>

የሰባት አመታቱ ኢዶች እና የዘንድሮው የምስራች (ሳዲቅ መሀመድ)

የሰባት አመታቱ ኢዶች እና የዘንድሮው የምስራች
ሳዲቅ መሀመድ
ከሰባት አመታት በፊት መንግስት በሐይማኖት ውስጥ ያደረገው ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው።ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች መንግስት እጁን ከሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ማውጣት አለበት ሲሉ ቁጣቸውን ገለጹ።መንግስት ህገመንግስቱን ይተገብር ዘንድ 17 የኮሚቴ አባላት ያሉትን የመፍትሔ አፈላላጊ ህዝበ ሙስሊሙ መረጠ።
የህዝብን ውክልና የተቀበለው ኮሚቴ አቤቱታውን ለመንግስት አሰማ።ሽማግሌም በመሆን መንግስትና ህዝብን ለማቀራረብ ሞከረ።የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጥረቱ ሁላ ‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ› ሆነ።በመንግስት ጥርስ ተነከሰበት።ከኮሚቴው መካከል ተሰሚነት ያላቸውና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑት ተመርጠው ታሰሩና ማእከላዊ የምርመራ ማእከል እንዲገቡ ተድረገ።
ሐምሌ 2004 ወርሃ ረመዳን የተበሰረበት የተስፋ ወር ቢሆንም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ወኪሎቼ ናችሁ ያላቸው ምርጥ ልጆቹ የታሰሩበት ወር በመሆኑ በኢትዮጵያዉያን ሙስሊሙች የታሪክ ሒደት ውስጥ መንግስት በህዝብ ላይ አሳቃቂ ወንጀልን የፈጸመበት ግዜ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል። ሰላምን ያሉ፣እናስታርቅ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በጾመኛ እቅማቸው ገላቸው ሊጋፈጠው የማይችለው ፈተና «የሰው ልጆች ቄራ» ተብሎ በሚነገርለት ማእከላዊ የምርመራ ማእከል ውስጥ ገጠማቸው።ገላቸው ቢጎዳም መንፈሳቸው በለውጥ እሴት የተሞላ ነበርና ሊሰበር አልቻለም።መንፈሳቸውም ሊሰበር ባለመቻሉ በቴሌቭዥን መስኮት በነርሱ ላይ ጅሃዳዊ ሐረካት የተሰኘ የሐሰት ዶክመንታሪ ቀረበባቸው።በካንጋሮ ፍርድ ቤት ቀርበው እስከ 22 እመታት የሚደርስ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው።
በ2004ቱ ሐምሌ በወርሃ ሐምሌ የጀመረው መንግስታዊ ጥቃት አሳቃቂ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የተስፋ ብርሃንን የሰነቀ አገራዊ ንቅናቄ ተወለደ። «ድምጻችን ይሰማ» የሚባል። የድምጻችን ይሰማ ንቅናቄ የሰላም እሴትን ሰንቆ ጨቋኞችን ተጋፈጠ።ጨቋኞች የመጨቆኛ ክንዳቸው እስኪዝል ድረስ ታገላቸው።ሰላማዊ ትግሉ ተፋፍሞና ከሌሎች አገራዊ ትግሎች ጋር ተቀላቅሎ ዛሬ አገሪቷ ውስጥ የታየው ለውጥ መጣ።በዚህ ሒደት ውስጥ ብዙዎች ተሰደዋል፣ብዙዎች አካለ ስንኩል ሆነዋል፣ብዙዎች ሞተዋል፣ብዙዎች ተገርፈዋል፣ብዙ ቤተሰቦች ተለያይተዋል። ያ ሁሉ አለፈ። ከ2004-እስከ 2010 ድረስ የነበሩት ስድስት ረመዳኖች የሐዘን ደመናን ያዘሉ ቢሆንም በ2011 ረመዳን ላይ የተስፋ ዝናብ ዘነበ።
√ ታሪካዊው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢፍጣር
ኤምባሲዎች ያገራቸው ህዝብ መኩሪያ ናቸው።ኤምባሲዎች ካገር ውጪ ያሉ ዜጎችና ተወላጆች የአገርን ሽታ የሚያሸቱባቸው የራስ ቀዬዎች ናቸው።ዋሽንግተን ዲሲ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለሰባት አመታት ለዚህ ሚና አልታደለም ነበር።አገር ውስጥ ያለው ጭቆና ይቆም ዘንድ ዜጎች የቅዋሜ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መድረክ ሆኖ ቆይቷል።ኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ጉዳይን ከማስፈጸም ውጪ የሚገቡ ሁሉ ከአንባገነናዉያን ጋር ተባበሩ በሚል ይፈረጁ ስለነበር ኤምባሲ መግባት የሚያሸማቅቅ ነበር።
በዋሽንግተን ዲሲና በአካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የኢትዮጵያ መንግስት በሐማኖት ተቋማቸው ውስጥ ያደረገውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በአሜሪካው ቤተ-መንግስት ፊት ለፊት
