>
5:28 pm - Thursday October 9, 1310

የኢሳት ችግር የገንዘብ ሳይሆን የቦርድ ነው!!! (አበበ ገላው)

የኢሳት ችግር የገንዘብ ሳይሆን የቦርድ ነው!!!
አበበ ገላው
ሰሞኑን ኢሳት ላይ በደረሰው ጥፋት ዙሪያ ብዙ ሲባል ዝምታን የመረጥኩት ትንሽ የአርምሞ ጊዜ ያስፈልገኛል በሚል እንጂ እኔም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጣም አዝኛለሁ።
ኢሳትን ለስኬት ያበቃው በሺዎች የሚቆጠሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአንድነት አላማቸውን አስቀድመው እንደ ንብ በህብረት በመስራታቸው ነበር። ግንቦት 7ና አባላቱም ለኢሳት ስኬት ከምስረታው ጀምሮ ትልቅ አስተዋጾ አበርክተዋል። ለዚህም ማንም ምስጋና ሊነፍጋቸው አይገባም። ድርጅቱ ከሰራቸው ትልቅ ስራዎች አንዱ በመላው አለም በርካታ ለህዝባቸው ነጻነትና አርነት ከልብ የሚቆረቆሩ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን ለመለገስ የማይሳሱ በያሉበት አርአያ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰቡ ነው።
ይሁንና ግንቦት 7 ከኢሳት ጀርባ በድጋፍ ሰጭነት ያደራጀው ቦርድ፣ በተለይም ደግሞ እራሱን “ገድሉ ኪዳኔ” እያለ የሚጠራው አዲሱ መንገሻ የተባለ የዘመነ 66 አንባገነን የዛሬ አመት ኢሳትን የሚከፋፍል ማኔጅመንቱን የሚያሽመደምድ ሰው ሰራሽ ቀውስ በመፍጠር ድርጅቱን አደጋ ላይ የሚጥል እርምጃ ወሰደ። ቀውሱና እና መከፋፈሉ ከውስጥ አልፎ በአለም ዙሪያ በሚገኙና ለኢሳት የጀርባ አጥንት ወደሆኑት የድጋፍ ኮሚቴዎች ተዛመተ። በዚህም ምክንያትት ከአመት በላይ ኢሳት በቀውስ ተወጥሮ ነገሮች ሁሉ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ መሄድ ጀመሩ።
በአዲሱ መንገሻ ፊት አውራሪነት የድርጅቱ ችግር ሳይፈታ ሌላ ችግር ጨመሩለት። ያለምንም ምክክር፣ ጥናት፣ እቅድና ዝግጅት ማኔጅመንቱም ይሁን ሌሎች ባለድርሻዎች ሳያውቁ አገር ቤት ህዝባዊ መሰረት ያለውን ኢሳትን የግል አክስዎን ማህበር አድርገው ማስመዝገባቸው ተሰማ። የድርጅቱን አሰራርና ደንብ በጣሰ ሁኔታም አዲሱ መንገሻ የአዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ በማድረግ ከሚድያ ጋር ምንም ቅርበት የሌለው ሰው ከመመደብ አልፎ ኢሳት የግልሰብ ጓዳ ውስጥ በደባልነት ገብቶ ስቱድዮ ከፈተ ተባለ። ክፍፍሉና አለመተማመኑ የበለጠ ተባባሰ።
አንድ ድርጅት በአግባቡ ካልተንቀሳቀሰና ካልተመራ የገንዘብ ችግርን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ለማንም ግልጽ ነው። እንደውም ኢሳት ከአንድ ትልቅ ለጋሽ ድርጅት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። እሱም በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተበላሸ።
ከአንድ አመት በላይ ኢሳት ሃዲዱን የሳተ ባቡር ስለነበር ከባድ ጉዳት እንድሚደርስበትና እንደሚያደርስ ግልጽ ነበር። የኢሳት ችግር የገንዘብ አይደለም። ትርፋማ እንዳልሆነ ድርጅት ዋና ገቢው የህዝብ መዋጮ ነው። በአግባቡ የሚያስተባርና የሚመራ ያስፈልጋል እንጂ ቸገረኝ ቢል ሚሊዮኖች ያዋጣሉ። ብዙዎች የአንገታቸውን ሃብል ሳይቀር በጥሰው ሲሰጡ መስክረናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ያልታደልነው መሪ ነው። መሪዎች ሃላፊነት የማይሰማቸው ከሆነ ህዝባዊ አላማን ወድ ጎን ብለው የያዙትን ሃላፊነትና ስልጣን የግል ጥቅምና ፍላጎት ማርኪያ ካደርጉት አሰራራቸው ከሸርና ከሴራ ካልጸዳ ወደፊት መራመድ አይቻልም። ኢትዮጵያም ወደ ፊት መራመድ ያልቻለችው ከራሳቸው በላይ አገር የማይታያቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች ዘወትር ህዝብን ለኪሳራ ስለሚዳርጉ ነው።
ለማንኛው ይሄንን ጉዳይ ሰሞኑን ሰፋ አድርጌ በዝርዝር አመለስበታለሁ። መልካም ሳምንት!
Filed in: Amharic