>
5:13 pm - Thursday April 20, 6873

ደህንነት መስሪያ ቤት ያቺን ሴራውን ካላቆመ አደጋ ላይ ነን... !!! (አበበ ቶላ ፈይሳ)

ደህንነት መስሪያ ቤት ያቺን ሴራውን ካላቆመ አደጋ ላይ ነን… !!!
አበበ ቶላ ፈይሳ
ትላንት የነ እስክንድር ነጋ ሰናይ ሚዲያ በሂልተን ሆቴል ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እነ እስክንድር እና ጌታነህ ባልቻ እንደነገሩን በደህንነት መስሪያ ቤት ቀጭን ትዕዛዝ ሊሰረዝ ግድ ሆኖበታል። ትላንት ለማጋራት እንደሞከርኩት ሂልተን ሆቴልን ስለ ሁኔታው ጠይቄ እንደ ድሮው ቼልሲ ዝግት አድርገው የሚጫወቱት ሂልተኖች ምንም ፍንጭ ሊሰጡኝ አልቻሉም። ምንም ፍንጭ አለመስጠታቸው ግን ራሱን የቻለ ፍንጭ ነው። እንደኔ ግምት ሂለተኖች ጋዜጠኛ ነኝ ብሎ ለደወለ ሰው አደባባይ ሊያውለው እንደሚችል እያወቁ እውነቱን ለመናገር እና መረጃ ለመስጠት ያልደፈሩት እውነቱ የሚያመጣባቸው አንዳች ጦስ እንዳለ ስለተረዱ ነው።  ወይም ከእውነቱ ጀርባ ያለው ሃይል ከባድ ነው ማለት ነው የሚል ፍንጭ እናገኛለን።
በዛችኛዋ ኢህአዴግ ግዜ በነበረኝ ልምድ ለምሳሌ ወደኔ ዘንድ ተልኮ የነበረው ደህንነት (ቴውድሮስ ይባላል። አሁን ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ውስጥ የሆነ ስራ ሂደት ሃላፊ ሆኖ እየሰራ እንዳለ በቴሌቪዥን አይቼው እዚሁ ፌስ ቡኬ ላይ አጋርቻችሁ እንደነበር ልባሞች ታስታውሳላችሁ።) ቴውድሮስ ለስድስ ወራት ያክል የቁም እስረኛ አደርጎ የት ገባህ የት ወጣህ ሲለኝ እና እንቅስቃሴዎⶬን ሲገድባቸው ለኔ ደህነነት እንደሆነ መታወቂያውን አሳይቶ ቢነግረኝም ለሌላ ለማንም ሰው ትንፍሽ እንዳልነግር እና ይሄንን ጉዳይ አስመልክቶ የተናገርኩ እንደሆነ እንደማይምረኝ አሳስቦኝ ነበር።
ካነሳነው አይቀር እኔ ግን በጣም ለተወሰኑ ሰዎች ነግሬ ነበር። በየሳምንቱ ስፅፍ በነበረው የፍትህ አምዴ ላይም በአጠቃቀስኩ ስለርሱ እናገር ነበር። ስለ ጉዳዩ ከነገርኳቸው በጣም ውስን ሰዎች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ናቸው።
ፕሮፍ ደህንነት ነኝ ያለ ሰውዬ መውጪያ መግቢያ አሳጣኝ ወይ አልከሰሰኝ ወል አልተወኝ ግራ የገባ ነገር ሆነብኝ ብዬ ብላቸው፤ ”ቀጥታ ሄደህ ጌታቸው አስፋን ምንድነው ችግሩ ብለህ አናግረው… እኔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን የመሰረትን ግዜ ባልደረቦቻችንን እንዲህ ሲያደርጓቸው ክንፈን ቀጥታ ሄጄ ነበር የማናግረው” ብለውኝ ነበር። ፕሮፍ ምንም ቢሆን ፕሮፍ ናቸው፤ እኔ ጌታቸው አሰፋን ሄጄ አናግረዋለሁ ብል አስባችሁታል…?
