>
12:15 am - Thursday December 1, 2022

"የጠቅላይ ሚኒስትሩም እጅ ከደም ንጹህ ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ሁኔታ የለም!?!" (ያሬድ ጥበቡ)

“የጠቅላይ ሚኒስትሩም እጅ ከደም ንጹህ ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ሁኔታ የለም!?!”
ያሬድ ጥበቡ
ባላወቅኩት ምክንያት በተለይ የሁለቱ ጄኔራሎች የሰአረና የአሳምነው ሞት መረረኝ ። ልጅነታቸውን ለህዝብ ትግል የሰጡ ጀግኖች በአልባሌ መንገድ ሲገደሉ ያማል። ጦር ሜዳ ላይ ከጠላት ጋር ተናንቀው መስዋእት ሆነው በነበሩ የለመድነውን “ትግል አይሞትም” እየዘመርን በሸኘናቸው ነበር ። አሟሟታቸው ለቀባሪ እንኳ ለማርዳት አይመችም። ለምን ተገደሉ? ማን ገደላቸው? እንዴት ተገደሉ? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች ቀላል መልስ አልተገኘላቸውም። የሰአረን ሞት ከክንፈ አሟሟት ጋር የሚያመሳስሉ ብዙዎች ናቸው። እጅግ የበዙ ጥያቄዎች በዜጎች አንደበት እየተመላለሱና እየተነገሩ ነው።
ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚነሱት ጥያቄዎች ይህን ይመስላሉ።
1) የአዴፓ ከፍተኛ አመራር እንዴት ቅዳሜ ከሰአት በኋላ በ11 ሰአት ስብሰባ ሊጀምር ቻለ? ምን አጣዳፊ አጀንዳ ቢያጋጥመው ነው በሰንበት ምሽት ስብሰባ የጠራው? የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ደመቀ፣ ለህክምና ወደ ዲሲ በሄዱበት ቀን እንዴት የአመራሩ ስብሰባ ሊጠራ ቻለ?
2)ስብሰባው የጄኔራል አሳምነውን በስልጣን መቀጠል አለመቀጠል ለመወሰን የተጠራ ነበርን? ጄኔራል አሳምነው ስብሰባው የት እንደሚካሄድና በምን አጀንዳ ላይ እንደሚወያይ ያውቁ ነበርን? ስብሰባው ከአዲስ አበባው ባለአደራ ኮሚቴ አባላት መምጣትና በሚቀጥለው ቀን ከሚደረግ ስብሰባ ጋር የተያያዘ ነበርን? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዚህ ስለ እሁዱ ስብሰባ መደረግ ሃሳብ (ከንሰርን) ነበራቸውን? እንዲቆም ትእዛዝ ሰጥተው ነበርን? ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስክንድር ባህርዳር የሄደው ከጄኔራል አሳምነው ጋር መንግስት ሊያውጅ ነው የሚል ፍርሃት ነበራቸውን? ይህን ፍርሃታቸውን ለአዴፓ ከፍተኛ አመራር ገልፀው፣ አስቸኳይ ስብሰባ በቅዳሜ ምሽት የተጠራው ለዚህ ይሆን? ከሆነ የዶክተር አምባቸው አመለካከት ምን ነበር? በዶክተር አምባቸውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሃል አለመግባባቶች ነበሩን? ዶክተር አምባቸው፣ “አማራ ሙያው በልቡ ነው!” ብለው ለህዝብ ሲናገሩ ከዶክተር አቢይ የደረሰባቸው ተቃውሞ ነበርን? በአጠቃላይ ግንኙነታቸው እንዴት ነበር?
3) የአዲስ አበባው ግድያ በስንት ሰአት ተካሄደ? ከባህርዳሩና ከአዲስአበባው ግድያ የትኛው ይቀድማል?
4) ዶ/ር አቢይ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደ ነው ብለው ካመኑ፣ አዲስ አበባ  ላይ የሚካሄደውን የቺፍ ኦፍ ስታፋቸውን ግድያ ትተው እንዴት ባህርዳር ሊሄዱ ቻሉ? ለሥልጣናቸው ይበልጥ የሚያሰጋው ከባህርዳሩ ይልቅ የአዲስ አበባው ግድያ አይደለምን?
