>

ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ ሹመት እንጂ እስር አይገባውም!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ ሹመት እንጂ እስር አይገባውም!!!
ያሬድ ጥበቡ
 
መፈንቅለ መንግስትም በምሽትና ጭለማ እንደማይካሄድም እንኳንስ ጄኔራል አሳምነው የአቢይ ሪፐብሊካን ጋርድስ ተራ ወታደሮችም የሚያውቁት ሀ…ሁ ይመስለኛል። በሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ፍፁም እምነት ያለው ወጣቱ ምሁር በሪሁን አዳነ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የጅል የምሽት መፈንቅለ መንግስት ውስጥ እጁን ሊያስገባ አይችልም!
ከታች ከተያያዘው የቪዲዮ ምስል ላይ ንግግር ሲያደርግ የምታዩት ወጣት ምሁር በሪሁን አዳነ ይባላል። በሪሁን የመፅሃፌ አርታኢ ወይም ኤዲተርና ከማስተየብ እስከ ማረም፣ እስከ ማሳተምና ማከፋፈል አእምሮውን ፣ ጊዜውንና ጉልበቱን የሰጠኝ ወጣት ምሁር ነው። ከበሪሁን ጋር አንተዋወቅም ነበር። ከሶስት አመታት በፊት ለፋሲካ ድሮ በላከልኝ ስጦታው ነው የተዋወቅነው። ስጦታውም፣ ከየቦታው አሰባስቦ በአንድ ላይ ያስጠረዘው የመፅሃፌ ስብስብ ነበር ።
ባለፈው ዓመት በነሃሴና መስከረም ወራት አዲስ አበባ ባደረግሁት ቆይታ ወቅት ከበሪሁን ጋር ብዙ ጊዜያት ለማሳለፍ እድል አግኝቻለሁ። በሪሁን የአማራ ብሄርተኛ ምሁር ነበር። ዝም ብሎ በስሜት ሳይሆን በጥልቅ  ምርምር ላይ ተመሥርቶ የደረሰበት አስተሳሰብ ነው። የብሄረሰቦች ፌዴራሊዝምን ከልቡ የሚያምን ሰው ነበር። አቋሙንም ሲከራከር ከበለፀጉት የአውሮፓ ሃገሮችም ጋር እያወዳደረ ጭምር፣ የብሪታንያንና በውስጧ ያቀፈቻቸውን የስኮቲሽ፣ ኢንግሊሽና አይሪሽ ብሄረሰቦች ህብረት ጭምር እያነሳ፣ አንድ የብሪታኒያ ዜጋ የወጣለት የአይሪሽ ብሄርተኛ ጭምር መሆን ይችላል ፣ ሁለቱ አይጋጩም የሚል ክርክር የሚያነሳና፣ በተመሳሳይ መንገድም አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኦሮሞነቱን ፣ አማራነቱን የሚወድና የሚያከብር ቢሆን የሚቻል ብቻ ሳይሆን የሚመረጥም ነው የሚል ወጣት ምሁር ነበር እኔ የማውቀው በሪሁን ።
ለምን መፅሃፌን ለማሳተም ያን ያህል እንደደከመ ስጠይቀውም “ጋሽ ያሬድ የተራዘመ ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኝነትን ለአስርተ አመታት የተከራከርክ፣ የፃፍክ፣ ያስተማርክ በመሆኑ፣ ሥራህን ስለወደድኩት ነው፣ ፅሁፎችህ ተበትነው እንዳይቀሩ ነው ያሰባሰባኳቸው” ብሎ ነው የመለሰልኝ። ከ15 ቀናት በፊት ለሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ በቆየሁባቸው ቀናት ከበሪሁን ጋር አልተገናኘንም፣ በስልክ እንኳ አላወራንም ። ለሚያውቁት ወዳጆቹ “በሪሁንን ማግኘት አልቻልኩም ስላቸው፣ በአስራት ሚዲያ ሥራ መጠመዱን” እንደሚገምቱ ነገሩኝ።
ከትናንት በስቲያ፣ በሪሁን በመንግስት ግልበጣ ተባባሪነት ጥርጣሬ ተይዞ ፖሊስ በትናትናው እለት የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆና ፍርድቤቱም ፈቅዶለት ወደ እስርቤት ወርዷል ። በሪሁን የማንዴላና የማርቲን ሉተር ኪንግን አስተምህሮዎች ከፖለቲካ ሳይንስ እውቀቱ ጋር አዳበሎ፣ በኢትዮጵያ ያልተሞከረው የተራዘመ የህዝባዊ ሰላማዊ እምቢተኝነት ትግል ውጤት የሚያመጣና፣ ህዝቡንም የሚያጎለብት empowering መሆኑን የሚያውቅ ወጣት ምሁር ነው ። በሪሁን አዳነን በግድያና አመፃዊ የመንግስት ግልበጣ መክሰስ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው።
ጄኔራል አሳምነው ኢህአዴግ ካሉት የጦር መኮንኖች በእውቀቱ የተሻለው መኮንን ነበር። የመከላከያውን የስታፍ ኮሌጅም ለዓመታት የመራ ሰው ነው። የመንግስት ግልበጣ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያውን ሳትይዝ፣ የአየር ማረፊያውን ሳትቆጣጠር፣ የክልሉን መሪዎች ብቻ በመግደል ያሸንፋል ብሎ ሊያስብ አይችልም። መፈንቅለ መንግስትም በምሽትና ጭለማ እንደማይካሄድም እንኳንስ ጄኔራል አሳምነው የአቢይ ሪፐብሊካን ጋርድስ ተራ ወታደሮችም የሚያውቁት ሀ…ሁ ይመስለኛል። በሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ፍፁም እምነት ያለው ወጣቱ ምሁር በሪሁን አዳነ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የጅል የምሽት መፈንቅለ መንግስት ውስጥ እጁን ሊያስገባ አይችልም። በሪሁን ከአማራ ብሄርተኝነቱ ውጪ ምንም አይገኝበትም። የአማራ ብሄርተኛ መሆን ደግም ፈፅሞ ወንጀል አይደለም። የእነሌንጮን ምክር የሚያዳምጥ ጠቅላይ ሚኒስትር በምን  መለኪያ ነው የአማራ ምሁራንን በወንጀል ሊጠይቅ የሚችለው?
የአቢይ አስተዳደር በሰላማዊ የአማራ ምሁራንና ባለሃብቶች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት አባላትና ደጋፊዎች ላይ የጀመረው የጅምላ አፈሳ አሁን ከማየታችን በፊት፣ ቅዳሜ ምሽት “የመንግስታዊ ግልበጣ” ክስ ሲጀምር፣ ተቀናቃኝ ነው ብሎ ያመነውን የአማራ ብሄርተኝነት ለመጨፍለቅ የተፈጠረ ጭምብል እንደነበር ግምቱ የነበረን ቢሆንም፣ ለሃገር መረጋጋት ስንል ዝምታን መርጠን ነበር ። ሆኖም የዝምታችን ውጤት ፍፁም ሰላማዊ የሆኑ የበሪሁንን ዓይነት ለሃገር ሊተርፉ የሚችሉ ወጣት ምሁራንን ጭዳ የሚያደርግ ከሆነ፣ ምሬታችንን ይጨምረዋል ። ስለ በሪሁን ሰላም ወዳድነትና ህገመንግስቱን አክባሪነት በፍትህ አደባባይ ቆሜ ልመሰክርለት ፈቃደኛ ነኝ። በሪሁንና እሱን መሰል በግፍ የታሰሩ የአማራ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ የጦር መኮንኖች፣ ወዘተ በአፋጣኝ ፍትህ ሊያገኙና ሊፈቱ ይገባቸዋል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል ልዩ ሃይልና ፋኖ አባላት ላይ የተብዛዛ እስራትና ግድያ እየተካሄደ መሆኑን እንሰማለን። የሚወጡት አሃዞች የሚሰቀጥጡ በመሆናቸው ልንደግማቸው እንኳ ያስፈራናል። መንግስት ወይ ከመጀመሪያው እነዚህ የታጠቁ ሃይሎች እንዳይመለመሉ፣ እንዳይሰለጥኑ፣ እንዳይመረቁ፣ እንዳይታጠቁ ማድረግ በሚችልባቸው ወራት ተባባሪ ሆኖ ቆይቶ፣ በጄኔራል አሳምነው የሸንጎ ንግግሮች መደናገጥ ሲጀምርና ይህንንም ለማስቆም በወጠነው መሰረት በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከለላና ሽፋን የነዚያ የታጠቁ ክልላዊ ሃይሎች አባላት በሆኑ የአርሶአደርና የድሆች ልጆች ላይ የሚያካሂደው ፍጅት መቆም ይኖርበታል። እስካሁን ላካሄደውም እልቂት መጠየቅ ይኖርበታል ።
የኢህአዴግ ከፍተኛው ምክርቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ እዚህ ብካይ ላይ እንዴት ሊደረስ እንደቻለ፣ ለምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጀመሪያው የነዚህን የልዩ ሃይሎች፣ ቄሮና ፋኖዎች አደረጃጀት በቸልተኝነት እንዳዩት፣ ለምን የዚህን አደጋ ለማሳየት የሞከሩ ዜጎችን ምክር ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልነበሩ (የራሴን የቀድሞ ማሳሰቢያዎች ይጨምራል)፣ አሁንም ቄሮ እየተጠናከረ ባለበት ሁኔታ የፋኖ መሳደድ ምን ያህል ፍትሃዊ እንደሆነ፣ ወደፊትስ እነዚህ ክልላዊ ሃይሎችና የሪፐብሊካን ጋርድስ በምን ደረጃና ውሱንነት፣ የአመራር፣ አደረጃጀትና ትጥቅ ጥንካሬ ሊደራጁ እንደሚገባ፣ ከመከላከያ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ጋር ያላቸው የእዝ ሰንሰለት ወዘተ በሚመለከት ውሳኔዎች ማሳለፍና ሁኔታውን መቆጣጠር ይኖርበት ይመስለኛል። ጄኔራል ሰዓረም የተገደሉበት ሁኔታ በጣም አጠራጣሪ በመሆኑ፣ የኢህአዴግ ምክርቤት የራሱን አጣሪ ኮሚሽን አቋቁሞ ሊመረምረው የሚገባ ይመስለኛል።

https://www.facebook.com/507322742/posts/10157539951357743/

Filed in: Amharic