>

በእርጋታ እንነጋገር!  ከሰኔ 15 በኋላ የሆነው ይብቃ! (ጌታቸው ሽፈራው)

በእርጋታ እንነጋገር!  ከሰኔ 15 በኋላ የሆነው ይብቃ!
ጌታቸው ሽፈራው
ማሕበራዊ ሚዲያው ላይ ብዙ ብዥታዎች አያለሁ። እርስ በእርስ ከሚጨቃጨቁት መካከል በጣም ጥቂቶቹ ብቻ እውነታውን እያወቁ የሚያጠፉ ናቸው። ቀሪዎች ስለ ወቅታዊ ሁኔታው መረጃ የሌላቸው ይመስለኛል።  በባሕርዳሩ ጉዳይ በርካታ መረጃዎች አሉ።  መረጃዎቹ አሁን ቢዘረገፉ ግን አይጠቅሙንም። ከክስተቱ ወርና ሁለት ሳምንት በፊት ባሕርዳር ላይ የነበረ ሰው እውነታውን ያውቀዋል። እኔ ባሕርዳር ነበርኩ። በዚህ መጠንም ባይሆን  ችግሮች እንደነበሩ ግንዛቤ ነበረኝ። በአንድ የባሕርዳር ስብሰባ ወቅት ያልተባለ ነገር ተብሏል ተብሎ ሲናፈስ የአቅሜን ለማረጋጋት ሞክሬያለሁ። ሌሎቹ ላይ የሚከበሩ ሰዎች በመሃል እንዲገቡና እንዲመክሩ የአቅማችን መክረን ነበር። ለምንቀርባቸው ሰዎች።  መራራ ሀቆች አሉ። እነሱን በማሕበራዊ ሚዲያ መዘርገፉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።  ጉዳዩ ከተከሰተ ጀምሮም “ተረጋጉ” የምንለው ቢሳቡ የማያልቁና አማራውን ጠልፈው የሚጥሉ ገመዶች በመብዛታቸው ነው።  በመሆኑም  ከሴኔ 15 በኋላ የተፈጠረው ውዥንብር ይበቃ ዘንድ የበኩላችንን እናድርግ!
1) የተፈፀመውን አሳዛኝ ድርጊት እንደ ድል የሚቆጥሩ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ይደረግ፣ ይመከሩ። ይህ ድርጊት አማራው አቀበቱን ለመውጣት ሲጥር ወደኋላ ያሽቀነጠረ ድርጊት ነው። ለአማራ ሕዝብ እቆማለሁ እያለ የምንቃወማቸው ሰዎችም ቢሆኑ በሞታቸው ላይ አታሞ የሚደልቅ አካልን አንቅሮ መትፋት ይገባል።
2) በይሆናልና የግምት መረጃ  አንታጠር። ፀሐይ የሞቀውን ሀቅና እውነት ለመደባበቅ በምናደርገው መንደፋደፍ ከስህተታችን ሳንማር በዚህ ክስተት የተደበቁትን ወንጀለኞች ከመደበቅ ውጭ ሌላ ውጤት አናገኝም።  ከቻልን እውነታውን በደንብ ለማወቅ እንጣር። እውነታውን ሳናውቅ በዚህና በዛ የምንይዛቸው ነጠላዎች ለጠላት እንጅ ለአማራው አንዳች ጥቅም የላቸውም። ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የምናውቃቸው የሚመስሉን አንዳንድ እውነታዎችን ይዘን ስንሮጥ ብንሰነብት ነገ ከነገ ወዲያ ትዝብት ላይ ይጥሉናል። እናፍርባቸዋለን። የተደረገን ነገር አልተደረገም ብለን አንድረቅ። ያልተደረገን ነገር ተደርጓል ብለን ሕዝብ ላይ ውዥንብር አንልቀቅ። ሰሞኑን ማሕበራዊ ሚዲያው ላይ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይም በሀሰት ብዙ ወሬዎች ተወርተዋል። ማሕበራዊ ሚዲያው ተዘግቶም ጠላቶች ያልተጣሉትን ወንድማማቾች ተጣሉ ብለው አስወርተዋል። ያልታሰረ ታሰረ፣ ያልተገደለ ተገደለ ተብሏል። ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያናቁሩ እንደሚውሉት በፋኖ እና በልዩ ኃይል፣ በነባርና በአዲስ ተመራቂው ልዩ ኃይል፣ መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ በሚገኙ የአማራ ልጆችና በልዩ ኃይል መካከል ብዙ ጠብ ለመፍጠር ጥረው አብዛኛው ክፉ ሀሳባቸው መክኗል። ማሕበራዊ ሚዲያውም ከዚህ መማር አለበት።
