>
5:57 pm - Sunday July 3, 2022

የመብራት የመጥፋት ትዝታ!! የቀጠለ (በእውቀቱ ስዩም)

የመብራት የመጥፋት ትዝታ!! የቀጠለ
በእውቀቱ ስዩም
ከጥቂት አመት በፊት የረር በር እኖር ነበር፤አንድ ቀን መብራት በጊዜ ጠፋ፤እስከ እኩሌሊት ድረስ ስላልመጣ ተስፋቆርጠን ተኛን፤ ዘጠኝ ሰአት ላይ ሚስቴ ቀሰቀሰችኝና ወደ  ምኝታቤቱ መስኮት ጠቆመችኝ፤ የሆነ ግዙፍ እጅ ጥላ  መስኮቱን ሲዳብስ ይታየኛል፤
“ሌባ ነው?” አልኩዋት፤
ራሱዋን ባዎንታ ወዘወዘች፤
“መስኮቱን ምን እያረገው ነው?” አልሁ እምለው ጠፍቶኝ፤”
“እየወለወለው” አለችኝ በብሽቀት በሹፈት፤
( እኔ ግን እንዲህ አይነት ደደብ ጥያቄ እንዴት እጠይቃለሁ?)
ወድያው ኡኡኡ ማለት ጀመረች፤ መጀመርያ እማደርገው ነገር ጨንቆኝ ተገትሬ ቀረሁ፤ሱሪየን ለመታጠቅ ስሞክር የግሬን ማስገቢያ ሶስት ጊዜ ሳትኩት፤ ሚስቴ “ ጋሽ ኤባ! እትየ አምሳለ! አቶ ዮፍታሄ !ኡኡ ድረሱልን!  ሌባ ሌባ ትላለች!”  እኔም የበኩሌን ለማድረግ ሞከርኩ ፤ ጉሮሮየ ትንሽ ተግደረደረና  በመጮህና በመፎከር መሀል የሆነ ነገር ለጎረቤት  አስተላለፈ፤
(አቤት  ይሄኔ አባቴ ቢሆን ኖሮ! ድሮ ልጅ እያለሁ፤ አባቴ ሌባ የሳሎኑን በራችንን  ሲሰረስር ከሰማ፤ ብንን ይልና እናቴን “ እሽሽሽ ! አደራ  ጮሀሽ እግዜር በስንት መከራ የመጣልኝን  ቀማኛ እንዳታስመልጭብኝ” ይላታል፤ከዚያ በጉዋሮ በር  ሾከክ ብሎ ይወጣና ኮቴውን አጥፍቶ፤ ከሌባው ጀርባ መጥቶ በሾኬ መቶ ይጥለዋል ፤ከዚያ እኛን ከጣፋጭ እንቅልፋችን ቀስቅሶ ይዞን ይወጣና ፤” አያችሁ ልጆች?  ተግታችሁ ካላጠናችሁ እንደዚህ ሌባ ትሆናችሁ” በማለት ተግሳፅና ምክር ይለቅብናል፤ ሌባው  ፌይንት ካደረገበት  ሲነቃ አባየ ሌባውን ቁልቁል  በንቀት እያየው” እናስ አንት ሞላጫ!  ነገ ባደባባይ  ድንጋይ ተሸክመህ ይቅርታ ትጠይቀኛለህ ፤ወይስ  አሁን ድንጋዩን  ደረትህ ላይ  እንድፈልጥ ትፈቅድልኛለህ?” ይለዋል! አይ አባየ! አይ ቆራጥ!
አሁን ወደ እኔ ስመለስ በፉከራና በጩከት መካከል የሆነ ድምፅ አወጣሁ፤ሚስቴ  ግን እሪሪሪታውን በተለያየ ቅኝት እየለቀቀችው ነው! ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ግቢያችን በፈጥኖ ደራሽ ጎረቤት ተወረረ፤ሌባው በበጀት እጥረት ምክንያት  የሰርከስ ኢትዮጵያ የተቀነሰ ሳይሆን  አይቀርም፤ በልብስ ማጠቢያ ጎማ ላይ ነጥሮ፤ ግንቡን በቅልጥፍና ዘሎ አቀጣጥኖታል!