ከዛ በኋላ የደህነነቴ ነገር በጣም አሳሳቢ ሲሆንብኝ ነው ሃገር ጥዬ የጠፋሁት። በወቅቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ “ደህነንት አስፈራራኝ  ደህንነት አላንቀሳቅስ አለኝ የሚባለው ነገር ውሸት ነው ከሃገር ለመውጣት የምትቀመር ቅጥፈት ናት” ብሎ መፃፉን አስታውሳለሁ።
እንግዲህ ከትላንቱ የሰናይ ሚዲያ ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከል ጀርባ ለማንም ትንፍሽ ትሉና ዋ ያለ አንድ ሃይል እንዳለ ለመረዳት የሂልተኖች ፍንጭ አለመስጠት ፍንጭ ይሰጠናል።
ግን ደግሞ እንዲህ ብሎ መንግስት አፋኝ ሆኗል ወይም ደህንነት መስሪያ ቤት የድሮ ሴራውን ጀምሯል ወደሚል ድምዳሜ መድረስም ከባድ ነው። ይሄንን የምንለው ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ ስናጣ ነው።
አንደኛ፤ መንግስት አፈና ካደረገ እነ እስክድር ከአዳራሽ ውጪ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ እንዴት ዝም ይላል?
ወይስ አፈናው ጥላ ቦታ የመሰብሰብ አፈና ነው? ብለንም መጠየቅ ይገባናል። ከዚህ አከል አድርገንም በሁለተኛነት፤ መንግስት ወይም ደህንነት ከዚህ አፈና ወይም መግለጫ ክልከላ ምን ሊያተርፍ ይችላል? ብሎ መጠየቅም ግድ ይለናል።
እንደምናውቀው እስክንድር ኢትዮጲስ የተባለ ሚዲያ አለው። በኢትዮጲስ ላይ ምንም አፈና ወይም ክልከላ ሲደረግ እስካሁን አላየንም። አፈናው ወይም ክልከላው እስክንድር ላይ ያነጣጠረ ከሆነ ኢትዮጲስ ሚዲያ እንዴት ምንም ተግዳሮት ሳይገጥማት ቀረ?  የሚለውንም በሶስተኛነት መጠየቅ ይገባል።
ሌላው ሰናይ መልቲ ሚዲያ ጋዜጣዊ መግለጫ አደረገ አላደረገ ምን ይጎድልበታል? ወደ ምስረታ ዝም ብሎ መሄድ አይችልም ወይ? የሚለውም መነሳት ይገባዋል። (ምስረታው ላይ ወይም ፈቃድ ጥየቃ ላይ ካልተከለከለ ጋዜጣዊ መግለጫ በመከልከል ብቻ መንግስት ወይም ደህንነት ምን ማሳካት ይችላል?)
አሁን እንዳየነው የሰናይ መልቲ ሚዲያ ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከል ይበልጥ ድርጅቱን ከማስተዋወቅ የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም። ደህንነት መስሪያ ቤት ይሄንን አጥቶት ነው ወይስ… ? ብለን ሌሎች ጥያቄዎችንም ስናብሰለስል ደህንነት መከልከሉን እንጠራጠራለን። የሂልተን ሆቴልን ለምላሽ መሽኮርመምን ስናይ እና የእስክንድርን እና ጌታነህን ቃል ስንሰማ ደግሞ ደህንነት ያቺን ጨዋታ ጀምሯል ማለት ነው? እንላለን።
በመጨረሻም ሃቅ ሆይ ከወዴት አለሽ? እያልን ደህንነት መስሪያ ቤት ያቺን ሴራ ዳግም ጀምሯት ከሆነ ግን አደጋ ላይ ነን። በማለት እናንተ ግን እንዴት ናችሁ? ብለን እናሳርጋለን!
Filed in: Amharic