3) ከተገደሉት አመራሮች በተጨማሪ አማራው  ብዙ  ነገር አጥቷል። ዓለም አቀፍ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሆኗል። ከአራቱ ታዋቂዎች በተጨማሪ ብዙዎች ተገድለዋል። ቆስለዋል። ሟቾቹ አይመለሱም። ማዳን የምንችለው ወደፊት የተጋረጠብንን ነው። ወደፊት በርካታ ነገር ተጋርጦብናል። ሌላ ስህተት እንዳይፈጠር ከፈለግን መረጃዎችን እናጣራ። ካጣራን ሆን ብለው ከሚያጠፉት ውጭ ብዙዎች ውዥንብር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ይቻላል። ፌስቡክ ላይ እየወጡ ከመዘላለፍ በውስጥ መስመር እንነጋገር። መረጃ ካላቸው አካላት እንጠይቅ። ከታማኝ የመረጃ ምንጮች መረጃ እንውሰድ።  የተፈጠረው ባሕርዳር እንደመሆኑና የአማራ ክልል መንግስት አብዛኛውን መረጃ የሚሰጠው በአማራ መገናኛ ብዙሃን ነው። እንደ እኔ እምነትና መረጃ በአማራ መገናኛ ብዙሃን የሚነገሩት አብዛኛዎቹ ነገሮች እውነትነት አላቸው። ከፌደራል መንግስቱ የተጫኑ የችኮላ ፍረጃዎች፣ የአማራን ሕዝብ ስም ለማጥፋት የሚደረጉ አካሄዶች፣ ራስን ለማዳን ከሚደረጉ መከላከሎች፣ የግለሰቦች የተለጠጡና የተንሸዋረሩ አገላለፆች ባሻገር በጥሬ ሀቅነት የሚነገሩ እየመረረን ልንቀበላቸው የሚገቡ፣ ካልተቀበልንም መጨቃጨቂያ የማይሆኑ ጉዳዮች አሉ። በስተጀርባው ማን አለ? ለምን ይህን አደረገ? የሚሉት ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው ገደለ አልገደለም እያልን የውሃ ወቀጣ ውስጥ መግባቱን ጨምሮ በዚህ አጣዳፊ ወቅት ልንነታረክባቸው የማይገቡ ነገሮች ብዙ ናቸው።
4) ከምንፅፈው በበለጠ የሚያነበውና በቦታው ያለው ሕዝብ የሚያውቀው እውነታ አለ። ሕዝብ መሪር ሀዘኑን ችሎ ለመረጋጋት ሲጥር እኛ በትርፍ ጊዜ በምናገኛት መረጃ ተነስተን ሌላ ውዥንብር ከመፍጠር ብንቆጠብ መልካም ነው።  እኛ ውሃ እየወቀጥን የአማራ ሕዝብ ላይ በርካታ የጥፋት እቅዶች እየወጡ ነው። የአማራ ሕዝብ ሀዘኑን ዋጥ ባደረገበት ወቅት አጉል ዳስ መጣሉ አግባብ እንዳልሆነ ሁሉ አንዱን በሌላኛው ላይ ከማግነን ብንቆጠብ መልካም ነው። ለሟች ቤተሰቦች፣ ለሟቾች ስንል ብቻ ሳይሆን ለአማራው የሚጠቅመው ግለሰቦችን ከማግነን በላይ እየገነነ   የመጣውን የጠላት ሴራና በትር መመመከት ነው። የሚጠቅመው ሟችም ገዳይም የሆኑትን ከማውገዝም በላይ ቀጣይ ፈተናዎችን ለመወጣት የሚያስችለው ላይ ማተኮር ነው። ይህን ፈተና የምንወጣበትን፣ ሌላ ስህተት የማይፈጠርበትን መፍትሔ መትለም ነው። ሌሎቹን መረጃዎች ፍንትው ሲሉ የምደርስባቸው ናቸው።  ያኔ ትዝብት ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ አለብን። ያኔ በራሳችን እንዳናፍር ዛሬ መጠንቀቅ አለብን!
