>
3:37 pm - Thursday May 19, 2022

ግልጽ ደብዳቤ  ለክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዓብይ አህመድ (የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል!)

ግልጽ ደብዳቤ
 ለክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዓብይ አህመድ  የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  አ.አ ኢትዮጵያ
 
የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል!
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር:
   ላለፉት 27 ዓመት ህወሓት መራሹ የኢህአዲግ አምባገነን ስርዐትን የዜጎች የሃስብ ልዩነት ይከበር ብለን ሰንቃወምና አቅማችን በፈቀደው ሁሉ ሰንታገለዉ ቆይተናል፤ ላለፈው አንድ አመት ደግሞ በእርሶ የሚመራው በተለምዶ ቲም ለማ የሚባለው የለውጥ ሃይል በኢትዮጵያ ህዝብ ግፊት ያመጣውን ለውጥ የተለያዩ ችግሮች ብናይበትም የችግሮቹ መንስኤዎች ከለውጥ ሂደቱ ጋር እንደተከሰቱ በማመን ይህን የለውጥ ሃይል እያደረገ ያለውን ጥረት እያደነቅንና ለውጡንም አቅማችን በፈቀደ እየደገፍን እንገኛለን፤ ነገር ግን ላለፉት 27 አመታት ሲሰበክ የነበረው ዘርን ያማከለ የፖለቲካ አካሄድ ፍሬ አፍርቶ አሁን ከማናቸውም ጊዜ በተለየ በመላው የአገሪቷ ክፍል የፌደራል መንግስት የሌለ እስኪመስል ስርዐት አልበኝነት ሰፍኖ ማየት ብቻ ሳይሆን ዜጎችንም ማፈናቀል በመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ሲከናወን እያስተዋልን ነው።
 ይህንንም ድርጊት ለመከላከልና የአገሪቷን ሰላም ከማስከበር ረገድ ከመንግሰት እየተወሰደ ያለው እርምጃ በቂ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም በፌደራል መስሪያ ቤቶች በኤንባሲዎችም ጭምር አሁንም እንደቀድሞው አስተዳደር በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት እየተያዘ መሆኑ አሳሳቢና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ከመሆኑም በላይ በማህበረሰባችን ውስጥ በለውጡ ላይ እምነት እያሳጣ በመምጣቱ የችግሩን አሳሳቢነት በመመልከት አስቸኳይ ማስተካከያዎችን መውሰድ ያስፈልጋል እንላለን፤ እንዲሁም ህጋዊና የግለሰቦችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብና የህግ የበላይነትን በመላው አገሪቷ ማስፈን ግዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፣ በዚህ ላይ መንግስት ችግሮች እንዳይከሰቱ ቅድመ መከላከል በተገቢው መንገድ ስለማያረግና ችግሮች ሲከሰቱም ችግሩን የሚቀርፍ መፍትሄ በወቅቱ ባለመውሰዱ የለውጡ ሂደት ከመንገዱ አቅጣጫ እየሳተ ሲወጣ ሲለው ወደ አቅጣጫው እየተመለሰ ህዝቡን ግራ እያጋባና ለለውጡም ሂደት እንቅፋት እየሆነ መሆኑን እያስተዋልን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ አርአያችን በምናየው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ በመንግስት ሃይላት እየተወሰዱ ያሉትን ማዋከቦች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እንዳይሰጥ እና ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማገድ በፍጹም የማንቀበላቸውና በቸልታም የምናየው ጉዳይ አይደለም፤ በተለይ ፅንፈኛ የብሄር አክቲቪስቶች የሚያሰማሯቸው መረን የለቀቁ ጋጠወጦች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በእስክንድር ነጋ ላይ የግድያ ዛቻ በአደባባይ ሲያደርጉ አስተውለናል፤ ይህንም ድርጊት አየተመለከተ ዝምታን የመረጠው የአገሪቷ ህግ አሰከባሪ ሃይል የሰብአዊ መብት ተሟጋቹን እሰክንድር ነጋን በየጊዜው ሲያዋክብ ስናይና በአንጻሩ ከ 17 ግዜ በላይ የህዝብ ባንክ የዘረፉ፣ ህዝብን ለእርስ በርስ ግጭት የሚቀሰቅሱ አክቲቪስቶችም ሆኑ ቡድኖች በዝምታ ሲታለፉ ስናይ ሆን በሎ መንግሰት በእርሱ ላይ ጫና እንዲፈጠር የፈቀደው ድርጊት ነው አስብሎናል፤ ይህ ህገ ወጥ ድርጊት በአፋጣኝ ካልታረመና ወንጀለኞቹ በአስቸኳይ ለፍርድ የማይቀርቡ ከሆነ የህዝብን በመንግስት ላይ ጥርጣሬ እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ እኛም ለረጅም ግዜ የቆምንለትና የታገልንለት የሃሳብ ልዩነት መከበር በተደጋጋሚ መጣስ በዝምታ የምናልፈው ጉዳይ አለመሆኑን እየገለጽን ይሄንንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ አስቸኳይና የማያዳግም እርምጃ ይወስዱ ዘንድ እንጠይቃለን፤ እኛም ለሚፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አቅማችን በፈቀደ ድምጻችንን የምናሰማ መሆኑን እንገልጻለን።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!
ግልባጭ፡ ለአምባሳደር ፍጹም አረጋ
Filed in: Amharic