>
10:17 am - Tuesday July 5, 2022

ኢትዮጵያን ከሚያስተዳድራት ኃይል ጋር እንተዋወቅ (ግርማ በላይ)

ኢትዮጵያን ከሚያስተዳድራት ኃይል ጋር እንተዋወቅ

ግርማ በላይ

ታላላቅ ሰዎችን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ እንደግሪክ አማልክት በመድረኮች ሣይቀር በይፋ የሚመለከው ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ የሚዘውረው ቲም ለማ ከሚባለው የኦህዲድ ገዢ ኃይል ጋር አይደለም የምንተዋወቀው፡፡ ሌላ ነው፡፡ “የዶ/ር አቢይ ኢትዮጵያዊነት ከእኔም የኢትዮጵያዊነት (ስሜት) ይበልጣል” ከሚለው እወደድ ባይና አድር ባይ የቤተ መንግሥት ተስፈኛ ቡድን ጋርም አይደለም እዚህ አሁን የምንተዋወቀው፡፡ ሌላ ነው፡፡ በአንዱ ወይ በሌላው ዘር/ጎሣ/ነገድ ጥላቻ የታወሩ የውስጥ ምንደኞችን እያሠለጠኑና በበጀት እየደገፉ በየወቅቱ ጃዝ እያሉ ከሚልኩብን ፀረ-ኢትዮጵያ የውጭ ኃይሎችን ጋር አይደለም የምንተዋወቀው፡፡ ሌላ ነው፡፡ እንመለስበታለን፡፡

ሰሞኑን ኢትዮጵያ “ከከሸፉ መንግሥታት ውስጥ ትመደባለች/አትመደብም” በሚል የሚወዛገቡ ምሁራንን በሚዲያዎች እየተከታተልን ነው፡፡ በመሠረቱ ክርክር ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ተከራካሪዎችም እንዲሁ፡፡ እንደየእምነቱ፣ እንደየጥቅምና ፍላጎቱ፣ እንደየዓላማው … በአንድ ጉዳይ ላይ የሚከራከር ሁሉ ይለያያል፡፡ ትዝብትና ምን ይሉኝ እዚህ ላይ አይሠራም፡፡ ሎጂክም በሉት አመክንዮ ዋጋ የለውም፡፡ የፈጠጠ እውነትና በግልጽ የሚታይ ሀገራዊና ማኅበራዊ ክስተት ግምት ውስጥ አይገባም፡፡ ዋናው ሊደረስበት የሚፈለገው ውጤት ላይ የሚያደርሰው መንገድ ነው – የትም ፍጪው ዓይነት፡፡ የአስተሳሰብ ጎራንና ፍልስፍናን እንደዬወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ መለዋወጥ ደግሞ ችግር አይደለም፡፡ ዕድሜ ለዚህ በልቶ ለማይጠረቃ ከርስና ናላ ለሚያዞር የሥልጣን ፍቅር አቋምን እንደሸሚዝ መቀያየር የዘመኑ ፋሽን ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ አቶ “ምን ይሉኝ” ሞቶ ከተቀበረና ተዝካሩ ከወጣ ዘመናት አለፉ፡፡

ሀገራችን ለጊዜው በተጋባዥ እንግድነትም ቢሆን ከወደቁ/ከከሸፉ መንግሥታት ተርታ ብትሠለፍ ዕድሜ ለሕወሓትና ቦታውን ለተካው ኦህዲድ ጠላትን የሚያኮራ ስኬታማ ውድቀት ላይ በመገኘቷ ማዕረጉ አይበዛባትም፡፡ በሞተ ፀጉራም ውሻ ልትመሰል የምትችለውን ሀገራችንን ትንሣዔዋ እስኪበሰር ድረስ እንደከሸፈች ብትቆጠር ማጋነን አይደለም፡፡

ትናንት ማታ ነው፡፡ መንገድ ላይ እየሄድኩ ከፊቴ የነበረን ተሸከርካሪ ታርጋ ስመለከት “ኦሮ” ይልና ሁለት አኃዝ ብቻ ነው ቁጥሩ፡፡ እዚችው አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ እኔ የማውቀው አኃዝ ቢያንስ አምስት ነው፡፡ ቆሜ ሰዎችን ብጠይቅ “ይህማ ምን አለው፤ ስንትና ስንት ነገር እየሆነ አይደለም እንዴ ወንድም፡፡ እችን አገር አታውቃትም ማለት ነው?” አሉኝ፡፡ ለማን ልናገር? ማንስ ሰሚ አለ? እየተናደድኩ ወደ በይተይ ገባሁ፡፡ ይህ ነገር ለብዙዎች ቀላል ነገር ምናልባትም የማይገባቸው ትንሽ ነገር ሊመስል ይችላል፡፡ በሌሎች ሀገሮች ግን ከትላልቅ ወንጀሎች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ያለታርጋ መንቀሳቀስ ማለት እኮ ነው፡፡ መንግሥት ባለበት ሀገር ካለ ታርጋ መንቀሳቀስ ከተቻለ ወንጀልን መሥራትና ማምለጥ በጣም ቀላል ነው፡፡ በምኑ ይያዛል? አንድ በሉ፡፡

አንዱ ጓደኛየን ትራፊክ ፖሊስ ይይዘዋል፡፡ ይህን እንኳን ልተወው፡፡ ብቻ ግን ቆንጆ ብዕር ቢሰጠው እያገላበጠ በብርቅ ዐይን ተመልክቶ ሊጽፍበት ብዕሩን ከቅጣት ወረቀቱ ካዋደደ በኋላ መንጃ ፈቃዱን መልሶ ሰጠውና “ንካው” አለው፡፡ ህግ የለም፡፡ ህግ በገንዘብና በቁሳቁስ ከተለወጠ ደግሞ ሀገር የለችም፡፡ በየቦታው የሚከናወነውን ይህን መሰል የህግ አለመከበርና በገንዘብ መለወጥ ስትሰሙ ሀገር እንደሌለን ትረዳላችሁ፡፡ በፍርድ ቤት ፋይል ማስጠፋት፣ ክስን ማሰረዝ፣ ሰውን የመሰለ ክቡር ፍጡር ገድለህ/አስገድለህ መረጃን ድራሹን ማስጠፋትና ምስክሮችን ሳይቀር በገንዘብ ደልለህ ወይም በነፍሳቸው ዝተህ አፋቸውን በማስያዝ የፍትህ ዐይኖችን ማጥፋት፣ የትኛውንም ህግ ተላልፈህ በዘርህ ጥላ ወይም በገንዘብህ ግርማ ሞገስ መዳን በጣም ቀላል ነው፡፡ ሁለት በሉ፤ ከአሁን በኋላ ራሳችሁ ቁጠሩ፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥና ዙሪያ የሚፈጸመው የሙስና ወንጀል ከምን ጊዜውም የተለዬ ነው፡፡ የገዛ ንብረትህን ለምሣሌ ቤትህን ለመሸጥ ያለው ጣጣና ቢሮክራሲ እንዲሁም የሙስና ትስስር አንጎልህን ያዞረዋል፡፡ አቃቂ አካባቢ አንድ ሰው ቤቱን ሊሸጥ ፈለገ፡፡ ከመዝገብ ቤት ጀምሮ ከዝቅተኛ ክፍያ ብር 1000 እስከ ብር 50000 በመጠየቁ አሁን በሃሳብና በጭንቀት እየዋለለ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ላለመክፈል ቢያንገራግር “የትም ሄደህ መክሰስ ትችላለህ” መባሉ ነው – “ሰባራ ዶሮ እንዳይቀድምህ…” ትባላለህ፡፡ ከእጅ አይሻል ዶማው የዐቢይ መንግሥት ጉድ እያፈላ ነው፡፡ ዘረፋው በገሃድ ሆኗል፡፡ በተለይ አዲሶቹ ተረኞች ሆዳቸው ከወያኔ ይበልጥ ተምቦርቅቆላችኋል – ደምበኛ ላስቲክ፡፡ ያዩትን ሁሉ ካለደረሰኝ ገቢ ማድረግን ሥራየ ብለው ተያይዘውታል፡፡ እውነትም የኬኛ መንግሥት፡፡ የትም ብታመለክት ማንም የማንንም ዝምብ እሽ አይልም – ግም ለግም ነዋ የሚያዘግም፡፡ ሁሉም ተፈራርቶ በየፊናው ያገኘውን መዛቅና ማሸሽ ነው – ለመቋቋሚያ፡፡ ከዚያ ዘወር ማለትና ለተረኛ መልቀቅ፡፡ ከሳሹም ተከሳሹም ዳኛውም ዐቃቤ ህጉም ሙሰኛ መሆናቸው ስለሚገመት አቤት የሚባልበት የለም፡፡