5) ዶ/ር አቢይ አዲስ አበባን መቼ ለቀቁ? ባህርዳር በስንት ሰአት ደረሱ? የሲቪል አቪየሽን ሎጎች ወይም መዘርዝሮች ምን ይላሉ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስንት ሰአት የነረራ መስመር ጠየቁ? ምን ያህል ጦር አስከትተው ሄዱ? መቼም መፈንቅለ መንግስት ለማክሸፍ የሚጠብቋቸውን ሪፐብሊካን ጋርድስ ብቻ ይዘው ተጓዙ ብሎ ለማመን ከባድ ነው? ወይስ የጄኔራል ሰዓረን ሞት ሳይሰሙ ነው ወደ ባህርዳር ያቀኑት? የባህርዳሩን ጉዳይ ከጄኔራል ሰዓረ ጋር ተወያይተውበት ነበርን? ከተወያዩበት መፈንቅለ መንግስት አለ የለም፣ የፌዴራል መከላከያ ጦር ይግባ ወይስ አይግባ ላይ በጄኔራል ሰዓረና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሃል የሃሳብ ልዩነት ነበርን? ጄኔራል ሰዓረ “ይህ የክልሉ ጉዳይ ነው ጣልቃ መግባት የለብንም፣ ከገባንም የክልሉን ምክርቤት ጥሪ ካገኘን በኋላ ብቻ መሆን ይኖርበታል” ብለው በመተክል ላይ ቆመው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ እምቢተኛ ሆነው ሊሆን ይችላል? ጄኔራል ሰዓረ ይህን መሰል ፕሮፌሽናል ወታደራዊ መኮንንና በውሳኔያቸው የሚተማመኑ ሰው ነበሩን?
6) ጄኔራል ሰዓረ ስለተባለው “መፈንቅለ መንግስት” ያውቁ ነበርን? ካወቁ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሁኔታውን ለመቆጣጠር አመራር መስጠት አልበነረባቸውምን? አመራር እየሰጡ ከነበረ ቤታቸው ምን ያደርጉ ነበር? አመራር እየሰጡ ከነበረ ጡረታ ከወጣ ጓደኛቸው ጋር እንዴት እየተዝናኑ አመራር ይሰጣሉ? ወይስ ሰለ ባህርዳሩ ሁኔታ ሳያውቁና የባህርዳሩ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ነው ጄኔራል ሰዓረ የተገደሉት? ከባህርዳሩ በፊት ከሆነ የተገደሉት እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባን ለቀው ወደ ባህርዳር ሊሄዱ ይችላሉ?
7) የጄኔራል ሰዓረ “ገዳይ ነው” የተባለው ጠባቂያቸውን በሚመለከት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈትቤትና ፖሊስ የሰጣቸው እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ዜናዎችና መረጃዎች መንስኤያቸው ምን ይሆን? አንዴ ይዘነዋል፣ ከዚያ የራሱን ነብስ አጥፍቷል፣ ከዚያ ቆስሎ ህክምና ላይ ይገኛል ወዘተ የሚሉት በጣም የሚጋጩ መረጃዎችን መንግስት እንዴት ሊሰጥ ቻለ? ከግድያው ባህሪ የመነጩ ችግሮች ናቸውን? ገዳይ ነው የተባለው ዘብ ስም ማን ነው? ማን መረጠው? የሪፐብሊካን ጋርድ አባል ነውን? ለምን ያህል ወራት ወይም ዓመታት ይህን መሰል የባለሥልጣናት ዘብነት ሥራ ሠራ? ከዚህ በፊት እነማንን አገልግሎ ነበር? ስለቀድሞ ባህርዩ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? ስለፖለቲካ አመለካከቱስ? አክራሪ የአማራ ብሄርተኛ ሊባል የሚችል ነውን? ይህ ይታወቅ ነበርን? ከታወቀስ እንዲህ ዓይነት ሥራ እንዴት ሊሰጠው ቻለ? ምን ያህል ጊዜ ከጄኔራል ሰዓረ ጋር ሰርቷል? ከጄኔራል አሳምነው ጋር ግንኙነት ነበረውን? በተለይ የግድያ እርምጃውን የወሰደ ቀን ከጄኔራል አሳምነው ጋር ተደዋውሎ ነበርን? የዘቡ የስልክ ሬከርዶች ወይም መረጃዎች ምን ይነግሩናል? ገዳይ ከተባለው ዘብ በቀር ሌሎች ዘቦች በቦታው ነበሩን? በዝርዝር ስለሁኔታው ምን ይላሉ?
