>

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የተከተሉ አልነበሩም !!! (አምንስቲ ኢንተርናሽናል)

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የተከተሉ አልነበሩም !!!
አምንስቲ ኢንተርናሽናል
DW
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አምንስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ያወጣቸው የምርመራ ሪፖርቶች “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ማዕቀፎችን እና ደረጃዎችን የተከተሉ አልነበሩም” አለ። በፍትህ ላይ የሚፈጸሙ መዛባቶችን ለማስተካከል በመንግስታዊው የሰብዓዊ ተቋም ላይ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት አምንስቲ አሳስቧል።
አምንስቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በጎርጎሮሳዊው 2016 እና 2017 ዓ. ም. የታተሙ ሰባት የኮሚሽኑን የምርመራ ሪፖርቶችን መፈተሹን ገልጿል። ኮሚሽኑ ተፈጸሙ በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራዎችን ሲያደርግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ የሰብዓዊ መብት ማዕቀፎች እና ደረጃዎች ውጭ ይንቀሳቀስ እንደነበር በፍተሻው ደርሼበታለሁ ብሏል። ኮሚሽኑ ለምርመራ በተከተላቸው ዘዴዎች እና በምርምራ ግኝቶቹ ላይ “ጉልህ ክፍተት” ማግኘቱን አምንስቲ በመግለጫው ጠቁሟል።
ከተፈተሹት ሪፖርቶች መካከል ሁለቱ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በነበሩ ተቃውሞዎች ላይ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በመዳሰስ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡ ናቸው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጠየቀው መሰረት በእስር ወቅት ተፈጸሙ የተባሉ የማሰቃየት ድርጊቶች እና መጥፎ አያያዞችን የመረመሩ አራት የኮሚሽኑ ሪፖርቶችን አምንስቲ ተመልክቷል። ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ስላሉ እስር ቤቶች ሁኔታ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ያስገባውን ሪፖርት መፈተሹንም አምንስቲ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጸጥታ ኃይሎች ተፈጸሙ የተባሉ ጥሰቶችን በጥልቀት ከመርመር እና ከማጋለጥ ይልቅ ሌሎች አካላትን ለመወንጀል እንደሚፈጥን አምንስቲ በዳሰሳው ተመልክቷል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የተወካዮች ምክር ቤት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደረሶብናል ያሉ ተጠቂዎች ሳይቀር በውንጀላው ተካትተው መገኘታቸውን አምንስቲ ይፋ አድርጓል።
የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ጆአን ናያናዩኪ“ኮሚሽኑ በተጠቂዎች ላይ ያለው ያፈጠጠ አድልዎ እና ቅሬታዎቻቸውን የማጣጣል አቋም በተቃውሞ ግድያዎች እና የእስር ቤት ሁኔታዎች በተመለከቱ ሪፖርቶቹ፤ ለተጠቂዎች እና በሀገሪቱ ላሉ ሁሉ ነገሮችን ለማስተካከል የነበረውን ዕድል ያመከነ ነው” ብለዋል በመግለጫው።
ኢትዮጵያ “ቀድሞ ከነበረችበት የጭቆና አካሄድ ለመላቀቅ እየሞከረች ባለችበት በዚህ ወቅት ኮሚሽኑ ያንን ዓላማ ለማሳካት ብቁ አይደለም” ያሉት ዳይሬክተሩ “ኮሚሽኑ የአዲሱ መንግስትን የሰብዓዊ መብት አጀንዳዎች እንዲደግፍ እና አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች እና ጥሩ ተሞክሮዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት ግድ ይላል” ሲሉም አሳስበዋል።
Filed in: Amharic