ህዳር 11/2004 የተቃዉሞ ሰልፍ ካደረጉ በሗላ ዋሽንግትን ካለው ኤምባሲ ጋር ተቆራርጠዋል። ብዙዎች ወደ ኤምባሲው የሚያቀኑት ለተቃውሞ ሰለፍ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ኢትዮጵያ ውስጥ በ2010 የሰፈነው የለውጥ ድባብ ወደ አሜሪካ ዘለቀ።በጠ/ሚ ሐይለማሪያም ደሳለኝ ምትክ ዶ/ር አብይ መምጣታቸው አገርም ይሁን ዲያስፖራ ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተስፋን የሰነቀ ታላቅ ብስራት ሆነ። በወርሃ ሐምሌ 2010 ኢትዮጵያዉያን ዶ/ር አብይን ለመቀበል በሚደረገው ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ለመሆን ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ይገቡ ጀመር። ኤምባሲው በሐምሌ 19/2010 የማህበረሰብ ተወካዮችና የለውጥ አቀንቃኞችን ምስጢራዊ እንግዳ አለኝ ብሎ ጠራ።በኤምባሲውና አሜሪካ ባሉ ኢትዮጵያን መካከል ተገንብቶ የነበረው ሐሳባዊ ግንብ ያኔ ፈረሰ። በር ላይ ተቃዉሞ ሲያሰማ የነበረን ግለሰብ ዶ/ር አብይ አቅፈው ወደ አዳራሹ ገቡ።
ኤምባሲው ከኢትዮጵያዉያን አሜሪካውያንና ከኢትዮጵያን ጋር የነበረውን የሻከረ ግንኙነት አደሰ።በዚሁ በታደሰ ግንኙነት የተጓዙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቋማዊ መሻከርን ለማደስ በአምባሳደር ፍጹም አረጋ አሰባሳቢነት ለኢፍጣር ተሰባሰቡ።እኛ ፈርስት ሒጅራህ ፋውንዴሽን፣በድር ኢትዮጵያና ሰላም ፋውንዴሽን ብንባልም በመንፈሳዊና በምድራዊ ህይወት የምንለያይ አይደለንም ሲሉ የግንቦት 19/2011 የኤምባሲውን የጋራ ኢፍጣር ተቋደሱ። ኢፍጣሩ ታሪካዊ ነበር
√ የረመዳን ዋዜማው እርቀ-ሰላም
ሚያዝያ 23/2011 ታሪካዊ ቀን ናት።ለሰባት ድፍን አመታት ተራርቀው የነበሩ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የተቀራረቡበት፣ልዩነትን አጥብቦ በጋራ ለመስራት የተስማሙበት፣ልዩነት ውበት መሆኑን የተማመመኑበት፣‹ለማሸነፍ መሽነፍ› የሚለውን የለውጥ ብሂል ተግባር ላይ ያዋሉበት ቀን ነበር ቀኑ።
የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ለዘጠኝ ወራት የሰራውን ጥናት ለተመረጡ 300 ሙስሊም ባለድርሻ አካላት አቀረበ።ጠ/ሚ አብይ አህመድ በስብሰባው ላይ በመገኘት የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ብሶት እልባት ያገኝ ዘንድ የመሰረት ድንጋይ ጣሉ።የሰላም ሚኒስቴሯ ወ/ሮ ሙፈሪኻት ካሚል ከስምምመት ምህዋር ላይ አፈንጋጭ የሆኑን ወንዶችን ለመገሰጽ የብሶት እንባቸውን አነቡ። ተራርቀው የነበሩ ተቃቀፉ።እርቀ-ሰላም ወረደ።
ከብዙ መስዋእትነት በሗላ ውጤት ተገኘ።ጨቋኞችን የሚያሸማቅቅ ታሪክ በሚያዚያ 23/2010 ተሰራ። ሰይጣን ተረታ።ይህ ድል እንዲገኝ አቅሙ የቻለውን ሁሉ ያደረገው ‹የድምጻችን ይሰማ› ትውልድ የትግሉን ከፍታ በህይወት ዘመኑ ለመቃኘት በቃ።ለሐያ አመታት በማህበረስብ ውስጥ ንሮ የነበረው ቁጭት ረገበ። ለሰባት አመታት የድምጻችን ይሰማ ትውልድ የከፈለው መስዋእትነት ፈር ያዘ። ደስታው ለየቅል ሆነ።
በእምነት ተቋም ውስጥ የወረደውን እርቀ-ሰላም ለመዘከር በተቀደሰው ወርሓ-ረመዳን እስከ አስር ሺ የሚጠጉ ምእምናን የታደሙበት የጋራ ኢፍጣር ፕሮግራም በታላቁ መላሚየም አዳራሽ ውስጥ በግንቦት 15/2011 ተደረገ። ጠ/ሚ አብይ አህመድ በዚህ የኢፍጣር ፕሮግራም ላይ የክብር እንግዳ ነበሩ።
እርቀ-ሰላም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ የወረደበት ረመዳን ተገባዶ ኢድ ላይ ተደርሷል።
በዚህ የደስታ ወቅትም ትላንትና እና ዛሬን መፈተሹ ግድ ይላል።የትላንትን መሪር ጭቆና ለህዝብ የጋቱ በዳዮች በቁም ሲታሰሩ ተበዳዮች ታሪክ ሰርተዋል።ይህ ቀን እንዲመጣ መስዋእት የሆኑ ሰማእታት ደረጃ በፈጣሪ ዘንድ የላቀ ነው። ክብር በዚህ የሰላማዊ የትግል መስክ ተሰማርተው የዛሬይቱን ቀን በደማቸው፣በእስር ቤት ግርፋት፣በስደት፣በስቃይና በመከራ ለዋጁ ጀግኖች ይሁን።አነዚያ መስዋእት የሆኑ ጀግኖች የዘንድሮ ኢድ የተለየ እንዲሆን አድርገዋል።ኢድ የደስታ ቀን ነው።መደሰቱ ተገቢ ነው።
ኢድ ሙባረክ!
ልብ ያለው ልብ ይበል!
Filed in: Amharic