀው አያውቁትም ነበር፡፡ ብዙዎች ወያኔ እስክንድርን በሰበብ አስባቡ እየከሰሰ ሲያስረው “ወያኔ ፈርቶ ነው” ከማለት ይልቅ “እስክንድር ከአጉል ሰዎች ተነካክቶ ነው” ብለው መጠርጠር ይመርጡ ነበር፡፡ ስለዚህ እነ እስክንድር በእስር ሲንገላቱ “የሆነ ነገር አጥፍተው ሊሆን ይችላል” እያሉ ቢጠረጥሩም ውሎ-አድሮ ከእስክንድር ጥፋት ይልቅ የወያኔ ፍርሃት ጎልቶ ወጣ፡፡ ይህን ግዜ “benefit of doubt” ከእስክንድር ይልቅ ለወያኔዎች የሰጡ በሙሉ የህሊና በፀፀትና ቁጭት ውስጥ ገቡ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፡፡
ከወያኔ ይልቅ እስክንድርን በመጠርጠሬ ከፍተኛ የህሊና ፀፀትና ቁጭት ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባሁ ሲሆን በመጨረሻ እነ እስክንድር ከእስር እስካልተፈቱ ድረስ ለራሴ ፈፅሞ ይቅርታ እንደማላደርግለት ወሰንኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ስለ ዴሞክራሲ እና ፍትህ ያለ ማቋረጥ መጮህ ጀመርኩ፡፡ ራሴን ከህሊና ዕዳ ለማዳን ስለ የወያኔን ፈሪነት፣ የእነ እስክንድርን ጀግንነት ያለመታከት ፃፍኩ፡፡ እነ እስክንድር ከእስር በተፈቱ ማግስት ግን እኔ ታሰርኩ፡፡ ከእስር ቤት ስወጣ ደግሞ እነ እስክንድር  እቅፍ አበባ ይዘው ጠበቁኝ፡፡ ወያኔ በግፍ ያሰራቸው ሁሉ ሲፈቱ ህሊናዬ ከፀፀትና ቁጭት ነፃ ሆነ፡፡
ባለፉት አምስት አመታት ካለፍኩበት ሕይወት የተማርኩት ዋና ነገር በፅሁፍና የንግግር ቃላት ከሚሟገት ጋዜጠኛ ይልቅ በስልጣን ላይ ላለ መንግስት “benefit of doubt” መስጠት ፍፁም ስህተት መሆኑን ነው፡፡ ካለፈው ስህተቱ የማይማር እድሜ ልኩን ሲፀፀትና ሲቆጭ ይኖራል፡፡ እስክንድር ነጋ ግዴታውን ሳይወጣ ቀርቶ የሌሎችን መብት የጣሰ እለት “በህግ አግባብ ሊጠየቅ ይገባል” ብለው ከሚሟገቱት ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ የማንንም መብት ሲነካ አላየሁም፡፡ ከዚያ ይልቅ በእስክንድር ትግል ወደ ስልጣን የመጣው የዶ/ር አብይ አመራር በእሱ ላይ የመብት ጥሰት እየፈፀመ ነው፡፡
ስንት ነገር የሆንኩለት፣ ብዙ ነገር የጠበቅኩበት የዶ/ር አብይ አመራር ወያኔ የፈፀመውን ስህተት ዳግም እየፈፀመ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የእስክንድርን ብሶትና አቤቱታ ችላ ብዬ የዶ/ር አብይ አመራር የሰጠውን ማስተባበያ ይዤ መውጣት መርጬያለሁ፡፡ የባልደራስ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ በመንግስት ሃይሎች ጣልቃ-ገብነት እና ጫና ሲቋረጥ ከእስክንድር ይልቅ አንድ የመንግስት ሃላፊ የነገረኝን ተቀብዬ ፌስቡክ ላይ ለጥፌያለሁ፡፡
ዛሬ እነ እስክንድር ነጋ በኢትዮጵያ ሆቴል ሊያካሂዱት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በተመሣሣይ መንገድ መስተጏጎሉን ስሰማ ባለፈው “የባልደራስ ምክር ቤት በቤተ_መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መግለጫ መስጠት ይችላል” ያለኝ የመንግስት ሃላፊ ጋር ደወኩ፡፡እሱም ጋዜጣዊ መግለጫው ለምን እንደተከለከለ እንደማያውቅ ከነገረኝ በኋላ ነገ ጉዳዩን አጣርቶ እንደሚነግረኝ ቃል ገባልኝ፡፡ እኔም በቃሉ ከፀናው እስክንድር ይልቅ ቃልና ምግባሩ ለተምታታበት መንግስት የአንድ_ቀን “benefit of doubt” መስጠት መረጥኩኝ፡፡
ቸር ያሰማን!!! 
Filed in: Amharic