>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9217

የባላደራው አመራሮችና አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ -ፖሊስ የጠየቀውን የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድቤቱ ተቀብሎ አጽንቷል!

የባላደራው አመራሮችና አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ
ኢትዮ 360 
* ፖሊስ የጠየቀውን የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድቤቱ ተቀብሎ አጽንቷል!!!
የአዲስ አባባ ባላደራ ምክር ቤት አመራርና አባላት ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ ተብለው ከተወሰዱ በኋላ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተሰማ።
የባላደራውን ሕዝብ ግንኙነት ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ መርከቡ ሃይሌ፡በሪሁን አዳነ፡ጌዲዮን ወንደሰንና ማስተዋል አረጋ በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነው ከባላደራው ያገኘንው መረጃ የሚያመለክተው።
ከባህርዳሩ የግድያ ወንጀል ጋር እጠረጥራቸዋለሁ በሚል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ያደረገው ፖሊስ የጸረ ሽብር ህጉን  መሰረት አድርጎ ምርመራ እንደሚያካሂድም ገልጿል።
ለዚህ ምርመራው ደግሞ የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን ነው መረጃው የሚያመለክተው።
ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ መፍቀዱ ተሰምቷል።
ፖሊስ የጸረ ሽብር ህጉን መሰረት አድርጌ ምርመራ አካሂዳለሁ ማለቱ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከምክር ቤቱ አባላት ሌላ ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ለኢትዮ 360 የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
እስካሁን ከ60 በላይ ሰዎች መያዛቸውን የሚገልጸው መረጃው ዜጎችን እያሳደዱ ማሰር አሁንም መቀጠሉን ነው ያስታወቀው።
Filed in: Amharic