>
5:01 pm - Monday December 3, 0604

ኧረ የመካሪም የአማካሪም ያለህ? (ዘመድኩን በቀለ)

ኧረ የመካሪም የአማካሪም ያለህ?  
     ዘመድኩን በቀለ
• ለእኔ ሰኔ 20 ም ሆነ ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ ክቡር ህይወታቸውን በከንቱ ሲገብሩ የኖሩበት ዘመን ያበቃበት ቀን ነው።
የአቢቹ ደብዳቤ ደስ አትልም። አንዳንዴም እኮ ባላየ ባልሰማ ይታለፋል። ኧረ የአማካሪም የመካሪም ያለህ። 
 የኢትዮጵያዬ ጠቅላይ ሚንስትር የእኔው ጉድ ጠሚዶኮዬ አቢይ አህመድ የኤርትራ ተገንጣዮች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ያለፉበትን ቀን በማስመልከት ለኤርትራው አቻው ለአይተ ኢሳይያስ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ አለ። [ የሚበሰጨው ደብዳቤው የተጻፈው በታላቋ ሀገር በኢትዮጵያ ስም መሆኑ ነው]።
••• ደብዳቤው
የተከበርከው የኤርትራ ህዝብ በሙሉ፤ ለሰማእታት ቤተሰቦች ደሞ በተለየ፤ ሰኔ 20 እነዚያ ሀገር ለምፍጠርና ለመጠበቅ ሲሉ የተሰዉ የኤርትራ ሰማእታት የሚከበሩባት ቀን ናት። የሀገር ባለቤት ለመሆን በሰማእታት ደምና አጥንት ከፍለህ እንጂ እንዲሁ በብላሽ አይደለም። ሀገርን ማነፅና መጠበቅ ደግሞ በሰማእታት ክብር ይደምቃል። የትናንት ሰማእታትን ውለታ የሚረሳ ህዝብ ዛሬም ነገም ጀግኖች አይኖሩትም። ስለሆነም የኤርትራ ህዝብና መንግሥት የትናንት ሰማእታቶቻችሁን ማከበራቹችሁ ተገቢና ትልቅም ነገር ነው።
•••
የኤርትራ ሰማእታት ቀን ሌላም ተጨማሪ ክብር አለው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ካባለፈው ዓመት ጀምሮ አዲስ አመራር ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ላቀረበችው የሰላም ጥሪ ክቡር ፕሬዚደንት ወንድም ኢሳያስ አፈወርቂ በሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረዉን የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስና ህይወት እንዲዘራ ያለው ዕድል ለሁለቱም ህዝቦች የተበሰረበት ዕለት መሆኑ ነው። ስለሆነም የሰማእታት ቀን ኤርትራ ያለፈዉን መስዋእት የሚከበርበት ቀን ብቻ ሳይሆን መጪው የህዝቦች ተስፋም የተበሰረባት ዕለተና ተስፋም ጭምር ናት። ይሄን የሚለው የኢትዮጵያዬ ችግኝ ተካይ መሪዬ ነው።
•••
በታሪክ የኢትዮጵያ መሪ ሆኖ በጠላትነት ተነስቶ ኢትዮጵያም ላይ ጦር ሰብቆ የኢትዮጵያን ወታደሮች ለገደለ፣ ላዋረደ፣ በአደባባይም ከመኪና ኋላ በገመድ አስሮ ለጎተተ፣ ጥርስና ፓንት ሳይቀር ነቅሎና እስወልቆ በግፍ ላባረረ፣ የማረካቸውን የኢትዮጵያ ወታደሮች በጅምላ ለረሸነ፣ በእሳት ላቃጠለ፣ በወኅኒ ላበሰበሰ፣ እስከዛሬም ድረስ በከባድ የጉልበት ሥራ ላይ ላሰማራና ጠላት ነኝ የጠላት ሀገርም መሪ ነኝ ለሚል ድርጅትና ሀገር እንኳን የኢትዮጵያንም ሠራዊት ሲዋጉ ለወደቁት፣ ለሞቱትና ሰማዕታት ለተባሉት ለታጋዮችህ የሞት ቀን አደረሰህ፣ እንኳንም ደስ ያለህ የሚል ኢትዮጵያዊ መሪ አይቼም፣ ሰምቼም አላውቅ።
•••
ግንቦት 20 የእኛዋ ህወሓት ወንድሞቿን ገድላ የነገሰችበት ስለሆነ እንኳን ወንድም ወንድሙን ለገደለበት ቀን አደረሳችሁ አልልም ብሎ ጮቤ ያስረገጠን መሪያችን ከትግራይ ተሻግሮ አስመራ አደባባይ ለሚገኙት ፀረ ኢትዮጵያውያን የሸአቢያ ጉጅሌዎች እንኳን የኢትዮጵያን ሠራዊት ሲዋጉ ለሞቱት ወታደሮቻችሁ ቀን በሰላም፣ በጤና፣ እና በፍቅር አደረሳችሁ ብሎ ማሽቃበጥን ምን ይሉታል?
