>

ከገደል አፋፍ የተመለሰው የፕ/ር መስፍን ባቡር ወቅታዊ ተስፋና ስጋት (ሳምሶን አስፋው)


ከገደል አፋፍ የተመለሰው የፕ/ር መስፍን ባቡር ወቅታዊ ተስፋና ስጋት

ሳምሶን አስፋው – ቋጠሮ ገጽ

አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን እንደ ሃገር በባቡር ፤የወያኔን መንግስት በባቡሩ ሹፌር፤ የኢትዮጵያ ህዝብን በተሳፋሪ መስለው ያቀረቡትን ወቅቱን ያገናዘበ ንፅፅር ብዝዎቻችሁ የምታስታውሱት ይመስለኛል።

ፕ/ር በምሳሌያዊው ገለጻቸው፤ የባቡሩ ሹፌር (ወያኔ) ጠመንጃውን ይዞ ፊቱን ወደ ተሳፋሪዎች አዙሮ ተቀምጧል።  ባቡሩ ወደ ገደል እየሄደ መሆኑን አያይም። ተሳፋሪው (ህዝብ) ደግሞ ባቡሩ ወደ ገደል እየገባ መሆኑን እያየ ጠመንጃውን ፈርቶ ዝም ብሎ በጭንቀት እየተጓዘ ነው። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የባቡሩ(የኢትዮጵያ) መጨረሻ ገደል መግባት ነው። ሲሉ አመላክተዋል።

ፕ/ር በኮፒ ራይት እንደማይጠይቁኝ ተስፋ በማድረግ የዛሬውስ የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በፕ/ር ተምሳሌያዊ አቀራረብ እንዴት ሊገለጽ ይችላል ? ብዬ ሳስብ የታየኝ ነገር ተሳፋሪው ህዝብ ዝምታውን ሰብሮ መሪውን ከነፉርጎው አሸቀንጥሮ ባቡሩ ከገደል አፋፍ ላይ ሲደርስ መትረፉ ነው።

አዲሱ ሹፌሩ ጠመንጃውን አስቀምጦ ፊቱን ወደ መንገዱ አዙሮ በአግባቡ መንዳት ጀምሯል። ባᎇሩን ከገደል የታደጉት (የለውጥ ኃይሎች) ከባቡሩ ፊት እየቀደሙ ሃዲዱን እየዘረጉለት ጉዞውን ቢቀጥልም፤ ጉዞው ግን አሁንም የተስተካከለ አይደለም። ከባቡሩ ኋላ እየተከተሉ ሃዲዱን የሚነቅሉና ፉርጎ በጥሰው ለማስቀረት የሚሯሯጡ አጥፊዎች ጉዞውን እያሰናከሉት ነው። በየፉርጎዎች ውስጥ ሁከት ይሰማል። ሁከቱን ማስቆም ባይቻልም ጉዞው ግን በተስፋና በስጋት ቀጥሏል። ባቡሩ በሰላም ይገባ ይሆን? የአብዛኛው ተሳፋሪ የጭንቀት ጥያቄ ነው። ….

አዎ! በባቡር የተመሰለው የሃገራችን ፖለቲካ ግራ እያጋባን ነው።

  • ጠዋት የህግ የበላይነትን ስለማስፈን አስፈጻሚው አካልና ምሁራን ውይይት አደረጉ የሚል ዜና ትሰማና ከሰዓት በኋላ በዚህ ክልል ይህን ያህል ሰዎች ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገደሉ ትባላለህ ።
  • ረፋዱ ላይ “በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የጋዜጠኞች ሚና” በሚል ርዕስ ባለድርሻ አካላት መከሩ ትባልና ቀትር ላይ እስክንድር ነጋ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ ታገደ ሲባል ትሰማለህ።
  • በጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ አዲስ አበባን ለማስዋብ ይህን ያህል ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ፕሮጀክት ተነደፈ በሚል ምድረ-ገነት የሆነ ፕላን አይተህ ዞር ስትል ይህን ያህል አባወራ ቤቱ በቡልዶዘር ፈርሶበት ጎዳና ወደቀ የሚል ርዕስ ላይ አይንህ ያርፋል።
  • ትናት የሰለጠነ የሃሳብ ትግል ስለማድረግና ስለ ፖለቲካው ምህዳር መስፋት ጎን ለጎን ቁጭ ብለው “ወንድሜ እንዳለው! ጓዱ እንዳለው” እየተባባሉ በመሞጋገስ ሲያወሩ ያየሃቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች በማግስቱ ተከታዮቻቸው በገጀራና በዱላ ሲዛዛቱ ታገኛቸዋለህ።
  • ማህበረዊ ሚዲያው እገሌ የተሰኘው ት/ምቤት እየፈረሰ ነው በሚል ሲቀወጥ ይውልና ማምሻውን ደግሞ ከንቲባው ብቅ ብለው እየፈረሰ ነው ለተባለው ት/ቤት ተማሪዎች በሙሉ ዩንፎርም በነጻ አልብሳቸዋለሁ በማለት ቃል እንደገቡ ይዘገባል።

እረ ጎበዝ አያ እቶኔ ሁለት መንግስት ነው ያለው ነገር እውነት ይሆን እንዴ?  አንዱ ገንቢ ሌላው አፍራሽ ። አንዱ ሃዲድ እየዘረጋ ወደ አገረ-ሰላም ሊጓዝ የሚጥር፤ ሌላው ሃዲዱን እያፈረሰ ሊያተረማምስ የሚታትር … ሌላ ምን ይባላል?

