>

ሃገር የሚያፈርስ ሕግ ተሸክሞ ስለ አንድነት እሞታለሁ የማለት ከንቱ ውዳሴ!!! (ሀይለገብርኤል አያሌው )

ሃገር የሚያፈርስ ሕግ ተሸክሞ ስለ አንድነት እሞታለሁ የማለት ከንቱ ውዳሴ!!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ኢትዮጵያችን በከባድ የዘውግ ወጀብና በአደገኛ የፖለቲካ ንፋስ እየተናወጠች ያለችበት ወቅት ላይ ደርሳለች:: ለዚህ አስፈሪ ምዕራፍ እንድትደርስ የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅትና የኦሮሞ ጽንፈኛ ተገንጣይ ቡድን ከፍ ያለ ድርሻ ይወስዳሉ:: ሕወሃት ለሻብያ የጭን ገረድ ኦነግ የሲያድባሬ ሽርጥ ያዥና የሚሲዮናውያን ተላላኪ በመሆን እናት ሃገር ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የቅጥረኝነት ተልዕኮ ከያዙበት ግዜ አንስቶ በንጹሃን ደም እየታጠቡ ሃገሪቷን ሲገዘግዙ ኖረው ዛሬ ላለችበት ሁኔታ አብቅተዋታል::
ኢትዮጵያ እንኳን በተላላኪዎች በላኪዎቻቸው ወረራ እንኳ ልትፈርስ ያልቻለች ጠንካራ ሃገር ነች:: ኢትዮጵያ ሃብትና እውቀት ተራራ ላይ ከደርሱት  ምዕራባውያን በላይ ከነድህነቷ የምታስጎመዥ እግዚአብሄር አስተካክሎ የፈጠራት የቅድስና ስፍራ የሚስጥር ማሕደር ናት::
ኢትዮጵያ ትንቢት የተነግረላት ሱባዔ የተገባላት አባቶች እራዕይ ያዪላት እነሼህ ጅብሪል የተቀኙላት  ብትንገዳገ የማትወድቅ ሃገረ እግዚያብሄር ናት:: አለም ሊጥላት የሚገፉት መርገሙን ሊያራግፍ ክብሯን ሊገስ ነውሩን የሚልክባት ከፈጣሪ በቀር ወዳጅ የሌላት ምስኪን ግን ሃያል ሃገር ነች ኢትዮጵያችን::
የኢትዮጵያ አንድነት የእንቧይ ካብ አይደለም በእልፍ አዕላፉት ጀግኖች ደምና አጥንት የተገነባ የብረት አምድ ነው:: ቢችሉማ የእናት ጡት ነካሾች የባእዳን ባሪያዎች የሆኑት ሕወሃትን ኦነግ ሃገሪቷን አፍርሰው ጌቶቻቸውን ባስደሰቱ ከታሪክም መዝገብ ባስፉቋት ነበር:: ስለማይችሉና ስለማይቻል አልሆነላቸውም:: እንደ አሜባ ተበጣጥሰው ማቀውና ደቀው የትቢያዋ ሲሳይ እንደሆኑ አይተናል:: ይህም ይቀጥላል:: ኢትዮጵያ ነክቶ የተሳካለት ማንም የለም:: የተዳፈራት ፍጻሜው ውርደትና ውድቀት ነው::
ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ደስ የሚልም የሚያስገርምም ንግግር ለፓርላማው እድርገዋል:: የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ በእስኪሪብቶ ሳይሆን ጠመንጃ ይዘን እንዋጋዋለን ብለዋል:: መልካም ነው:: ይደልሆም ያስብላል:: ነገር ግን ክቡርነታቸው ኢትዮጵያን አመንምኖ ያከሳትን እንደ መርገም ጨርቅ የገለማውን ሕገ መንግስት ሕይወትም መንገድም እሱ ብቻ ነው:: እሱን ያልተቀበለ ከኛ ጋር ወዳጅ አይሆንም ብለዋል:: ይሄ አላዋቂነት ወይስ አስመሳይነት::