በዚያ ላይ የኑሮ ውድነቱን እግዜር ያሳያችሁ፡፡ አሁን አሁን ሳስበው ብዙ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ የገንዘብ ማተሚያ ማሽን ሳይኖራቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ብዙዎች ወጪን አይፈሩም፡፡ ከተሞቻችን በዘመናዊ መኪኖችና በሚያማምሩ ሕንጻዎች ተጥለቅልቀዋል – ኢትዮጵያ ሰው መሥራት አቁማ አሸዋና ስሚንቶ እየቆለለች ትገኛለች፡፡ ዕንቆቅልሽ ምን አውቅልሽ ነው፡፡ ሚሊዮኖች ግን ከሀብታሞች ቤት የተጣለ ፍርፋሪ ለመሻማት የቆሻሻ ገንዳዎችን የሙጥኝ እንዳሉ ናቸው፡፡ በረንዳዎችና የድልድይ ሥሮች በጎዳና ተዳዳሪዎች ጢም ብለዋል፡፡ ለማኙና ዕብዱ፣ ሰካራሙና ወፈፌው ከተሞቻችንን ከጊዜ ወደጊዜ እያጨናነቀ ሀገራችን ወደ ትያትር መድረክነት ተለውጣለች፡፡

በሌላ በኩል ዐይጥ እምታህል ከብዙ ካርቶንና ከጥቂት ብረታማ ላስቲክ የተሠራች ሚጢጢ መኪና ከአምናው የብር ሁለት መቶ ሽህ ምናምን ዋጋዋ በአንዴ ተሰቅላ አምስትና ስድስት መቶ ሽህ ብር መግባቷን ትሰማላችሁ፡፡ ይህ እንግዲህ የመለስተኛ ሀብታሞች ወሬ ነው፡፡ ወደኛ ስትወርዱ ደግሞ የዛሬ ሃያ ምናምን ዓመት አሥመራ ላይ በኩንታል አንድ ሽህ መግባቱን ስንሰማ “እሰይ! ወደው ነው! ይበላቸው!” ብለን በሣቅ የተንፈቀፈቅንበት ጤፍ እዚሁ እደጃችን ብር ሦስት ሽህ አምስት መቶ ብር ሲገባ ያኔ የሣቅንበትን ጥርሳችንን ከድነን ማልቀስ ይዘናል – ጡር መጥፎ ነውና ከጡረኛ ንግግር እንቆጠብ ታዲያ፡፡ የ15 ብር የምግብ ዘይት በአንዴ 90 ብር ሲገባ ከዝምታና ከይብስ አታምጣ ውጪ የምንለው የለም፡፡ ምክንያቱም ከእግዜሩም ተጣልተናል፤ በዚያም ምክንያት የኛ ነው ለማንለው የባዕድ አገዛዝ ተዳርገናል፡፡ በአፉ እየደለለ በተግባር ግን የስቃያችንን ደብዳቤ ለሚያድስ መንግሥት ተጋልጠናል፡፡ ሀገር ካምሱሩ በተፈታ ፈንጂ ላይ ተቀምጣ እያለ እዚህና እዚያ እየሄዱ እሥረኞችን በማስፈታት በሚገኝ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ራስን ማታለል ተለመደ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውስጡ ግፍና በደል – መፈናቀል፣ መሳደድና መሰደድ፣ ቤት መፍረስ፣ ከሥራ መባረርና መሥሪያ ቤቶችን በራስ ዝርያ መሙላት…. የጊዜው ወረት መሆኑ ይያዝልኝ፡፡ እስረኞችን ማስፈታት መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም – ታይቶ የማይታወቅ ግሩም ነገር ነው፡፡ ግን የቤታችን ጣጣ ትልቅ ትኩረት እንደሚጠይቅ መረዳት ይገባል፡፡ አንዱን ካንዱ እየሞጀርኩት ተቸገርኩ እንጂ የዚህ አንቀጽ ዋና መልእክት ኑሮው ወደ ሰማይ ሲምዘገዘግ እኛ ወደ እንጦርጦስ መውረዳችንን ለመግለጽ ነበር፡፡ አዎ፣ እውነቴን ነው – የምንኖረው በተዓምር ነው፡፡ ገቢህ አንድ መቶ ወጪህ አሥር ሽህ ዓይነት፡፡ አነስተኛው ባለ አራት ዲጂት ደሞዝተኞች እንዴት እየኖሩ እንዳሉ ዐይናችሁን ጨፈን አድርጉና አስቧቸው፡፡ ከሞቱት በታች ካሉትም በታች፡፡ የሞቱት በለጡን፡፡ ያስቀናሉ፡፡ “በዚያን ዘመን ሞትን ይመኙታል ግን አያገኙትም” የተባለው ደረሰ፡፡ ተንደላቀው እየኖሩ ያሉት ባብዛኛው ኅሊናቸውን በገንዘብ ሸጠው ገንዘብ ለመሥራት ከፀሐይ በታች የሚገኝ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀልና ኃጢኣት የሚፈጽሙ ቅል ራሦች ናቸው፡፡