የሚገርመው ደግሞ አብዛኞቹ ዜና ዘጋቢዎችም ወይ ነጩን ወይ ጥቁሩን ዜና እየመረጡ የሆነውን ሳይሆን እንዲሆን የሚፈልጉትን  መዘገብ ማዘውተራቸው ነው። አንዱ ወገን የሰላም የዲሞክራሲና የብልጽግና ጎዳና ላይ በሰአት 120 እየበረርን እንደምንገኝ ክሊፕ ሰርቶ በሃሴት ያፍነከንከናል  ሌላው ወገን ደግሞ ከሱማሌ፤ ከሶሪያና ከየመን ቀድመን ወደ መቃብር እየተጓዝን እንደሆነ የሚያሳይ የእልቂት ሟርት እያዘነበ ሆድ ያስብሰናል።

ግነት የተጣባው የሁለቱም ወገኖች አተያይ አብዛኛውን ወገን ግራ እያጋባው ነው።  እንደ እኔ አተያይ ነጩ የሰላም ባንዲራም ሆነ ጥቁሩ የመከራ ከል ሃገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ አይገልጹም። በነጭና በጥቁር መካከል ግራጫ (ግሬይ) የሚባል ቀለም አለ። ተስፋ ሰጪም ስጋት አመንጪም ክስተቶች አሉ።

ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ አፈ-ታሪክ ትዝ አለኝ። ነገሩ እንዲህ ነው። ሰውየው መንገድ እየተጓዘ ስንቅ ያልቅበታል። በረሃብ እየተሰቃየ ብዙ ከተጓዘ በኋላ በአንድ የገጠር መንደር  ውስጥ የባቄላ እሸት ማሳ ያገኝና ዘሎ ይገባል። ረሃቡ ግዜ ስላልሰጠው እሸቱን ሳይፈለፍል ከነልጣጩ እየጨረገደ ይጎሶጉስ ገባ። ረሃቡ ትንሽ ጋብ ሲልለት በአግባቡ እየፈለፈለ ፍሬውን እያወጣ መብላት ጀመረ። ጠገብ ሲል ደግሞ ባቄላው ፍሬ ውስጥ ያለቺውን ትንሿን እንቡጥ እያወጣ ይበላ ጀመር። እሸት አይከለከልምና ይህ ሁሉ ሲሆን የማሳው ባለቤት በሩቁ ያየው ነበር። በኋላም በሰውየው አበላል ተገርሞ “ሰማህ ወይ ጌታው” ብሎ ይጠራውና “እንደ መጀመሪያውም አትብላ እንደ መጨረሻውም አትብላ እንደ መካከለኛው ብላ” አለው ይባላል።

እናም እንደ ራበው መንገደኛ የመጀመሪያ አበላል መልካም ፍሬውን ከነልጣጩ እየጨረገዳችሁ ከየመን ከሱማሌና ከሶሪያ ቀድመን መቃብር ልንወርድ ነው የምትሉን ሟርተኞችም ሟርታችሁን ቀነስ አድርጉ። እንደ መንገደኛው 3ኛ አበላል የመልካም ፍሬውን እንቡጥ ብቻ እየፈለቀቃችሁ በሰላም፤ በዲሞክራሲና በብልጽግና ጎዳና ላይ በ120 እየበረርን ነው የምትሉትም ወገኖች ፍጥነታችሁን ቀንሱ።

የዜና አውታሮች እንደ መካከለኛው አበላል ፍሬውን ከገለባ ለይታችሁ እውነቱን ከሃሰት አጥርታችሁ የብርሃኑን ጥልቀትም ሆነ የጨለማውን ግዝፈት ሳታጋንኑ አቅርቡልን።

የጨለማው ግዝፈት በትክክል ከታወቀ ጨለማውን ሊደመሥስ የሚችለውን የብርሃን መጠን ለማወቅ ያስችለናል። የብርሃኑን መጠን ማጋነንም የጭለማውን ግዝፈት ይሸፍናልና መጨረሻችን “ጸጉራም ውሻ አለ ሲሉት ሞቶ ይገኛል” ይሆናልና አይበጅም ።

ባጠቃላይ ለመሪዎች ፍጹም የሆነ ድጋፍም ሆነ ፍጹም የሆነ ተቃውሞ አይጠቅማቸውም ። ፍጹም የሆነ ድጋፍ መታበይን ያስከትላል ፤ መታበይ ደግሞ ትዕቢትን ትዕቢትም አምባገነን ይፈጥራል። ፍጹም የሆነ ተቃውሞም ቂም በቀልንና መጠፋፋት ያስከትለል።

እናም ማንም ይሁን ማን ጥሩ ሲሰራ እንደግፈው። የበለጠ እንዲሰራ ይበረታታልና። በዘው መጠን መጥፎ ሲሰራም እንቃወመው ድጋሚ ጥፋት እንዳይሰራ ማስታወሻ ይሆነዋል።

የኢትዮጵያ ሃዲድ ነቃዮቹን ቢቻል ጥፋታቸውን አጥፎቶ አልያም ራሳቸውንም ቢሆን ባቡሩን ከነተሳፋሪዎቹ በሰላም ያግባልን!

ኢትዮጵያ በክብርና በነጻነት ለዘላለም ትኑርልን!

Filed in: Amharic