>
11:52 am - Tuesday May 17, 2022

በቋፍ ያለን ሕዝብ አትነካኩት በተቀደሰው ስፍራ ርኵሰት፤ ኢትዮጵያውያን እናስተውል (ከይኄይስ እውነቱ)

በቋፍ ያለን ሕዝብ አትነካኩት!
በተቀደሰው ስፍራ ርኵሰት፤ ኢትዮጵያውያን እናስተውል

ከይኄይስ እውነቱ

 

ኢትዮጵያውያን በእምነታችን (ክርስትናም ሆነ እስልምና – በጎላው ለመናገር ነው) እና በባህላችን (የእምነቶቻችን አሻራዎች በእጅጉ ዐርፎበታል) ለመነጋገርም እንኳ ባይነኬነት ከሚታወቁ፣ የአስጸያፊነትና አስነዋሪነት ጥግ ተደርገው ከሚታዩ ርኵሰቶች ግንባር ቀደሞቹ ግብረ ሰዶማዊነትና ግብረ ጎሞራነት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችንም ወንጀል ነው፡፡ ሰሞኑን በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎች ራሳቸውን በይፋ ግብረ ሰዶማውያን ነን የሚሉ ባዕዳን ‹‹ሰዎች›› TOTO በሚባል አስጎብኚ ድርጅት አማካይነት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኝት ወደ አገራችን እንደሚገቡ እየተነገረ ነው፡፡ በስም የተጠቀሰው አስጎብኚ ድርጅት ስለዚህ ርኵሰት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አመለካከት እያወቀና ጉዞውን እንዲሠርዝ በግልጽ ተነግሮት እምቢተኛ መሆኑም ተሰምቷል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ በሙስሊምና ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ላይ በተለይ በቀጥታ የተቃጣ ንቀትና ማንአለብኝነት መሆኑን አንባቢ ያስተውል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር የቤተ እምነቶች እና የምእመናኑ ደኅንነት ጉዳይ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ መሆኑን የሚገነዘብ መንግሥት ካለ ይህንን እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በቸልታ ያልፈዋል የሚል ግምት አይኖረኝም፡፡ ይሁን እንጂ ግምቴ ስህተት ሆኖ መንግሥት ለሚገኝበት ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ጊዜያዊ አጀንዳ ማስቀየሪያ አድርገው የሚመለከቱ ጅል ፖለቲከኞች ካሉ መዘዙ የሚያባራ አይመስለኝም፡፡ ባብዛኛው አስተያየቶቼ ላይ ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዐሥርታት (ያለንበትን ጨምሮ) የምትገኝበትን ሁናቴ ዕብደትና ድንቊርና የነገሠበት ዘመን እንደሆነ ደጋግሜ ተናግሬአለሁ፡፡ ይህም ጆሮን ጭው የሚያደርገው የርኵሰት ወሬ የዕብደቱ አንድ መገለጫ ነው፡፡ ያለንበት የፖለቲካ ድንቊርናና ዕብደት ባንድ በኩል፤ የለየለት ድኅነት/ የኑሮ ውድነትና ማኅበራዊ ልሽቀት በሌላ ወገን ወደጠርዝ ገፍቶት የሚገኘውን ምስኪን ሕዝብ መነካካት ላገርም ለወገንም አይጠቅምም፡፡

የተጠቀሱት ርኲሰቶቸ ባንድ ወቅት በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ይፋዊ ገጸ ድር (ኦፊሲዬል ዌብ ሳይት) የከፋ የጤና እክል/በሽታ (perversion) መሆኑ ተገልጾ መጻፉን በዓይኔ በብረቱ አንብቤአለሁ፡፡ አሁን ያ ጽሑፍ ተነሥቷል፡፡ የማኅበራዊ መበስበሱ (social decadence) ጥግ አንዱ መገለጫ የሆነው የምዕራቡ ዓለም ይህንንና ሌሎች ርኵሰቶችን በሰብአዊ መብትነት ሽፋን ሕጋዊ ጥበቃ አድርጎለት ነውሩን ‹‹ክብር›› አድርጎታል፡፡ ራሳቸውን የዓለም የሞራልና ሥነምግባር ደረጃ መዳቢ በማድረግም ይህንን ርኵሰት በዓለም ሁሉ ለመናኘት አጥብቀው እየሠሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በየአገሩም ቅጥረኛ ሠራዊት እንዳላቸውም የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ መንግሥታዊ በሆኑና ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በኤምባሲዎች፣ በቱሪስቶች/አገር ጎብኚዎች ወዘተ. ሽፋን በኅቡእ እንደሚንቀሳቀሱም ይነገራል፡፡ ‹‹የሙሉ ዓለም›› (globalisation) አንዱ ‹‹ትሩፋት›› መሆኑ ነው፡፡

በፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውስ የሚናጡ የአፍሪቃና በአጠቃላይ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ሕዝብ የእንደዚህ ዓይነቱ ርኲሰት ዒላማና ማራገፊያ ነው፡፡ አንዳንዴም በረቀቀ መንገድ ለብድርና ለርጥባን በሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ተጠቃልለው እንደሚቀርቡ አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ የሚያስታውስና የሚያስተውል ካለም በእኛም አገር በወያኔ ትግሬ ዘመን በበብዙኀን መገናኛ ይህንን ነውር ለማለማመድ ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡

ለመሆኑ እነዚህ ከአፍሪቃ ክፍለ ዓለም እንደሚመጡ የተነገረው ‹‹ጎብኚዎች›› የኢትዮጵያን የተቀደሱ ስፍራዎች የመጎብኘት ዓላማ ምንድን ነው? እነዚህ ‹‹ጎብኚዎች›› እንደተባለው አፍሪቃውያን ከሆኑ ራሳቸውን ባያዋርዱ መልካም ነው፡፡ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የኩራትና ክብር ምንጭ የሆነችን አገር ለመፈታተን መሞከር በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ጥቁር ሕዝብ ላይ የተሠነዘረ ጥቃት ተደርጎ እንደሚታይ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ርኲሰት፣ ዕብደትና ድንቊርና ‹‹መብት›› ነው ከተባለ ባሉበት መርከስ፣ ማበድና መደንቆር ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መደፈር የመጣው ኢትዮጵያ ባለቤት አልባ (በቤተመንግሥት/ በቤተመስጂድ/ በቤተክህነት) ሆና ይሆን?

የኢትዮጵያ አምላክ የእኛን የወገኖቹን ተካክሎ መበደል ሳይመለከት (ስለ ‹ምርጦቹ› ብሎ) ሊመጣ ካለው ‹መቅሰፍት› ይታደገን፡፡

Filed in: Amharic