>

የደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ (81ኛ) ፤ የጳውሎስ ኞኞ (27ኛ) የሙት ዓመት መታሰቢያ (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ (81ኛ) ፤ የጳውሎስ ኞኞ (27ኛ) የሙት ዓመት መታሰቢያ
ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል
፩). የደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ 81ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ
በፋሺስት ወራሪ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ድሎችን የተቀዳጁትና ለኢትዮጵያ ነፃነት/ሉዓላዊነት ታላቅ ገድል ፈፅመው መስዋዕት የሆኑት ስመጥሩ አርበኛ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ያረፉት ከዛሬ 81 ዓመታት በፊት (ግንቦት 29 ቀን 1930) ነበር፡፡
ደጃዝማች ኃይለማርያም የፀረ-ፋሺስት ተጋድሏቸውን ያደረጉት በደብረ ብርሃንና አካባቢው ነበር፡፡ በጀግንነታቸውና በጦር አመራር ስልታቸው እጅግ የተደነቁና የተከበሩ አርበኛ ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ኃይለማርያም በጠላት ጦር ላይ ባደረሱት ተደጋጋሚ ጉዳት የፋሺስት ጦር ደጃዝማች ኃይለማርያምን ከዋነኛ ጠላቶቹ መካከል አንዱ አደርጎ እንዲፈርጃቸው ተገዷል፡፡
በደብረ ብርሃንና አካባቢው የነበረው የፋሺስት ጦር ደጃዝማች ኃይለማርያምን መደምሰስ ስላልቻለ በርካታ ወታደርና ትጥቅ ከሌሎች አካባቢዎች ለመውደስ ተገዶ ነበር፡፡
ጀግናው ደጃዝማች ኃይለማርያም ግንቦት 28 ቀን 1930 ዓ.ም ቡልጋ ውስጥ በተደረገ ከባድ ጦርነት ላይ ሞቱ፡፡ የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላም ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በስማቸው ት/ቤት ተገንብቶላቸዋል፡፡ (ይህ ት/ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን የሚያፈራ ት/ቤት ነው፡፡)
አዳማ (ናዝሬት) ከተማ የሚገኝ ሆስፒታልም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥም በስማቸው የተሰየመ መንገድ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ 75ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ ሲከበርም ከሌሎች 25 ታላላቅ አርበኞች ጋር በስማቸው የመታሰቢያ ቴምብር ታትሞላቸዋል፡፡
ለደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ጀብድና ጀግንነት ከተገጠሙ ግጥሞች መካከል …
ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ይኸንን ሶላቶ ነዳው እንደበሬ።
መተኮሱንማ ማንም ይተኩሳል፣
ኃይለማርያም ማሞ አንጀት ይበጥሳል።
ሀይለማሪያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ፈረሱን እንደሰዉ አስታጠቀዉ ሱሬ፡፡
ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
እያላጋው መጣ ነጬን ከነጭ በሬ፡፡
እንስራው ቢሰበር ይተካል ግመሞ፣
ከነሚስቱ ተኳሽ ኃይለማርያም ማሞ፡፡
መቼም ኢትዮጵያ የሞቱላትን ረስታ የገደሏትንና የሚገድሏትን ማክበር ልማዷ በመሆኑ፣ የጀግናው ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ልጅ የሆኑት እማሆይ ዘነበች ኃይለማርያም በአሁኑ ወቅት መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ ይገኛሉ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ፎቷቸው ከታች በአስተያየት መስጫ ሳጥን (Comment Box) ላይ ተቀምጧል፡፡
፪). የጳውሎስ ኞኞ 26ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ
በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሃፌ ተውኔት፣ ሰዓሊ፣ የታሪክ ፀሐፊ … ጳውሎስ ኞኞ ያረፈው ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት (ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም) ነበር፡፡
ከግሪካዊው መርከበኛ ኞኞ እና ከወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ የተወለደውና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበረው ጳውሎስ ኞኞ፣ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ ያለው ቦታ ግንባር ቀደም ነው፡፡ እናቱ ያወጡለት ስም ‹‹አማረ›› የሚል ነበር፡፡
