>
4:02 pm - Wednesday July 6, 2022

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት አባላትን ማሰር ማንገላታቱ እስከ ባህርዳር ዘልቋል!!! (ኢትዮ 360)

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት አባላትን ማሰር ማንገላታቱ እስከ ባህርዳር ዘልቋል!!!
(ኢትዮ 360 – ሰኔ 18/2011)
በአዲስ አበባ የባላደራው ምክር ቤት ባልደራስ አባላትንና ሌሎችን ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል ማሰር መጀመሩ ተገለጸ።
እስካሁንም የባላደራውን ሕዝብ ግንኙነት ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ ሌሎችም በታሰራቸውን የባላደራው ጸሃፊ ኤልያስ ገብሩ ለኢትዮ 360 ገልጿል።
በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ አብሮ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረው መርከብ ሃይሉ፡ሶስት የአብን አባላትና እንዲሁም የኢሳት አዲስ አበባ የኦሮምኛ ክፍል ባልደረባ የሆነው አማኑኤል መንግስቱም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
የባላደራው ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ሰናይት ታደገም ለጥያቄ ይፈለጋሉ በሚል የተለያዩ ሰዎች ቤታቸው መላካቸውንና እሳቸውን ማግኘት አለመቻለቸውን፡ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ወይዘሮ ሰናይት ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ነው ኤልያስ ገብሩ የገለጸው።
አባላቱ ይፈለጋሉ ስለተባለበት ጉዳይ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
እንደ እሱ አባባል ከሆነ እንዲህ አይነቱ ማንገላታትና ክትትል በባህርዳሩም ጉዞ የታየ ነበር ብሏል።
ገና ከመጀመሪያው ቦታ የለም በሚል በተለያየ በረራ እንድንሄድ ነው የተደረግንው የሚለው ኤልያስ አጋጣሚ ሆኖ ግን አራታችንም በህርዳር አይሮፕላን ማረፊያ መገናኘት ችለናል ይላል።
በወቅቱም የተፈጠረው ነገር ምን እንደሆነ ባያውቁትም ከጸጥታ ሃይሎች ግን ከተማ ውስጥ ችግር መኖሩንና ወደዛም መግባት እንደማይችሉ እንደተናግራቸው ነው የገለጸው።
እንደሱ አባባል ከሆነ ችግር ካለ ወደ መጣንበት እንመለስ ለሚለው ጥያቄያቸውም  የተሰጣቸው ምላሽ እዚሁ ኤርፖርት ማደር እንጂ መንቀሳቀስ አትችሉም የሚል ነበር።
በቀጣዩ ቀንም ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተከራካሪው እስክንድር ነጋ በጸጥታ ሃይሎች ለጥያቄ እንደሚፈለግ ከተነገረው በኋላ የቀረበለት ሃሳብም ወደ አዲስ አበባ መሄድ አትችሉም ነገር ግን ወደ ባህርዳር ከተማ ገብታችሁ ዝግጅቱን ማከናወን ትችላላችሁ የሚል መሆኑን ነው ኤልያስ ገብሩ የገለጸው።
ነገር ግን የእስክንድር ምላሽ የተከሰተው ነገር እጅግ የሚያሳዝንና ልብ የሚሰብር ነው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምንም አይነት ዝግጅት ማድረግ እንደማይቻልና የባላደራውን አባላት ለተለየ ጉዳይ የሚፈልጓቸው ከሆነ ግን አጠገባቸው መሆናቸውን መግለጹን አመልክቷል።
በወቅቱም በነበረው በረራ ወደ አዲስ አበባ መመለስ እንደምንፈልግ ቢናገርም ምላሹ ግን ወደ አዲስ አበባ መሄድ አትችሉም ወደ ባህርዳር ከተማ ብቻ ነው መሄድ የምትችሉት የሚል ነበር።
ምንም አማራጭ ስለሌለን ወደ ከተማ ገባን የሚለው ኤልያስ በከተማዋ ውስጥ ገብተን ምንም ማድረግ ስለማንችል ብሎም እስክንድር የጋዜጣዬ መታተሚያ ጊዜ በፍጹም ማለፍ የለበትም በማለቱ ተሽከርካሪ ማፈላለግ ተጀመረ ይላል።
በተገኘው ተሽከርካሪ እስክንድርና ስንታየሁ ቸኮል እንዲሄዱ ተደረገ የሚለው ኤሊያስ እስክንድር መውጣቱን ያረጋገጠው አካል ቀሪዎቹ ማደሪያ በማፈላለግ ላይ እያሉ 11 ተኩል በረራ ስላለ ኑ የሚል የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው ነው የሚገልጸው።
አየር መንገድ ሲደርሱ እስክንድር ከተማ ውስጥ ስላለ ልጥራውና አብረን እንሂድ የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ የተሰጠው ምላሽ ቢመጣም በዚህ አይሮፕላን አይሳፈርም የሚል ነው።ለምን ለሚለው ጥያቄ ግን ምላሽ የሚሰጠን አካል አላገኘንም ይላል ኤልያስ።
የእነ እስክንድር ጉዞም ቢሆን እጅግ ከባድና በየቦታው በፍተሻ የታጀበ ነበር ሲል ገልጿል።
ኤልያስ ገብሩ አስደንጋጭና አስገራሚ በሚል ያስቀመጠው ነገር ቢኖር እነ እስክንድር የተሳፈሩበት ተሽከርካሪ መሳሪያ የጫነ ስለመሆኑና በፍተሻ ጣቢያው ሰራተኞች ርምጃ እንዲወስዱበት ትዕዛዝ የመተላለፉ ጉዳይ ነው።
የፍተሻው ጣቢያ ሰራተኞች ግን የተባሉትን ርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት በተሽከርካሪው ላይ ያደረጉት ፍተሻ በእነ እስክንድር ላይ ተደግሶ የነበረውን የሞት አደጋ አስቀርቶታል ይላል።- የፍተሻ ጣቢያ ሰራተኞቹም ያሉት ይህንኑ ነው።ከባዱን አደጋ አልፋችሁታል የሚል
ኤልያስ ገብሩ እንደሚለው እንዲህ አይነቱ ማዋከብና እውነትን ለመደበቅ የሚደረገው ሩጫ አሁንም ቀጥሏል።
ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል የታሰሩትን የነስንታየሁ ቸኮልን ጉዳይም ለማጣራት እስክንድርና ሌሎች የባላደራው አባላት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ለኢትዮ 360 ገልጿል።
Filed in: Amharic