•••
ኧረ የአማካሪ ያለህ? ኧረ የመካሪም ያለህ ማለትስ አሁን ነው። 
• ከሸአቢያና ከህወሓት ጋር ሲዋጋ የነበረው ደርግ እኮ ኢትዮጵያዊ ነው። ሰኔ 20 ሲዋጋ ክቡር ህይወቱ ያለፈውም የኢትዮጵያ ወታደር ነው። የደርግ ወታደርም የኢትዮጵያ ወታደርና የኢትዮጵያውያንም ስብስብ ነው። ከደርጎች ስብስብ መሃል ዜግነቱም ፓስፖርቱም ኢትዮጵያዊ ያልሆነ እንኳ የለም። አይገኝምም። ወታደሩም ወዛደሩም ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ብዙ የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ የዐማራ፣ የአፋር፣ የሱማሌ፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ በአጠቃላይ የሀገር ተወረረች ዜና የሰበሰባቸው ኢትዮጵያውያን ነበሩ። እናም በምን ሂሳብ ነው እነዚህን ኢትዮጵያውያን ለገደለ፣ ለረሸነ፣ ላሰቃየ የጠላት ሀገር ፓርቲ እንኳን የኢትዮጵያን ሠራዊት ለገደልክበት በውጊያውም ወቅት ለሞቱብህ ወታደሮችህ የሀዘን ቀን አደረሰህ የሚባለው?
•••
ችግኝ መትከል፣ ቆሻሻ መጽዳት ብቻውን ጎበዝ፣ ትጉህ ፣ ብልህ፣ አዋቂም አያስብልም። የእኔው አቢቹ ምራቅ የዋጠ አማካሪም መካሪም ያለው አይመስለኝም። እሱም ምክር ለመስማት ፈቃደኛ አይመስለኝም። ተግባሩ ሁሉ ልክ እንደ እስራኤል ዳንሳና ኢዩ ጩፋ ነው። የታላቅ ሀገርና የታላቅ ህዝብ መሪ መሆኑን ያወቀ የተረዳም አይመስለኝም አቢቹ። የ3ሺ ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆነች ታላቅ ሀገር መሪ ሆኖ እንደታላቅ ሀገር መሪ ማሰብና መራመድ የቻለም አይመስለኝም። በዚሁ ከቀጠለና ምራቁን እንደዋጠ ታላቅ ሰው መራመድ ካልቻለ ግን አወዳደቁ እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው።
•••
አሁን የሚታየው የፕሮሞሽን ሥራ ሲደክም፣ ሲደበዝዝ ዛሬ የሚያጨበጭብልህ የሚመስለው ሁሉ ይሰሰቀል፣ ይሰቀል ሲል ሰከንድ እንዳይፈጅበት ማወቅ ይገባል። ኧረ በፈጠረህ ተረጋጋ አቢቹ። ከምር አትቸኩል። ይልቅ ከሸአቢያ ጋር ለሚኖረው ቀጣይ ጦርነት ከወዲሁ መዘጋጀቱ ብልህነት ነው። ሸአቢያና ህወሓት ኦነግም ጭምር ኢትዮጵያ ሳትፈራርስ እንቅልፍ እንደማይኖራቸው ሊታወቅ ይገባል። እባብ ለመደ ተብሎ በኪስ አይይዛም እንዲል ታማኝ በየነ። እንደዚያ ነው።
•••
• ሻእቢያ ፤ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ሲል ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሠራዊት የወጋ። [ አሁን በአቢቹ እየተወደሰ ያለ ባለ ጊዜ የጠላት ወዳጅ ]
• #ወያኔ_ህወሓት ፤ ለምን እንደሚዋጋ ሳያውቅ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሠራዊት የወጋ። [ አሁን በአቢቹ እየተገፋ ያለ፣ ጊዜና ዘመን የከዳው የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ ]
• #ዚያድ_ባሬ ፤ እስከ ናዝሬት ድረስ የታላቋ ሶማሊያ ግዛት ናት በማለት ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳና በኢትዮጵያ ሠራዊት ህልሙ በአጭር ተቀጭቶ ድራሽ አባቱ የጠፋ።
• #ደርግ ፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስብስብ። ሀገር ለመምራት አቅዶ ያልተነሳ የወታደር ስብስብ። ጊዜና ዕድል ታሪክም ሀገር እንዲመራ ያደረገው የወታደር ስብስብ። በመሃል ሀገር ከኢህአፓና ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ጉረሮ ለጉረሮ የተናነቀ። በሰሜን ከሸአቢያና ከስመ ብዙዋ ማሌሊት፣ ትህነግ፣ ወያኔና ህወሓት ጋር የሞት ሽረት የሚዋጋበት፣ እንደ ኦነግ ከመሰለው ጋርም ከኢድዩና ከሌሎች ጋርም ሲለባለብ የኖረ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት እንደብራና ተወጥሮም ለማስቀጠል በብዙ የጣረ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማይታማና ከነ ስህተቱ ኢትዮጵያዊ መንግሥት የነበረ መንግሥት ነበረ።
•••
እነዚያን ለሀገር አንድነት ሲሉ የተሰዉ ሰማዕታትን ክብር ለኢሳይያስ አዲስና ወረተኛ መሠረቱም ላልጸና በድብሽት ላይ ለተመሠረተም የእንቧይ ካብ ፍቅር ሲባል በአደባባይ ማዋረዱ አግባብ አይደለም።
•••
ሻሎም !  ሰላም !  
ሰኔ 13/2011 ዓም 
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic