>
10:27 am - Monday August 15, 2022

መንግስት "መፈንቅለ መንግስት!" የምትለዋን ማስጮህ ለምን ፈለገ?!?  (ዶ/ር ሰማህኝ ጋሹ)

መንግስት “መፈንቅለ መንግስት!” የምትለዋን ማስጮህ ለምን ፈለገ?!? 
ዶ/ር ሰማህኝ ጋሹ
መንግስት ሁኔታዎችን ተቆጣጥሮ የባህር ዳርን አካባቢ ሰላም ማስጠበቁ የሚያስመስግን ነገር ነዉ። ግጭቶች ከዚህ በላይ ቢባባሱ ብዙ እልቂት ሊደርስ ይችል እንደነበር መገመት ይቻላል። ከሚወጡት መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለዉ በጀነራል አሳምነዉ ፅጌና በክልሉ መስተዳድር መካከል የክልሉን ፀጥታ አከባበር በተመለከተ አለመግባባቶች ነበሩ።  የክልሉና የፌዴራል መንግስቱ ጥቃቱ የተፈፀመዉ በጀነራሉ እንደሆነም በግልፅ  አሳዉቀዋል። ነገር ግን የዚህ ጥቃት አፈፃፀምና አላማ ለመረዳት ብዙ ዝርዝር መረጃዎችን ማወቅ ይጠይቃል። አንዳንድ ጉዳዮች ግን ከወዲሁ ጥያቄ የሚያጭሩ ናቸዉ። መንግስት የደረሰዉን ጥቃት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው ብሎ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ለምን አላማ ታስቦ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ጀነራል አሳምነዉ ልምድ ያላቸዉ ወታደር እንደመሆናቸዉ የክልሉን መሪዎች በመግደል መፈንቅለ መንግስት አድርገዉ ስልጣን ለመያዝ አስበዉ ነበር የሚለዉን ግምት  አጠያያቂ ያደርገዋል ።
ጀነራል አሳምነዉ ምን ያህል ሃይል ቢኖራቸዉ ነው የክልሉን ሃይል ተቆጣጥረዉ የራስቸዉን መንግስት እመሰርታለሁ ብለዉ ሊያስቡ የሚችሉት? ይህም ቢሳካላቸው የፌዴራል መንግስትን ሰራዊት መክቼ አስተዳድራለሁ ብለው አስበው ነው እንዴት ማለት ይቻላል? ጉዳዩን በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የተደረገ ግድያ እንደማለት መንግስት መፈንቅለ መንግስት ነው ማለቱ የአለም አቀፉን  ማህበረሰብን ትኩረት እዲያገኝ አድርጎታል። ይህ ሁኔታ አገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስም የበለጠ በማበላሸት አገሪቱ በኢንቨስትመንትም ሆነ በቱሪዝም የምታጋኘዉን ጥቅም ያሳጣታል። አንድ ሃላፊነት የሚሰማዉ መንግስት ሁኔታዎች መፈንቅለ መንግስት የማይመስሉትን ሁኔታዎች በዚህ መልኩ መግለፅ አይደለም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ቢኖረው እንኳን በአገሪቱ ገፅታና በህዝብ ስነ ልቦና ላይ የሚያሳድረዉን ተፅእኖ በመረዳት ጥቃቱን በዚህ መልኩ ከመግለፅ ሊቆጠብ ይገባ ነበር።
ጉዳዩን በመፈንቅለ መንግስት መልክ አስቀድሞ መፈረጅ መንግስት ጉዳዩን በገለልተኛነት ያጣራዋል ብሎ ለማሰብ የማያስችል ከመሆኑም በተጨማሪ መንግስት ጥቃቱን በዚህ  መልኩ በመግለፅ ሊያሳካው የፈለገው ፖለቲካዊ ግብ አለ የሚል ግምት ይሳድራል። በተለይ  በክልሉ ያሉትን ተቃዋሚ ብሄርተኛ ሃይሎች ለመምታት እንዲያመች ተደርጎ ጥቃቱ በመፈንቅለ መንግስት መልኩ እንዲስተጋባ ስላለመደረጉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በዚህ ጥቃት ሰበብ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸዉን ተቃዋሚ ሃይሎችን ለማጥቃት ሙከራ ከተደረገ ችግሩን ሊያባብሰዉ የሚችልበት እድል ከፍተኛ ነዉ። ይህ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
የባህርዳሩን ጥቃት አዲስ አበባ ከነበረዉ ግድያ ጋር ያለው ግንኙነት ግልፅ አይደለም። ጀነራል አሳምነዉ ልምድ ያለዉና አሁን ያለዉን የሃይል አሰላለፍ የሚረዳ ሰው እንደመሆኑ ጦሩ በእነማን እንደሚመራ እያወቀ ጀነራል ሰአረን በመግደል ወደ ባህር ዳር ጦር እንዳይላክ ሞከረ የሚለዉ ምክንያት ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም። ከጀነራል አሳምነው ጋር ግንኙነት የነበረዉ ሰዉ ወይም ሊኖረዉ የሚችል ሰዉ ጀነራል ሰአረን በዚህ ቀዉጢ ወቅት እንዲጠብቅ ይደረጋል ብሎ ለመገመትም  ያስቸግራል።  ጀነራል ሰአረ ምናልባት ባህርዳር የተፈፀመዉን ጥቃት ይመሩ ከነበረ ጥሮተኛዉ ጀነራል እቤታቸዉ መጥተው አብረዉ ጊዜ ያሳልፉ ነበር ብሎ ለማሰብም  አስቸጋሪ ነዉ። የጀነራሉ ግድያ የባህር ዳሩን ጥቃት በማሳበብ ሊያስወግዳቸዉ የፈለገ ሃይል ስራ ወይም በግል ስሜት ተነሳስቶ ግድያ የፈፀመ ግለሰብ ድርጊት ነው ሊሆን የሚችለዉ። ግድያዉ ከጀነራል አሳምነዉ ጋር ይገናኛል ከተባለ መንግስት ይህንን የማስረዳት አቀበት ይጠብቀዋል።
Filed in: Amharic