አንዱ መንጃ ፈቃዱን ሊያሳድስ ወደ አንዱ የአዲስ አበባ ዳርቻ ከተማ ይሄዳል፡፡ ነገሩ ሳይገባው አሥራ አንድ ወራትን በመንከራተት አሳልፎ በቅርቡ ተሰጠው፡፡ ለካንስ በቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ ሰውዬውን ያንገላቱት አንዲት ብጣሽ ወረቀት መስጠት አቅቷቸው ሳይሆን ጉቦ ፈልገው ኖሯል፡፡ ከታች ጀምሮ እስከላይ ለማንኛውም ዓይነት ትንሽም ይሁን ትልቅ ጉዳይ ጉቦ ካልተከፈለ ምንም ነገር አይፈጸምም – የትም ቦታ፡፡ በመንግሥትም በቤተ እምነትም፡፡ በቤተ አምልኮው እንዲያውም ባይብስ፤ ከፈጣሪም ከመንግሥትም መቆራረጥ ማለት እንግዲህ እንደዚህ ነው፡፡ አቤት የምትልበት የበላይ አካልም ብትሄድ ለአቤቱታ ሰሚው ጉቦ መክፈል ይኖርብሃል፡፡ እንዲህም ሆኖ የጉቦ ተቀባዩን አድማስ አሰፋሃው እንጂ የትም ቢሆን ገንዘብህን መከስከስህ አይቀርልህም፡፡ በዜግነቴ አገኛለሁ የምትለው ነፃ ነገር የለም – ምናልባት አየርና ፀሐይ … ደግሞም ምናልባት በሀገር መቀበርን፤ በዚያስ ከማንም እኩል ነህ፡፡ እፉካም ውስጥ ግባ እመሬት እኩል ነህ፡፡ በምሥጦች ዓለም ዘረኝነትና ጎሠኝነት አይታወቅም፡፡
የዘረኝነት መዘዙ ከባድ ነው፡፡ ተከፍሎ የማያልቅ ትልቅ ዕዳ ውስጥ የዘፈቀን የዘረኝነትና ጎሠኝነት ጣጣ ነው፡፡ ዜጎችን በነገዳዊ ማንነት እየፈረጅህ የምታስተዳድር ከሆነ በሰውነታቸው የወል ባሕርይ ላይ ግርድና አመሳሶን የሚለይ ሰው ሠራሽ ድንበር ተክለህ አንዱን ለመጥቀም ሌላውን መጉዳትና ከዚያም ባለፈ ሀብት ንብረቱን መቀማት ዘሩንም ከናካቴው ማጥፋት የቀነ ከሌት ቅዠትህ ይሆናል፡፡ በነአቢይ አዲሱ እስስታዊ መንግሥት እየተከናወነ ያለው ይህ ነው፡፡ ሰው ግን አልገባውም፤ ዕድሜ ለ“መተቱ” ደግሞ ወደፊትም ውስጠ ምሥጢሩ ሳይገባቸው ብዙዎች እንደተጃጃሉ ይቀጥላሉ፡፡ አሁንም ከዚያ ሁሉ የመድሎ ሥራ በኋላ፣ ከዚያ ሁሉ ኢ-ኦሮሞ ዜጋን ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ሥልጣን እንዲሁም ከአዲስ አበባ አካባቢዎች የማፈናቀል ተግባር በኋላም በአቢይ ፍቅር ተጠምደው በየመሸታ ቤቱ “በአቢይ የመጣ በዐይኔ መጣ” የሚሉ ገልቱዎችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ እጅግ የሚገርመኝ ይህ ዓይነቱ አፍዝ አደንግዝ ነው፡፡ ጠበል ወይ የሥነ አእምሮ ሐኪም ያስፈልገዋል፡፡

ግሩም ትያትረኛ ጧት ቤተ ክርስቲያን ማታ ደግሞ ጠንቋይ ቤት እየሄደ ለሁለቱም ተቃራኒ ኃይሎች ሊሰግድ ይችላል፡፡ ኢያጎን የመሰለ ድንቅ ተዋናይ ጤፍ በሚቆላ ምላሱ ለአንዱ ሌላ፣ ለሌላው ሌላ በማዋሸክ ንጹሓን ሰዎችን ሊያጋድል/ሊያገዳድል ይችላል፡፡ ዴዝዴሞናን የመሰለች ንጽሕት የሼክስፒር ምናባዊ ፍጡር የሞተችው በዚህ መልክ ነው፡፡ ሻይሎክን የመሰለ ገብጋባ የራሱን የገንዘብ ቋት ለመሙላት ሲል የሌሎችን ኩላሊትና ጉበት በሃራጅ እስከመሸጥ ሊደርስ ይችላል፡፡ በአዲሱ የኦሮሞ መንግሥት እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ ወያኔን የሚያስንቅ የማጭበርበርና የማቂያቂያል ሥልት እየተጠቀሙ ሀገሪቱን ጠቅልለው በወለድ አገድ ሊይዟት የቀራቸው ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡ አዲስ አበባ ምስክር ናት ለዚህ፡፡ የትም ግባ እነሱው ናቸው፡፡ እውነቴን ነው – ከወያኔ የባሰ ይሉኝታቢስና ዘረኛ በምድር ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ወያኔ እየፈራ እየተባ 27 ዓመት የፈጀበትን በዘር ላይ የተመሠረት አድልዖና ዘረፋ እነዚህ ጉዶች በአንድ ዓመት አስከንድተውት አረፉ፡፡ ዱሮም በግሪክ ፈላስፎች እንዲህ ይባል ነበር – “ተማሪ መምህሩን ካልበለጠ መምህሩ ከድካሙ አላተረፈም፡፡”

ጥቂት ‹ልራቀቅባችሁ› – ት’ግስታችሁን፡፡ በአቢይ የሚሾሙ ሰዎችን እንመልከት፡፡ በአንደኛ ደረጃ የሚሾሙት ወጣት ፕሮቴስታንት ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ የሹመቱ አካሄድ ደግሞ ከወያኔ የተቀዳ ህገ ወጥ ነው – ከመነሻው ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ህግ ባይኖርም፡፡ ህገ ወጥነትን ህጋዊ ለማስመሰል በሚደረግ ከንቱ ጥረት በምክትል ሹመቶች የተጥለቀለቅነውም ለዚህ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚሾሙት ወጣት ፕሮቴስታንት ሴቶች ናቸው፡፡ “ሴቶችን ማብቃት” በሚል የጊዜው የማስመሰያ ፈሊጥ ታዛዥ እንስቶችን ራሳቸው ግራ ተጋብተው ሌሎችን ግራ ወደሚያጋቡበት ከፍተኛ የሥልጣን እርከን እያመጡ መኮልኮል እንደፋሽን ተይዟል፡፡ ከነዚህም መካከል በሙያ ብቃት ማነስ ብቻም ሳይሆን በመጥፎ ባሕርያትና ኢ-ሞራላዊ ምግባራት የሚታሙ ተሸዋሚዎች እንዳሉ በስፋት ይነገራል፡፡ አንድም ልምድ የሌላቸውን እመቤት መከላከያ ሚኒስትር አድርጎ መሾም የሚቻለው ደግሞ በማፈሪያዋ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን በእግረ መንገድ መጠቆሙ አግባብ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚሾሙት ኢ-አማራና ኢ-ትግሬ ወጣት ፕሮቴስታንቶች ሲሆኑ የሚመጡት በአብዛኛው ከደቡብ የሀገራችን ክፍል ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ የሚሾሙት ቦታው ላይ ይቀመጡ እንጂ ስለሥራቸው በቂ ዕውቀትና ሙያዊ ሥልጠና የሌላቸው የፖለቲካ ታማኝ ጅሎች ናቸው – ምናልባትም ለኮታና ብሔረሰቦችን ለማስደሰት – “የኔ ሰው እዚህ ቦታ ተቀመጠልኝ” እንዲባል፡፡ በስልክ የሚዘውራቸው ግን አቢያችን ነው፡፡ በአምስተኛ ደረጃ የሚሾሙት በቅርብ ርቀት በራዳርና በስልክ ወይም በራስ ሁነኛ ሰው ምክትልነት የሚመሩ የማንኛውም ነገድ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ናቸው፡፡ የትምህርት ደረጃቸው ዜሮም ሆነ ዲግሪያቸውን በፌክ የትምህርት ሂደትና በፎርጅድም ያግኙት ሹመታቸው ግን ለይስሙላም ቢሆን ያው ሹመት ነው፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ በዘዴያቸውና በተባባሪዎቻቸው ያገኙትን ቦታ ካገኙ በኋላ ወደፍጹም አምባገነንነት እየተለወጡ እንደሆነም ከውስጥ ዐዋቂዎች እየሰማን ነው፡፡ በትኅትና ጥያቄ የሚያቀርቡ የተከበሩ ዜጎችንና ባለሙያዎችን መወረፍ፣ ተናጋሪዎችን እያሸማቀቁ በታዳሚዎች ዘንድ መሣቂያና መሣለቂያ በማድረግ በሰዎች ኪሣራ አጉል ተወዳጅነትን መገንባት፣ ለከባድ ጥያቄዎች ያልተገባ መልስ መስጠት ወዘተ. በጠሚው እየተለመዱ እንደመጡ ይወራል፡፡ ቤተ መንግሥቱ የተረገመ ነው፡፡ እንደምንም ብሎ ወደዚያ የገባ ሰው ባህርዩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጦ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያን ጭምር ራሱ የፈጠራቸው ይመስለዋል፡፡ ከዚህ ነጥብ አንጻር ቀ.ኃ. ሥላሤ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ መለስ ዜናዊና ዶክተር ዐቢይ በብዙ ነገር ይመሳሰሉብኛል፡፡ በመሠረቱ አምባገነኖች በበርካታ ነገሮች መመሳሰላቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ የፈላጭ ቆራጭነት ስሜት የሚጠናወታቸው እነዚህን መሰል ሰዎች ሂስንና ትችትን ይጠየፋሉ ብቻ ሳይሆን ሃያሲዎቻቸውንና ተቺዎቻቸውን እስከመግደልና ደብዛ እስከማጥፋት ይደርሳሉ፡፡ ዕብሪታቸውና ትዕቢታቸው ወሰን የለውም፡፡ የተቀመጡበት ወንበር ዘላለማዊ ይመስላቸዋል፡፡ አጠገባቸው የሚገኝ ዜጋ ሁሉ ከነሱ በታችና እነሱን ለማገልገል የተፈጠረ ያህል ይሰማቸዋል፡፡ በነሱ ቤት እርጅና የለም፤ መታመም የለም፤ ሞት የለም፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ሞኞችም ናቸው፡፡ ራሳቸው በሚፈጥሩት የብዥታ ዓለም (ኢሉዥን) ውስጥ የሚኖሩ አሳዛኝ ፍጡራን ናቸው፡፡ እነሱ ከሌሉ አገር የምትኖር አትመስላቸውም፡፡ የያዙት ሥልጣን የሁሉን ዐዋቂነትና የሁሉን ቻይነት ትምክህታዊ ባሕርይ ስለሚያላብሳቸው ሲሻቸው የህክምና ዶክተር ሆነው መርፌ ሲወጉና ክትባት ሲከትቡ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ሲፈልጉ የእርሻ ኢንጂኔር ሆነው ችግኝ ሲተክና ደን ሲያለሙ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ሲሻቸው የሣኒቴሪ ኢንጂኔር ሆነው ከተሞችን ሲያጸዱ ሊታዩም ይችላሉ፡፡ ከፈለጉ ደግሞ እንደራሽያው ፑቲን አየር አብራሪ ሆነው ኮክፒቱን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ፡፡ ብቻ የማይሆኑት የለም፡፡ እንደሕጻንም፣ እንደጃጀ ሽማግሌም ያደርጋቸዋል፡፡ መቻል ነው፡፡ ወደ ጀመርኩት ልመለስማ ወንድማለም….

ከማንኛውም ነገድ ያሉ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ያላቸው ሰዎች አይሾሙም፡፡ ለምሣሌ ወዳጄ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሣ በምንም መንገድ አይሾምም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው – አንድም ፍቅሬ ኢትዮጵያዊ ነው፤ ሁለተኛም እምነቱ ፕሮቴስታንት ላይሆን ይችላል – ይህን አላውቅም፡፡ ሦስትም ፍቅሬ ትልቅ ሰው ነው – በዐይን ጥቅሻና በስልክ እንደልብ አይታዘዝም፡፡ አራትም በዕድሜና በተሞክሮ ትልቅ በሆኑ ቁጥር የኢትዮጵያዊነት ስሜት አየል ስለሚል ለሹመት አያሳጭም – ሦስተኛዋና አራተኛዋ የትወራ ማዕቀፎች እንደ ዳውድ ኢብሣ ያሉትን የእንጨት ሽበቶች አይጨምርም፡፡ ወዲያም ገልብጡት ወዲህም ገልብጡት እውነቱ ይሄው ነው፡፡ (ይቺን የዳውድ ኢብሣን የኢሊሌ ሆቴል ወጪ ግን ማን ነው የሚሸፍናት… እ? ብዙ ጉዳጉድ ያለበት መንግሥት አለን፡፡ የሚገድላትን የምትጦር፣የሚያድናትን የምትበላ ጉደኛ ሀገር፡፡ ዝቅ ሲል አልኩህ እኮ – ዋናው “አትቀደም!” ነው፡፡)

አቢይ የሚለውን ቢሆን ኖሮ የመንገድ ላይ ትራፊክ ፖሊስ ሳይቀር በፌዴራል ቋንቋ ችሎታቸው መከራቸውን የሚያዩ ሰዎችን በዘመቻ በሚመስል መልክ ከኦሮሚያ ሰብስቦና የገረፍ ገረፍ ሥልጠና ሰጥቶ አዲስ አበባን ባላጥለቀለቀ ነበር፡፡ የቲም ለማ ሰዎች በርግጥም ኢትዮጵያዊነት ሱሳቸው ቢሆን ኖሮ አየር መንገድን፣ ባንክን፣ መከላከያን፣ ፖሊስን፣ ገቢዎችን፣ ምናለፋችሁ ሱቅ እንደገባ ሕጻን ሁሉንም በመመኘትና በመቀራመት የፌዴራል ተብዬውን መዋቅር በሙሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ባልተቆጣጠሩ ነበር – ይህንንም ውሸት ነው በሉና እንደልማዳችን አስቁን፡፡ ቀልድ ለከት ሲኖረው ያምራል፡፡ መሪር ቀልድ እየቀለዱ “ሀገር ሱስ ናት” ማለት ውኃ በማያሰኝ ዱላ ወገብ ዛላን ካነጎዱ በኋላ “አፈር ያብላህ” የሚል ስድብ እንደመመረቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የማን ናት? በግልጽ አማርኛ የኦሮሞው ኦህዲድ ንብረት ናት፡፡ ወያኔ ሳይታወቀው የአንገት ማነቂያ ገመዱን ለኦህዲድ አሳልፎ ሰጠና ራሱም ሊታነቅ ቀናት ብቻ ቀሩት – እመኑኝ እውነቴን ነው – ለአማራ ያጠመደው ወጥመድ ለራሱም ተትረፍርፎ ይደርሰዋል፡፡ ያቺ ገልቱ ሚስት ምን አደረገች ነው እሚባለው – አዎ፣ ባሏን የጎዳች መሰላትና የእግሮቿን መጋጠሚያ በጋሬጣ … እ?፡፡ “ማታ ሲመጣ በዚህ አይደል የሚዝናናው? የታባቱንስና አበለሻሽቼ እጠብቀዋለሁ!” አለችና ንፍዕቲ ወያኒት ራሷን ሆስፒታል አልጋ ላይ አገኘችው፡፡ ሕወሓት “የኢትዮያን ሀብትና ንብረት ዘርፌ በሀገረይ ዋሻዎችና ተራራዎች ግርጌ አከማቻለሁ፤ በዚያውም ‹ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ትግራይ›ን መሥርቼ እስከወዲያኛው ጎጆ እወጣለሁ” በሚል ቀሽም ሂሳብ ታውሮ ከዳር እዳር ተጋሩ የተንሠራፉባትንና ሀብት ንብረት ያፈሩባትን ኢትዮጵያ ለባሰ ጭራቅ ሰጠና ራሱም ሳያስበው ጉድ ሆነ – በ1982 ደራ ላይ የወለደውና ተንኮልን ከግፍና በደል ጋር እየሸረበ በአማራ ጥላቻ ድርና ማግ እየጎነጎነ ያሳደገው ወጣት ዝንጀሮ ከኋላው ሲከተል ከርሞ እርምጃው ከአባቱ ከወያኔ ጋር መስተካከሉን ሲረዳ ኦህዲድ አባቱን ቀምቶ የጌታውንና የፈጣሪውን ሚስት ኢትዮጵያን አገባ – ሁለቱም እናታቸውን አግብተው የሶፎክልስን ድርሰት ዘመን ተሻጋሪ ገጸ ባሐርይ ንጉሥ ኦዲፐስን ሆኑ፡፡ ዋጋቸው ግን አለ፡፡ ታሪክና ትውልድ በሚገባ ይከፍሏቸዋል፡፡ ምድረ አሽቃባጭና አንፋሽ አከንፋሽም አይቀርለትም፡፡ የማይቀር ፍርድን መግለጼ እንጂ መቼ እንደሚሆን አታስዋሹኝ አላውቅም፡፡ ግን ብዙ ሩቅ አይመስለኝም፡፡ ይልቁናስ “ንስሃ እንግባ”ና ወደሀገር እንመለስ፡፡

አሁን ጊዜው የአትቀደም ነው፡፡ በቃ አንተም አትቀደም፡፡ ብትታሰር አሳሪህም አይታወቅም፡፡ አስፈቺም የለህም፡፡ በኪነ ጥበቡ ውለን እንገባለን፡፡ ተገዢው እንጂ ገዢው አይታወቅም፡፡ የጨረባ ተዝካር፡፡ የኳስ አበደች የጥለዛ ወቅት፡፡ ጰራቅሊጦሳዊ የጉሽ ጠላ መሰል ስካር፡፡ ፍርድ ቤት የብላኔ ነው፡፡ ልድገመው – ሀገሪቱ ባለቤት የላትም፡፡ እውነቴን ነው ኢትዮጵያ አሁን አንድም የኔ ነሽ የሚላት ጠበቃ የላትም፡፡ ህጋዊም ይሁን ወንበዴ፣ ማጋጣም ይሁን ወለፈንዴ አንድም አለሁሽ ባይ የሌላት ገደል አፋፍ የቆመች ሀገር ናት – አንዳንድ የዋሆች ቢጨንቃቸው “ወያኔ ይሻል ነበር” የሚሉት ወደው አይደለም – ችግራቸው ይገባኛል፡፡ አይበለውና አንድ የውጭ ኃይል የኢትዮጵያን ስስ ብልቶች ፈልጎ ቦምብ ለማጥመድና በአንዴ ሀገሪቱን ለማደባየት ቢያቅድ ስስ ብልቶቿን – ካሏት – ለማግኘት ለአንዱ ፖሊስ ወይም መከላከያ ትንሽ ገንዘብ መክፈል ይበቃዋል፡፡ ሀገራችን ለገንዘብና በገንዘብ ተሸጣለች፡፡ አዲዮስ! – Ethiopia money can buy – ማለት አሁን ነው፡፡ ሁሉም ወይም አብዛኛው ወጣት በየዘር ቋጠሮው ስለመሸገ የጋራ ሀገር ነገር አይታሰብም – በዚያ ላይ ምዕራባውያን ምሥጋን ይንሳቸውና ትውልዱን በምናምንቴያቸው አጥፍተውታል – እናንተው ዕወቁት፡፡ ከምድር የጠፉት እነሱ ብቻ አይደሉም – እኛንም በሰይጣናዊ ሸቀጦቻቸው አጥፍተውናል – ጫቱ፣ ሲጋራው፣ ሀሽሹ፣ መጠጡ፣ ራቁት ዳንሱ፣ ኢሞራላዊ ስም አይጠሬ ውስልትናው… ሁሉም የብልግናና የነውረኝነት ፓኬጅ ተረባርቦ አብዛኛውን ወጣት ከመስመር አውጥቶታል – የካባሊስቶች የቆዬ ዕቅድም ይሄው ነው፤ ዓለምን በተለይም የዓለማችን ተስፋ የሆነውን ወጣቱን ከፈጣሪና ከነባር ወግ ልማድ በመነጠል በነሱ በምትመሠረት የአዲሲቷ ዓለም ባርያ ማድረግ፤ ይህ ዕቅዳቸው በቅድስቲቷ ኢትዮጵያ ተንቀራፎባቸው ነበር – አሁን ግን ውስጣዊ ትክሎቻቸው እያጣደፉላቸው ነው፡፡ በአውሮፓና አሜሪካ በሚገባ ተሳክቶላቸዋል – የቸገራቸው የምሥራቅ አፍሪካው ቅርንጫፍ ነበር፡፡ አሁን ግን የፓትርያርክ ጽ/ቤትንና ቤተ መንግሥትን ያህል ታላላቅ ቦታዎች ከተቆጣጠርክ ሌላው ቀላል ነው፡፡ ለተጨማሪ ማብራሪያ – Secret Societies in the 20th Century … የሚል ነገር መፈለጊያህ ላይ ጻፍና ጉግል አድርገህ የሚመጣልህን መጽሐፍ መልከት መልከት አድርግ – ምን ይልሃል? ምንም፡፡

በዚያ ላይ ማንበብ የሚባል ነገር – ትምህርት የሚባል ነገር – ዕውቀት የሚባል ነገር በመጨንገፋቸው ከጫፍ ጀምሮ በተለይ ይሄ መከረኛ እንግሊዝኛ መከራውን እያዬ ነው፡፡ ቋንቋ የግንዛቤ ስፋትንና ጥበትን ጠቋሚ መሆኑን ደግሞ አንዘንጋ፡፡ በሌላ ወገን አንድን ቋንቋ አለማወቅ በራሱ ምንም ማለት አይደለም – በምታውቃቸው ሌሎች ቋንቋዎች ዕውቀትን መቅስም ስለምትችል፡፡ አለማወቅን ባለማወቅ የማያውቁትን ቋንቋ ከሚያውቁት ቋንቋ እያዛነቁ/እያቀላቀሉ በጉራማይሌ ውስጥ ያልተገባ ስህተትን መፍጠር ግን በተለይ ለከፍተኛ የሀገር ባለሥልጣናት አይመከርም፡፡ ስለዚህ እባካችሁን ታላላቅ ባለሥልጣናት በምታውቁት ቋንቋ ተናገሩ፤ የብቃት እንጂ የጉድለት አብነቶች አትሁኑ፡፡ ከእናንተ አልፎ እኛንም የሰው መሣቂያ አታድርጉን፡፡ አንዱ የወያኔ ፕሮፌሰር EPRDF has winned the election. ብሎ በሣቅ ከገደለን ወዲህ ብዙ መሰማት ያልነበረባቸው መናኛ ስህተቶችን ስንኮመኩም ቆይተናል፡፡ የእግረ መንገድ መልእክቴ ነው፡፡ እኔ ብሳሳት ግዴለም – ምንም አይደለሁምና፡፡ የኔ መሪዎች ሲሳሳቱ ግን የሚያስተላልፉት ምስል ቀላል አይደለም፡፡ የዱሮዎቹን ባለሥልጣናት እንግሊዝኛ እናስታውስ፡፡ በአማርኛችን ወይ በኦሮምኛችን ወይ በትግርኛችን እንራቀቅ፡፡ እንግሊዝኛውን ስንችለው ብቻ እንናገርበት፡፡ “ፓርላማችን ጉዳዩን equivocally ከተገነዘበው ቆይቷል” ነገር እያላችሁ ግን አታስቁብን፡፡ ወደሩቁ ሄድኩ አይደል? የቅርቡን መጥቀስ የፈራሁ አላስመሰለብኝም? ፈሪ አይጠድቅም፡፡

አሁን “ኢትዮጵያ” ማለት በሀፍረት የሚያሸማቅቅ ሆኗል… ለማንቻውም፡፡ በሌላ በኩል በአፍላ የወረት ፍቅር የተያዘው ኦሮሚያ አማሪያ ትግራይ ….ማለት በኩራት የሚያዘባንን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብትጠበስ ብትቀቀል ስሜት የማይሰጠው የቁቤ ትውልድ (ቄሮም በሉት ኤጄቶ) ሥልጣኑን በተቆጣጠረበት ሁኔታ ፒያሣ ላይ ቆመህ “ማዘጋጃን ላነደው ነበር፤ የትኛው ነው?” ብለህ ብትጠይቅ በጣቱ እየጠነቆለ “ያውልህ!” የሚለው ይበዛል፡፡ “የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ ያድራል” እንዲሉ ሀገሪቱ በደናቁርት መጠላለፍና በሥልጣንና በሀብት ክፍፍል ገብጋባነት ምክንያት ባለቤት አጥታ ወደ ሞቷ እየተጣደፈች ናት – ትንሣዔዋ እውነት መሆኑን መካድ ባንችልም፡፡ ወደዚህች ዓይነት ኢትዮጵያ እደርሳለሁ ብዬ በህልሜም በውኔም አስቤው አላውቅም፡፡

“እንዲህ ሆኜ ነው ወይ ባል እምሆንሽ” አለ አሉ አንዱ፡፡ እንዲህ ሆኖ መንግሥት ሊኮን፡፡ አድምጠኝ! ከፍ ሲልም ሆነ ዝቅ ሲል እንደጠቀስኩልህ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት፡፡ ሕይወት ያለች የምትመስለው በመጠኑም ቢሆን አዲስ አበባ ላይ እንጂ በሌሎች ቦታዎች ልክ እንደዘመነ መሣፍንት ነው፡፡ ጌታና ሎሌው አይታወቅም፡፡ ባለጉልበትና ባለገንዘብ ብቻ የሚኖርባት ሀገር ተፈጥራለች፡፡ ተጠያቂ መንግሥት፣ ጠያቂ ሕዝብ የለም፡፡ በተዓምር ይመሻል፤ በተዓምር ይነጋል፡፡

ምግብ ውድ ነው በሚል ብቻ አይገለጽም፡፡ ሌላ ቃል መፈጠር አለበት፡፡ ዱሮ በወር 300 ብር ለአስቤዛ የምሰጣት ባለቤቴ በቀደምለት እንደምንም አብቃቂው ብዬ ወንድ ወጥቶኝ ከወትሮ አምስት መቶ ብር ጨምሬ 5500 ብር ብሰጣት አጉረመረመችብኝ፡፡ ዝርዝሩን ልትነግረኝ ጀመረች – “መብራት 1000፣ ጤፍ ለ50 ኪሎ 1650፣ ዘይት 800፣ በርበሬ ….” ብላ ልትቀጥል ስትል በህግ አምላክ ብዬ አስቆምኳት፡፡ ከቀጠለች የቀጣዮቹን ስድስትና ስምንት ወሮች ደመወዜን በብድር ወስጄ ብሰጣትም ዝርዝሩን እንደማልሸፍነው ተረዳሁ፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የምንኖረው? በኪነ ጥበቡ! አሁን አንድ በሬ የሚገዛበት ገንዘብ በልጅነቴ አሥራ አምስት ቪላ ቤት ሠርቶ ሃምሣ ድል ያሉ ሠርጎችን ይደግስ ነበር – ያኔ በብር 25 እና 30 ኩንታል ነጭ ጤፍ በሚገዛበት ደግ ዘመን፡፡ ከተማዋን ስትዞር ብትውል በብዙ ማደያዎች ነዳጅ የለም – ቢኖርም በወረፋና በውድ ዋጋ ነው – የመኪና ቤንዚን ባገር ዋጋ 21.34፡፡ አንዳንዴ ሲቸግርህ በዕውቅ ሰው የተሰረቀ ቤንዚን በሊትር ሃምሳና ስልሳ ብር ገዝተህ ጉዳይህን ትፈጥማለህ፡፡ … በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከገባችበት ማጥ እስክትወጣ ከእንግዲህ ለጤንነቴ ስል ዝም ብል ነው የሚሻለኝ፡፡ “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ነው” እሚባል፡፡ ችግራችን ደግሞ በንግግር እንደማይፈታ አውቀናል፡፡ ስለዚህ ወዳጆች ካላችሁኝ እንዲያስችለኝ ጸልዩልኝ፡፡