5) በዚህ ወቅት የምንመረምራቸው፣ ረጋ ብለን የምናያቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ረጋ ካላልን የምንጠለፍባቸው፣ የአማራ ሕዝብ የሚጠቃባቸው ነገሮች በርካቶች ናቸው። በውስጥ የምንፈታቸው ነገሮች ይኖራሉ። ገመናውን ሁሉ ሌላ ስላስጮኸው እኛም የምንቀባበለው መሆን የለበትም። ስህተት የመሰለው ሁሉ የአማራ ጠላት ስላጦዘው አብረን የምናጦዘው አይደለም። ለምሳሌ ያህል በትናንትናው ዕለት የኦነግ ሰዎች እና የአማራ ሕዝብ አንቅሮ የተፋቸው የአንድነት ኃይል ነን ባዮች ያጮሁት ስንቀባበል ውለናል። እነዚህ ኃይሎች የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ንግግር ነው የተባለውን  ተናብበው ወደ አደባባይ ሲያወጡት ለአማራው አዝነው አይደለም። ኮ/ል ደመቀን አድንቀውና ወድደው አይደለም። ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ካለነው በላይ ለእነዚህ ኃይሎች ማርከሻው ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ነው። ሁለቱ ኃይሎች ይህን ጉዳይ ተናብበው አደባባይ ላይ አስጥተውት የዋሉት የሰሞኑን ስስነታችን ስላዩ ነው። እርስ በእርስ አናቁረውን ማለፍ ስለፈለጉ ነው። ጉዳዩ ስህተት ነው ብለን ብናስብ እንኳ  እነሱ ገምደው የሰጡንን ጅራፍ ስናጮህ ባልዋልን ነበር። በእነዚህ ኃይሎች ደባ በርካታ ወንድሞቻችን ሰለባ እየሆኑ እኛ  ሌላ ቦታ ሲያጫውቱን ይውላሉ። እኛም እነሱ ባቀዱልን መሰረት በራሳችን ሜዳ ስንጫወትላቸው እንውላለን።
ገመናውን ከራሱ ወገን ጋር ተነጋግሮ መረዳት የማይችል መቼም ቢሆን መጠቀሚያ ከመሆን አይድንም።  ኮ/ል ደመቀ ለጄነራል አሳምነው፣ ጄነራል አሳምነው ለኮ/ል ደመቀ የሆኑት ያህል እኛ እነማን ሆነን ነው?  የአማራ ክልል መንግስት ከጄነራል አሳምነው በፊት በቦታው እንዲቀመጥ የፈለገው ኮ/ል ደመቀን ነበር። ኮ/ል ደመቀ የራሱን ምክንያቶች አስቀምጦ ቦታው ላይ መሆን እንደማይፈልግ ብቻ አይደለም የተናገረው። ለቦታው የሚሆን ሌላ አማራጭ ሰው እንዲቀመጥ ጭምር ነበር ተደጋጋሚ ምክር የሰጠው። ኮ/ል ደመቀ የጠቆመው ጄነራል አሳምነውን ነው። ጄነራል አሳምነው  በዚህ ቦታ ከተቀመጠ በኋላም የኮ/ል ደመቀን ያህል አማካሪ እና የቅርብ ሰው አልነበረውም። ከአዴፓ ሰዎች ጋር አለመግባባቶች ሲፈጠሩም በመሃል መከሪ  ኮ/ል ደመቀ ነበር። ዛሬ ተነስተን የተሰጠንን አጀንዳ ከማጦዝ በፊት እነዚህን ጉዳዮች እንኳን ልብ አንላቸውም። ከብዙዎቻችን በላይ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እና ጄ/ል አሳምነው ይተዋወቃሉ። አብረው ሰርተዋል። ይህንም  ሁለቱን በቅርብ ከሚያውቃቸው ሁሉ ማረጋገጥ ይቻላል።
6)መተማመን ያለብን የችግሩ መነሻ ራሳችን ነን። ጠላቶች ክፍተቱን ተጠቅመው እዚህ አሳዛኝ ድርጊት አድርሰውናል። የተጠመዘዝነው፣ መጠቀሚያ የሆነው፣ የመጀመርያውን ስህተት የተሳሳትነው እኛው ነን።  ትናንት የእኛውን ክፍተት ተጠቅመው ያ አሳዛኝ  ድርጊት እንዲፈጠር ያደረጉት አካላት ዛሬም ነገም የትናንቱን ብቻ ሳይሆን በየቀኑ የሚፈጠሩትን እየተጠቀሙ አማራውን አንገት ማስደፋት ነው ስራቸው። በትናንትናው አብዝተን ስንጨቃጨቅ፣ በትናንትናው አብዝተን ስንነታረክ ለጠላት ሌላ ክፍተት፣ ለአማራው ሌላ መጠቂያ እየፈጠር ነው። በመረጃ የተደገፈ ነገርን አልሆነም እያልን ስንነታረክ፣ መረጃ የሌለውን  ሆኗል እያልን ስንጨቃጨቅ በመሃል ድርጊቱን የፈፀሙትን፣ ሴራ የሚጎነጉኑልንን እየሳትን ነው። ለቀጣይ ፈተና እየተመቸናቸው ነው። ለቀጣይ ክፍተት እየፈጠርን ነው።  ክፍተት መፍጠር፣ ለጠላት መመቸት ይብቃን። በመረጃ የተደገፈን ነገር እየካድን፣ መረጃ የሌለውን ሆኗል እያልን ውሃ በመውቀጥ ሕዝብን ውዥንብር ማስገባት መቆም አለበት። በራስ ጉዳይ ከራስ ጋር መጣለት ይብቃ። የራስን ጉዳይ ከወገን ጋር ተነጋግሮ ለጠላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ማድረግ እንጀምር!
7) በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እያንዳንዳችን ሀሳብ ስንሰነዝር፣ ስንፅፍ ከእያንዳንዱ ሀሳባችን በስተጀርባ ጠላት ምን ክፍተት ያገኝብናል የሚለውን አንዘንጋ። ከእያንዳንዱ ሀሳብና ፅሁፍ በስተጀርባ  እንወደዋለን የምንለው ሕዝብ ምን ትርፍ ያገኛል? ምን ጉዳት ያስከትልበታል የሚለው በአንክሮት ማስላት አለብን! ይህን ካሰብን ጠላት ያሰመረልንን የተንኮል መስመር በቀላሉ እናልፈዋለን። ለአማራ ሕዝብ የተደገሰውን ክፉ ሀሳብ በሚገባ እናሸንፈዋለን። ይህን ረጋ ብለን ካሰብን ጠላቶች ከአቀበት ሳይመልሱን ወደምንፈልገው መዳረሻ እንወጣለን!
Filed in: Amharic