>
8:52 am - Tuesday July 5, 2022

የቅቡልነት እጦት የሚንጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ (በፍቃዱ ኃይሉ)

የቅቡልነት እጦት የሚንጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ
በፍቃዱ ኃይሉ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሥልጣነ በትሩን ከጨበጠ ከዓመት በላይ ቢሆነውም ቅሉ ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት መግባት አልቻለችም። እርሳቸው ከመምጣታቸው በፊት ከነበረው ቀውስ አንፃር አለመረጋጋቱ በከፊል ቀንሷል፤ በከፊል ምንጩ ተቀይሯል። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመጡ የነበራቸውን ያህል ተደማጭ ሆነው መቀጠል አልቻሉም።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ አመራሮች በሕገ ወጦች እና ጠብ አጫሪዎች ላይ ቆራጥ ርምጃ መውሰድ ያልቻሉበት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችም የ”ተሐድሷቸው” ተባባሪ ያልሆኑበት መንሥኤ ምንድን ይሆን?
በሕልም መፎካከር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሥያሜ “ተፎካካሪዎች” በሚል ቀይረውታል። የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ መሪዎች አንዱ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ “ተፎካካሪ ሕልሞች” የሚንጡት ፖለቲካ ስለመሆኑ ብዙ ጽፈዋል። እነዚህ ተፎካካሪ ሕልሞች ለበርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ስብስቦች መፈልፈል መንሥኤ ሆነዋል። የፖለቲካ ድርጅቶቹ ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነው በመቆየታቸው የራሳቸውን ትርክት ማስደመጥ አልቻሉም ነበር። ይሁንና የፖለቲካ ለውጡ ተከስቶ ትንሽ እፎይታ ሲያገኙ ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ያላቸው ተስፋ እና እንቅስቃሴ ጨምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን ሲይዙ ብዙዎቹ ተፎካካሪዎች በፈንጠዝያ ነበር የተቀበሏቸው። እነዚህ ተፎካካሪ ሕልም ያላቸው ቡድኖች የእርሳቸውን መምጣት በጋራ እና በደስታ ያከበሩበት ምክንያት ልዩነታቸውን ለማስታረቅ በማለም ሳይሆን፣ እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ሕልም በእርሳቸው ውስጥ እናሳካለን በሚል ተስፋ ነበር ብሎ መገመት ለስህተት የሚዳርግ አይመስልም።
ይህንን ተስፋ በምሳሌ ለማስረዳት ሰኔ 2010 ዓ.ም ተዘጋጅቶላቸው የነበረውን ሰልፍ መጥቀስ ይጠቅማል። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተፎካካሪ ሕልሞች መገለጫዎች አንዱ ሰንደቅ ዓላማ ነው። በድጋፍ ሰልፉ ዕለት ሰልፈኞች ይዘዋቸው የወጧቸው ሰንደቅ ዓላማዎችም የተለያዩ ነበሩ። የፌዴራል አርማ ያለበት እና የሌለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ፣ “የኦነግ” የሚባለው ባንዲራ፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲሁም “የገዳ” የሚባለው ባንዲራን የያዙ ሁሉ ሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።
እነዚህ እና ሌሎችም የፖለቲካ ቡድኖች አንድም ሕልማቸውን ሥልጣን በተቆጣጠረው ወገን በኩል፣ አሊያም በራሳቸው መንገድ ለማሳካት መፍጨርጨራቸው የግድ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ግን የትኛውንም ሕልም ወይም ቡድን በይፋ ባለመደገፉ ምክንያት ብዙዎቹ በርሳቸው ላይ ተስፋ አጥተዋል። ይህም በተለወጠ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ያልተለወጠ የፖለቲካ አጨዋወት እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል። አሁን የሚታየው የፕሮፓጋንዳ ፉክክር እና እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ግጭቶች አንዱ መንሥኤ ይኸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ቢሆኑ አሁን ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ የመጣውን ቅቡልነታቸውን አግኝተው የነበረው ለሁሉም ተሥማሚ መሥለው በመታየታቸው ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ስብስቦች፣ አክቲቪስቶች እና ሌሎችም በሕግ የሚያስጠይቅ ነገር ሲሠሩ እንዳላየ የሚያልፉትም ይህንን ቅቡልነታቸውን ላለማጣት ይመሥላል።
ሕልሞቹን ማስታረቅ
ብዙዎች “መራዘሙ አይቀርም” ብለው የሚገምቱት አገር ዐቀፍ ምርጫ በደንቡ መሠረት መካሔድ ያለበት የሚቀጥለው ዓመት ነው። ነገር ግን የፖለቲካ ፉክክሩ ከመቼውም በላይ በጦዘበት በዚህ ጊዜ ምርጫ ማካሔድን ግጭት እንደመደገስ የሚቆጥሩት እንዲሁ ብዙ ናቸው። ሆኖም ምርጫ አለማዘጋጀትም ቢሆን በተለይ በምርጫው አንድ ድል እናስመዘግባለን ብለው ለሚያስቡት ቡድኖች በራሱ የቁጣ እና የግጭት መንሥኤ ነው። በዚያ ላይ ምርጫ የማራዘም ሥልጣንም፣ የማስገደድ ኀይልም ያለው ቡድን የለም።
ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት የሚያስችለው መንገድ ከምርጫው በፊት የተፎካካሪዎቹን ስብስቦች ሕልማቸውን ማስታረቂያ መድረክ መፍጠር  ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ። ይሁንና በተለይ በዋልታ ረገጥ ብሔርተኞች መካከል ሕልምን ለማስታረቅ ከመሞከር ይልቅ ልዩነትን በማክረር ደጋፊዎችን ማነቃነቅ የፖለቲካ ባሕል ሆኗል። እነዚህን ተፎካካሪዎች በድርድር ለማሥማማት መሞከር ደጋፊ የሚያስገኝላቸውን የመፎካከሪያ ነጥብ ስለሚያሳጣቸው የመሳካት ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው።
መውጫ መንገድ
ተፎካካሪ ሕልመኞቹ ወደ ግጭት የማምራት ዕድል የሚኖራቸው ሕልማቸውን ለማሳካት ከሰላማዊ ፉክክር ይልቅ በኃይል እናሳካለን ብለው ስለሚያምኑ ነው። መንግሥት ደግሞ ከሰላማዊ መንገድ ያፈነገጡ ቡድኖችን በሕግ ለመጠየቅ የሚያስችል ቅቡልነት የለውም፤ ጉዳዩ የፖለቲካ ትርጉም ይሰጠዋል። ብቸኛው አስታራቂ መንገድ ይኸው እንደ እሳት የተፈራው ምርጫ ራሱ ነው።
ምርጫ ለሚመሠረተው መንግሥት ቅቡልነት ያጎናፅፈዋል። ሕልማቸውን በኃይል ለማሳካት የሚሞክሩትንም በሕግ ለመጠየቅ የሚያስችል ቅቡልነት ያስገኛል። ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልኂቃን ዘንድ ሥምምነት የመፍጠሪያው ብቸኛ መንገድ በደሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት መመሥረት ብቻ ነው የሚለው ሐሳብ ቢያመዝንም፥ መንግሥት ግን በሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተጠምዶ ከዓመት በታች ለቀረው ምርጫ ቅድመ ዝግጅቱን ትኩረት አልሰጠውም ማለት ይቻላል።
Filed in: Amharic