8)የጄኔራል ሰዓረ ቤተሰቦችና የቤት ውስጥ ሠራተኞችስ በግድያው ወቅት የት ነበሩ? ማን ግድያውን እንደፈፀመ አይተዋልን? ገደለ ስለተባለው ዘብ የታዘቡት ነገር አለ? በቤታቸው ውስጥና በቤታቸው አካባቢ ያዩት የተለየ እንቅስቃሴ ነበርን? ከጄኔራል ገዛኢ ሌላ ከውጪ የመጣ ሰው ወይም ሰዎች ነበሩን? ጄኔራል ሰዓረ የሞቱ ቀን፣ ከዛፍ ተከላ ስምሪታቸው ከተመለሱ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲወያዪ ተደምጠዋልን? ሲበሳጩ፣ በሃይለቃል ሲናገሩ ወይም ሲቆጩ ያዳመጣቸው የቤተሰብ አባል ነበርን?
9)ቅዳሜ እለት የጄኔራል አሳምነው ውሎ እንዴት ነበር? ለእነ እስክንድር ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ሲተጉ ነው የዋሉት የሚሉት መረጃዎች እውነት ናቸውን? የጄኔራሉ የስልክ ጥሪዎች (የላኩዋቸውና የተቀበሉዋቸው) ለማንና ምን ይዘት የነበራቸው ነበሩ? ኢንሳ የባለሥልጣናትንና የሚጠረጠሩ ሰዎችን ስልክ ጠልፎ ስለሚተይብና የድምፅ ፋይልም ስለሚያስቀምጥ፣ እነዚህ ፋይሎች ምን ይሉ ይሆን?
10) የመፈንቅለ መንግስት ወሬ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ካወሩ በኋላ ጄኔራል አሳምነው ለአንድ የአዲስ አበባ ጋዜጣ የሰጡት አጭር ቃለምልልስ ስለ ጄኔራሉ የወቅቱ ግንዛቤ ምን ይነግረናል? ይህ ቃለምልልስ በስንት ሰአት ተካሄደ? ያደረገውስ ጋዜጠኛ ማን ነው? የድምፅ ፋይል አለው ወይ? ጄኔራል አሳምነው ፈፅሞ በማያውቁት ሁኔታ ውስጥ ነው ወይ የተጠለፉት? ጄኔራል አሳምነው ለምን ተገደሉ? በምን ሁኔታ ነው የተገደሉት? ለመማረክ አይቻልም ነበርን፣ ወይስ መያዝ እየተቻለ ነው የተገደሉት? ጄኔራል አሳምነውን የሚያሳድደው አሃድ ከየትኛው ጦር የተውጣጣ ነበር? ወይስ ራሳቸው ባሰለጠኑት ልዩ ሃይልና አርሶአደር ነው የተገደሉት? የተልእኮው መሪ ማን ነበር? ተልእኮውንስ የሰጠው ማን ነበር? በህይወት ይዛችሁ እንዳትመጡ የሚል ተልእኮ ነበርን? ከሆነ ለምን?
11) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ባህርዳሩ ሁኔታና ስለ ጄኔራል ሰዓረ መገደል መቼ አወቁ? እንዴት አወቁ? ማን ደውሎ ነገራቸው? እንደሰሙ ምን እርምጃ ወሰዱ? እንደ አዲስ የታደሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ውስጥ አሜሪካኖቹ ዘ ዎር ሩም የሚሉት ዓይነት የአስቸኳይ ጊዜ አመራር የሚሰጥበት ከውጪ በቀላሉ የማይደፈር የስብሰባ አዳራሽ አለ ወይ? ካለ፣ እነማን ተሰበሰቡ? በመካሄድ ላይ ያለው መፈንቅለ መንግስት ነው የሚለው ውሳኔ ላይ እንዴት ተደረሰ? ለምን ይህን መወሰን አስፈለገ? ይህ ውሳኔ የተካሄደው የጄኔራሉ መገደል ከመታወቁ በፊት ነው ወይ? ጄኔራሉ ከተገደሉ በኋላ ከሆነ ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ከተማቸውን ለቀው ለመሄድ እንዴት ወሰኑ? ግድያው በጄኔራል ሰዓረ ብቻ ይቆማል ብለው እንዴት ሊተማመኑ ቻሉ? ጄኔራል አሳምነው በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ልዩ ሃይሎችና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የገበሬ ሚሊሺያዎች እያሰለጠነ ነው የሚል እምነት ከነበራቸው፣ እንዴት በአፋጣኝ ወደባህርዳር ሄዶ እሳት ውስጥ ራሳቸውን መማገድ የተሻለው አማራጭ ነው ብለው ሊያስቡ ቻሉ? በአክሱም ጉዟቸው ወቅት ከዶክተር ደብረፂዮን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለዚህ የአማራ ክልል የልዮ ሃይልና ሚሊሺያ አደረጃጀት ተወያይተው ነበር ወይ? ከተወያዩ ምን መረዳዳት ላይ ደረሱ? አንዲት ፍየል ወደ ትግራይ እንዳታልፍ በታገደች ቁጥር በማነታችን የጥቃት ዒላማ ተደርገናል ብለው የሚያለቅሱት የወያኔ ሊቀመንበር እንዴት በሁለቱ የትግራይ ጄኔራሎች ግድያ መንግስቱን ሳይወቅሱ ቀሩ? ደብረፅዮን የሚያውቁት እኛ የማናውቀው መረጃ አለ ወይ? ወይስ በባህርዳር የተደረገው ፍጅት የአማራውን ክልል ያዳክመዋል እኛንም ወደማእከላዊ ሥልጣን ይመልሰናል፣ እስረኞቻችንንም ለማስፈታት ይረዳናል ብለው ስላመኑ ይሆን?
ከላይ እንዳያችሁት ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው። የጄኔራል ሰዓረ ገዳይ መያዙንም ሆነ መሞቱን እ  ደገና ከሞት መነሳቱን በሚነግረን የፖሊስ ሃይል ሊጣራ ይችላል ብለን ለማመን አይቻለንም። ከአገዛዙ ነፃ በሆነ አጣሪ ኮሚሽን ሊጣሩ የሚገባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ጥያቄዎች አሉ። በፌዴራል ደረጃ ነፃ አጣሪ ኮሚሽን የሚያስፈልገውን ያህል፣ በአማራ ክልል ደረጃም ነፃ አጣሪ ኮሚሽን ያስፈልግ ይሆናል። በክልሉ ውስጠ  ከሚገኙ የኮሌጅ መምህራንና ሠራተኞች፣ ከህግ ባለሙያዎች ወዘተ የተውጣጣ ኮሚሽን ማቋቋም ይቻል ይመስለኛል። ማድረግ የማንችለው እንዲህ ዓይነቱን የተወሳሰበ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትተን እጃችንን አጥፈን መቀመጥ ነው። የውጪ ሃይሎችም እንዲገቡበት መፍቀድ የለብንም። ያ ፈሱን መቋጠር በማይችል አይሁድ ጥላቻ ምእራቡ ከማን ወግኖ እንደቆመ ግልፅ ስለሆነ፣ ነፃ ኮሚሽን ውስጥ ሊካተቱ አይችልም፣ አይገባምም ።
ዛሬ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩም እጅ ከደም ንጹህ ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ሁኔታም ስለሌለ፣ እርሳቸው በሚያቋቁሙት አጣሪ ኮሚሽንም መተማመን የምንችል አይመስለኝም።  የኮሚሽኑ የማጣራት ውጤት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ነፃ የሚያወጣቸው፣ አለበለዚያ በጥርጥሬ ውስጥ የወደቀው አመራራቸው ትልቅ ችግር ይገጥመዋል የሚል ፍርሃት አለኝ። የራሳቸውን ንፅህና ለማሳየት ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው የዚህን ብሄራዊ ነፃ አጣሪ ኮሚሽን የማቋቋም ጥሪ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲሆን ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል። የትም ሃገር ጉብኝት ከመውጣታቸው በፊት ሊያከናውኑት የሚገባ ቀዳሚ ተግባር ነው ብዬ አስባለሁ።
Filed in: Amharic