የበሽታችን ምንጭ የመከራችን ገደል የልዩነታችን ምክንያት የግጭት መቀስቀሻ የእርስ በእርስ መናከሻ የሆነውን:: ጠላቶቻችን መርቀው የሰጡን የሞት መንገድ የሆነ ሕገመንግስት ይዞ ሃገር እወዳለሁ ማለት የታሪክ ስላቅ ነው:: እርግጥ ነው ሕገመንግስቱን የድላችን ሃውልት የሕልውናችን መሰረት የትግላችን ውጤት ነው የሚሉት አህዛቦቹ ሕወሃትና ኦነግ ለዚህ ሰይጣናዊ የኑፉቄ ሰነድ ልዩ ፍቅር አላቸው::
ሕወሃትም ኦነግም የወጡበትን ሕዝብ ፍላጎት ለማሳካት ሳይሆን  በበታችነት እግረሙቅ አስረው በጥላቻ አጥምቀው የለቀቋቸው የሃገራችን ጠላቶች ፍላጎት ለማስፈጸም ነው:: ኢትዮጵያዊ ሆነው ተፈጥረው የጥቁር አለም ያላግኘውን የክብርና የነጻነት ካባ ጥለው የባርነት እግረሙቅ የናፈቁት ኦነጎች : ከቅድስና ስፍራ ፈልቀው የአረቦች አሽከር የሰዶም ከረጢት የሆኑት ሕወሃቶች ሕገ መንግሱቱን መዳኛችን ከማለታቸው ውጪ የትኛውም ኢትዮጵያዊ አይፈልገውም::
 ይህ ሕገ መንግስት ለዚህ የግሎባላይዜሽን ዘመን የማይመጥን የድንቁርና መገለጫ የድንጋይ ዘመን ሰነድ ነው:: ሃገር የሚያፈርስ ሕግ ተሸክሞ ስለ አንድነት እሞታለሁ ማለት ከንቱ ውዳሴ ከመሆን አያልፍም:: ሃገርን የሚወድ መሪ ታሪክ ሰርቶ ያልፍል:: ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በእርግጥ እንደ ቃላቸው ሃገሪቷን ከወደዷት ሊያደርጉላት የሚገባው የመለያያውን ግንብ አፍርሰው የጥላቻውን ሰነድ ያቃጥሉት ::ሕዝብ የሚፈልገው ያንን ነው:: አንድነትችን የሚጠነክረው ሕግና ስርዐት የሚሰፍነው ይህ ሕገ መንግስት ሞቶ ሲቀበር ብቻ ነው::
የኢትዮጵያ አንድነት ጠንቁ ሕገ መንግስቱ ነው:: እበት ትል ይወልዳል እንዲሉ ሕወሃትና ኦነግ የፈለቁት ከዚህ የዲያቢሎስ እዳሪ ላይ ነው:: በመላዕክት ከተማ በሰማየ ሰማያት የታወቀውን : በቅዱስ ቁራን ላይ ደምቃ በመጽሃፍ ቅዱስ ተደጋግማ የምትነሳውን ኢትዮጵያን ስሟን መጥራት የሚጠየፉ በረታቸውን ሃገር ለማድረግ የሚተጉት ሕወሃትና ኦነግ ከነእንክርዳድ አስተሳሰባችው የሚወገዱበት ግዜ እሩቅ አይደለም:: መከራው ሊያይል ወጀቡ ሊበዛ መዋዕትነቱ ሊጠነክር ይችል ይሆናል:: በእርግጠኝነት በነዚህ የእፉኝት ልጆች ሕወሃትና ኦነግ መቃብር ላይ ታላቂቷ ኢትዮጵያ ዳግም አብባ በክብርና በሞገስ ትነሳለች::
ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር፡
Filed in: Amharic