የጳውሎስ ኞኞ ስም ሲነሳ ወደአብዛሃኛው ሰው ዓዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ስራው ነው፡፡ በዘመናዊ ትምህርት አራተኛ ክፍልን ያልተሻገረው ጳውሎስ፣ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል፡፡
በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሰራ ‹‹ጋዜጠኝነትስ እንደጳውሎስ!›› የተባለለት ይህ ሰው፣ በርካታ መፅሐፍትንና ትያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡
ከመጽሐፍቱ መካከል ‹‹የሴቶች አምባ››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ››፣ ‹‹አጤ ቴዎድሮስ››፣ ‹‹አስደናቂ ታሪኮች››፣ ‹‹የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ ከሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች››፣ ‹‹አራዳው ታደሰ››፣ ‹‹የኔዎቹ ገረዶች››፣ የጌታቸው ሚስቶች››፣ ‹‹ቅይጥ››፣ ‹‹ምስቅልቅል››፣ ‹‹እንቆቅልሽ››፣ ‹‹ድብልቅልቅ››፣ ‹‹እውቀት››፣ … ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ለሕትመት ከበቁት ስራዎቹ በተጨማሪ፣ ያልታተሙት ስራዎቹም በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ‹‹የአጤ ዮሐንስ ታሪክ››፣ ‹‹የአዲስ አበባ ታሪክ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ››፣ ‹‹ሰዎቹ››፣ ‹‹የልጅ ኢያሱ ታሪክ›› እና ‹‹አዜብ›› ይጠቀሳሉ፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶች በውስጡ ሰርፀው እንደቀሩ በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ በተለይም ‹‹ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ›› ለሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት የተለየ ትኩረትና ፍቅር እንደነበረው ገልጿል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ ከትዳር አጋሩ ወይዘሮ አዳነች ታደሰ ያፈራውን ልጁን ስሙን ‹‹ሐዋርያው›› ብሎ በመሰየም ለሐዋርያው ጳውሎስ ያለውን ፍቅርና አድናቆት ገልጿል፡፡
መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ቁራጭ ወረቀት ሁሉ በማንሳት ማንበብ ልማዱ የነበረው ይህ አንጋፋ ባለሙያ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገር ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አብዝቶ ጠያቂና ተመራማሪ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለሚጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሾችን ከበቂ ማብራሪያዎች ጋር የመስጠት ብቃቱ ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል፡፡
ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል፡፡ ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል፡፡ ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል፡፡ ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገንደራሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው፡፡ በድርቅና በረሀብ ለተጎዱ እንዲሁም ጠያቂና ዘመድ ለሌላቸው ሰዎች ደራሽ ነበር።
ጳውሎስ የትዳር አጋሩንና ትዳሩን አክባሪ፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪ፣ ለማኅበራዊ ሕይወት መጠንከር ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር፡፡ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ አድናቂ እንደነበርም በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡
አንድ ታላቅ የአገራችን ጋዜጠኛ ‹‹ጋዜጠኛ ከሆኑ አይቀር እንደ ጳውሎስ ነው፤ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን እንኳ ጳውሎስን የሚተካ ጋዜጠኛ/ሰው እስካሁን አልተገኘም›› ብለው ነበር፡፡
ለእውነት ሟች የነበረው ጳውሎስ፣ በመጨረሻዎቹ የእስትንፋሱ ቀናት እንኳ ‹‹እኔ እንደማልድን አውቀዋለሁ፤ ግን ብሞትም እውነት እየተናገርኩ ነውና ከሞትኩ ነፍሴ አትጨነቅም›› ብሎ ነበር፡
(ምንጮች ፡ ልዩ ልዩ መጻሕፍትና ጽሑፎች)
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic