>
5:36 pm - Wednesday November 30, 2022

ኦሮቦሮው ኢህአዴግ እና ኦሮቦሮአዊ ባህሪው ! (አሰፋ ሃይሉ)

ኦሮቦሮው ኢህአዴግ እና ኦሮቦሮአዊ ባህሪው !
አሰፋ ሃይሉ
 
“ኦሮቦሮ” (“Ouroboro”) ራሱን በራሱ የሚበላ ዘንዶ ነው። በሽክርክር ክብ መስመሮች በእባብ እና በደራጎን አምሳል የተሰሩ ጥንታዊ የግብፃውያን ኮከቦች ከክርስቶስ ልደት 1ሺህ ዓመታት በፊት በነገሥት ኦሲሪስና በጣዖቱ ራ መካከል የተፈጠረውን ከፊል ሰዋዊ፣ ከፊል አምላካዊ የሆነውን (የነገሥታቱን ዘላለማዊ ሆኖ የመዝለቅን ባህርይ ለማመልከት) በጥንታዊው የቱታንካሙን የምድር ውስጥ መቃብር ውስጥ ይሄን ራሱን በራሱ የሚናከስ ኦሮቦሮ በቱታንካሙን አናት ላይ ተንጣልሎ በግድግዳ ላይ ተቀርፆ ይገኛል።
በኮከብ ቅርፅ የተሠራው ኦሮቦሮ እና ክቡ ኦሮቦሮ “ሲምቦሊክ ሪፕሬዘንቴሽንስ” በኋላ ላይ በጥንተ ግሪኮችና ጥንተ ሮማውያን ዘንድ ተሠራጭተው በተለያዩ የአስማተ ነገሥታት ይዘትን በሚያስቃኙ ጥንታዊ ገድሎች ውስጥ ምስላቸው በተለያዩ ቀለማት ተነድፈው እናገኛቸዋለን።
ኋላም ላይ የዓለምን ህይወት ያላቸው ፍጥረታትንና ህይወት የሌላቸውን ግዑዛን ቁሶች ሁሉ ያያያዘውን አንድ ምድራዊ ወ ሠማያዊ ምሥጢር እናገኛለን ብለው በምትሀታዊ የኢሊክሲር የከበሩ ደንጋያት አስማታዊ ምርምሮችን ሲያደርጉ ለዘመናት የዘለቁት የዓለማችን አልኬሚስቶች (ቀደምት ኬሚስቶችና አስትሮሎጀሮች) ይህን በጥርሱ ጭራውን የነከሰ – ራሱን በራሱ የሚበላ ኦሮቦሮ – የዘለዓለማዊነት፣ የቀጣይነት፣ የአልሞት ባይነት፣ ሁሌ ጉዞው የማይስተጓጎል የዘለዓለማዊ ዑደት ተምሳሌት በማድረግ – ክቡን ኦሮቦሮ መሐሉ ላይ በእባብ ቅርፅ ከነተሠራው ኮከብ ጋር – ዋነኛ ምልክታቸው አድርገው በመጠቀማቸው – በተለያዩ ታዋቂነትን ያተረፉ ጥንታዊ ጥራዞች ውስጥ ይህንኑ የኦሮቦሮ ክብና ኮከባም እባብ ምስል ማግኘት የተለመደ እንዲሆን አድርገውታል።
በአጠቃላይ – ይህ ራሱን በራሱ የሚበላ ኦሮቦሮ – ኦሮቦሮውን አርማውና ባንዲራው አድርጎ ከነኮከቡ ካስቀረፀው ከወያኔ-ኢህአዴግ ጀምሮ – በተቀመጡበት መንበረ ሥልጣን ለዘለዓለም ኃይልና ጉልበታችንን አስጠብቀን እንኖራለን ብለው በሚመኙ ከቻይና እስከ ፔሩ በተሠራጩ የኋለኛው ዘመን ጦረኞች ሁሉ ዘንድ – የንግሥ ማህተም ተደርጎ ግልጋሎት ላይ መዋሉን – በአሁኑ ዘመን የ”ኦከልት ሲምቦሊዝም” አረዳድም – ራሱን በራሱ እየበላ ነፍሱን የሚያቆየው ኦሮቦሮ – የዘለዓለማዊነት ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ ብዛት ያላቸው ድርሳናት አስረግጠው ይነግሩናል።
ሁላችንም ከታሪኩ እንደምናውቀው – ኦሮቦሮው ኢህአዴግ – ከበረሃ (ከጫካ) ትግሉ ጀምሮ – “ጠላቴ ናቸው” ያላቸውን ውጫዊ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን – በአቋም ተቃርነው የተገኙትን የገዛ ራሱን ውስጣዊ ኃይሎችና የፖለቲካ ሰዎችና ቡድኖች የተለያዩ ስሞች እየሰጠ – “አንጃ”፣ “ባንዳ”፣ “ፀረ-ሕዝብ”፣ “አደናጋሪ”፣ “ተላላኪ”፣ “አደናቃፊ”፣ “ከሃዲ”፣ ወዘተ ወዘተ የሚሉ ቅፅል ታርጋዎችን እየለጠፈ – በየሜዳው ስልቅጥ አድርጎ እየበላ፣ ለግብዓተ መሬታቸው እያበቃ፣ “አብዮት…” – ልክ እንደ ኦሮቦሮ – “የገዛ አብራኳን ክፋዮች ልጆቿን ዋጥ ስልቅጥ አድርጋ እንደምትበላ” – በተግባር እያረጋገጠልን የመጣ ራሱን በራሱ የሚበላና ከዚያም ነፍስን ዘርቶ አንሠራርቶ ጉዞውን የሚቀጥል – ለዘለዓለምም በሥልጣነ መንበሩ ላይ ተጠምጥሞ መኖርን በእጅጉ የሚመኝ – በህይወት ያለ የዘመናችን ኦሮቦሮ ድርጅት መሆኑ  የሚታበል አይደለም።
(በነገራችን ላይ፥ ስለ ኢህአዴግ ኦሮቦሮአዊ ባህርይ የሚጠራጠር ካለ፥ ካስፈለገ ከራሱ ከኢህአዴግ እውነተኛ ታሪክ የተመዘዙ እና አሁንም እየተከናወኑ ያሉ በርካታ ኦሮቦሮአዊ አብነቶችን በብዙ ጥራዞች ነቅሶ ማውጣት አዳጋች ሥራ እንደማይሆን አሳምሮ ማወቅ ይገባዋል!)
የሆነ ሆኖ ኦሮቦሮው ኢህአዴግ – አሁን ወደ ፍፃሜው እኩሌታ ቁልቁል እየተንደረደረ ባለበት የማምሻ ዕድሜው ላይም ሆኖ እንኳ – ማምሻም ዕድሜ ነው በሚለው የዘለዓለም ፈሊጡ – የቀረችውን ርዝራዥ የሥልጣን ዕድሜ ለማስቀጠል – ኦሮቦሮአዊውን ራሱን በራሱ የሚበላ ባህርዩን – እነሆ – “የሊቀ ኦሮቦሮው ኢህአዴግ የጥፋት መልዕክት ወደ አማራ ሰዎች” በሚል አዲስ ራሱን በራሱ የመብላት ፓኬጅ – በአማራዎቹ የሕዝብ ልጆች – በእነ ብ/ጄነራል አሳምነው ፅጌ፣ በእነ ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ እና በእነ ኮ/ል አለበል አማረ፣ እና በሌሎችም “ጀሌዎች” ብሎ በሰየማቸው ቁጥራቸው በውል በማይታወቁ በግልፅ አደባባይ ንፁህ አቋማቸውን ይዘው እኩይ አካሄዱን በተገዳደሩት ኢትዮጵያውያን ላይ – ጥርሶቹን ስሎ ለተለመደው ኦሮቦሮአዊ ንድፊያ ሠራዊቱን በግዮን ምድር አሠማርቶ – የንክሻ ነጋሪቱን – ለዓለም ሚዲያ ቀን ከሌት እየጎሰመ እያየነው ነው።
እንደሚታወቀው – በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ – ኦሮቦሮው ኢህአዴግ – በያቅጣጫው ሆድና ጅራት ሆነው በተፃራሪ አቅጣጫ በቆሙ በዘር የተደራጁ አባል ድርጅቶቹ የተነሳ – ከድሮው ርዕዮተ ዓለሙ፣ ተክለ ቁመናውና ማንነቱ –  ስሙንና ስሙን ብቻ ይዞ – መለመላ ራቁቱን የቀረ እና አብርቶ ሊጠፋ የተቃረበ ጅራታም ኮከብ ሆኖ ቀርቷል። ኦህዴድ ስሙንም ማስተረፍ አልሆነለትም። ኦዴፓ ሆኖ በኦነጋውያን ተተክቷል። ብአዴንም ከቀደመ ማንነቱ ኢህዴን የሚለውንም፣ ብአዴን የሚለውንም ስሙን አላስተረፈም። ግራ የገባው አዴፓ ሆኖ ቀርቷል። ህወሀት የራሱንም የሌላውንም መሬት በጉልበቱ ተቆጣጥሮ በይፋ ያልታወቀ የራሱን መንግሥት እያንቀሳቀሰ ስለ መገንጠል እያሟረተ ይገኛል። ሌላውም ዚቁ ብዙ ነው።
እና እንግዲህ ይሄ – ከድሮ ማንነቱ – ስሙ ብቻ የቀረ – አፈኛው – ኦሮቦሮው ኢህአዴግ ነው – አሁን – ባለ በሌለ ጥርሱ – “ለውጥ! ለውጥ!” እያሉ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ የግዮን ልጆቹን ሊበላ ያሰፈሰፈው!!
ኦሮቦሮው ኢህአዴግ – የራሱን ልጆች ተናክሶ የሚያላምጥበት ጥርስ – እና የሚያብላላበት ዕድሜ ይኖረው ይሆን??
መልሱን ለጊዜ ሰጥቼ ተሰናበትኩ። ጀግና ጊዜ ነው። ሰው አይደለምና።
ኦሮቦሮው ኢህአዴግ። የሥራህን ይስጥህ። እንደ ጭካኔህ መጠን – አውሎ ያግባህ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ።
የተሰወረብንን ልቦና ይግለጥ።
አበቃሁ።
Filed in: Amharic