>
12:32 pm - Sunday December 4, 2022

የኦዲፒ መኳንንት እግዜርን ፍሩ! (መስከረም አበራ)

የኦዲፒ መኳንንት እግዜርን ፍሩ!
መስከረም አበራ
 
* እስክንድር ፌስታል አንጠልጥሎ እስር ቤት ሲገባ አዲሱ አረጋ የህወሃትን ብቅል ይፈጭ ነበር! ታላቁ እስክንድር ከባለፀጋ ወላጆቹ ቤት ወጥቶ ያለ እድገቱ ፌስታል ያንጠለጠለው ለገዳይ ብቅል አልፈጭም ስላለ ነው!
__
ያስፈነደቀን፣ተስፋ ያሰነቀን፣”በስመ አብይ ወ ለማ አሜን” ያስባለንን ለውጥ ለመጀመሪያን   ጊዜ ያዘንኩበት የአዲስ አበባ ልጆችን ለቃቅሞ በማሰር አይጥ በበላ ዳዋ ሲመታ ነው። ያኔ በደንብ ተግባባን!ከለውጡ ተስፈኝነት ባቡር ለመውረድ የመውጫውን በር ማማተር እንደማይከፋ ለራሴ የነገርኩት በዛች ቅፅበት ነበር።
በመሃል ብዙ ተወራ ብዙ ተደረገና የለገጣፎው መፈናቀል ላይ ተደረሰ።ነገስታት የእርጉዝ የአራሶችን ዋይታ፣የአዛውንቶችን ኤሎሄ ሌላው ቀርቶ የፈረንጆችን ጩኸት አልሰማሁም ያሉጊዜ እንጥፍጣፊ ተስፋየን ላስቀራት ብወድም አሻፈረኝ ብላ ስትሰናበተኝ ታወቀኝ።
ከዛ  በሃላ የምኖረው ለወትሮው እንደ እኔው ይመስሉኝ የነበሩ ሰዎች ይህን ሁሉ እያዩ የሚያደርጉትን ተስፋ ለመዋስ፣ከ”አማኝ ፣ቅን” ነፍሳቸው ነፍስ ለመንሳት  በመሟሟት ነው።እነዚህ የማከብራቸው ፣አንዳንዴም ትክክለኝነቴን የምለካባቸው ሰዎች ዛሬም ተስፈኛ ናቸው፤ አሁንም ዝም ብሎ ማመን ብቻ ያድናል ባይ እንደሆኑ ከእልፍኙ ባለመጥፋታቸው ያስመሰክራሉ፣።የባሰውን ሲያመጡት ደሞ “አብይን ብታዩ እኔን ምን ኢትዮጵያዊ ነው ትሉ ነበር” ይላሉ፣ “አብይን የምንመክረው በዘመድ ጉባኤ ነው እንጅ ቀድሞ በወያኔ እንደምታውቁት አይደለም ፣ይህም ለውጥ ለመኖሩ ምልክት ይሁናችሁ ” ይላሉ። በዘመድ ጉባኤም ሆነ በሰንበቴ ፣በወንድሞች ህብረትም ሆነ በኳየር ጉባኤ መክረውት   ቢያንስ የክረምቱን የምስኪኖች መፈናቀል ቢያስቀሩልን ኖሮ እውነትም  የዘመድ ጉባኤው የነብያት ጉባኤ ነው ማለታችን አይቀርም ነበር!አልሆነም……..
 ስለዚህ በወዶ ገባ ተቃዋሚ ፓርቲወች እና በዘመድ አዝማዶችጉባኤ ተስፋ ስንቆርጥ ኦዴፓ ፈጣሪን ፈርቶ ጥጋቡን በልክ እንዲያደርግ መለመናችን አይቀርም።  ጥጋብ አንድ ከለገጣፎ ተፈናቅለው  በየቤተክርስቲያኑ ጓሮ የክረምት ዶፍ የሚወርድባቸው ሰዎች ፍርድ ቤት ሄደው አቤት ማለት እንደማይችሉ የከለከለበት “ትንሿ ጣቴ ከህወሃት ወገብ ትወፍራለች”   ያለበት ጥጋቡ ነው  ። ይህን የዘገበው የአዲስ አበባው ኢሳት ነው።  ሰወቹ ከቤት ተባረው መሰቃየታቸው ሳያንስ በደላቸውን ለፍርድ ቤት ለማሰማት እንኳን እንዳይችሉ ንጉስ ኦህዴድ ከልክሏል።  በደላቸው ፍርድ ቤት ለመቅረብ    ከበቂ በላይ መሆኑን ለሃገር ያወቀው ሃቅ ነው።  ባይሆን እንኳን ፍርድቤት ሰምቶ ውድቅ ያድርገው እንጅ የኦሮሚያ መንግስት ምን አግብቶት ነው ጉዳያችሁ ፍርድ ቤት እንኳን አይቀርብም ባይ የሆነው? ጥጋብ ሁለት አዲሱ አረጋ የተባለ ካድሬ እስክንድርን ፌስታል ይዞ እንዲወጣ ያደረጉት የኔ ዘር ጎረምሶች ናቸው ያለው ሰማይ በርግጫ አይነት ጥጋብ ነው።
 በመጀመሪያ  እስክንድርን ፌስታል የያስያዘው ሻንጣ አጥቶ ሳይሆን የሚታገልለትን ደሃ ህዝብ ወደመሆን የመጠጋቱ ልዕልና ነው። ይህ ሰብዓዊ ከፍታ ዓለም ማለት ስልጣን እና የስልጣን  ፍርፋሪ ያመጣውን ጮማ መዋጥ ለሚመስለው የኢህአዴግ ካድሬ ይግባው አይግባው አላውቅም!የሚገባው ግን አይመስለኝም ፣ ምልክቱ አዲሱ አረጋ በእስክንድር ላይ ሊሳለቅ መሞከሩ ነው! እስክንድር ፌስታል አንጠልጥሎ እስር ቤት ሲገባ አዲሱ አረጋ የህወሃትን ብቅል ይፈጭ ነበር! ታላቁ እስክንድር ከባለፀጋ ወላጆቹ ቤት ወጥቶ ያለ እድገቱ ፌስታል ያንጠለጠለው ለገዳይ ብቅል አልፈጭም ስላለ ነው! እስክንድርን ዛሬ በማንም ፊት ቀጥ ብሎ የሚቆም ብረት ያደረገው የራሱ ፅናት ነው።  ካድሬ ፌስታል የያዘ ሁሉ ደሃ ፤ በከረቫት የታነቀ ፣ደሃ ህዝብ ዘርፎ ፎቅ የገተረ ሁሉ ባለፀጋ ይመስለዋል።
 እኛ ደሞ ገልብጠን እንረዳለን ፣ዘርፎ ፎቅ ከሰራ  ካድሬ ይልቅ ለህዝብ ሲል ፎቅ ቤቱን ለመቀማት ጨክኖ  ድሎቱን ወርውሮ ፣ፌስታል ይዞ እስር ቤት የገባው ፣ስጋው ከስቶ ነፍሱ የወፈረው እስክንድር ነጋ ከብሮ ይታየናል።
Filed in: Amharic