በምኖርባት አዲስ አበባ መብራት በፈረቃ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በፈረቃም አለፈረቃም መብራት እንደማያገኙ ይናገራሉ፡፡ መብራት ኃይል ሠራተኞች ሲፈልጉ በአካባቢህ ይመጡና አጥፍተውብህ ይሄዳሉ፡፡ ለማሰቀጠል ጉቦ መክፈል አለብህ፡፡ በማኅበርም አዋጣ፣ በቅሬና በድርጅትም ይከፈላቸው ደንታቸው አይደለም፡፡ ሰው የተያያዘው ከችግሩ ማምለጡን እንጂ ህግና ክስ ስለሌለ የሚፈራቸው የለም፡፡ የመብራ ፈረቃውን ስታይ ደግሞ ተንል እንዳበት ትረዳለህ – ሕዝብን የማማረር ተልእኮ፡፡ ጧትና ማታ መብራት እንዳይኖርህ ታልሞ የተደረገ ሤራ ነው፡፡ በዜጎች ላይ የሚያስከትለው ኪሣራ ደግሞ ይታይህ፡፡ ሥራቸውን ካለኤሌክትሪክ የማያከናውኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከሠሩ፡፡

ውኃ ካለባቸው አካባቢዎች የሌለባቸው ይበልጣሉ፡፡ የውኃውም ጥራት በኢትዮጵያ ለሰው መጠጥ፣ በአፍሪካ ለእንስሳት መጠጥ፣ በአውሮፓ ደግሞ ለተክሎች እንኳን የማይሆንና የማይመከር ነው፡፡ የቧምቧህ አፍ ባይጠባቸው ውኃ ስትከፍት በጭቃ የተለወሱ ዕንቁራሪቶች የደቀንከውን ባልዲ ወይ ሸንኬሎ ሊሞሉት ይችሉ ነበር፡፡ እሱም በወረፋ ነው፡፡ ክፍያው ደግሞ የመብራቱም ሆነ የውኃው ሌላውም የመንግሥት ድርጅቶች የአገልግሎት ዋጋ ሁሉ ሰማይ ነው፡፡

ሀኪም ቤት የለም፤ ሀኪምም የለም፡፡ እየሮጥክ በእግርህ ወይ በመኪናህ በገባህበት ሆስፒታል በተሳሳተ ህክምና ይገድሉህና ቤተሰቦችህ ሬሣ እንዲወስዱ ሊጠሩ ይችላሉ – ሊያውም ብዙ ሽህ ብር የግድያ ካሣ ከፍለው ነው ሬሣውን የሚወስዱት፡፡ የምትገርም ሀገር፡፡ ደርግ የገደለበትን ጥይት እያስከፈለ ሬሣን ለወላጅ ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ገድለው ሲያበቁ ሃምሳና መቶ ሽህ ብር ሽልማት ይገባናል ሲሉህ አያፍሩም፡፡ ለአልጋ የሚጠይቁት ደግሞ የአንዳንዶቹ ከሸራተንም በላይ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂ የለም፡፡ዘይቱ ፎርጅድ፣ ቅቤው ፎርጅድ፣ ማሩ ፎርጅድ፣ እንጀራው ጀሶ፣ በርበሬው ሸክላ፣ ልብሱ ሻማ፣ ጫማው ነዲድ፣ ዳኛው ጉቦኛ፣ መስተዳድሩ ቀበኛ፣ ጌታው ሸረኛ፣ ሎሌው አድመኛ ኤዲያ…. በአገርህና በቀየህ ሰላም መኖር ዱሮ ቀረ፡፡ የዕቃ ዋጋና የአገልግሎት ክፍያ ሲተመን ደመወዝና የወር ገቢ ታሳቢ ተደርጎ አይደለም፡፡ በደም ፍላትና በስሜት ነው፡፡ በድንቁርናም ነው፡፡

መንገድ የለም፤ ሊሠራ ከሆነም አንድ ወር የማይፈጀው አጭር መንገድ ለዓመታት እየተኙበት ሕዝቡን ከተሸከርካሪ ጋር ያጨናንቁታል፡፡ ያሉት መንገዶችም በተለይ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓቶች … ኧረ ከዚያም ውጪ… ዝግትግት ያሉ ናቸው፡፡ በእግርህ ብትሄድ ይሻላል፡፡ በመኪና የአሥር ደቂቃው መንገድ ሰዓታትን ሊፈጅ ይችላል፡፡ አምቡላንሶችና የእሳት አደጋ መኪኖች በዚህ መሀል እንደጀት ተወርውረው ነው እንግዲህ ወላድና ታማሚን ወደህክምና ጣቢያዎች የሚያደርሱት፤ በሴከንድ ብዙ ንብረት ቡን የሚያደርግን ሰደድ እሳት “በፍጥነት ደርሰው” የሚያጠፉት፡፡ ጉድ ነው ዘንድሮ!
ሠራተኛ ሥራ ገባ አልገባ የሚቆጣጠር የለም፡፡ ደመወዙም አይረባም፤ ሥራውም አይረባም፤ የሀገር ፍቅር ስሜትም የለም፤ ሁሉም ሞቶ ሀገር በደመ ነፍስ … በ inertia… እየተጓዘች ናት፤ ወረደ መቃብሯም በኦህዴድ ካህናት፣ በሕወሓት ጳጳሣትና በብአዴን ታዛቢነት እየተከናወነ ነው፡፡ በጥቅሉ የዞምቤዎች ሀገር ሆናልሃለች – ኢትዮጵያ፡፡ ደግሞም ልብ በል – ካልሁት ያላልሁት ይበልጣል፡፡
ትምህርቱም ቆሟል ማለት ትችላለህ፡፡ ለነገሩ ስሙን አስተካክሎ የማይጽፍ የዲግሪ ተመራቂ አገር ምድሩን ከሞላው ወዲህ የትምህርቱ መቆም ግልጽ ነበር፡፡ አሁን የሚሰማው ደግሞ ለጆሮም የሚቀፍ ነው፡፡ የአንድን ክልል ተማሪዎች በብዛት ለማሳለፍና ከፍተኛ የትምህርት ተቋትን በአንድ ነገድ ተማሪዎች ብቻ ለመሙላት የተጠነሰሰ ሤራ እንዳለ ተጋለጠ አሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ለምሣሌ ዛሬ 12ኛ ክፍሎች ሲፈተኑ ኢንተርኔት ዝግ የነበረው – ግን መልሱ ቀድሞ ተላልፎ ቢሆንስ? ሁሉ በጃቸው ነው፡፡ የልብን ከሠሩ በኋላ ለይምሰል ኢንተርኔት ቢያጠፉ እውነቱን ነገ እናየዋለን፡፡ ደግሞም የኢንተርኔትን መጥፋት ብናይ ብዙ የዞረ ድምር አለው፡፡ ብዙ መሥሪያ ቤቶች ካለ ኢንተርኔት አይሠሩም – ኖሮም አልሆነላቸው እንኳንስ ጠቅላላውን ተዘግቶ፡፡ ትንንሽ ኢንተርኔት ካፌዎችም እንጀራቸው ተዘጋ፡፡ እነአቢይ ይህችን ሀገር ማስተዳደር አልቻሉም – ባጭር ቃል፡፡ አታሞ በሰው እጅ…

