>
9:57 am - Wednesday December 7, 2022

ከቡርቃ ዝምታ: ወደ ፊንፊኔ ጫጫታ !! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

ከቡርቃ ዝምታ: ወደ ፊንፊኔ ጫጫታ !!

አሥራደው ከፈረንሳይ

ኳኳታ የሃሳብ ድህነት መግለጫ መሆኑን ብናምንም፤ ከአፍ ወለምታው በስተጀርባ ያለውን ትልቅ ስብራት ወጌሻም አይጠግነው !!

ማስታወሻ :

በዚህ ርዕስ መጣጥፍ ለማቅረብ አስቤ ከጎረምሶችቹ ጋር አብሮ አቧራ ላለማቡነን ስል ትቼው ነበር፤ ሆኖም ጎረምሶቹ የሚያቦኑት አቧራ ዛሬም እያገረሸ በማስቸገሩ፤ ማለት የሚገባኝን ለማለት ወሰንኩ፤ እናም ይኸው::

አገር እበት ወልዳ ጡቶጯን ትል ሲጠባው እያየን ብንታገስ፤ ጭራሹኑ ይባስ ብለው፤ ትዕግስትን እንደ ፍርሃት በመቁጠር፤ አፋቸው ከጥብጣባቸው የሰፋ የኦህዴድ/ኦነግ “ሁንዱማ ኬኛ” ሁሉም ነገር የኛ! ባይ፤ ባለ ተረኛ ነን ፖለቲከኞች፤ ዛቻና ማስፈራሪያ ፈር እየለቀቀ በመምጣቱ፤ “አህያን በአህያነቷ፤ ተራገጠች ብሎ የሚቀየማት ባይኖርም፤ ዳግም እንዳትራገጥ፤ መጀመርያ በብዕር ልምጭ ለመግራት፤ እምቢ ካለችም ህግ ካለ፤ በህጋዊ ፍልጥ፤ ሃይ እንድትባል ለማመላከት ነው ::
” ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከደጅ ታሳድራለች ” እንዲሉ ሆነና ጠ/ ምኒስትር አብይ አህመድ በእስክንድር ነጋ ላይ ጦርነት እስከማንሳት ያደረጉትን ዛቻ በመጠቀም፤ ዛሬ አቶ አዲሱ አረጋ ቀጤሳ “በቄሮ ትግል ፌስታሉን ይዞ ከእስር ወጥቶ ሲያበቃ ………….. ” በማለት ቀጣዩን የኦህዴድ/ኦነግ ጥምር የፖለቲካ ዝሙተኖች አጀንዳ ሰፋ አድርገው ነግረውናል :: እኛም አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል እንዲሉ ነውና በሚገባ ከትበናታል ::

– የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ! እንኳን ከሸውራራውና ሌባው የህወሓት ዘመን፤ ወደ ሸፋፋው የኦህዴድ/ኦነግ ጥምር የፖለቲካ ወሲበኞች ዘመን፤ በመከራ አደረሰን !! ልብ ተብሎ ይነበብልኝ በደስታ አላልኩም፤ በመከራ እንጂ !!

አይምሰላችሁ የኛ መከራ ገና አላለቀም፤ ጠግበው የበሉ የህወሓት ጅቦች ተሰናብተው፤ የተራቡ የኦህዴድ/ኦነግ ጥምር ጅቦች ናቸው፤ ተጠራርተው፤ አውው !!! እያሉ ያገኙትን ሁሉ ጭዳ ለማድረግና፤ የቀረች የህዝባችንን አንጡራ ሃብትና አጥንት እንደገና ሊግጡ ያሰፈሰፉት ::

ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! እያለ ጮሆ የተናገረ ሁሉ ዕውነት ይናገራል፤ ዝም ያለ ሁሉ ይዋሻል ያለው ማን ነው ?!
ጠቅላይ ምኒስትሩ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞችን ለማሽኮርመም፤ ከነሱ ጋር ሲሆኑ የነሱን ቋንቋ፤ ከእኛ ጋር ሲሆኑ የኢትዮጵያዊነትን ካባ ለብሰው፤ በመልካም ቃላት፤ የአገራዊ አንድነት ፈላጊውን ቡድን የማደንዘዣ መርፌ፤ መውጋቱን ከወዲሁ ቢያቆሙት ይመረጣል::

አብይ አህመድ፤ የወለጋ ባንክ ዘራፊ ወንበዴዎችን፤ የሰላሌ የኦህዴድ/ኦነግ ነብሰ ገዳዮችን፤ አንዲ ቃላት ትንፍሽ ሳላሉ፤ ብዕርና ወረቀት ብቻ በያዘና ብዙ መስዋዕትነት በከፈለ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ጦርነት ማወጅ ለምን ፈለጉ ? ለምን ፈሩት ?

ለመሆኑ ጠ/ ምኒስትሩ ከኡጋንዳው ጉብንታቸው ምን ተምረው ተመለሱ ?

በኡጋንዳ በዘርና በጎሣ የተነሳው የህዝብ እልቂት፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ላለው የዘርና የጎሣ ፖለቲካ መፈናቀልና ሞት ትምህርት ሆኗቸው፤ እንደተመለሱ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ: ኢትዮጵያን ከመቅበሩ በፊት እንዲቀበር ያደርጉ ይሆን? ብዬ ነበር :: ምን ያደርጋል ምንም ሳይማሩ ተመለሱ ::

የጌዴዎ፤ የንፋስልክ ላፍቶ፤ የአዲስ አበባ ዙሪያ፤ የሱሉልታ፤ የወልቃይት ጠገዴ፤………ወዘተ. ተፈናቃዮች ወገኖቻችን፤ በጥቅሉ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ፤ ከተለያዩ የአገራችን ክፍላተ ሃገራት፤ በዘርና በጎሣ ሰበብ እየተፈናቀሉና እየሞቱ፤ ጠ/ ምኒስትሩ ” የራሷ እያረረ የሌላ ታማስላለች ” እንዲሉ በየ ጎረቤት አገሮች የሚያደርጉት የልታይ፤ ልከበር፤ ልደነቅ ጉዞና ሽምግልና፤ በእጅጉ ያሳዝናል: ትዝብት ውስጥም ይከታል ::
የአገራዊ አንድነት ካባ ለብሶ: የኦህዴድ/ኦነግ ጥምር አንጃን ማሽኮርመም አደጋው ብዙ ነው…………….

ክቡር ጠ/ምኒስትር ዕውነቱን ልንገርዎ !
በኢትዮጵያ ጦርነት ለሁል ጊዜ የምናስታውሰው፤ ሠላም ለረጅም ጊዜ የምንረሳው እንዳይሆን ያሰጋል !!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ !!

ሰኔ 15 ወን 2011 ዓ.ም. ( 22/06/2019)

Filed in: Amharic