ከሰፈራችን  ትጥቅ የሌለኝ እኔ ብቻ መሆኔን ያንቀን ተረዳሁት፤ እነፌሮ  እነ ከዘራ   ሳይቆጠሩ በግቢያችን ውስጥ ሁለት ክላሽ አንድ ኡዚ ታየ፤ ጎረምሶች ትከሻየን እየዳበሱ አበረታቱኝ፤ሴቶች ሚስቴን አፅናኑዋት፤
የማረጋጋቱ ስራ በጥሩ ሁኔታ እንደቀጠለ አንድ ነገር ተፈጠረ ፤ ጋሽ ኤባ ሳቃቸውን በጋቢያቸው ለማፈን እየሞከሩ  “ለመሆኑን እሱን ምን ልታረገው ነው የያዝከው?” አሉኝ
 አይኔ ወደ ቀኝ እጄ  ላክሁት፤ለካ በድንጋጤ፤ ትራሴን ይዤው ወጥቻለሁ፤
የግራ  ጎረቤታችን  ወይዘሮ አምሳለች እንዲ ሲሉ ሰማሁዋቸው፤
“ ሌባውን አፍኖ ሊገልበት ይሆናላ እንግዲህ”
የማብራትና ማጥፋት ወግ!!! – (የመጨረሻው ክፍል)
ባገራችን፤ በባላባት ስርአት ወግ  “ፈናወጊ “ የተባሉ አገልጋዮች ነበሩ፤የስራ ድርሻቸው ፋኖስ፤ አንዳንዴም ጡዋፍ  ይዞ መቆም ነበር፤ራት ላይ ከጌቶች እና ከእመቤቶች ማእድ ትንሽ ፈንጠር ብለው ቆመው ያበራሉ፤ በቤተመንግስት ውስጥ መብራት ተሸክመው የሚያነጉም  ነበሩ፤የመጀመሪያዎቹ የመብራት ምስሶዎች ነበሩ ማለት ይቻላል፤
ታድያ አንዳንዴ፤ ከውሃ ልማት ድልድይ ተነስቼ፤  ሽቅብ ወደ እንግሊዝ ኢምባሲ የሚያወጣውን አስፋልት ተከትየ ስራመድ፤ የግረኛው መንገድ ዳር ተደርድረው የቆሙ የመብራት ምሶሶዎችን እመለከታለሁ፤ብርሃን የሚባል ነገር  አይደማቸውም፤ ላለፉት አምስት አመታት አንድ ቀን እንኩዋ ሲያበሩ አይቻቸው አላውቅም፤ “ የኢትዮያ መጥፋት ሃይል ባለስልጣን ለምን እንደማያስጠግናቸው ካልሆነ ደሞ የመሸበት ሰካራም እንዳይፈነክቱ ለምን እንደማይነቅላቸው አይገባኝም፤ በነሱ ቦታ ከመብራት ሃይል መስርያቤት ሰራተኞች መሀል ረዘም ረዘም ያሉት ተመርጠው፤ ሶላር ባውዛ አንጠልጥለው እንዲቆሙ ቢደረግ ተገቢ ነው እላለሁ፡
ከማንኩሳ ምርቃት አንዱ “እራትና መብራት ይስጣችሁ” የሚል እንደነበር የሆነ ቦታ ጠቅሻለሁ፤ይህ ባለም አንደኛ ምርቃት መሆኑን ኖረህ ያረጋገጥከው ይመስለኛል፤ጨለማ ከሚፈልፍላቸው ጉዶች አንዱን እንሆ! ( ማሳሰቢያ፤ ቀጣዩ ጨዋታ የቅሌት የምንዝርና የምኝታ ነገር አለበት፤ እንዲህ አይነት ጨዋታ አይመቸኝም ካሉ፤ ከዚህ አንቀፅ ይመለሱ፤)
 እስካሁን እዚህ ነዎት?