… ይህችን በአድልዖና በዘረኝነት ያጠነቧትን ኢትዮጵያ እየመሩ ነው እንግዲህ “ኢትዮጵያ ሱሴ ናት” እያሉ የሚያጨናብሩን፡፡ ሀፍረትን መሸጥ እንዲህ ነው፡፡ ሣልሣይ ወያኔ በ‹ፊንፊኔ› – ኦህዲድ፡፡
አንድ መሠረታዊ ነጥብ ላክል – ስለቋንቋ፡፡ አማሮች አማርኛን ይዘው ከምድረ ገጽ ቢጠፉ እመኑኝ ኢትዮጵያም አብራ ትጠፋለች – የምሬን ነው፡፡ ትግሬዎች ለምን በትግርኛ አልገዙም? ኃይል አጥተው? ብልጠት አጥተው? ይሉኝታ ይዟቸው? በፍጹም! የጋራ ቋንቋ በስሜትና በዐዋጅ አይገኝም፡፡ የጋራ ቋንቋ ስለጠላኸውና ስለወደድከው አይገኝም ወይም አይጠፋም፡፡ ሽንት ቤት ተቀምጠህ ምንትስ ገማኝ ልትል እንደማትችል ሁሉ የጋራ ሀገር እያስተዳደርክ የ87 ጎሣና ነገድ የጋራ ገንዘብ የሆነውን አእምሯዊ ንብረት ጠልተህ በራስህ ልትተካ ብትሞክር የመታነቂያ ገመድህን በራስህ እየፈተልክ መሆንክን መረዳት አለብህ፡፡ የጋራ ቋንቋ በአንድ አዳር አይገነባም፤ በአንድ ጀምበርም አይሰረዝም – የራሱ ህግ አለው፡፡ በአንድና በሁለት የቁጩ ምርጫዎች ሥልጣን መያዝም አትመሠርተውም፡፡ እውነቱ እንዲያ ቢሆን በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የሥራም በሉት የፌዴራል መግባቢያ ቋንቋ ትግርኛ በሆነ ነበር፡፡ አንድን ቋንቋ ከነተናጋሪው አምርረህ ልትጠላው ትችላለህ፡፡ ተናጋሪውን ከምድረ ገጽ ልታጠፋው ትችልም ይሆናል፡፡ የቋንቋውን አገልግሎት ለመተካት ግን ሽዎች ዓመታትን መጠበቅ ሊኖርብህ ነው፡፡ ስለዚህ ነባራዊ እውነት ቅንጣት ግንዛቤ የሌላቸው ደናቁርቱ የኦህዲድ ካድሬዎች አማርኛን በኦሮምኛ ለመተካት ቀን ከሌት ሲደክሙ ይታያሉ – በበኩሌ ይህን ጥረታቸውን አደንቃለሁ፤ አልቃወምም – ግን መንገዳቸው የተሳሳተ በመሆኑ አርመውና አስተካክለው ቢጓዙ ደስ ይለኛል፡፡ ቀን ሰጠኝ ብለህ ስለተስገበገብክ አንድም ነገር አይሳካልህም፡፡ በአስተውሎትና በብልኃት ከተራመድክ ግን ይሳካልሃል፡፡ “አስተውሉ” እላለሁ፡፡ አለበለዚያ አወዳደቃቸው አያምርም፡፡ እየተጣሉ ያሉት ከአማራው ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ከሁሉም ጋር ነው፡፡ አማርኛ ተነገረ አልተነገረ ላማሮች ምንም ማለት አይደለም፡፡ አማርኛን ለማጥፋት የሚነሣ ጠላት ማፍራት የሚጀምረው ከራሱ ጎሣ ውስጥ መሆኑ ደ’ሞ ይታወቅ፡፡ አማርኛ ለሁሉም ስለሚያስፈልግ እንጂ ለቅንጦት የሚነገር ቋንቋ አይደለም፡፡ ስለዚህ አማርኛን ከአማሮች ለዩ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ቋንቋ ማለት የሰው ልጅ የወል ሀብት እንጂ የአማራ፣ የትግሬና የኦሮሞ የምትለው ነገር አይደለም፡፡ ይሄ የኔ ያንተ የሚባለው በቋንቋ አይሠራም – በትንሹ አላዋቂነት ነው፡፡ ሱማሊው ከአፋሩ በምን ይግባባ? ደራሳው ከኮንሶው በምን ይነጋገር? ሌሎቹስ ከሌሎቹ ጋር ሃሳባቸውን በምን ይለዋወጡ? … ነው እንደኦቦ በቀላ ገርባ “ነጋቲ ቡላ” ተባብለው በ“ዳቦው ተገመሰ፤ ጨዋታው ፈረሰ” የልጆች ጨዋታ ዓይነት የተለያዩ ቁጫጭ መንግሥታትን ይመሥርቱ? ምን ዓይነት እርጉም መንፈስ ነው በነዚህ ሰዎች የገባው? የጋራ ቋንቋ ጦጣኛም ይሁን ዝንጀሮኛ ሁሉንም እስካግባባ ድረስ መሸለምና መወደስ ሲገባው መወገዙና መረገሙ ለምን ይሆን? ከዚህ በላይስ ሞኝነት የት ይገኛል? እንዴት ያለ ድውይ አስተሳሰብ ነው በቤተ መንግሥት አካባቢ የሚታየው? መሻሻልን ስንጠብቅ እየባሰበት የሄደው ምን እንድንማር ተፈልጎ ይሆን? እዚህ ላይ መጠርጠር ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከንቱነት የመጣው እንድንማርበት መሆን አለበት፡፡ ማን ለማን እንደሚበጅ፣ በአንጻራዊነት የትኛው ከየትኛው እንደሚሻል እናውቅ ዘንድ ፈጣሪ የፈቀደውን ይህን ፈታኝ ዘመን እንድናልፈው የታዘዘ ያህል ይሰማኛል፡፡ ስትሞት ዐፅምህ ብቻ ለሚቀረው አሁን በቋንቋ መጣላት የጤና አይደለምና ኦህዲድ ሆይ አቅል ጀባ፡፡

ከዚህ አኳያ “አሁን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ኃይል፣ አሁን ኢትዮጵያውያን ለይቶላቸው በገሃድ እንዳይጠፋፉ እንደነገሩም ቢሆን አውሎ የሚያስገባቸው ተዓምር ምንድን ነው?” ብለን ስንጠይቅ ብዙዎቻችን መልሱን በቀላሉ ላናገኝ ወይም የሚመስለንን የተለያየ ግምት ልንሰጥ እንችላለን፡፡ አንዳንዶቻችን ግን የፈጣሪ ኃይል እንደሆነ እናምናለን፡፡ ካለፈጣሪ ጣልቃ ገብነት ይህ ሁሉ ግፍና በደል በዜጎች ላይ በየዕለቱ እየተፈጸመ ሀገርና ሕዝብ በ“ሰላም” ውለው ማደራቸው ከተዓምር የሚተናነስ አይደለም፡፡ ምናልባትም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም “ኢትዮጵያ ብትወድቅም መነሳቷ አይቀርም” እየተባለ በብዙዎች የሚነገረውና የሚታመነው፡፡ ለዚህ አባባልና ሕዝባዊ እምነት ታሪክ ራሱም ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያችን በየዘመናቱ ብዙ ጊዜ ወድቃ የመነሣቷ ምሥጢር ፈጣሪዋ ጥሎ እንደማይጥላት አመላካች ነው፡፡ እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ከአስመሳይ መሲሖችም ይጠብቅልን፡፡ የተበተንነውን ይሰብስበን፤ የመልካም ትንቢቶችን ፍጻሜ ያሣየን፡፡ gb5214@gmail.com

Filed in: Amharic