ሰውየው የስማልባ ቀበሌ የገበሬዎች ማሀበር ሊቀመንበር ነው፤ይቺም ስልጣን ሆና ይባልግባታል፤ ቀን በቀበሌው ውስጥ የሚኖሩ  ኮማሪዎችን ጋር አለሙን ይቀጫል፤ ሲመሻሽ፤ በካቲካላና በቆነጃጅት ገላ ራሱን አዳክሞ ታጥቦ የተጠመዘዘ ፒጃማ መስሎ  ፤ወደ ቤቱ እየተጎተተ ይገባል፤  ሚስቱ ፍቅርና ድርያ አምሩዋት ስትጠጋው ይሸሻታል፤ “ አንቱ  እማያቅፉኝ ምን ሁነው ነው? “ስትለው “ አሃ! የጥርስ መፋቂያ አደረግሺው እንዴ?  ጠቦት በግ ታርዶ  እንደተገረዝኩ ማን በነገረሽ ” እያለ ያካብዳል፤ ከዚያ ጀርባውን ሰጥቱዋት እንቅልፉን እየለጠጠ ስለተጨማሪ ሹመት ሲያልም ያድራል  ፤ ሚስት ደግሞ ወጣት ነች፤እሸትም ነች! መታሸት ትፈልጋለች ፤ቢቸግራት  አይኑዋን ከፍታ ዙርያዋን መቃኘት ጀመረች፤ ቤት ውስጥ አንድ የተቀጠረ እረኛ አለ፤ ሸጋ  ጎረምሳ ነው፤ የደረቱ ስፋት  መስቀል አድባባይ ነው፤የክንዱን ብርታት ልገልፀው አልሁና ደከመኝ፤ አንዳንዴ ገደል ወድቆ የተሰበረ በሬ  ሲያገኝ፤ እንደ ህፃን ልጅ  በደረቱ አቅፎ፤ ከብት ሀኪም ቤት ያደርሳል፤   ይህ ሸጋና ብርቱ እረኛ ቀን ቀን ከብት ሲያግድ ፤ ውሎ ማታ ማታ  የባልና ሚስቱን ምኝታቤት በሚያዋስነው በረት ውስጥ ከጥጆች ጋር ይተኛል፨
ቀስ በቀስ፤ሚስት እና  እረኛው ንቀትና  ቸል መባል አግባባቸው፤ የተፈጥሮ ግፊትም አቀራረባቸው፤  ባይን ጥቅሻ  በስሜት ተግባቡ፤ማታ ማታ ፤ሚስትዮ ወደ በረቱ  ጀርባዋን ዞራ መተኛት አመጣች፤ እረኛው ፈተናውን አልቻለውም፤ አንድ ምሽት ከእምርቱ ራስጌ  ዝቅ ተመለከተ፤ጭኑ መሀል አማራጭ ክንድ የመሰለ ነገር ተዘርግቶ ተመለከተ፤ያንን በበረቱ ፍርግርግ አሾልኮ ሰደድ አረገው!
ይኸኔ_ከዚያስ? ከዚያስ ይላል አንባቢ፤
“ከዚያ ወድያማ
ከዝያ ወድያማ
ምን ልንገራችሁ
ታውቁት የለም ወይ፤ በየቤታችሁ” የሚለውን የባላገር ዘፈን ጠቅሰን ዝርዝሩን እንዝለለው፤ አንድ ምሽት ላይ ባልየው ከንቅልፉ የሆነ ድምፅ ቀሰቀሰው፤ ሚስቱ የእልልታና የእሪታ ድብልቅ ድምፅ ታወጣለች፤
“ምን ሆነሽ ነው እምታለከልኪ?”
“ጥጃው እግሬን እየላሰኝ ነው እንጂ”
ባልየው “ ቆይ ቦታ ልቀይርሽ አለና እሱዋ በምተኛበት ቦታ ጀርባውን ለበረቱ ሰጦ ተኛ፤
ጨለማ ነው፤ ኩራዙ ወድሙዋል፤ ምድጃው ከስሙዋል፤የሆነ ለውጥ አለ፤ እረኛው ለውጥ መኖሩን የሚረዳበት ሁኔታ አልነበረም፤
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባልየው “  ኣኣኣኣኣ” ብሎ አቃሰተ፤
“ አንተንም ጥጃው ላሰህ”
“አይ እኔን እንኩዋ በቀንዱ ነው ያገኘኝኝ”
እራቱስ ግዴለም! መብራት አይንሳችሁ ወገኖቼ!
Filed in: Amharic